Content-Language: am ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ገጽ ሁለት
header image




(ድረ ገጽ 2)

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ



Mussolini troops departing to invade Ethiopia
ወራሪ የፋሽስት ወታደቶች
ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ ሲሳፈሩ
Credit to: Photo link
የኢጣሊያ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እንደሚከፍት ለማስታወቅ ፋሽስቱ ቤኒቶ ሙሶሎኒ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በተሰበሰበበት፤
“…የዓለም ማሕበር በኢትዮጵያ ላይ ያለውን መብታችንን በማወቅ ፈንታ እኛን ለመጨቆን ያስባል፡፡
…ነገር ግን ጨቋኞችን ማህበርተኞች፤ በፖለቲካም ቢመጡብን፤ በጦርነትም ቢመጡብን፤ እንመልሳቸዋለን፡፡
…ኢትዮጵያን 40 ዓመት ታገሥን፡፡ አሁን ግን በቃን፡፡
…አስቀድመን ደህና አድርገን ሳንዋጋ፤ ወደኋላ ሊመልሰን የሚችል እንደሌለ ሁሉም ይወቅ፡፡”

በማለት የትዕቢትና የማንአለብኝነት ንግግር ተናግሯል፡፡
ከዚያ በኋላ የኢጣሊያ ሠራዊት በመርከብ ተሳፍሮ፤
“ኢጣሊያ ሆይ ከባሕር ወዲያ አልፈን ተራራና መሬት እናወርስሻለን፡፡”
እያለ መዝሙር እየዘመረ መጓዝ ጀመረ፡፡
Mussolini
ቤኒቶ ሙሶሎኒ
image link
ሙሶሎኒም የአገሩ ንጉሥና የሮማው ጳጳስ በእርሱ ሀሳብ እንደተስማሙና እንደሚተባበሩት ባወቀ ጊዜ፤ ጦርነቱን ባወጀ በማግሥቱ ማለትም፤ መስከረም 21 ቀን 1928 ዓ.ም. የኢጣሊያ
De Bono
የኢጣሊያ ጀነራል ደቦኖ
image link
ሠራዊት የኢትዮጵያ ወሰን የነበረውን የመረብን ወንዝ ተሻግሮ ጦርነቱ እንዲጀመር ኤርትራ ለነበረው ለጀነራል ደቦኖ በቴሌግራም ትዕዛዝ አስተላለፈለት፡፡

የሮማው ሊቀ ጳጳስ፤ በዓለም ሰላም እንዲሆን በመስበክና የተጣሉትንም ወገኖች በማስታረቅ ፈንታ፤ ለሙሶሎኒ የቀኝ እጅ በመሆን በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው የጦርነት ዘመቻ፤ 'የተቀደሰ ዘመቻ ነው' እያሉ ግፊት በማድረግና አልፎ ተርፎም የሊቀ ጳጳሱን አብነት በመከተል፤ ብዙ የካቶሊክ ጳጳሳት ለዘመቻው ዕርዳታ የሚሆን ብዙ ወርቅና ገንዘብ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም በሮማው ሊቀ ጳጳስ ድርጊት ያዘነና የተገረመ አንድ የስዊድን ጋዜጠኛ በስብሰባው ላይ ባደረገው ንግግር፤
"…ቅዱሰ ሆይ፤ እኔ በሰሜን አገር የተወለድኩ አንድ ፕሮቴስታንት ነኝ፡፡
…እኔ አንድ ምስኪን ኃጢያተኛ ነኝ፡፡ እርስዎ ግን የመድኃኒታችን ምትክ ነዎት፡፡
…እርስዎ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ዋና ነዎት፡፡ ካቶሊካዊት ማለት፤ የሁሉ ማለት ነው፡፡
…ከርስዎ በታች ያሉት ሌሎች ጳጳሳት፤ ኢትዮጵያ ለኢጣሊያ ቅኝ አገር እንድትሆን የሚገባ ነው ብለው ተናገሩ፡፡
…ዘመቻውም የተቀደሰ ዘመቻ ነው በማለት፤ ለዘመቻው የተሰለፈውን ታንክና መሣሪያ ባረኩ፡፡
…እርስዎ መቸም የሐዋርያው ጴጥሮስ ተከታይ ነዎትና አይሳሳቱም፡፡
…ቅዱስ ሆይ፤ ኢጣሊያ (የእግዚአብሔርን) የፍርድ ሥራ ትሠራለች ብለው ሰብከዋል፡፡
…እንግዲህ ሌላው ዓለም ሁሉ የኢጣሊያንን ሥራ ቢቃዎም፤ የእግዚአብሔርን ፍርድ እንደተቃወመ ይቆጠር ይሆን?
…እርስዎ እንዳሉት ኢጣሊያ የፅድቅ ውጊያ የምትዋጋ ከሆነ፤ ሌላው ዓለም ሁሉ እግዚአብሔርን የካደ ነውን?
…እርስዎ እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ ሰዎች አገራቸውን ለመጠበቅ ቢከላከሉና፤ የኢጣሊያ አይሮፕላኖች ጥርግ አድርጐ ቢያጠፋቸው፤ ሴቶችንና ሕፃናትን በቦንብ ቢያጠፋ፤ እግዚአብሔርን አገለገሉ ማለት ነውን?
…ይህ ሁሉ ካሁን በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ አላገኘንም ነበርና እርስዎ አሁን ሰላስተማሩን ትልቅ ነገር ነው፡፡
…እርስዎ የዓለም ሁሉ አባት ነኝ እያሉ፤ የሙሶሎኒ ባሪያ ሆነዋል፡፡
…እርስዎ የሚያመልኩት አምላክ ጣዖት ነው እንጅ አምላክ አይደለም፡፡
…ኢትዮጵያም እርስዎ ለሚያመልኩት አምላክ ፀሎት ልታሳርግ አትችልም፡፡
…እርስዎ ከእግዚአብሔር ይልቅ ለሰውየው ለሙሶሎኒ የሚታዘዙ ሆነዋል፡፡”
በማለት ታሪክ የማይረሳው ድንቅና እውነትን የተመረኮዘ ንግግር ተናግሯል፡፡


Mussoloni war strategy
ቤኒቶ ሙሶሎኒ በሁለት አቅጣጫ ኢትዮጵያን ለመውረር ያወጣው እቅድ
image credit to: Photo link  (edited by the webmaster)
የኢጣሊያ ጦር የመረብን ወንዝ ተሻግሮ በሦስት መስመር በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት በመክፈት ወረራውን መስከረም 22 ቀን 1928 ዓ.ም. ጀመረ፡፡
የኢጣሊያ ወረራ አንዱ ዓላማ፤ ጣሊያኖች በ1888 ዓ.ም. የሀፍረት ማቅ የተከናነቡባትን የዐድዋ ሽንፈት ብድር ለመመለስ የታቀደ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡
በዚህ መሠረት የመጀመሪያ ወረራቸውን በማእከላዊ ትግራይ በሚገኘው እንጢጮ በተባለው ሥፍራ ጀመሩ፡፡ አከታትለውም ሁለተኛውን ወረራ በአዲግራት ላይ ከፈቱ፡፡

የኢትዮጵያ ጦር የኢጣሊያንን ወረራ ለመመከት የዘገየበት ምክንያቶች ምን ምን ነበሩ?

ሁለት ምክንያቶች ቀደም ብለው ታስበው ነበር፡፡
አንደኛው፤ በዓለም ሕብረተሰብ ዘንድ የኢጣሊያንን ወራሪነት በግልጽ ለማሳየት ሲሆን፤
ሁለተኛው፤ ደግሞ የኢጣሊያንን ጦር ወደ መሀል አገር ስቦ በማስገባትና የስንቅና ትጥቅ መተላለፊያ መንገዱን በመዝጋት አቅርቦቱ ላይ ችግር ለመፍጠር ነበር፡፡




Haile Selassi Gugsa with Debono
አገር ከሀዲው ኃይለሥላሴ ጉግሳ ከጀነራል ደቦኖ ጋር
ኢጣሊያ ወረራውን በጀመረ በሁለተኛው ቀን፤ ማለትም መስከረም 24 ቀን 1928 ዓ.ም. አዲግራት በኢጣሊያ ጦር እጅ ስትወድቅ፤ ደጃዝማች ኃይለሥላሴ ጉግሳ ወዲያውኑ ጓዙን ጠቅልሎና ጠቃሚ መረጃዎችን ይዞ አገሩን በመክዳት ያለምንም ማንገራገር ወደ ኢጣሊያ ካምፕ ገባ፡፡
በማግስቱ፤ መስከረም 25 ቀን 1928 ዓ.ም. የኢጣሊያ ጦር ዐድዋን በቦምብ ደብድቦ በቁጥጥሩ ሥር አደረገ፡፡
የኢጣሊያ ጦር መረብን ተሻግሮ ዐድዋ በገባ ጊዜ፤ ኃይለሥላሴ ጉግሳ፤ ሊከዳ ሲል እጁን ይዘው ሊያስቀሩት ካሰቡት ከአባቶቹ አሽከሮች አምልጦ ሌሊቱን ሲጓዝ አድሮ ከኢጣሊያ ጋር ተቀላቀለ፡፡
ወዲያውኑም የኢጣሊያ ጦር አዛዥ ከሆነው ከጀነራል ደቦኖ ጋር ተገናኝቶ፤ ኢጣሊያ ድል የምታደርግበትንና መቀሌንም የምትይዝበትን መንገድ ያመላክት ነበር፡፡
ኃይለሥላሴ ጉግሳ፤ የአፄ ዮሃንስ የልጅ ልጅ ከሆኑት ከራስ ጉግሣ አርዓያ ሥላሴ የተወለደ ሲሆን አፄ ዮሃንስ ቅደመ አያቱ ናቸው፡፡
አባቱ ራስ ጉግሣ አርአያሥላሴ፤ ልጃቸው ኃይለሥላሴ ጉግሳ፤ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ሁለተኛ ልጅ የሆነችውን ልዕልት ዘነበወርቅን እንዲድሩለት ንጉሠ ነገሥቱን ለምነው፤ በተፈቀደላቸው መሠረት፤ ኃይለሥላሴ ጉግሳ በተወለደ በ 24 ዓመት ዕድሜው፤ የ 14 ዓመቷን ልዕልት ዘነበወርቅን አገባ፡፡
ሆኖም ልዕልት ዘነበወርቅ፤ የሰባት ወር ነፍሰጡር እንደነበሩ በጠና ታመው ስለነበረ አድሜአቸው 20 ዓመት ሳይሞላ ሕይወታቸው አለፈ፡፡

Haile-Selassie-Gugsa.jpg
ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ እራሱንና ተከታዮችን
ጨምሮ ወደ ኢጣሊያ ጦር ሲቀላቀል
የምሥራቅ ትግራይ አገረ ገዥ ሆኖ የተሾመው ኃይለሥላሴ ጉግሳ፤ የምዕራብ ትግራይ ገዥ ሆነው ከተሾሙትና የአፄ ዮሃንስ የልጅ ልጅ ከሆኑት ከልዑል ራስ ሥዩም መንገሻ ጋር፤ በግዛትም ሆነ በማዕረግ አኩል ሥልጣን ለምን አይኖረኝም በማለት በልቡ ቂም ቋጥሮ ቆይቶ እንደነበረ ይነገራል፡፡ ጣሊያኖችም ይህን ሀሳቡን ተረድተው ኖሮ፤ ከኃይለሥላሴ ጉግሳ ጋር በመገናኘት፤ “እኛ ኢትዮጵያን ድል ብናደርግ፤ ሙሉ የትግሬን ግዛት ከራስ ስዩም መንገሻ ነጥቀን ለአንተ እንሰጥሀለን፡፡” በማለት ቃል ገብተውለት ስለነበር ቃላቸውን አምኖ በእነርሱ እየተደገፈ ከጠላት ጋር በማበር የራሱን አገር ሲወጋ ቆየ፡፡
ሆኖም ጣሊያኖች ቀደም ሲል በዐድዋ የደረሰባቸውን ሽንፈት በማውሳት፤
“በዶጋሊ፣ በሰሐጤና በዐደዋ የረገፉትን የወንድሞቻችንን ደም ተበቀልን፡፡ እንዲሁም ሰፊ የቄሳር አገር ለሕዝባችን አወረስን፡፡”
ከማለት ውጭ ለኃይለ ሥላሴ ጉግሳ ምንም ያደረጉለት ነገር አልነበረም፡፡
ኃይለሥላሴ ጉግሳ ግን፤ ጣሊያኖች ምንም ነገር እንዳልፈየዱለትና የአገሩ ጠላት እንደሆኑ እያወቀ፤ እርሱ ግን እስከመጨረሻው ከጣሊያኖች ጋር መወገኑን መረጠ፡፡
ጣሊያኖች ለዓለም ማሕበር ስለኢትዮጵያ በዝርዝር ጽፈው ካቀረቧቸው አንቀጾች ውስጥ፤
“የኢትዮጵያ መኳንንቶች እርስ በርስ ሰምምነት ስለሌላቸው፤ የምስራቅ ትግራይ አገረ ገዥ የሆነውና አባቱ ከንጉሠ ነገሥት ጋብቻ ከአፄ ዮሃንስ የልጅ ልጅ የተወለደው ኃይለሥላሴ ጉግሳ፤ ይኸው በመጀመሪያው ጦርነት ከኛ ጋር ገባ፡፡”
በማለት እንደማስረጃ ያቀረበው ጉዳይ፤ ለኢትዮጵያውያን ለጊዜውም ቢሆን አሳፋሪ ተግባር ነበር፡፡
De Bono
በሰሜን ጦር ግነንባር የኢጣሊያ ጦር አዛዥ ጀነራል ኤሚሊዮ ደቦኖ
የጀነራል ደቦኖ ሠራዊት አድዋን ከተቆጣጠረ በኋላ ወደፊት ገፍቶ መቀሌን እንዲይዝ ከሙሶሎኒ ትእዛዝ ስለደረሰው፤ የሁለት ክፍለጦር ሠራዊት ወደ ቦታው ላከ፡፡
ወደመቀሌ ከተላኩትም የጀነራል ደቦኖ ሠራዊት ውስጥ የጠላትን ጦር ይመሩ የነበሩት የከዳተኛው የኃይለሥላሴ ጉግሳ አሽከሮች ነበሩ፡፡
ከአድዋ የተነሳው የጠላት ጦር በመቀሌ አካባቢ ሲደርስ፤
 ከደጃዝማች ገብረ ሕይዎት፤
 ከደጃዝማች ወረስና
 ከደጃዝማች አሠጋኸኝ
ወታደሮች ጋር ጦርነት ገጥመው፤ በብዙ የኢጣሊያ የጦር ሹማምንቶችንና ከኤርትራ በዘመቱ ወታደሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል፡፡
እንዲሁም በደንከል በረሃ ይጓዝ ከነበረው የኢጣሊያ ተጠባባቂ ጦር ጋር ደጃዝማች ካሣ ስብሃት የተባሉ ጀግና፤ ወታደሮቻቸውን ይዘው ከፍተኛ ጦርነት ካደረጉ በኋላ የኢጣሊያ የጦር አዝማቹ ሲቆስል፤ ሁለት የኢጣሊያ ጦር ሹማምንቶችና 300 የሚደርሱ የኢጣሊያ ወታደሮች ተገለዋል፡፡
የኢጣሊያ ጦር፤ ወረራውን በጀመረ በ 35 ቀናት ውስጥ ከስትራተጂ አንፃር ቁልፍ ሥፍራ የሆነችውን የመቀሌን ከተማ ጥቅምት 27 ቀን 1928 ዓ.ም. ለመያዝ ችሏል፡፡

በሰሜን ጦር ግንባር የኢትዮጵያ ጦር አሰላለፍ

  1. በልዑል ራስ ካሣ ኃይሉና በልዑል ራስ ሥዩም መንገሻ የሚመራው ጦር፤ ከዐድዋና ከመቀሌ በስተ ደቡብ በተንቤን በኩል፣
  2. በራስ እምሩ የሚመራው ጦር፤ በሽሬ በኩል፣
  3. በራስ ሙሉጌታ ይገዙ የሚመራው ጦር፤ ከዐድዋና ከመቀሌ በደቡብ ምስራቅ፤ በእንደርታ አምባ ራዶም በኩል፣
  4. የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘበኛና ሌሎችን ወታደሮች ጨምረው በደቡብ በኩል አሸንጌ ላይ፤
ተሰልፈው ነበር፡፡


Ethiopian Warriors to their way to the Northern Front
የኢትዮጵያ ተዋጊው ጦር እየፎከረና እየሸለለ
ወደ ማይጨው ጦር ግንባር ሲዘምት
image link
የኢጣሊያን ጦር በሰሜን ኢትዮጵያ በኩል የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት ከሆነችው ከኤርትራ አስመራ በመነሳት የኢትዮጵያን ድንበር የሆነውን የመረብ ወንዝ ተሻግሮ፤ አክሱምን፤ አድዋንና መቀሌን ከተቆጣጠረ በኋላ፤ ከአሁን አሁን አፀፋውን ይመልሳል ተብሎ የታሰበው የኢትዮጵያውያን የማጥቃት እርምጃ ዘግይቶ ከአራት ወራት በኋላ በጥር ወር 1928 ዓ.ም. ተጀመረ፡፡
በራስ እምሩ የሚታዘዘው ጦር፤ መሽጐ የነበረውን የጠላት ጦር ወግቶና ድል አድርጐ እስከ ዐድዋ ድረስ ደርሶ ወደ ኤርትራ ጠረፍ ማቅናት ጀምሮ ነበር፡፡
በሌላ በኩል፤ በልዑል ራስ ካሣ ኃይሉና በልዑል ራስ ሥዩም መንገሻ የሚመራው ሠራዊት ውስጥ ከነበሩት የጦር አለቆች መካከል፤ በተራ ቁጥር 1 እና 2 የተጠቀሱት የሰላሌው የልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ ዳርጌ ልጆች የገኙበታል፡፡
  1. ደጃዝማች ወንድወሰን ካሣ፣
  2. ደጃዝማች አበራ ካሣ፣
  3. ደጃዝማች አድማሱ ብሩ፣
  4. በጅሮንድ ለጥይበሉ፣
  5. ደጃዝማች ወርቅነህና፣
  6. ፊታውራሪ አንድአርጌ፣

Ethiopian Warriors to their way to the Northern Front
የፋሽስት ኢጣሊያ አይሮፕላኖች
በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ
የሙስታርድ ጋስ ቦመብ ሲያዘንቡበት
image link
ሁሉም በያሉበት ከተንቤን ከተማ ወደ ዐቢዐዲ ለጦርነት መጓዝ ሲጀምሩ፤ እርዳታ እንዳይደረስ የጠላት ጦር መተላለፊያ መንገዶችን ሁሉ ዘግቶ ያስጠብቅ ነበር፡፡
ተንቤን ላይ የሠፈረው የልዑል ራስ ካሣና የልዑል ራስ ሥዩም መንገሻ ጦርም ከጠላት ጋር ውጊያ ሲጀምር ሌላ እርዳታ እንዳይደርስለት፤ የጠላት ጦር አስቀድሞ የሸለቆ መተላለፊያወችን ሁሉ ዘጋ፡፡

የኢትዮጵያ ወታደሮች ግን ሩቅ ለሩቅም ሆነው በመድፍ ጠላትን ይወጉ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ጦር፤ ከመሸገበት ሥፍራ እየለቀቀ ወደ መቀሌ የሚወስደውን መንገድ ይዘው በጀግንነት እየተዋጉና በሩጫ እየፎከሩ ጠላት ምሽግ ውስጥ በመግባት በጐራዴ ጠላትን ሲጨፈጭፉ ሳለ፤ መቀሌ የመሸገው የጠላት ጦር ተስፋ ቆርጦ፤ ስንቃቸውንና የጦር መሣሪያቸውን ጭነው ሊሸሹ ሲሉ የኢጣሊያ አውሮፕላኖች ደርሰው፤
Ethiopian Warriors to their way to the Northern Front
የኢትዮጵያ ሠራዊት ከሙስታርድ
የጋስ ቦመብ ለማምለጥ ሲሸሽ
image link
በጀግንነት እየተዋጋ ድልን ይጠባበቅ በነበረው በጀግናው የኢትዮጵያ ጦር ላይ በጄኔቫ ኮንቬንሽን ጥቅም ላይ እንዳይውል የተከለከለውን መርዛማ የሙስታርድ ጋስ ቦምብ ያለማቋረጥ እንደ ዝናብ በኢትዮጵያ ሠራዊትና በቀይ መስቀል አመቡላንሶችና ሆሰፒታሎች ላይ ሳይቀር እየተመላለሱ አርከፈከፉበት፡፡

ጀግናው የኢትዮጵያ ሠራዊት ያ ሁሉ የሙስታርድ ጋዝ የቦንብ ዝናብ እየዘነበበት፤ ለሦስት ቀንና ለሦስት ሌሊት ጠላትን ፊት ለፊት እየተጋፈጠ ይዋጋ ነበር፡፡
የጦር ምኒስትሩ ራስ ሙሉጌታ ይገዙ አምስት ቀን ሙሉ ከጠላት ጋር ሲዋጉ ሳሉ፤ በአይሮፕላን የሙስታርድ ጋዝ የቦንብ ጥቃት ምክንያት ብዙ የኢትዮጵያ ሠራዊት እነዳለቀባቸው ባዩ ጊዜ፤ በጦርነት የደከመውን ሠራዊታቸውን ይዘው
Ras Mulugeta Yegezu
የዐድዋው አርበኛ ጀግናው
ራስ ሙሉጌታ ይገዙ
ከነልዑል ራስ ካሣና ከነልዑል ራስ ሥዩም መንገሻ ሠራዊት ጋር ተደባልቀው ለመዋጋት ወደኋላ ሊመለሱ ሲሉ፤ የጠላት ጦር አይሮፕላኖች፤ በሙስታርድ ጋዝ ቦምብ በተከታታይ የኢትዮጵያን ሠራዊት በመደብደብ ከፍተኛ ጉዳት አደረሱበት፡፡
የኢትዮጵያ ጦር ግን በዚህ እሳት መካከል ሆኖ እንኳን ተስፋ ሳይቆርጥ በጀግንነት ይዋጋ ነበር፡፡
ብዙውን ጊዜ የያዘውን የነፍስ ወከፍ ጠመንጃውን እየተወ፤ በፉከራ እየገሠገሠ እስከ ጠላት ታንክና መድፍ አፍ ድረስ እየደረሰ በያዘው ሠይፍና ጐራዴ ጠላቱን ይጨፈጭፈው ነበር፡፡
እነዚህን ሞት ምንም የማይመስላቸውን የኢትዮጵያ ጀግኖች ወታደሮችን ደፋርነት በቦታው ያዩ የኢጣሊያን ጋዜጠኞች እጅግ ይገረሙ እንደነበር ተዘግቧል፡፡
በዚህ የውጊያ ቀን፤
  • ከኢትዮጵያ ወገን፤ 1,000 ሞተው፤ 2,000 ደግሞ በአይሮፕላን ቦምብ ቆስለዋል፡፡
  • ከጠላት ወገን ደግሞ፤ 1,500 ሲሞቱ፤ ብዙ ምርኮኞች ተይዘዋል፡፡

Bitewoded Mekonen Demesew
ጀግናው አርበኛ
ቢተወደድ መኮንን ደምሰው
ይህን በጦርነት ፋታ ያላገኘውንና የተጐሣቆለውን የኢትዮጵያ ሠራዊት በጉዞ ላይ ሳለ ሌላ ያልጠበቀው ፈተና ገጠመው፡፡
ይኸውም የራያና ያዘቦ ሕዝቦች፤ አስቀድሞ በኢጣሊያ ስብከትና በሚሰጣቸው ገንዘብ በመደለል፤ የጦር መሣሪያ ሳይቀር እየሰጠ ኢትዮጵያን ከድተው የወገንን ጦር እንዲወጉ ይልካቸው ስለነበር፤ በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ ተኩስ ከፍተው ውጊያ ሲጀምሩ፤ በነዚህ ሰዎች በተተኮሰች ጥይት ሳቢያ፤ አይበገሬው የዐድዋው ጀግና አርበኛ ሙሉጌታ ይገዙ፤ ከ 40 ዓመት የዐድዋ ድል በኋላ በዚህ ጦርነት ላይ በጀግንነት ወደቁ፡፡
በዚህ ለአምስት ቀናት በተካሄደው ጦርነት የተዋጉት ሌላው ጀግና፤ ቢተወደድ መኮንን ደምሰው ሲሆኑ፤
“እኔ የደምሰው ልጅ፤ ምንም ቢሆን ፊቴን ወደ ኋላ መልሼ ጀርባየን ለጠላቴ አላሳየውም::” ብለው፤ እርሳቸው ከመዝመታቸው አስቀድሞ ንጉሠ ነገሥቱ ፊት ይዘው የፎከሩበትን ሻምላ መዘው ጠላት መሽጐ የሚዋጋበት ሸለቆ ውስጥ ገብተው ብዙ የጠላት ወታደሮችን ከረፈረፉ በኋላ በጥይት ተመተው በክብር ወደቁ፡፡
ከእርሳቸውም ጋር ታማኝ አሽከሮቻቸው ሳይቀሩ ለኢትዮጵያ ክብር ሲሉ አብረው ወድቀዋል፡፡
ይህን ሁሉ የጠላት ጦር ጥቃት ለመከላከልና የተረፈውን የኢትዮጵያ ጦር ለመርዳት፤ ራስ ካሣና ራስ ስዩም መንገሻ ሁለተኛውን ዙር የተምቤን ጦርነት ከጠላት ጋር ሲጋጠሙ፤ የጠላት ጦር ብዛት ከኢትዮጵያ ጦር ጋር ሲወዳደር በአራት እጥፍ ይበልጥ ነበር፡፡
Leul Ras Kasa Hailu Dargie
ልዑል ራስ ካሣ
ኃይሉ ዳርጌ
image link
ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉልዑል ራስ ሥዩም መንገሻም የሚችሉትን ያህል ከተከላከሉ በኋላ፤ የጠላት ጦር ያለማቋረጥ በአይሮፕላን፤ የሚያዘንበው
Leul Ras Seyoum Mengesha
ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ
image link
የሙስታርድ ጋስ ቦምብ እጅግ ብዙ የኢትዮጵያ ሠራዊት ስለጨረሰና ጦርነቱን በዚህ ሁኔታ መቀጠሉ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን በመሆኑ፤ ሠራዊቱን ይዘው ወደ ኋላ በመመለስ ከንጉሠ ነገሥቱ ጦር ጋር ተቀላቀሉ፡፡
የኢትዮጵያ ጦር የተሻለ ውጤት የታየበት በሽሬ ግንባር የነበረው በራስ ዕምሩ የሚመራው ሠራዊት ሲሆን፤ በኢጣሊያ በቅኝ ግዛት ወታደሮች ላይ ከፍተኛ ድል በመቀዳጀቱ፤ ራስ ዕምሩ የነበራቸው የተሻለ የጦር አመራር በጣሊያኖች ሳይቀር የተፈራ ነበር፡፡
Leul Ras Immiru
ጠላት የሚፈራቸው ጀግናው
አዋጊ ልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ
ሆኖም የጠላት አይሮፕላን ሳያቋርጥ የሚያዘንበውን የቦምብና የጋዝ መርዝ ተቋቁሞ መዋጋት የማይቻል በመሆኑ፤ የኢትዮጵያ ጦር የሚዋጋበትን ሥፈራ ለቆ ወደኋላ ወደ ተከዜ በመመለሱ ጠላት ሽሬን ሊይዝ ችሏል፡፡
በሰሜን ግንባር በተከፈተው ጦርነት፤ አጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው የኢትዮጵያ ጀግኖችና የጦር ሹማምንቶች በጦርነት መሐል እየገቡና ግንባር ለግንባር በጨበጣ ውጊያ እየተዋጉ በጀግንነት በአንድላይ ወድቀዋል፡፡
በዚህ የሰሜን ጦር ግንባር በጀግንነት ሲዋጉ ከወደቁት የኢትዮጵያ የጦር ጀግኖች መካከል ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
  1. ደጃዝማች መሸሻ ወልዴ
    በዚህ ጦርነት መካከል ሲዋጉ ቆስለው ስለነበረ መጋቢት 15 ቀን 1928 ዓ.ም. አረፉ፡፡

  2. ደጃዝማች በየነ ሀብተ ማሪያም
    በተንቤን ጦርነት በርካታ የኢትዮጵያ ሠራዊት ከጠላት ታንክ፣ ከአይሮፕላን ቦምብና መትረየስ ጋር ሲፋለም በነበረበት ሰዓት፤ ብዙ የኢትዮጵያ ሠራዊት አልቆ፤ የተወሰነው ወደኋላ ሲመለስ፤ደጃዝማች በየነ ግን፤
    “እኔ በየነ ጠላቴን በፊቴ አስቀምጨ ልመለስ አልችልም” በማለት፤ በመጀመሪያ በመድፍና በመትረየስ በሚያስደንቅ አኳኋን ተዋግተው ሲጨርሱ፤ ወዲያው ጐራዴያቸውን መዘው መድፍና መትረየስ በሚያዘንቡባቸው የጠላት ወታደሮች መካከል ገብተው፤ በሳንጃ ሊወጓቸው የሚመጡትን የጠላት ወታደሮች በቅልጥፍና እየቀደሙ ብዙዎችን የጠላት ወታደሮች ጥለው እርሳቸውም በመጨረሻ በጥይት ተመተው ወደቁ፡፡

"በሰላሙም ሆነ በጦርነት ጊዜ አገሩን የሚከዳ ሰው፤ የሙት ሕያው እንደሆነ ይቆጠራል፤ ለአገሩ የሚሞት ሰው ግን፤ ለዘለዓለም ሕያው እንደሆነ ይኖራል፡፡"

ተክለ ጻድቅ መኩሪያ 1961 ዓ.ም.



Italian Troops Advancing to Addis-Ababa
የፋሽስት ኢጣሊያ ጦር አዲስ አበባ ሲገባ
image link
ማይጨው በደቡብ ትግራይ የምትገኝ የወረዳ ከተማ ነች፡፡
በማይጨው ጦር ግንባር የተሰለፈው አዲሱ ኃይል፤ የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘበኛ ጦር ሲሆን ሌላው ከሰሜን ጦር ግንባር አፈግፍጐ ማይጨው ላይ የተደባለቀው ጦር ነበር፡፡ የማይጨው ጦርነት ሲጀመር ጣሊያኖች ሰማዩን በአየር ኃይላቸው ያለእረፍት እንደተቆጣጠሩት ቀጥለውበታል፡፡
በኢትዮጵያ አመራር በኩል ሁኔታወችን በአስቸኳይ ገምግሞ ፈጣን ወታደራዊ ትእዛዝ መስጠቱ ላይ ዳተኝነት እንደታየበት ተዘግቧል፡፡
አዲሱ የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘበኛ ጦር፤ ምንም እንኳን የነበረው የማሸነፍ ዕድል ጠባብ ቢሆንም፤ በነበረው ዕድል ተጠቅሞ በወቅቱ ማጥቃት ሊጀምር አልቻለም፡፡
ምክንያቱም ንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘበኛ ጦር የሚያጠቃበትን ጊዜ ካንዴም ሁለት ጊዜ ሰላስተላለፉት ነበር፡፡
በመጨረሻም መጋቢት 22 ቀን 1928 ዓ.ም. ሠራዊቱ ወደ ጠላት ምሽግ እንዲጠጋ ታዞ፤ ጦርነቱ መጋቢት 23 ቀን 1928 ዓ.ም. ተጀምሮ፤ ያለምንም ፋታ 13 ሰዓት የፈጀ ኃይለኛ ውጊያ ተካሄደ፡፡
ይሁን እንጅ፤ የኢትዮጵያ ጦር በጀግንነት ቢዋጋም ቅሉ፤ ጠላት ከአየር ያለማቋረጥ የሚያዘንበውን የቦምብ ፍላፃና ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሰውን ሙስታርድ ጋስ ሊቋቋመው ስላልቻለ ድሉ የግድ የጣሊያኖች ሊሆን ቻለ፡፡
Damage Incurred by mustard gas
የሙስታርድ ጋስ ቦምብ ከሞት ባሻገር
የሚያደርሰው ጉዳት ይህን ይመስል ነበር

image link
በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ጦር፤ በለመደው መልኩ መዋጋት ስላልቻለ፤ በየቦታው መበታተን ጀመረ፡፡
የኢጣሊያ ጦርም በየሥፍራው በተበታተነው የኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ በአይሮፕላን የሙስታርድ ጋስ ቦብ በመጠቀም ያለርሕራሔ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰበት፡፡

ከዚህ አሳዛኝ ሽንፈት በኋላ የደሴ መንገድ ለጣሊያኖች ክፍት ስለነበረ፤ ጣሊያኖች በደሴ በኩል ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም. ሰተት ብለው ያለአንዳች ከልካይ አዲስ አበባ መግባት ችለዋል፡፡

በውጊያው መጀመሪያ ቀናት በአንዳንድ የውጊያ ቀጠናዎች ላይ የኢትዮጵያ ሠራዊት ድሎችን ማስመዝገብ ቢችልም ቅሉ ያለማቋረጥ በተከታታይ እንደዝናብ የሚወርደውን የጠላትን የአይሮፕላን ድብደባ ፈጽሞ ሊቋቋሙት አልቻሉም፡፡
የኢጣሊያ ጦር፤
  1. በድርጅት፣
  2. በወታደራዊ አመራር፣
  3. በአየር ኃይል፣
  4. በጦር መሳሪያዎች አይነትና ብዛት፣
  5. በሎጂስቲክ አቅርቦት፣
  6. በሕክምና አገልግሎቶች፣
  7. በመጓጓዣ እና፣
  8. በግንኙነት መሣሪያዎች እና በመሳሰሉት
እስከ አፍንጫው ድረስ በመታጠቁ ያለጥርጠር የኃይል ሚዛኑ ወደ ጣሊያኖች ያደላ ነበር።
በተጨማሪም የቅኝ ገዥ አገሮች ኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ ከውጭ እንዳታስገባ ማዕቀብ በመጣላቸው ምክንያት የኢትዮጵያ ጦር ከፍተኛ ችግር ገጥሞት ነበር፡፡

Haile Selassie at Wuchale
ንጉሠ ነገሥቱ በማይጨው ጦር ግንባር
image link
የራያና ዘቦ ተወላጆች በጠላት አሳሳች ፐሮፓጋንዳ ምክንያት ተወናብደው ስለነበረ፤ የነራስ ሙሉጌታ ይገዙ ከሰሜን ጦር ግንባር መመለሳቸውን በተመለከቱ ጊዜ፤ በየጫካውና በየቁጥቋጠው ሥር እየተደበቁ በተመላሹ ጦር ላይ ተኩስ በመክፈት ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል፡፡
በዚህም ሳቢያ፤ ከኮረም ወደ ማይጨው ጦር ግንባር በመጓዝ ላይ የነበሩት የኢትዮጵያ ወታደሮች፤ በራሳቸው ወገኖች በደረሰባቸው ያልታሰበ ጥቃት ምክንያት የተገደሉትን የኢትዮጵያ ወታደሮችን ሬሣ በየሥፍራው ወድቆ በመመልከታቸው ከፍተኛ ሀዘን እየተሰማቸው ጉዞውን ቢቀጥሉም ቅሉ ይህ ወገን በወገኑ ላይ የደረሰው ያልታሰበ ጥቃት በውጊያ ሞራሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ሆኖ በመገኘቱ በዚህ ምክንያት ነገሩ ሁሉ እንደተበላሸ የተገነዘቡት ንጉሠ ነገሥቱ፤ የተረፈውን ጦር አሰልፈው፤ ራሳቸው የጦሩ ጠቅላይ አዛዥና መሪ ሆነው ለመዋጋት ወሰኑ፡፡
በዚህም መሠረት ንጉሠ ነገሥቱ፤ ከሰሜን ጦር ግንባር የተመለሱትን፤
Ethiopian Imperial Guard
የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘበኛ ጦር
Credit to: abyssiniancrisis
እና በተጨማሪም ኮረም ላይ ከየቦታው የተጠረቃቀመው ጦር በየግንባሩ ተመድቦ፤ የካቲት 21 ቀን 1928 ዓ.ም. ወደ ማይ ጨው ጦር ግንባር ጉዞ ተጀመረ፡፡
ንጉሠ ነገሥቱም በማይጨው ጦር ግንባር ደርሰው፤ በተፋፋመው ጦርነት መካከል በመገኘት አጠገባቸው ካሉት ቆራጥ ወታደሮቻቸው ጋር በመሆን ለመሞት ቆርጠው እየተዋጉ ወደፊት ይገሠግሡ እንደነበር ተዘግቧል፡፡
ይህን ድርጊት የተመለከቱ የንጉሠ ነገሥቱ መኳንንቶችና የቤተክርስቲያን አባቶች፤ ንጉሠ ነገሥቱ በጦርነቱ መሐል ቢሞቱ፤ በአገሪቱ ላይ ከባድ ቀውስና አደጋ ሊፈጠር እንደሚችል በመገንዘብ፤ ከፊታቸው እየቀደሙ በእግዚአብሔር ስም ለምነዋቸዋል፡፡
እርሳቸው ግን አልመለስም ብለው ወደፊት ሲገፉ፤ የቤተክርስቲያን ቀሳውስት ወዲያውኑ የሥላሴን ስም በመጥራት ገዘቷቸው፡፡
Etalian tank captured by Ethiopian troops
በንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘበኛ
ጦር የተማረከው የኢጣሊያ ታንክ
Credit to: abyssiniancrisis

ዙሪያቸውን የነበሩት ከፍተኛ የጦር አለቆቻቸውም፤ ኢጣሊያ ዛሬ ጊዜ እንዳገኘ ሁሉ እኛም ጊዜ እናገኛለንና ወደኋላ ተመልሰን ጊዜ ወስደን እንዋጋ ብለው አስረዷቸው፡፡
ሆኖም ንጉሠ ነገሥቱ፤
“ እኔ የመጣሁት ድል አደርጋለሁ ብዬ አይደለም፡፡ ድል ባላደርግም፤ ሕይዎቴ እስኪያልፍ ድረስ እንድዋጋ ነውና የፈቀደ፤ ከእኔ ጋር ይሙት፡፡ ይልፈቀደ፤ ይሂድ እንጅ ወደኋላ አልመለስም፡፡ ”
ብለው እምቢ አሉ፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ኮረም ተመልስው እንደገና ለመዋጋት ባሰቡ ጊዜ፤
 ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ
 ብፁዕ እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ
 ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ
 ደጃዝማች ወልደ አማኑኤል
 ራስ ብሩና
Emperor Haile Selassie is shown stepping on musatred gas bomb
ንጉሠ ነገሥቱ በማይጨው
ጦር ግንባር የወደቀውን
የሙስታርድ ጋስ ቦምብ ሲመለከቱ

image link
ሌሎችም መኳንንቶች አንድ ላይ በመሆን፤ንጉሠ ነገሥቱ ኮረም ላይ መዋጋትና መሞት ጠላትን ከመጥቀም በስተቀር ለኢትዮጵያ እንደማይበጃት አስረድተው ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ለመኗቸው፡፡
ንጉሠ ነገሥቱም፤
“እኔ መመለሴ ለሕይዎቴ ሳስቸ ሳይሆን ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ጥቅም ሲባል ያደረጋችሁት ለመሆኑ ቃል ግቡልኝ፡” ብለው ሲጠይቁ፤ ጳጳሱ ቃል ስለገቡላቸው ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ወሰኑ፡፡
በመጨረሻም ንጉሠ ነገሥቱ፤ በሚወዷቸው ታማኝ ወታደሮቻቸው ታጅበው፤ በኮረም፣ በየጁ፣ በወሎና በፍቼ አድርገው ከሁለት ወር የማይጨው ዘመቻ ቆይታ በኋላ፤ ፋሽስት ኢጣሊያ አዲስ አበባን ከመቆጣጠሩ ከ5 ቀናት ቀደም ብለው ሚያዝያ 22 ቀን 1928 ዓ.ም. ኀሙስ ቀን ከጧቱ በ3 ሰዓት አዲስ አበባ ገቡ፡፡

Maichew_War_Front



Dejazmach Nasibu Zeamanuel
ደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል
  1. የሐረርጌን ጦር በሙሉ አዝማች ሆነው የተመደቡት፤ ደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል
    (የጦር አለቃ ሆነው በአዝማችነት ሞያ እውቅና ስላልነበራቸው፤ በእርሳቸው ስር ሆነው ትእዛዝ ተቀብለው እንዲዋጉ የተሰለፉት የጦር አለቆች ጋር መናናቅና አለመከባበር በመኖሩ ያለአግባብ ጊዜ በከንቱ ይባክን እንደነበረ ተነግሯል፡፡)
  2. ደጃዝማች መኮንን እንዳልካቸው፤ የኢሉባቦር ጦር በሙሉ አዝማች ሆነው የተመደቡ፤
  3. ደጃዝማች ሀብተ ሚካኤል ይናዱ፤ የኮሎ ጦር በሙሉ አዝማች ሆነው የተመደቡ፤
  4. ራስ ደስታ ዳምጠውበሲዳሞ በኩል የጦሩ አዝማች ሆነው የተመደቡ፤
  5. ደጃዝማች አበበ ዳምጠው፤ (የራስ ደስታ ዳምጠው ወንድም) የጐፋና የባኮ ጦር በሙሉ አዝማች ሆነው የተመደቡ፤
  6. ደጃዝማች በየነ መርድበባሌ በኩል የጦሩ አዝማች ሆነው የተመደቡ፤

ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር መንስዔ የሆናት የወልወል ግጭት

ወልወል፤ በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት በምስራቅ ኦጋዴን አውራጃ በዋርዴር ወረዳ የሚገኝ፤ በኢትዮጵያ ግዛት ሥር የሚተዳደር ሥፍራ ነው፡፡
ወልወል የሚገኝበት ሥፍራ ጠረፍ እንደመሆኑ፤ በሥፍራው የነበረው የኢትዮጵያ የማዕከላዊ አስተዳደሩ የድንበር ቁጥጥር የላላ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ መንግሥትና በኢጣሊያ መንግሥት መካከል በ1920 ዓ. ም. በኦጋዴን በኩል የወሰን ስምምነት ተደርጎ ነበር፡፡
በተጨማሪም የእንግሊዝ መንግሥት እና የኢትዮጵያ መንግሥት በኢትዮጵያ ግዛት ያለውን ወሰን በደንብ ለማካለል ስምምነት አድርገው ነበር፡፡
ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር በተደረገው የወሰን ማካለል ስምምነት መሠረት፤ የእንግሊዝ መንግሥትና የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካዮች ኦጋዴን ውስጥ በወልወል በኩል አልፈው በሁለቱ መንግሥታት ድንበርተኛ የሆኑ ነገዶች ከብቶቻቸው የሚግጡበትንና ውሀ የሚጠጡበትን የመሬት ወሰን ለማካለል በተንቀሳቀሱበት ወቅት፤ ሶማሌን ያስተዳድሩ የነበሩት ጣሊያኖች የውሀውን ሀብት በመረዳት በሁኔታው ተደፋፍረው ወልወል ላይ መተላለፊያ በመከልከል 130 ኪሎ ሜትር ያህል ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ወደ ውስጥ ገብተው ምሽግ ገነቡ፡፡
በኋላም የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ወታደሮቹን በማስፈር አካባቢውን መቆጣጠር ሲጀምር፤ ጣሊያኖች ሥፍራውን አናስነካም በማለት ኅዳር 26 ቀን 1927 ዓ. ም. በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ተኩስ መክፈት ሲጀመሩ የወልወል ግጭት መከሰት መንስኤ ሆነ፡፡
በኢትዮጵያ በኩል በዚህ ድንገት በተከሰተው በወልወል ግጭት ምክንያት የኢጣሊያ መንግሥት ቀደም ብሎ ተዘጋጅቶበት ስለነበረ፤ ለውጊያ ባልተዘጋጀው የኢትዮጵያ እግረኛ ወታደሮች ላይ ጦርነት በመቀስቀስ ኢጣሊያ በአይሮፕላን ቦምብና በእግረኛ ወታደሮች ጭምር በመታገዝ ከፍተኛ ጉዳት አድርሳለች፡፡
በዚህም ጦርነት፤ 107 የሚሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሞተዋል፡፡ በኢጣሊያ ወታደሮችም በኩል፤ 75 የኢጣሊያ ወታደሮች ሲሞቱ 70 የሶማሊያ ወታደሮች ሞተዋል፡፡
ኢጣሊያ፤ በሰሜን የኢትዮጵያ ግንባር ካደራጀው ጦር ሌላ፤ በሶማሌ ግንባርም እንዲሁ ጀነራል ግራዚያኒ ሌሎች በርካታ ጀነራሎችን በሥሩ በመያዝ፤ ከኢጣሊያ ወታደሮች ጋር፤ የሊቢያንና የሶማሊያን የቅኝ ግዛት ወታደሮችን ጨምሮ ኢትዮጵያን እንዲወጋ ታዞ ነበር፡፡
በሰሜን በነበረው የኢትዮጵያ ጦር ግንባር በኩል፤ ደጃዝማች ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ፤ አገሩን፣ ወገኑንና የራሱን ኢትዮጵያዊነት ክዶ በሰሜን የኢጣሊያ ጦር አዛዥ ከሆነው ከጀነራል ደቦኖ ጋር እንደተደባለቀ ሁሉ፤ በኦጋዴን በኩልም እንዲሁ ወሎል ጂሌ የተባለው የኢትዮጵያን መንግሥት ከድቶ ከግራዚያኒ ጦር ጋር ተሰልፎ ወገኖችን ይወጋ ነበር፡፡
በሶማሌ ግንባር በኦጋዴን በኩል ጠላትን ለመከላከል የተሰለፈውን የኢትዮጵያ ጦር ይመሩ የነበሩት ዋና የጦር አዛዥና የሐረር ገዥ ደጃዝማች ነሲቡ ወልደ አማኑኤል ነበሩ፡፡

ደጃዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት በኦጋዴን የፈፀሙት የጀግንነት ገድል

Dejazmatch Afework Wolde Semayit
የቆራሔው ጀግና ደጃዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት
በሶማሌያ ጠረፍ በቆራሔ በኩል የነበረውን የኢጣሊያ ጦር ከወታደሮቻቸው ጋር ሆነው ከአንድ ዓመት በላይ መሽገው ይከላከሉ የነበሩት ስመ ጥር አርበኛ ግራዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት ነበሩ፡፡
ዋናው ጦርነት ሲጀመርም፤ አፈወርቅ ወልደሰማያት በምሽጋቸው ሆነው በጀግንነት እየተከላከሉ ብዙ የኢጣሊያ ወታደሮች ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡
የግራዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት የጀግንነት ዝና በግንባሩ በነበሩት የኢጣሊያና የሶማሌ ወታደሮች ዘንድ በጣም ገኖ ይወራ ነበር፡፡
በግንባሩ የኢጣሊያ ጦር አዛዣ የነበረው ግራዚያኒ፤ ወደ ጦር ግንባር ብዙ የኢጣሊያ እግረኛ ሠራዊት ሲልክ፤ አፈወርቅ ወልደሰማያት ድል እያደረጉ ሰለሚመልሱት፤ በሶማሌ የነበረውን አይሮፕላን በሙሉ አስነስቶ ምሽግ ውስጥ የነበሩትን የኢትዮጵያ ወታደሮች ያስደበድብ ጀመር፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ጀግናው አፈወርቅ ወልደሰማያት፤ የሚዋጉበትን መሣሪያ አስቀምጠው፤ በምትኩ የመድፍ መሣሪያ ይዘው እየተንከባለሉ በቆራጥነት ሲዋጉ በአይሮፕላን ቦምብ ተመተው ቆሰሉ፡፡
ጀግናው አፈወርቅ ወልደሰማያት ቆስለውም ቢሆን በቆራጥነት እየተዋጉ ሳላ ቁስላቸው የበረታ ስለነበረ ወታደሮቻቸው አይተው፤ ከነበሩበት ቦታ አንስተው ወደ ሌላ ስፍራ እንውሰድዎት ሲሏቸው አሻፈረኝ ካሉ በኋላ፤
“እስካሁን ድረስ ከጠላት ጋር በጽኑ ተከላክለን ባቆየነው ምሽግና እናንተ የጦር ጓደኞቸ በምትዋጉበት መካከል አስቀምጡኝ፡፡
ስሞትም ከአይሮፕላን አደጋ ለመከላከል በተቆፈረው ጉድጓድ ቅበሩኝ እንጅ አደራችሁን ከዚህ ስፍራ ወደ ሌላ እንዳትወስዱኝ፡፡”
በማለት ለወታደሮቻቸው ነገሯቸው፡፡
ንግግራቸውን ጨርሰው ጥቂት እንደቆዩ ሕይወታቸው አለፈ፡፡
የቆራሔው ጀግና አፈወርቅ ወልደሰማያት በተወለዱ ገና በ30 አመት የለጋ እድሜያቸው ለአገራቸው ነፃነት መከበር ከጠላት ጋር በቁርጠኝነት ሲፋለሙ በጠላት ጥይት ተመተው ወደቁ፡፡
በኋላም እንደወንድሞቻቸው ያዩዋቸው የነበሩት ወታደሮቻቸው በምሬት እያለቀሱ በዚያው ሥፍራ ቀበሯቸው፡፡

ይህን የግራዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያትን የጀግንነት ገድል የሰሙት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፤ ቦታው ድረስ በመሄድ ለነበረው የኢትዮጵያ ሠራዊት የማበረታቻ ንግግር ካደረጉ በኋላ፤ በፊታውራሪ ጓንጉል ኮላሴ መሪነት ተዋግተው አራት ታንክና በመኪና ላይ የተጠመደ መትረየስ የማረኩትን የኢትዮጵያ ወታደሮችና በውጊያ ወደቆሰሉት ወደ ፊታውራሪ ጓንጉል ሄደው ሽልማት በመሸለም አበረታቷቸዋል፡፡
ከዚያም ግራዝማች አፈወርቅ ወደተቀበሩበት ሥፍራ ድረስ በመሄድ በመቃብሩ ላይ የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል፡፡
እንዲሁም ለግራዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት የደጃዝማችነት ማዕረግ፤ ለደጃዝማች አፈወርቅ ልጅና ለሌሎችም በጦርነቱ የጀግንነት ሥራ ለሠሩ ወታደሮች ሁሉ የማዕረግ ስምና ሽልማት ሰጥተው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል፡፡

የግራዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት መሞት ለኢጣሊያ ሠራዊት እፎይታን ስለሰጠው፤ አዲስ ጦር ልኮ በአይሮፕላን ቦምብ በማስደብደብ በመጨረሻ ሥፍራውን ለመያዝ ችሏል፡፡

ምንጭ፤
  1. "የኢትዮጵያ ታሪክ - ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ"  ደራሲ፡- ተክለ ጻድቅ መኩሪያ 1961 ዓ.ም.
  2. "የኢትዮጵያ ታሪክ ከ 1847 እሰከ 1983"  ደራሲ፡- ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ
  3. "የታሪክ ማስታወሻ"  ደራሲ፡- ደጃዝማች ከበደ ተሰማ 1962 ዓ.ም.
  4. "ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ - ፩ኛ መጽሐፍ"  ደራሲ፡- ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት 1928 ዓ.ም.