Content-Language: am ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ገጽ አራት
header image



(የመጨረሻ ገጽ)

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ




  1. ለዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከዓለም ዙሪያ የተላኩ የደሰታ መግለጫዎች

    ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ድል አድራጊ ሠራዊታቸውን እየመሩ ግንቦት 13 ቀን 1888 ዓ.ም. አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ከዓለም ዙሪያ በርካታ የደሰታ መግለጫዎች ደርሷቸዋል፡፡ ከነዚህም መካከል፤
    ከአውስትራሊያና ከቬንዙየላ ከተጻፉት ደብዳቤዎች መካከል፤ “የእርሰዎ ወታደሮች መሆን እንፈልጋለን” የሚሉ ጽሁፎች ይገኙበታል፡፡
    በኤርትራ አዲስ የተሾመው የኢጣሊያ ጦር አዛዥ ጀነራል ባልዲሴራ እንደታዘዘው ከኢጣሊያ በመጣው አዲስ ጦር ኢትዮጵያን እንደገና ሊወጋ አስቦ ነበር፡፡
    ነገር ግን ውጊያውን ቢጀምር በአድዋ ጦርነት የተማረኩት የኢጣሊያ ወታደሮች እነደሚገደሉ ስለገባው በቅድሚያ ምርኮኞችን ለማስለቀቅ ስለፈለገ፤ ምርኮኞቹ እንዲለቀቁ ለምኒልክ መልዕክት ላከ፡፡
    ዳግማዊ አፄ ምኒልክም ኤርትራ የገባው አዲስ የኢጣሊያ ጦር ከፍተኛ ኃይል ያለው መሆኑን ስለተረዱና በውጊያና በነበረው ረሀብ ምክንያት ከተዳከመው ከእርሳቸው ጦር ጋር የማይወዳደር መሆኑን ስለተገነዘቡ፤
    የውጫሌው ውል መፍረሱንና አዲስ ውል መዋዋላችንን ለዓለም መንግሥታት ሁሉ ካላሳወቃችሁ ምርኮኞቹን አለቀም ብለው መልስ ሰጡ፡፡

  2. በዐድዋ ጦርነት ስለተማረኩ የኢጣሊያ ወታደሮች አያያዝ

    የኢጣሊያ ምርኮኞችን ብዛት በተመለከተ፤ ስለምርኮኞቹ ጉዳይ ለመነጋገር ወደ ኢትዮጵያ ተልከው ከመጡት መካከል ዎርዝዊዝ የተባሉት ቄስ በጻፉት ጽሁፍ፤ በሸዋ ውስጥ ብቻ 2‚864 ምርኮኞች ነበሩ ብለዋል፡፡
    ሌላው መልከተኛ ደግሞ የኢጣሊያ ምርኮኞች ቁጥር 4 ሺህ እነደሚሆንና ኢጣሊያ ከቅኝ ግዛቶቿ ያሰለፈቻቸው የአፍሪካ ወታደሮች ቁጥርም ያንኑ ይህል እንደሆነ ተናግሯል፡፡
    ኒኮላስ ሊዎንቲፍ የተባለው ጸሀፊ ስለኢጣሊያ የተማረኩ ወታደሮችን በተመለከተ ሲጽፍ፤
    Prisoner's of war of Battle of Adwa
    በዐድዋ ጦርነት የተማረኩ
    ሁለት የጣሊያን ወታደሮች
    “...እጅ የሚሰጡት የኢጣሊያ ወታደሮች እንዳይገደሉ ምኒልክ በአዋጅ አስጠነቀቁ፡፡
    ...የኢጣሊያ ወታደሮች ሬሳ በብዛት ተከምሯል፡፡
    ...የኢጣሊያ ወታደሮች ሬሳ በተከመረበት ስፍራ ላይ ይወርድ የነበረው ደም ወደ ትንሽ ወንዝነት ተለውጧል፡፡
    ...የቆሰለውም ሆነ ያልቆሰለው የጣሊያን ወታደር ሁሉ እንዳይገደል በመፍራት እራሱን ከሬሳ መሀል እያመሳሰለ ይተኛ ነበር፡፡
    ...ኢትዮጵያውያኖቹ በሕይወት ያለውን የኢጣሊያ ወታደር ከሬሣ መሀል እየመረጡ ማወጣቱ ከብዛቱ የተነሳ ጊዜ ስለወሰደባቸውና አድካሚም በመሆኑ ቦታውን እሳት ለቀቁበት፡፡
    በዚህን ጊዜ ሬሣው መሐል የተኙት የኢጣሊያ ወታደሮች ሁሉ ጭሱ ሲያፍናቸው ጭሱን ከለላ እያደረጉ ለማምለጥ እየሮጡ መሸሽ ጀመሩ፡፡
    ኢትዮጵያውያኖቹም በዚህ ዘዴ ተጠቅመው ለማምለጥ የሚሮጡትን የኢጣሊያ ወታደሮች እያባረሩ መያዝ ጀመሩ፡፡”
  3. በማለት ገልጾታል፡፡

    የምርኮኞቹን አያያዝ በተመለከተ ግሊከን የተባለው ጸሐፊ ሲጽፍ፤
    “...ምርኮኞቹ አዲስ አበባ እንደደረሱ በተቻለ መጠን ጥሩ ኑሮ እንዲኖሩ ተደረገ፡፡
    ...ንጉሡም በተቻላቸው መጠን እስረኞቹን በማስደሰት የኢትዮጵያ መንግሥት የሠለጠነ መንግሥት መሆኑን ለማሳወቅ ሲሉ፤
    አልፈው ተርፈው (ለእያንዳንዱ ምርኮኛ) በነፍስ ወከፍ ሶስት ሶስት ብር ሰጥተዋል፡፡”
    በማለት ገልጾታል፡፡

    ሐምሌ 8 ቀን 1888 ዓ.ም. ቴምፕስ የተባለው ጋዜጣ፤
    ...ጣይቱ በግቢያቸው ውስጥ ባለው ሜዳ ላይ ምረኮኞቹን ይጋብዙ ነበር፡፡
    ...ከጀነራል አልቤርቶኒ ጀምሮ ሁሉም በአንድነት በአውሮፓውያን ደንብ መሠረት ይጋበዛሉ፡፡
    በሚመገቡበት ጠረጴዛ ላይ፤ ሰሀን፣ ሹካ፤ ማንኪያ፤ የአፍ መጥረጊያ ፎጣ፤ አበባና የሚጠጡት ቪኖ ሳይቀር ይደረገልቻው ነበር፡፡”
    በማለት ጽፏል፡፡
    ሌላው ቀርቶ ዋና እስረኛ የነበረው ጀነራል አልቤርቶኒ ሳይቀር በጥበቃ ስር ሆኖ ለግሉ መኖሪያ ድንኳን እና ፈረስ ከአሽከሮች ጋር ተሰጥተውት ነበር፡፡
    የምርኮኞቹም የሥራ ችሎታ እየተጠየቀ፤ ሐኪሞች፣ ሰዓሊዎች፣ አናጢዎች፣ መካኒኮች ሥራ እየተሰጣቸው ይሰሩ ነበር፡፡

    በጦርነቱ ማግሥት የኢትዮጵያ ሴቶች ምርኮኞቹን በሚሰበስቡበት ጊዜ፣ ደረቱን በጥይት ተመቶና ራሱን ስቶ የነበረ በኤርትራ አምስት ዓመት የኖረ ምርኮኛ አግኝተው በነበረበት ወቅት፤ ስለተደረገለት ሁኔታ ራሱ በደረሰው መጸሐፍ ላይ፤
    “...ስነቃ ራሴን አንድ ጎጆ ውስጥ አገኘሁት፡፡ ...አንዲት አሮጊት ሴት በደም የተነከረ ጃኬቴን ፈታች፡፡ ...ልብሴንም ከሰውነቴ አስለቅቃ የቁስሉን ቀዳዳ ትመረምር ጀመር፡፡ ወዲያውኑምመድኃኒት አደረገችልኝ፡፡ ...አሮጊቷ ይህን ስታደርግ ሌሎች ሴቶች ተሰብስበው ያዝኑልኝና ይጨነቁ ነበር፡፡ ...ቁስሉም በጥቂት ቀናት ውስጥ ድኖ እኔም ምርኮኛ ሆኘ ተቀመጥኩ፡፡”
    በማለት ጽፏል፡፡

  4. ምርኮኞቹን ለማስለቀቅ ምን ተከናወነ?

    የኢትዮጵያ ሕዝብ ሐይማኖቱን እንደሚወድ ያወቁት ጣሊያኖች፤ በሮማው ሊቀ ጳጳስ አማካይነት ምርኮኞች እዲለቀቁ የልመና ደብዳቤ ሲጽፉ ካሰፈሯቸው ቃላት መካከል፤
    “...ኃያሉ ንጉሠ ነገሥት ሆይ! እባክዎ ምርኮኞቹ በቶሎ በነፃ ይልቀቁልን፡፡ በዚህም በሚያደርጉት የቸርነት ሥራ፣ እግዚአብሔር ይክስዎታል፡፡
    እግዚአብሔር በንጉሠ ነገሥቱና በቤተ ሰቦችዎ ላይ በረከቱን እነዲያወርድ እንፀልያለን፡፡”

    የሚል ሲሆን፤ ሊቀ ጳጳሱ በደብዳቢያቸው ላይ ብዙ የመማፀኛ ቃላትን የደረደሩት እውነት ለምርኮኞቹ መለቀቅ ተቆርቁረው ሳይሆን፤
    ዋናው እቅዳቸው ምርኮኞቹ ከተለቀቁ በኋላ ጀነራል ባልዲሴራ በኢጣሊያ መንግሥት ታዞ ባመጣው ትኩስና ልዩ ኃይል፤
    በረሀብ፣ በጥማትና በጦርነት የደከመውን የኢትዮጵያን ሠራዊት ሳያገግም አዲስ ውጊያ ከፍቶ ለመምታት እንዲቻል ነበር፡፡
    ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፤ እንዲህ አይነቱ የሴራ ጥንስስ መኖሩን አስቀድመው ያውቁ ስለነበር በደብዳቤው አጻጻፍ ሳይማረኩና ምንም ርኅራኄ ሳያሳዩ፤ መንግሥታቸው ከኢጣሊያ መንግሥት ጋር የጦርነት ካሣ እንዲከፍል በተዋዋሉት ውል መሠረት ለኢትዮጵያ መንግሥት አስር ሚሊዮን ሊሬ የጦርነት ካሣ ከከፈሉ በኋላ ምርኮኞቹ ተለቀው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ተደርጓል፡፡


ከአድዋ ድል በኋላ መላው የአውሮፓ አገራት በምኒልክ ላይ በአንድነት አደሙ፡፡
እንኳን መሳሪያ አንዲት ጥይት እንኳን ወደ ኢትዮጵያ እንዳትገባ እንግሊዝና ፈረንሳይ በየቅኝ ግዛቶቻቸው በኩል ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርጉ ተስማሙ፡፡
በአፍሪካ ቅኝ ግዛት የነበራቸው የአውሮፓ መንግሥታት በሙሉ በአንድነት ተሰባስበው የምኒልክን መንግሥት ለማጥፋት ዕቅድ አወጡ፡፡
ይህም የሆነበት ምክንያት፤ በአፍሪካ የሚገኙ የቅኝ ግዛት አገሮች፣ የምኒልክ ኃይል የአውሮፓን አገር ድል ማድረጉን ከሰሙ፣ የአፍሪካ ቅኝ አገሮቻችን በሙሉ ይነሱብናል በሚል ፍርሀት ነበር፡፡
ፍርሀታቸውም እውነት ነበር፡፡
እንደፈሩትም አልቀረም፤ የዐድዋን ድል መቀዳጀታችን፤ በቅኝ ግዛት ይገዙ ለነበሩት የአፍሪካ አገሮች ሳይቀር ፀረ ቅኝ ግዛት ትግላቸውን እንዲያፋፍሙ ፋና ወጊ ለመሆን ችሏል፡፡
ወደ 30 የሚጠጉ አፍሪካውያን እና የካሪቢያን አገራት የኢትዮጵያን ባንዲራ ቀለሞች የእነሱንም ሠንደቅ ዓላማዎች የሚወክሉበት ምክንያት ድንገተኛ አልነበረም፡፡
ዋናው ምክንያት፤ ኢትዮጵያን እንደ ነፃነት አርማቸው አድርገው በመቁጠራቸው እና የፀረ ቅኝ ግዛት ውጊያቸውንም ከኢትዮጵያ የነፃነት ትግል ጋር ስላቆራኙትም ጭምር ነው፡፡
ለምሳሌ ያህል፤ በዝምባቡዌ፤ በጋና፣ በናሚቢያ፣ በታንዛኒያ፣ በኬንያ፣ በዚምባቡዌ፣ በሞዛምቢክ፤ በአንጎላ፣ በጊኒ ቢሳውና በኬፕ ቨርዴ ጠንካራ የፀረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ በማድረግ ለነፃነታቸው ታግለዋል፡፡
ቨርጂኒያ ሊ ጃኮብስ የአድዋን አርአያነት ሲገልጽ፤
“እናም ኢትዮጵያ በቅኝ አገዛዝ ላይ ነፃነትን ለማምጣት በሚደረገው ትግል ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ተምሳሌት ሆነች፡፡
የነጭን የዘረኛ ልዕልና አሻፈረኝ በማለቷ፤ ኢትዮጵያ በቀላሉ የማትነቃነቅ ግዙፍ መሆኗን በኩራት አሳየች፡፡
በዓለም ዙሪያ ባሉ ህዝቦች ሁሉ በሚያስደንቅ ሁኔታ ታላቅ ክብር አገኘች፡፡
ከኢትዮጵያ ነፃነት በኋላ፤ ምንም እንኳን መደባቸው ቢለያይም፤ በርካታ የአፍሪካ አገራት መሠረታዊ የኢትዮጵያ ባንዲራ ቀለሞችን፤ ማለትም አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማትን ባንዲራዎቻቸው ላይ የነፃነት እና የማንነት ምልክት ማድረጋቸውን ቀጠሉ፡፡”
በማለት አስተያቱን አስፍሯል፡፡---የጽሁፉ ምንጭ: ታዲያስ መጋዚን - በአየለ በክሪ (ዶ/ር)

በአሜሪካ የሚኖሩ ጥቁር አሜሪካውያንም፤
“አፍሪካ አውሮፓን በጦርነት ድል አደረጉ” እያሉ የደስታ መግለጫ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ከባድ ርበሻ አስነስተው ነበር፡፡
ይህን የሰሙት የአውሮፓ አገራት በአንድነት በመተባበር የአድዋ ድል በአፍሪካም ሆነ በእስያ አገራት እንዳይወራ አሰከልክለዋል፡፡
ይሁን እንጅ ምኒልክ፤
“…ድሮም ቢሆን ጣሊያኖች አውከውኝ ያው እነደሰማችሁት አድዋ ላይ ተገላገልን፡፡
አሁን ደግሞ አገሬ እንዳትሰለጥን እንግሊዞች የሚያደናቅፉኝ ከሆነ፣
ሌላ የማደርገው ስለሌለኝ እነደ አድዋው ነው የማደርገው፡፡
ፈረንሳዮችም ዘመዶቻቸውን እየደገፉ እኔን ከጠሉኝ ላገሬ ስል ከነርሱም ጋር እገጥማለሁ፡፡
ይህን እንዲያስቡበት አድርጉ፡፡ ለሰዎቻችሁም ንገሩ፡፡”
በማለት ማስጠንቀቂያ አዘል ንግግር ተናግረዋል፡፡


Menelik II Emperor of Ethiopia
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የአድዋን ድል ከተጎናጸፉ በኋላ፤ አብዛኛውን መሳፍንቱንና ባላባቱን በፍቅርና በትህትና ስለቀረቡት፤ በመሳፍንት ግዛት ተበታትና የነበረችውን ኢትዮጵያን አንድነቷንና ነፃነቷን የጠበቀች ኢትዮጵያን ለመመስረት ቻሉ፡፡
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፤ እንደ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ሁሉ እጅግ ሥራ ወዳድ ስለነበሩ በርካታ የዕድገትና የሥልጣኔ ሥራ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በሳቸው ዘመነ መንግሥት ነው፡፡


ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የመጀመሪያ የሥልጣኔ አሻራወች

  1. በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሚኒስትሮች የተሾሙት ጥቅምት 14 ቀን 1900 ዓ.ም. ሲሆን ለመጀመሪያ ሰባት ሚኒስተሮችን ሾመዋል፡፡
  2. ምኒልክ፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነውን በአክስዮን ሽያጭ የተቋቋመውንና አቢሲንያ ባንክ (Bank of Abyssinia) ተብሎ የተሰየመውን የግል ባንክ የካቲት 7 ቀን 1988 ዓ.ም. መርቀው ከፈቱ፡፡
    የባንኩም የአክሲዮን ሽያጭ፤ በአዲስ አበባ፣ በፓሪስ፣ በለንደን፤በኒውዮርክና በቪየና ተከናውኗል፡፡
  3. ምኒልክ በ1895 ዓ.ም. የብር ማተሚያ መሣሪያ በቅድሚያ አስመጥተው ስለነበረ የአቢሲንያ ባንክ ሲቋቋም ብር መታተም ተጀመረ፡፡
  4. በ1898 ዓ.ም. የጋዜጣ ማተሚያ መሣሪያ ከውጭ አስመጥተው ሥራ ጀመረ፡፡
  5. ሐምሌ 17 ቀን 1900 ዓ.ም. የመጀመሪያ የሆነው ጎህ የተሰኘው ጋዜጣ ታትሞ ወጣ፡፡
  6. የመጀመሪዋን አውቶሞቢል አስገብተውና “perfect driver” የተሰኘውን የመንጃ ፈቃድ ተቀብለው አውቶሞቢሏን አሽከርክረው አሳይተዋል፡፡
  7. የእህል ወፍጮ
  8. ስልክ
  9. ካሜራ
  10. የጽሕፈት መኪና (ታይፕ ራይተር)
  11. በ1889 ዓ.ም. የሲኒማ ፕሮጀክተር ከነ ፊልሙ
  12. በ1890 ዓ.ም. የመጀመሪያው የሙዚቃ ሸክላ (ዲስክ) መቅረጫ መሣሪያ ከእንግሊዝ አገር ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀረፀው የምኒሊክና የጣይቱ ድምፅ ነበር፡፡
  13. ብስክሌት አስገብተው ራሳቸውንና እቴጌ ጣይቱንም ማሽከርከር አስተምረዋል፡፡
  14. የመጀመሪያው የፍልውሃ መታጠቢያ ቤት በምኒልክ ትእዛዝ በ1897 ዓ.ም. ተሠራ፡፡
  15. በአዲስ አበባ የውሃ ቧንቧ አስገብተዋል፡፡
  16. በ1872 ዓ.ም. ከጣሊያን አገር አራት የሕክምና ዶክተሮች አስመጥተዋል፡፡
  17. መጋቢት 7 ቀን 1890 ዓ.ም. የመጀመሪያ የሆነውን የምኒልክ ሆሰፒታልን መሰረቱ፡፡
  18. ህዳር 22 ቀን 1904 ዓ.ም. የመጀመሪያው ፋርማሲ ተከፍቶ ስራ ጀመረ፡፡
  19. በአዲስ አበባ ጣይቱ ሆቴል የተሰኘውን በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ሆቴል ከፍተውና ሚስታቸውን እቴጌ ጣይቱን ወጥ ቤት እንዲሰሩ አድርገው በራሳቸው ገንዘብ መኳንንቶችን እየጋበዙ ሆቴል መመገብን ያስተማሩ የመጀመሪያ ሰው ናቸው፡፡
  20. የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ፤ መደቡ ልሙጥ ሆኖ ቀለሙ ከላይ ወደታች አረንጓዶ፣ ቢጫ፣ ቀይ እንዲሆን በ1881 ዓ.ም. በአዋጅ ደንግገዋል፡፡
  21. ዩኒፎርም የለበሰ ፖሊስ ተቋቁሞ ሥራ የጀመረው በ ግንቦት ወር 1901 ዓ.ም. ነበር፡፡
  22. የተለያዬ ቀለም ያላቸውን አበቦችና ጽጌረዳዎችን፣ እንዲሁም የኮክ፣ የእንጆሪ፤ የወይንና የባሕር ዛፍ ተክሎችን ከውጭ አገር አስመጥተዋል፡፡
  23. በአዲስ አበባ፤ የመጀመሪያውን የውጭ አገር ትምህርት ቤት የከፈቱና ያቋቋሙ ምኒልክ ናቸው፡፡
  24. በ1887 ዓ.ም. የመጀመሪያውን የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከፍተውና 40 የተለያዩ የሞዚቃ መሣሪያወች ከውጭ አገር መምህራን አስመጥተው ትምህርት አስጀምረዋል፡፡
  25. ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት እንዲያስተምሩ አስገዳጅ ህግ አውጥተዋል፡፡
  26. ኤሌክትሪክ እንዲገባ አድርገዋል፡፡
  27. ጥይት ፋብሪካን በማቋቋም፤ “አፈሪካውያን ከቅኝ ግዛት መውጣት አለባቸው፤ ኢትዮጵያም የጥንት ክብሯንና ወሰኗን ለማስከበር ትነሳለች” በማለት ለአውሮፓውያን ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡
  28. ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር ተነጋግረው የባቡር ሀዲድ አዘርግተው ባቡር አስገብተዋል፡፡
  29. ዘመናዊ የመኪና መንገድ ሥራ አስጀምረዋል፡፡
  30. መኖሪያቸው የነበረውንና በ1874 ዓ.ም. የተመሰረተውን የእንጦጦን ከተማ ለቀው በ1879 ዓ.ም. ዋና ከተማቸውን አዲስ አበባ እንዲሆን ወሰኑ፡፡
  31. ሹመት በዘር እንጅ በሥራና በእውቀት ባልነበረበት ዘመን የተገኙት ምኒልክ፤ ሹመት በሥራ ብቻ እንዲሆን አወጁ፡፡
  32. ሴት ልጅ የምታገባው በወላጆቿ ምርጫ ሳይሆን በራሷ ፈቃድ የመረጠችውን ባል እንድታገባ ያወጁትና ለሴቶች ልጆች የታገሉት ምኒልክ ናቸው፡፡
  33. ማንኛውም አይነት ሥራ የተከበረ መሆኑንና ሰው በሚሰራው መሰደብና መነቀፍ የለበትም በማለት ሕብረተሰቡን ለማስተማር ጥር 17 ቀን 1900 ዓ.ም. አዋጅ አወጡ፡፡
    ምኒልክም፤ “ገበሬ ከንጉሥ ዘውድ ይበልጣል” የሚል እምነት ስለነበራቸው ይህን እምነታቸውን በግልጽ ይናገሩ ነበር፡፡ ለሥራና ለሠራተኛ የተለየ ክብር ነበራቸው፡፡
  34. ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል የጀመሩት ምኒልክ ናቸው፡፡




Statue of Emperor Menilk
በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን
ፊት ለፊት በሚገኘው አደባባይ ላይ እንዲቆም የተደረገው
የዳግማዊ አፄ ምኒልክን ሀውልት

ስለ ሀውልቱ አሰራር የበለጠ ለማንበብ....

ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ፤ የዓለም ታላላቅ ነገሥታት ስለውለታቸው ሐውልት የሚቆምላቸው መሆኑን ተመልክተው፤ አባታቸው ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ለኢትዮጵያ የደከሙላት፣ አንድነቷን ያስጠበቁላትና የሥልጣኔ በር የከፈቱላት መሆናቸውን ተገንዝበው፤ ሀውልት እንዲቆምላቸው ፈለጉ፡፡
በዚህም መሠረት፤ ሙሴ ቤርትል በተባለ የጀርመን መሐንዲስ በማስጠናት ከጀርመን አገር ተሰርቶ እንዲመጣ ተደረገ፡፡
በኋላም ሐውልቱ ሳይቆም ንግስቲቱ በድንገት በማረፋቸው፤ አሁን ዳግማዊ አፄ ምኒልክ አደባባይ ተብሎ በተሰየመው ቦታ ላይ ታላቅ ሠልፍና ክብረ በዓል ከተከናወነ በኋላ በልዑል አልጋ ወራሽ ንጉሥ ተፈሪ መኮንን የንግሥ በዓል ዋዜማ ዕለት ጥቅምት 22 ቀን 1923ዓ.ም. በታላቅ ድምቀት ሐውልቱ እንዲቆም ተደረገ፡፡
  1. ምኒልክ ለኢትዮጵያ ዘመናዊ አስተዳደር መሠረት የጣሉ ታላቅ መሪ ነበሩ፡፡
  2. ምኒልክ በአስተዳደር ችሎታ ዘዴኛና ጥበበኛ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡
  3. ምኒልክ ምንም ጊዜ ቢሆን መልካም ሰው በመሆናቸው ጠላቶቻቸውን በኃይልና በቁጣ ሳይሆን በፍቅር ለመሳብና ለማሳመን የሚጥሩ መሪ ነበሩ፡፡
  4. ይህን በተመለከተ ሁለት ምሳሌዎችን እንጥቀስ፤

    1ኛ)
    ከምኒልክ ጋር የተዋጉት ንጉሥ ተክለሐይማኖት በውጊያው ቆስለው ድል ከሆኑ በኋላ ቁስለኛውንና ምርኮኛውን ንጉሥ ተክለሐይማኖትን በህዝቡ ፊት ታቅፈው፣ ስመው፤
    ደማቸውን ራሳቸው በእጃቸው ጠራርገውና ከወጌሾች ጋር ሆነው ስላከሟቸው በዚህ ተግባራቸው በህዝቡ ዘንድ አድናቆትን አትርፈዋል፡፡

    2ኛ) ወላይታን ለማስገበር የዘመቱት ምኒልክ፤ የወላይታው ባላባት ጦና በጦር ተወግተው በማይረባ ቃሬዛ ይዘዋቸው ምኒልክ ፊት ቀረቡ፡፡
    ምኒልክም በማይረባ ቃሬዛ ያመጧቸውን ወታደሮች “ወነድሜን እንዲህ አደረጋችሁት?” በማለት ተቆጥተው ከዙፋናቸው ወርደው በለበሱት ጋቢ የጦናን ደም ጠርገውና እስኪድኑ ድረስ አስታመው መልሰው ወላይታን እንዲያስተዳድሩ ሾሟቸው እንጅ ከሥልጣናቸው አባረው አላሰሯቸውም፡፡

  5. ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ስለነበራቸው አስተሳሰብና ባሕርይ፤ የተለያዩ የውጭ አገር ፀሐፊዎች የታዘቧቸውን የግል አስተያየቶች ቀጥለን እንመልከት፤
    “...ምኒልክ የኃይለኝነት ጠባይ ቢኖራቸውም፤ አሳባቸው በመልካም   ሁኔታ እያስተዳደሩ የአገራቸውን እድገት ለማፋጠን ነው፡፡
    ... ታዋቂነታቸው በፖለቲካ ብቻ አይደለም፡፡ የሳይንስ ውጤት በሆኑ   ጥበባዊ ሥራዎችም እውቅ ናቸው፡፡”
    . . . ግሊከን

    “... የማያውቁትን ነገር ሁሉ ማየት፣ ማጥናትና መሥራት ይወዳሉ፡፡”

    . . . ሮድ

    ”...ወጣቶቻችን መማር ይኖርባቸዋል፡፡
    ገና ብዙ የሚሠራ ሥራ አለ፡፡
    በጣም ወደኋላ የቀረን ሕዝቦች ነን፡፡
    እቴጌ ጣይቱ የውጭ አገር ሰዎችን ስለማያምኑ የንጉሡን እርምጃ   ይቃወማሉ፡፡”
    . . . እስኪነር
  6. ምኒልክ ደሀን የማይንቁና ለደሀ የሚቆረቆሩ፤ ደሀ እነዳይበደል፤ ከነብሰ ገዳይ በስተቀር ደሀ እንዳይታሰር የሚጥሩ መሪ ነበሩ፡፡
    ደሀ የበደሉ አገረ ገዥዎችንም፤
    Menilk in 1889
    በ 1891 ዓ.ም. የተሳለ የአፄ ምኒልክ ስዕል
    ደሀ እነዳይበዱልና እንዳያጉላሉ እየተከታተሉና አቤቱታ እይተቀበሉ ይገስፁና ቅጣትም ይጥሉባቸው ነበር፡፡
  7. ምኒልክ ፍርድ በትክክል የሚፈርዱ ሰው እንደነበሩ ብዙ የታሪክ ፀሐፊዎች ጽፈዋል፡፡
  8. በአስተዳደር ዘመናቸው ሁሉ የሰውን ልጅ መብት የሚጠብቁ እንጅ ለራሳቸው ምቾት ሲሉ የሌላውን መብት የሚገፉ አልነበሩም፡፡
  9. ምኒልክ ራሳቸው ያወጡትን ደንብ ወይም ህግ ድንገት ተሳስተው ቢያፈርሱ፤ ሹማምንቶቻቸውን ይቅርታ የሚጠይቁ ሰው ነበሩ፡፡
  10. ሌላው ቀርቶ ምኒልክ፤ የእስልምናና የክርስቲያን ሐይማኖት ተከታዮች እንዲጋቡ የሚከለክል የሐይማኖት ቀኖና ወይም ደነብ ባለመኖሩ፤ ያለምንም ገደብ እንዲጋቡ ፈቅደዋል፡፡
    በዚህም መሠረት ልጃቸውን ወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክን ለወሎው ገዥ ለኢማም መሐመድ አሊ (በኋላ ንጉሥ ሚካኤል ለሆኑት) ድረዋል፡፡ ሸዋአረጋ ምኒልክም ከንጉሥ ሚካኤል፤ ልጅ እያሱን ወልደዋል፡፡
  11. ምኒልክ ቀልድና ጨዋታ የሚወዱ ስለነበሩ፤ ሁሉም ሰው እነደ አባት እንጅ እነደ ገዥ አያያቸውም ነበር፡፡
    በዚህም የተነሳ ህዝቡ እምዬ ምኒልክ ብሎ ቢጠራቸው አያስገርምም፡፡
  12. ምኒልክ ከአገር ውስጥ ቋንቋዎች፤ አማርኛኦሮምኛአፋርኛና ትግሪኛ ሲናገሩ፤ ከውጭ አገር ቋንቋዎች ደግሞ፤ ፈረንሳይኛእንግሊዝኛና ጣሊያንኛ አቀላጥፈው ይናገሩ ነበር፡፡


The Passing Away of Emperor Menelik
ላ ትሪቡና ኢሊውሰትራታ የተሰኘው የፈርንሳይ
ጋዜጣ በወቅቱ የአፄ ምኒልክን አሟሟት
በዚህ ሰዕል አማካኝነት ዘግቦታል
ምኒልክ ህመም የጀመራቸው ግንቦት 10 ቀን 1900 ዓ.ም. ነው፡፡ የኢትዮጵያንና የሞቃዲሾን የወሰን ስምምነት ከጣሊያን ጋር ከፈረሙ በኋላ በደም ብዛት ህመም ምክንያት የቀኝ ጎናቸው ፓራላይዝ ሆነ፡፡
ይህም ብቻ ሳይሆን ምኒልክ የልብ ህመምም ነበረባቸው፡፡
ህመማቸው ሲጀምራቸው እድሜያቸው 64 አመት ሆኗቸዋል፡፡
በውጭ አገር ሀኪሞች ህክምና አያገኙ ቢሆንም በጤናቸው ላይ ብዙ መሻሻል አልታየባቸውም፡፡
ሆኖም ምኒልክ በከዘራ እየተደገፉም ቢሆን ሥራወችን ለመሥራት ይሞክሩ ነበር፡፡
ምኒልክ ጤነኛ መስለው ይታዩ እንጅ፤ ነሐሴ 21 ቀን 1900 ዓ.ም. ህመማቸው ብሶባቸው ወገባቸው እንዳለ ፓራላይዝ ሆነ፡፡
ዋናው ህመማቸውም ፓራሊስስ (የወገብ ልምሻ) ነበር፡፡
ምኒልክን ለማከም ብዙ ሀኪሞች ከየአገሩ ማለትም፤ ከሶሪያ፤ ከቱርክ፤ ከፈረንሳይ፤ ከጀርመን መጥተው ህመማቸውን ያጠኑ ነበር፡፡
Dr. Martin.jpg
ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ (ዶክተር ማርቲን)

ስለ ዶክተር ማርቲን የበለጠ ለማንበብ… ethiopiaanything
ምኒልክ ጠበል ለመጠመቅ ደብረ ሊባኖስ በሚሄዱበት ወቅት፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሮይተር ጋዜጠኛ አብሮአቸው ሄዶ ነበር፡፡
ምኒልክን በጀርመን ሀኪሞች ብቻ አልታከሙም፡፡
ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ (ዶክተር ማርቲን) በቦታው ተተክተው እሰከመጨረሻው ሰዓት ድረስ አብረዋቸው ነበሩ፡፡
በርትሊ የተባለው ስለ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሲዘግብ፤
“...ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ (ዶክተር ማርቲን) ተጠርተው የተቻላቸውን ሁሉ ቢያደርጉም፤ ባጠገባቸው የነበሩት ታላላቅ ሰዎችና ቀሳውስት ዘመናዊ ህክምናውን ስለከለከሉ ንጉሡ ሞቱ፡፡
እነኝህ ሰዎች በፈረንጅ ህክምና አናምንም ብለው ህክምናውን ባይከለክሉ ኖሮ ምኒልክ አይሞቱም ነበር፡፡”

በማለት ጽፏል፡፡

e'eka Negist Mausoleum
የዳግማዊ አፄ ምኒልክ መታሰቢያ የሆነው
የታዕካ ነገሥት በአታ ለማሪያም ገዳም
አፄ ምኒልክ አርብ ታህሳስ 3 ቀን 1906 ዓ.ም. በተወለዱ በ 69 ዓመት ከ4 ወራቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እንዳረፉ፤ ሞታቸው ተደብቆ፤ አጽማቸው በሥዕል ቤት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አርፎ ነበር፡፡
ልጃቸው ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ከነገሡ በኋላ፤ አሁን የዳግማዊ አፄ ምኒልክ መታሰቢያ ቤት ተብሎ የተሰየመው የታዕካ ነገሥት በአታ ለማሪያም ገዳምን በ1910 ዓ.ም. እነዲመሠረት አድርገው፤ በ1920 ዓ.ም. የቤተክርስቲያኑ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ የዳግማዊ አፄ ምኒልክን አጽም አሳርፈውና ቤተ ክርስቲያኑ ለስማቸው መታሰቢያነት እንዲሆንና እንዲቀደስበት በማድረግ በዓሉን አክብረዋል፡፡

የዳግማዊ አፄ ምኒልክ፣ የእቴጌ ጣይቱና የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ
የመቃብር ሐውልቶች በታዕካ ነገሥት በኣታ ለማሪያም ገዳም ይገኛሉ

mausoleum.jpg
መሀል ያለው የዳግማዊ አፄ ምኒልክ፣ በግራ የእቴጌ ጣይቱ፣ በቀኝ የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ




...( ወደ ቤተ ድረ ገጽ ይመለሱ )




ምንጭ፤
  1. "አጤ ምኒልክ"  ደራሲ፡- ጳውሎስ ኞኞ የካቲት ወር 1984 ዓ.ም.
  2. "የኢትዮጵያ ታሪክ ከ 1847 እሰከ 1983"  ደራሲ፡- ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ
  3. "የኢትዮጵያ ታሪክ - ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ"  ደራሲ፡- ተክለ ጻድቅ መኩሪያ 1961 ዓ.ም.
  4. "መራራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ "  ደራሲ፡- ታዬ ቦጋለ አረጋ 2011 ዓ.ም.