በዚህ ድረገጽ የቀረቡት የአርበኞች ፎቶዎች ከነመግለጫቸው በአብዛኛው የተወሰደው፣
በቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ በ፲፱፻፰ ታትሞ ከነበረው፤ ”ቀሪን ገረመው የአርበኞች ታሪክ” ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ለተከበሩት ለዚህ መጽሐፍ ደራሲና ለቤተሰቦቻቸው በቅድሚያ ላቅ ያለ ምስጋና ለማቅረብ እንወዳለን፡፡
...የድረ ገጹ አዘጋጅ
የአቶ ታደሰ ዘወልዴ አጭር የሕይወት ታሪክ
አቶ ታደሰ ዘወልዴ በ1895 ዓ.ም. ከአባታቸው ከአቶ ዘወልደ ማሪያም ሀብተ ማሪያምና ከእናታቸው ከወይዘሮ ወለተ ማሪያም በሸዋ ጠቅላይ ግዛት በመንዝና ይፋት አውራጃ ተወለዱ፡፡
በ1919 ዓ.ም. ወደ ግብፅ አገር ሄደው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ከተመረጡት 21 ተማሪዎች ጋር እስክንደሪያ በመሄድ የፈረንሳይኛ ትምህርት ከተከታተሉ በኋላ ወደ ፈረንሳይ አገር ተጉዘው የቴሌኮሙኒኬሽን ትምህርት ሲማሩ እንደቆዩ በ1928 ዓ.ም. የጣሊያን ፋሽስት ወረራ በአገራችን ላይ ሲካሄድ የክተት አዋጁን በወዶዘማችነት ተቀብለው ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ማይጨው ዘመቱ፡፡
አርበኛው ታደሰ ዘወልዴ፤ አርበኞች በቁጥራቸው ማነስ ሳይጨነቁ ችግሩን ሁሉ ተቋቁመው ለሀገራቸው ነፃነት በቆራጥነት እንዲዋጉ የሞራልና የመንፈስ ማበረታቻ ዘዴ በመጠቀም አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
”አገሩን አፍቃሪ የሆነ ሰው ትግሉና ሩጫው ሁሉ ለትውልድ በሚሆን ነገር እንጅ ለራሱ በሚሆን ነገር ገንዘብና ርስት ለማግኘት በጠቅላላው ሀብት ለማድለብ ስላልሆነ ዛሬ በሞት የሚያልፈው ሰው የማይሞትና የማያልፍ ለትውልድ የሚሆን ነገር ሠርቶና ትቶ መሄድ አለበት፡፡”
”ሰው ከፍጥረታት ሁሉ በላይ ከፍ ያለ ፍጡር እንደመሆኑ መጠን አስተያዬቱ በግል ጥቅም የተወሰነና በዚህ ዓለምም የሚኖረው ራሱን ለማገልገል እንዳልሆነ ማወቅ ይኖርበታል፡፡“
...ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ - “ቀሪን ገረመው - የአርበኞች ታሪክ” ደራሲ