Content-Language: am ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ገጽ አንድ
header image

(ድረ ገጽ 1)


Minilk
The image is digitally edited by the webmaster


ዳግማዊ አፄ ምኒልክ





የዳግማዊ አፄ ምኒልክ የአስተዳደር፣ የሥልጣኔና የዐድዋ ድል ታሪክ

በአሥር የተለያዩ አርዕስቶች ተከፋፍሎ የቀረበውን ትረካ በእያንዳንዱ አርዕስት ሥር የሚገኘውን የድምጽ ማጫወቻ በመጠቀም ትረካውን ማዳመጥ ይችላሉ
ክፍል አንድ

ትወልድ፣ ከመቅደላ መጥፋትና
የግዛት አንድነትን ማስከበር

ክፍል ሁለት

የዳግማዊ አፄ ምኒልክ የአመራር
ጥበብና ዲፕሎማሲያዊ ብልሃት

ክፍል ሶስት

ፋሽስት ኢጣሊያ ከዓድዋ ጦርነት በፊት
የመረብን ወንዝ ተሻግሮ እንዴት ሊገባ ቻለ?

ክፍል አራት

የሐማሴንና የትግራይ መኳንንቶች ክህደት፣ የኤርትራ
በኢጣሊያ መያዝና የውጫሌ ውል ያስከተለው መዘዝ

ክፍል አምስት

በዐድዋ ጦርነት ዋዜማ የኢጣሊያ
ሰላዮች ፕሮፓጋንዳና ከፋፍሎ የመግዛት ሤራ

ክፍል ስድስት

የአምባላጌ ጦርነትና የመቀሌን ምሽግ ለማስለቀቅ
የእቴጌ ጣይቱ የጦር አመራር ብልሀት

ክፍል ሰባት

በዐድዋ ጦርነት የፋሽስት ኢጣሊያ ጦር እና
የኢትዮጵያ ሠራዊት አሠላለፍ፣
የአድዋ ጦርነት መጀመር

ክፍል ስምንት

ስለአድዋ ጦርነት በኢትዮጵያ የታሪክ ጸሐፍያን
ዕይታ፣ ከድሉ በኋላ የኤርትራ ጉዳይና
የአድዋ ድል ገፅታ በዓለም አደባባይ

ክፍል ዘጠኝ

ከአድዋ ድል በኋላ የተከናወኑ ሁኔታዎችና
በዐድዋ ጦርነት ስለተማረኩ
የኢጣሊያ ወታደሮች አያያዝ

የመጨረሻ ክፍል

የዳግማዊ አፄ ምኒልክ የግል ባሕርያት፣
ልዩ ልዩ ችሎታዎች፣ የምኒልክ መታመምና
ሕልፈተ ሕይዎት




ምኒልክ ከአባታቸው ከኃይለ መለኮት ሣህለ ሥላሴ እና ከናታቸው ከወይዘሮ እጅጋየሁ ለማ ቅዳሜ ነሐሴ 12 ቀን 1836 ዓ.ም ሰሜን ሸዋ በሚገኛው አንጎለላ በተባለው ስፍራ ተወለዱ፡፡
ምኒልክ ከተወለዱ በኋላ መንዝ ውስጥ በእናታቸው ሞግዚትነት ሰባት አመት ተቀመጡ፡፡
አፄ ቴዎድሮስ የምኒልክን አባት ኃይለ መለኮትን ለማስገበር ወደ ሸዋ በዘመቱ ጊዜ ኃይለ መለኮት ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር ሳይዋጉ በህመም ስለሞቱ ልጃቸውን ምኒልክን ማርከው ይዘዋቸው ሄዱ፡፡
ምኒልክ በአፄ ቴዎድሮስ ከተማረኩ በኋላ፤ ከ1847 ዓ.ም እስከ 1857 ዓ.ም. ድረስ ከአጎታቸው ከርዕሰ ርዑሳን ዳርጌ ሳህለ ሥላሴ፣ የምኒልክ እናት ከወይዘሮ እጅጋየሁ እና ከሌሎች እስረኞች ጋር ለ10 ዓመታት ያህል አፄ ቴዎድሮስ ዘንድ ታስረው ነበር፡፡
ምኒልክ ሲማረኩ የ11 ዓመት ልጅ ሲሆኑ አጎታቸው ዳርጌ ሳህለ ሥላሴ ደግሞ የ28 አመት ወጣት ነበሩ፡፡
አፄ ቴዎድሮስ ምኒልክን መቅደላ በሚገኘው ቤተ መንግሥታቸው ከወሰዱ በኋላ እነደ እስረኛ ሳይሆን እነደ ልጃቸው አድርገው ተንከባክበዋቸዋል፡፡
አንድ የውጭ አገር ጸሐፊ ምኒልክ ይደረግላቸው ስለነበረው እንክብካቤ አጫወቱኝ ብሎ እነደጻፈው፤
“አፄ ቴዎድሮስ፣ አባቴ ከሞቱ በኋላ ወደ ቤተ መነግሥታቸው ወሰዱኝ፡፡
ልክ እንደ ልጃቸው አድርገው ይወዱኝ ነበር፡፡
በታላቅ ጥንቃቄም አስተምረውኛል፡፡
ከልጃቸው ሳይለዩ አሳድገውኛል፤ ብለዋል፡፡”
በማለት ገልጾታል፡፡

አለቃ ገብብ ሥላሴ የተባሉ ጸሐፊ ደግሞ፤
“ምኒልክን የደጃዝማችነት ማዕረግ ሰጥተውና ጭፍራ (አጃቢ) በመመደብ በታላቅ ክብር አኖሩት፡፡ ሳይዋረድ፣ መከራ ሳይደርስበት በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ለ10 ዓመታት ተጠብቆ ኖረ፡፡”
በማለት ጽፈዋል፡፡
ዳግማዊ ቴዎድሮስ ልጃቸውን ወይዘሮ አልጣሽ ቴዎድሮስን ድረውላቸው ነበር፡፡



በቤተ ክህነት ሊቅነታቸው፣ ከ20 በላይ መጽሐፍትን በመድረሳቸውና በነበራቸው የቤተ ክህነትና የታሪክ እውቀታቸው ከዓለም ሊቃውንት ጋር የሚወዳደሩ እውቁና የተከበሩት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በጽሁፋቸው እንዳመላከቱን፤ ምኒልክ ከመቅደላ አምልጠው የሄዱበት ቀን ሰኔ 24 ቀን 1857 ዓ.ም. ሲሆን እድሜያቸውም 21 ዓመት እንደነበረ ገልፀውልናል፡፡
ምኒልክ በዳግማዊ ቴዎድሮስ ወደ መቅደላ ታስረው ሲወሰዱ አብረው የነበሩት አጎታቸው ዳርጌ ሣህለ ሥላሴ ነበሩ፡፡
አፄ ቴዎድሮስ ለዳርጌና ለወጣቱ ምኒልክ፤ የተለየ ፍቅርና ታላቅ አክብሮት ያሳዩአቸው ነበር፡፡
በተለይ ዳርጌ ለሚያሳዩት ጥረት አፄ ቴዎድሮስ አድናቆት ነበራቸው፡፡
በመጨረሻም ምኒልክ ከመቅደላ ጠፍተው እንዲሄዱ የረዷቸው ዳርጌ ነበሩ፡፡
ዳርጌም በእንግሊዝ ወታደሮች ከታሰሩበት ተፈተው ሲለቀቁ ወደ ሸዋ ተመልሰዋል፡፡

Emperor Menelik Palace at Entoto Hill
ዳግማዊ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ በ 1883 ዓ.ም.
ይኖሩበት የነበረው የእንጦጦ ቤተ መንግሥት
ምኒልክ ነሐሴ 24 ቀን 1858 ዓ.ም. በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት፣ በተወለዱ በ 22 አመታቸው “ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ሸዋ” ተብለው በአያታቸው በሸዋው ንጉሥ ኃይለ መለኮት ምትክ የአገዛዝ ሥርዎ መንግሥቱን ወረሱ፡፡
ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በሕይዎት እያሉ ነው ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ራሳቸውን ንጉሠ ነገሥት ብለው የሠየሙት፡፡
የሸዋ ንጉሥ ሲሆኑ የረዷቸውና ያስተባበሩላቸው አብሮ አደግ ጓደኛቸውና የቱለማ ኦሮሞ መሪ የዳጨ ልጅ የሆኑት ጎበና ዳጨ ናቸው፡፡
የሸዋ ንጉሥ የነበሩት የዳግማዊ አፄ ምኒልክ አያት ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ሲሞቱ የሸዋ ግዛት (አንኮበርን ጨምሮ መንዝና አካባቢው) በየባላባቱ ተከፋፍሎ እያንዳንዱ ባላባት ለማንም የማይበገር ራሱን የቻለ ትናንሽ መንግሥት ቢጤ ሆኖ ነበር፡፡
ጎበና ዳጨ የዳግማዊ አፄ ምኒልክን ግዛት ለማስፋፋት ያዘጋጁና ያመቻቹ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ወይዘሮ ጣይቱን ያገቡት በ30 ዓመት እድሜያቸው ነበር፡፡



ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በነገሡበት ወቅት፤ የፈረንሳይ የኢጣልያ የእንግሊዝና የግብፅ መንግሥታት አፋርን ለመያዝ እርስ በርስ ይሻኮቱ ስለነበር፤ አፋር በቅኝ ገዥዎች እጅ እንዳትወድቅ ለማድረግ ሲሉ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዲፕሎማሲያዊ ዘዴ በመፍጠር፤
“አባቶቸ ይገዙት የነበረውን የአዳልን ግዛት መልሼ ስለያዝኩት ደስ ብሎኛልና ደስ ይበላቸሁ፡፡”
በማለት ለእያንዳንዳቸው የቅኝ ገዥ መንግሥታት ደብዳቤ ጽፈውላቸዋል፡፡
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ይህን ደብዳቤ ለቅኝ ገዥ መንግሥታት የጻፉበት ምክንያት፤ አውሮፓውያኑ እንደተመኙት የአፋርን ግዛት እንይዛለን ቢሉ፤ የአፋር ግዛት የኢትዮጵያ መሆኑንና ገዥውም እርሳቸው እነደሆኑ እንዲያውቁ፤ ነገር ግን ቅኝ ገዥዎች ጦርነት እንገጥማለን ቢሉ ጦርነቱ ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጋር እንደሚሆን ስላሳወቋቸው አፋር በሰላም የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ግዛት ሆኖ ቀጠለ፡፡
በዚያን ጊዜም የሱዳን መሀዲስቶች፤ በሱዳንና በኢትዮጵያ ድንምበር የሚገኘውን መተማን ይዘው ኢትዮጵያን ለመውረር ተዘጋጅተው ነበር፡፡
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከመጀመሪያው ጀምረው ነገሮችን ሁሉ በሰላም የመጨረስ ፍላጎት ስለነበራቸው፣ በሸዋ አካባቢ ላሉት ለተከፋፈሉት የኦሮሞ ባላባቶች፤
“ያሳደጋችሁኝ ልጃችሁ፣ አብረን ያደግን ባልንጀራችሁ ነኝና በአባቴ አልጋ ከተቀመጥኩ በፍቅር ተገዙልኝ፡፡”
ይሉ ነበር፡፡
ጎበናም ለባላባቶቹ፤ ለማዕከላዊው መንግሥት ለዳግማዊ አፄ ምኒልክ በየአመቱ ግብር ከከፈሉ ግዛታቸውና ባላባትነታቸው እንደማይነካ፣ ይገልጹላቸው ነበር፡፡
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በሰላማዊ መንገድ እያሳመኑ አብዛኛውን የሸዋ ኦሮሞ ግዛት ይዘው ነበር፡፡
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የቀሩትን የኢትዮጵያ ግዛቶች አብዛኛዎቹን በሰላማዊ መንገድ፣ ጥቂቶችንም በጦርነት እያሸነፉ ወደ ኢትዮጵያ ማዕከላዊ ግዛት አሰገቧቸው፡፡
በተለይ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ኢጣሊያ ቢችሉ አንዳቸው በመላ ኢትዮጵያን ጠቅልለው ለመያዝ፣ ባይቻሉ ደግሞ በኢትዮጵያ ዙሪያ የያዙትን መሬት እያስፋፉ እያንዳንዳቸው ኢትዮጵያን ከፋፍሎ የመያዝ ሀሳብ ነበራቸው፡፡

በተለይ ኢጣሊያ የትግራዩን ራስ መንገሻ ዮሐንስን አባብሎ በመያዝ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ላይ እንዲያምፁ በከፍተኛ ደረጃ በመገፋፋት በሁለቱ መካከል ጠብ እንዲነሳ ካደረገች በኋላ ኢጣሊያ ለራስ መንገሻ፤
“ወዳጅ ነን” በማለት ከፋፋይ የሆነ ደብዳቤ በመጻፍ፤ “…ራስ መንገሻን የሚጠላ ጠላታችን ነው፡፡ ራስ መንገሻን የሚወድ ወዳጃችን ነው…” የሚሉ የሽንገላ ቃላትን የያዘ ውል ህዳር 29 ቀን 1884 ዓ.ም. መረብ ላይ በመዋዋል መሰሪ የሆነ ውል እንዲዋዋሉ አድርገዋል፡፡
ይሁን እንጅ ራስ መንገሻ ይህን ውል የተዋዋሉት፤ ዳግማዊ አፄ ምኒልክን ለማናደድ አስበው እንጅ ጣሊያኖችን ለመጥቀምና ኢትዮጵያን ለመጉዳት አልነበረምና በመጨረሻ ነገሩን ሲያስቡበት ድርጊታቸው የአፄ ዮሐንስን እና የትግራይን ሕዝብ ስም የሚያጠፋ መሆኑን በመረዳታቸው በድርጊታቸው በመፀፀት ይቅርታ ጠይቀው የዳግማዊ አፄ ምኒልክን ንጉሠ ነገሥትነት መቀበላቸውን ራሳቸው በጻፉት ጽሁፍ አረጋግጠዋል፡፡
ጣሊያኖች አሁንም ቢሆን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ በመግባትና ጦርነት በመክፈት በውጊያ እያሸነፉና ጉዳት እያደረሱ ሀገር ለመያዝ የሚያደርጉት ሙከራ በሰፊው ቀጥሎ ነበር፡፡
በኢጣሊያ የጦር ጀነራል በባራቴሪ የሚመራ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ ትግራይ ድረስ ገብቶ ከትግራይ ገዥ ከራስ መንገሻ ዮሐንስ ጋር በመዋጋት ጉዳት አድርሰዋል፡፡
ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያን ከድተው ወደ ኢጣሊያ የገቡትን እንደ ደጃዝማች ሐጎስ ተፈሪ የመሰሉ ባንዳዎችን ሳይቀር በትግራይ ምድር በመሾምና የጦር ምሽግ በመስራት መቀሌን ተቆጣጥሯል፡፡
ይህም ኢጣሊያ፤ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመቆጣር መሀል አገር ድረስ ዘልቆ በመግባት የወሰደው እርምጃ ለአድዋ ጦርነት መቀስቀስ መንስኤ መሆን ቻለ፡፡
  1. በሸዋ ውስጥ በቆየው የጥንት ሥርዓት ወስጥ፤ ጥፋት የተገኘበት ሰው፣ እጁን ታስሮ፣ ገንዘቡን ተወርሶ መሬቱ ይሸጥ ነበር፡፡
    ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ግን፣ የፍትሐ ነገሥት ሥርዓትን ተመልከተው፤
    “…ምንም ብታጠፋ ገንዘብህ ይወረስ እንጅ ከመሬትህ አትነቀል፡፡” የሚል አዋጅ አስነግረውና ተቀምተው የኖሩትን የጥንት ግዛታቸውን ሁሉ በማስመለስ፤ ግዛታቸውን የቀሟቸውንም ሁሉ አስማምተው፣ አዛምደውና በትዳር አስተሳስረው ከነባር የሸዋ ባለርስቶች ጋር አንድ ሕዝብ ሆኖ በኑሮው ተስማምቶ እንዲኖር አድርገዋል፡፡
  2. ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከነበራቸው ጠባይና ችሎታ ውስጥ ዋነኛው ችሎታቸው፤ በየባላባቱ የግዛት አስተዳደር ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ አለመግባታቸው ነበር፡፡
  3. ለማእከላዊ መንግሥት አልገብርም ካሉት ባላባቶች ጋር፤ በመጀመሪያ በሠላማዊ መንገድ እንዲቀበል ተደጋጋሚ ጥረት ያደርጋሉ፡፡
    በሠላማዊ መንገድ ጥረት ተደርጎ አልሳካ ሲል፤ በጦርነት አሸንፈው ዋናውን ባላባት ማርከው ሲይዙ፣ ያንኑ ቀድሞ የነበረውንና የተማረከውን ባላባት ወይም የባላባቱን ልጅ በራሱ አገር ላይ መልሰው ይሾማሉ፡፡
  4. ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በባላባቱ አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ የሚገቡት ተሿሚው የራሱን ሕዝቡ ሲበድል ብቻ ነው፡፡
    የሚሾም ባላባትም ከሌለ ሕዝቡን ሰብስበው የአገሩ ተወላጅ የሆነውን መሪውን እንዲመርጥ አድርገው ሾመው ይሄዳሉ፡፡
  5. ዳግማዊ አፄ ምኒልክን ገድለው መንግሥታቸውን ለመገልበጥ የተነሱት ሰዎች ተይዘው ሲጠየቁ ድርጊታቸውን ካመኑ በኋላ ሸንጎው የሞት ፍርድ ሲፈርድባቸው፣ እርሳቸው ግን የሞት ፍርዱን ሽረው በእስራት ይቀይሩላቸዋል፡፡
  6. ትግራይን እንዲያሰተዳድሩ የተሾሙት ገዥዎች በአብዛኛው ዳግማዊ አፄ ምኒልክን በተደጋጋሚ እየከዱ ሲያስቸግሩ ያየው ሕዝብም በትግሬዎች ላይ ቂም ይዞ መሳደብ ጀምሮ ነበር፡፡ ይህን የሕዝቡን አጉል ስሜት የተረዱት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፤
    (አንዳንድ ሰዎች አባባሉን ቢክዱም)፤
    …“አኔን የሚወደኝን የትግሬን ሰው ታስቀይማለህ አሉ፡፡
    …በአደባባይ ያለውን የትግሬን ሰው የሚያስቀይምን ሰው ይዘህ አምጣልኝ፡፡”

    የሚል አዋጅ አሳውጀዋል፡፡
  7. እስከ ሩዶልፍ ሀይቅ ድረስ የተጓዘው ውልቤ የተባለው ጸሀፊ፤

    “...በጠረፍ ያሉት ሰዎች ሁሉ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጥሩ ሰው እንደሆነ ያውቃሉ፡፡
    ...ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሁሉም ሰው በሐይማኖቱ ይደር ሰላለና በሕዝቡ መሀል አድሎና የኃይል ሥራ ስለማይሠራ ይወዱታል፡፡
    ...ሲያወሩም እንደሌሎቹ ንጉሦች መስሎን ሸሽተን ነበር፡፡
    ...በኋላ ይቅርታ እየጠየቅን ተመለስን፡፡
    ...አሁን ግን ግብራቸውን እየገበሩ በሰላም ይኖራሉ፡፡”
    በማለት ጽፏል፡፡

    ምኒልክን ያህል፤
    “አባት እሆንሀለሁ፣ ልጅ ትሆነኛለህ፣” በማለት አብዛኛውን ሀገር በሠላም አስገብሮ፣ በጣት የሚቆጠሩትን ሥፍራዎች ላይ ብቻ ተዋግቶ፣ አገርን ከቅኝ ገዥዎች ተናጥቆ፤ ህዝቡን ከባርነት ቀንበር አላቆ፣ ታላቅ አገር የገነባ መሪ በዓለም ታሪክ ውስጥ አናውቅም፡፡”

    "መራራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ" ደራሲ፡- ታዬ ቦጋለ አረጋ፤  ሰኔ 2011 ዓ.ም.

5. ዲፕሎማሲያዊ ብልሀት

1ኛ፤
የእንግሊዝ ጦር፣ በአፄ ቴዎድሮስ የታሰሩባቸውን እስረኞች ለማስፈታት ኢትዮጵያ ሲገቡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እነዲተባበሯቸው ለተላከላቸው መልእክት፤
“የምትመጡት ኢትዮጵያን አስገብሮ ለመያዝ ከሆነ በነገራችሁ አልስማማም፡፡”
በማለት መልሰዋል፡፡
እንግሊዞችም ድጋሚ በላኩላቸው መልእክት፤
“…እኛ ኢትዮጵያን ለመውረር አንመጣም፡፡ …እኛ በምንደርስበት ጊዜ ጦርዎን ወደ መቅደላ እንዲያስጠጉ ይሁን፡፡”
ሲሏቸው፤ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከእንግሊዞች ጋር መጣላት ሰላልፈለጉ፤
“ፋሲካ ስለደረሰ ፋሲካን የምውለው አገሬ ነው፡፡”
በማለት መልሰውላቸዋል፡፡
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ይህን መልስ የሰጡበት ምክንያት፤ አፄ ቴዎድሮስ ጦርነቱን ቢያሸንፉ አርሳቸውን እንደሚወጓቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ እንግሊዞች አፄ ቴዎድሮስን ቢያሸንፉ፤ እንግሊዞች ከትግራዩ ካሣ ምርጫ ጋር በተስማሙት መሰረት፤ ካሣ ምርጫ ከእንግሊዞች ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን እንደሚቀበል ስለሚያውቁ፤ ከካሣ ምርጫ ጋር ጦርነት ውስጥ ቢገቡ፤ የእርሳቸው መሣሪያ ብዛትና ዘመናዊነት የማይመጣጠን መሆኑን በመገንዘብ ብልሀት የተሞላበት መልስ ሰተዋቸዋል፡፡

2ኛ፤
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፤
“ቀድሞም ቢሆን ሐረርጌ ከኢትዮጵያ ውጭ ለሌሎች የውጭ ገዥዎች ተላልፎ ተሰጥቶ አያውቅም፡፡”
በማለት ሐርር፤ ለ 400 ዓመታት ያህል በዳግማዊ አፄ ምኒልክ አያቶች ሥር ስትተዳደር ስለነበር፣ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሐረርን ለውጭ ኃይሎች አሳልፈው መስጠት አልፈለጉም፡፡
በዚህም መሠረት በወቅቱ የነበረው የሐረር ገዥ ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጋር ሊተባበር ስላልፈቀደ እርሱን በውጊያ ካሸነፉ በኋላ፤ የኢጣሊያ መነግሥት ሐረርን ለመያዝ እጅግ ተነሳስቶ ስለነበረ ለኢጣሊያ ንጉሥ ኡምቤርቶ፤
የሐረሩን ገዥ ማሸነፋቸውንና ምንም ደም ሳይፈስና ምንም አይነት ዘረፋ ሳይፈጸም እርሳቸውና ጦራቸው ሐረር መግባቱን ገልጸው ሲጽፉ፤
“…ሰንደቅ ዓላማዬን በአገሬ ላይ አቆምኩ፡፡ ወታደሮቸም ገብተዋል፡፡ ይህን ያደረኩት ጣሊያኖችን ለመርዳት ስል ነው፡፡”
በማለት የጽሁፍ መልእክት ልከዋል፡፡፡


አባ ጁሴፔ የተባሉ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ኢጣሊያዊ በሐይማኖት ስብከት ምክንያት በጊዜው አሰብን ያስተዳድሩ ከነበሩት ሡልጣኖች ጋር ወዳጅነት ፈጠሩ፡፡
ጁሴፔ፣ የተፈጠረውን ወዳጅነት ተጠቅመው ለማረፊያ የምትሆን ትንሽ መሬት እንዲሸጡላቸው ሡልጣኖችን ሲጠይቁ፣ የፈለጉትን ያህል መሬት መግዛት እንደሚችሉ ቃል ገቡላቸው፡፡
ጁሴፔ በቀይ ባህር ዳርቻ ላይ ወደብ እንዲመሠረት ስለፈለጉ ከኢጣሊያ የመርከብ ኩባንያ ጋር በመነጋገር የመሬት መግዣ ገንዘብ ይዘው ከኢጣሊያ ተመልሰው መጡ፡፡
አባ ጁሴፔም የሚፈልጉትን መሬት አይተውና ለክተው ካበቁ በኋላ፤ አሰብንና ሰባት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን የባሕር ዳርቻ በ 1862 ዓ.ም. በ 8,100 ማሪያ ቴሬዛ ገዙት፡፡ (ማሪያ ቴሬዛ፤ እ.ኤ.አ በ1741 ለመጀመሪያ ጊዜ ከተመረተበት ጊዜ አንስቶ በአለም ንግድ ውስጥ ያለማቋረጥ ጥቅም ላይ የዋለ ከብር የተሠራ ሳንቲም ነው፡፡)
አባ ጁሴፔ ቦታውን በገዙ በማግስቱ 28 ጊዜ መድፍ ካስተኮሱ በኋላ፣ በዛሬው የአሰብ ምድር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢጣሊያ ባንዲራ (ሰንደቅዓላማ) መውለብለብ ጀመረ፡፡
የመርከቡ ኩባንያም ለ12 ዓመታት ከቆየ በኋላ ወደቡ የማይጠቅመው መሆኑን ሲረዳ ለኢጣሊያ መንግሥት ሸጠው፡፡

የኢጣሊያ መንግሥት አሰብን ለመግዛት ለምን ፈለገ?

ይህ ወቅት፤ ፋሽስቶች ለመውደቅ የሚንገዳገደውን የኢጣሊያ መንግሥት በእግሩ ካቆሙ በኋላ አገራቸውን ወደ ጥንቱ የሮማውያን አገዛዝ ለመመለስ ሲሉ የቅኝ ግዛት አገር የሚፈልጉበት ወቀት ነበር፡፡
በሜድትራንያን ባህር በኩል የሚዋሰኑ አገሮችን በቅኝ ግዛትነት ለመያዝ አስበው ነበር፡፡
ግን፤ ፈረንሳዮች አስቀድመው አልጀሪያንና ቱኒዚያን ይዘው ስለነበር፤ ጣሊያኖች ሞሮኮን ለመያዝ ቢያስቡም የሞሮኮው ሱልጣን የማይበገር ሀያል ሆነባቸው፡፡
ጣሊያኖች ተስፋ ሳይቆርጡ በሌላ አቅጣጫ በቀይ ባሕርና በሕንድ ውቅያኖስ በኩል የቅኝ ግዛት አገር ሲያፈላልጉ ሳለ፤ በድንገት በኢጣሊያ ፓርላማ፤ “ቀይ ባሕር ለሜድትራንያን ቁልፍ ነው፡፡” በሚል መፈክር ተሞላ፡፡
በዚህን ጊዜ ነው የኢጣሊያ መንግሥት በአባ ጁሴፔ አማካኝነት የተገኘውን የመርከብ ኩባንያ ገዝቶ ሰኔ 19 ቀን 1874 ዓ.ም. አሰብ የኢጣሊያ መንግሥት ግዛት መሆኑን ያወጀው፡፡

የኢጣሊያ መንግሥት የምፅዋን ወደብ መቆጣጠርና የኢትዮጵያ ምላሽ

በዚያን ዘመን አፍሪካ በአብዛኛው በግልፅም ሆነ በስውር በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ነበረች ማለት ይቻላል፡፡
በወቅቱም እንግሊዞች ከታላላቅ ኃይሎች ጋር የገጠማቸውን ትልቅ የፖለቲካ ሽኩቻ እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም፤ በሌሎች ኃያላን ዘንድ በንቀት ይታይ የነበረው የኢጣሊያ መንግሥት አንድ የወታደር ኃይል ወደ ምፅዋ እንዲልክና ሱዳን ውስጥ እንግሊዝን የሚበጠብጠውን የመሀዲስት ኃይሎች ለመቆጣጠር እንደሚቻል በማሰብ፤ ምፅዋን የያዙትን ግብፆችን አስወጥተው በምትኩ የኢጣሊያ መንግሥት ቦታውን እንዲረከብ የሚያስችል ውል እንግሊዞች ከኢጣሊያ ጋር ተፈራረሙ፡፡
በውሉም መሰረት በሚስጥር የተላከው የኢጣሊያ የወታደር ቡድን ጥር 28 ቀን 1877 ዓ.ም. ጧት ምፅዋ ገባ፡፡
አፄ ዮሐንስ እንግሊዞች ምፅዋን ያለእርሳቸው እውቅና ለኢጣሊያ መንግሥት አሳልፈው የመስጠታቸው ጉዳይ ግር ቢላቸውም፤ ጉዳዩን በማጣራት ላይ እንዳሉ የኢጣሊያ መንግሥት በምፅዋም ሆነ በአሰብ ወደብ ምንም ዓይነት የጦር መሣሪያ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ከለከለ፡፡
ዳግማዊ አፄ ምኒልክም ለኢጣሊያው ንጉሠ ነገሥት ደብዳቤ በመጻፍ የኢጣሊያ መንግሥት ከኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ጋር ጦርነት ለመግጠም አስቦ ምፅዋ መግባቱን በመስማታቸው ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡
ምፅዋም የጣሊያኖች የጦር መሣሪያ ማከማቻ መሆን ቀጠለ፡፡
ምፅዋ በኢጣሊያኖች መያዙን የሰሙት አፄ ዮሐንስም 159 ሺህ ጦር አሰልፈው ጣሊያኖችን ለመውጋት ዘምተው ቢጠባበቁም፤ የጣሊያን ወታደሮች 50 ኪሎ ሜትር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቀው በመግባት ሰሓጢ በተባለው ስፍራ መሽገው አልንቀሳቀስ አሏቸው፡፡
የአፄ ዮሐንስ ጦር ሁለት ወራት ሙሉ በመቆየቱ ስንቁን ጨርሷል፡፡
የደጋው ወታደር የቆላውን ሙቀት መቋቋም አልቻለም፡፡
የሱዳኑ የመሀዲስት ጦርም በጎንደር በኩል ገብቶ እየተዋጋ ድል እየቀናው ነው፡፡
በዚህ ምክንያት አፄ ዮሐንስ ወደ ደጋው ተጉዘው አሥመራ ከደረሱ በኋላ፤ የመረብ ምላሽ ገዥና የጦር አዛዥ የነበሩትን ራስ አሉላን ከሥልጣናቸው ሽረው ከአስመራ ተመለሱ፡፡



ጣሊያኖች የአፄ ዮሐንስን ደግነትና የዋህነት በተለይም በሐይማኖታቸው ጽኑ ዕምነት እንዳላቸው በሚገባ ያውቃሉ፡፡
ጣሊያኖች፤ ሐይማኖተኛ መስለው በገንዘብ የተገዙ መነኮሳትን አሰባስበው ወደ አፄ ዮሐንስ ዘነድ በመላክ፤
“ ከክርስቲያኑ የኢጣሊያ መንግሥት ጋር ተዋግተው ድል ቢያደርጉም፣ በነፍስዎ ግን ይበደላሉ፡፡
ከእስላሙ ከደርቡሽ ጋር ተዋግተው መስዋዕት ቢሆኑ እንኳ፣ መንግሥተ ሰማያት ይገባሉ፡፡”

እያሉ ትንቢት እያስመሰሉ ስለነገሯቸው፣ አፄ ዮሐንስም በየዋህነታቸው የኢጣሊያ መነኮሳት የነገሯቸውን ተቀብለውና ለመኳንንቶቿቸው ነግረው ከኢጣሊያ መንግሥት ጋር መዋጋቱን ትተው በቀጥታ ወደ መተማ ዘመቱ፡፡
ጣሊያኖች ግን ይህን ሁሉ ያደረጉት፤ ሆን ብለው በር አስከፍተው ግዛታቸውን ለማስፋፋት ያቀዱት ተንኮል ነበር፡፡
የኢጣሊያ መንግሥትም፤ የራስ አሉላን ከሥልጣን መሻርና የአፄ ዮሐንስ ሠራዊትም ሳይዋጋ መመለሱ ቦታውን ባዶ ስላደረገለት በአስቸኳይ ወሰኑን መረብ ምላሽ አድርጎ በመያዝ ወሰኑ ላይ የኢጣሊያ ባንዲራ (ሰንደቅዓላማ) አውለበለበ፡፡
የኢጣሊያ መንግሥትም፤ አፄ ዮሐንስ መተማ ዘምተው መሞታቸውን እንደሰማ፤ በ 1882 ዓ.ም. መረብ ምላሽ ቅኝ ግዛታቸውን ኤርትራ ብለው ሰየሙት፡፡






ምንጭ፤
  1. "አጤ ምኒልክ"  ደራሲ፡- ጳውሎስ ኞኞ የካቲት ወር 1984 ዓ.ም.
  2. "የኢትዮጵያ ታሪክ ከ 1847 እሰከ 1983"  ደራሲ፡- ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ
  3. "የኢትዮጵያ ታሪክ - ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ"  ደራሲ፡- ተክለ ጻድቅ መኩሪያ 1961 ዓ.ም.
  4. "መራራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ "  ደራሲ፡- ታዬ ቦጋለ አረጋ 2011 ዓ.ም.
  5. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ
  6. የትረካው አጃቢ ድምጻዊ፤ ፉከራና ቀረርቶ አንጋፋው አርቲስት ለማ ገብረ ሕይዎት - በኦርኬስትራ ኢትዮጵያ   ዩቲውብ
  7. Courtesy of: Rare WW2 Footage - German Infantry - No Music, Pure Sound  ዩቲውብ