Content-Language: am አፄ ዮሐንስ 4ኛ
header image

አፄ ዮሐንስ 4ኛ



የአፄ ዮሐንስ 4ኛ የአስተዳደርና የሕይዎት ዘመን ትረካ

በእያንዳንዱ አርዕስት ሥር የሚገኘውን የድምጽ ማጫወቻ በመጠቀም
ትረካውን ማዳመጥ ይችላሉ

ትውልድ፣ ዕድገት፣ ወደ ሥልጣን
የጉዟቸው መንገድና የንግሥ ሥነስርዓት
የአገዛዝ ዘይቤ፣ ስለሐይማኖት የነበራቸው
አቋምና የግብፆች የግዛት ማስፋፋት
በጉንደትና በጉራ ከግብፆች ጋር ያደረጉት ጦርነት፣
ከቅኝ ገዥወች እንግሊዝና ኢጣሊያ ጋር የነበራቸው ፍጭጫ
ከመሐዲስቶች ጋር ያደረጉት ውጊያና
በውጊው ላይ የደረሰባቸው ሕልፈተ ሕይወት



አፄ ዮሐንስ 4ኛ

Photo courtesy of: rastafari.tv
አፄ ዮሐንስ 4ኛ ከመንገሣቸው በፊት ልጅ ካሣ ምርጫ ይባሉ ነበር፡፡
ካሣ ምርጫ በትግራይ ክፍለ ሀገር በተምቤን አውራጃ ከአባታቸው ከምርጫ ወልደ ኪዳን እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ስላስ ድምጹ ሐምሌ 5 ቀን 1829 ዓ.ም. እንደተወለዱ ይገመታል፡፡
ካሣ ምርጫ ከቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ ነበሩ፡፡







ልጅ ካሣ ምርጫ በንጉሠ ነገሥት አፄ ቴወድሮስ በተሰጣቸው ሹመት ደሰተኛ አልነበሩም፡፡
ሁለቱ ወንድሞቻቸው የደጃዝማችነትና የቀኛዝማችነት ማዕረግ ሲያገኙ፣ እሳቸው ግን ዝቅተኛውን የባላምባራስነት ማእረግ በማግኘታቸው ደስተኛ ስላልነበሩና በተጨማሪም እስር ላይ የነበሩት አቡነ ሰላማ አፄ ቴወድሮስን በመቃወም የፃፉት ደብዳቤም በአፄ ቴወድሮስ ላይ ለማመጽ ምክንያት ሆናቸው፡፡
በኋላም በአፋር በስደት ቆይተው ወደ ትግራይ ከተመለሱ በኋላ ከአፄ ቴወድሮስ ባላንጣዎች ጋር በማበርና ተከታዮችን በማፍራት አፄ ቴወድሮስ በሾሟቸው የትግራይ ባለሥልጣኖች ላይ ጦርነት በመክፈት የአፄ ቴወድሮስ መንግሥት እንዲዳከም ምክንያት ሆነዋል፡፡
የእንግሊዙ ጦር አዛዥ ጀነራል ናፒር አፄ ቴወድሮስ ያሰሯቸውን የእንግሊዝ መልክተኞችን ለማስፈታት ጦሩን እየመራ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ ከትግራዩ ገዥ ከደጃዝማች ካሣ ምርጫ ጋር ስብሰባ አድርገው ተወያይተው ነበር፡፡
በውይይቱም መሠረት ካሣ ምርጫ የእንግሊዝ ወታደሮችን በሰላም ካሳለፉና ለእንግሊዝ ወታደሮች ቀለብ የሚያቀርቡ እንደሆነ፣ እንግሊዞች መቅደላ ዘምተው እስረኞቻቸውን አስፈትተው ሲመለሱ የጦር መሣሪያ እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸው ነበር፡፡
በዚህም መሠረት እንግሊዞች ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር ያደረጉት ጦርነት ሲያበቃ ለካሣ ምርጫ፤
  1. 12 መድፎች፣
  2. 280 የመድፍ ጥይቶች፣
  3. 900 ጠመንጃዎች፣
  4. 349 ሺህ ጥይቶችና
  5. 3 ሺህ 200 የሽጉጥ ጥይቶች
ሰተዋቸዋል፡፡
አፄ ቴወድሮስ ሞት በኋላ የሥልጣን ክፍተት በመፈጠሩ በአፄ ቴወድሮስ ተቀናቃኞች መካከል የሥልጣን ጥያቄ እንደገና ተቀሰቀሰ፡፡
በዚህም መሠረት አንደኛው ሥልጣን ፈላጊው፣ የአፄ ቴዎድሮስ ዋና ተቀናቃኝ እና የሰለሞናዊው ሥርዎ መንግስት አባል የነበረው የላስታው ዋግሹም ጎበዜ፤ (ላስታ፡- በሰሜን ወሎ የሚገኝ የቅዱስ ላሊበላ 11 ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት የሚገኙበት ወረዳ ነው) የወልቃይት ገዥ የነበረውን ጥሶ ጎበዜ የተባለውን ድል ቢያደርግም እነደ ካሣ ምርጫ ከወራሪዎቹ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ስላልነበረው በወራሪዎቹ የእንግሊዝ ወታደሮች አማካኝነት የጦር መሣሪያ አላገኘም፡፡
ሆኖም ዋግ ሹም ጎበዜ ራሱን አፄ ተክለ ጊዮርጊስ አሰኝቶ ነገሠ፡፡
የሸዋው ንጉሥ አፄ ምኒልክም የዋግሹም ጎበዜን መንገሥ ተቀብለውት ነበር፡፡
በጎጃም የነገሡት ራስ አዳል ተሰማም (በኋላ ንጉሥ ተክለሐይማኖት)፤ የዋግሹም ጎበዜን አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ተሰኝቶ መንገሥን በመቀበል የአፄ ተክለ ጊዮርጊስን እህት በማግባት በጋብቻ ተሳሰሰሩ፡፡
የካሣ ምርጫም እህት ወይዘሮ ድንቅነሽ የአፄ ተክለ ጊዮርጊስ ሚስት በመሆኗ በጋብቻ ተሳስሮ ቢቆይም ካሣ ምርጫን ከአመጽ እንዲታቀብ ስላላደረገው ከእህቱ ባል ከአፄ ተክለ ጊዮርጊስ ጋር ጦርነት ገጠመ፡፡
ይሁን እንጅ የካሣ ምርጫ ጦር በወራሪው የእንግሊዝ ጦር በተበረከተለት ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቀና እንዲሁም በእንግሊዛዊው የጦር አማካሪ ኪርክሃም አማካኝነት በዘመናዊ የውጊያ ስልት የታገዘ ስለነበረ 60 ሺህ የነበረው የአፄ ተክለ ጊዮርጊስ ተዋጊ ሠራዊት በ 12 ሺህ የካሣ ምርጫ ሠራዊት ድል ሆነ፡፡
ከስድስት ወር በኋላም ጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም. አፄ ዮሐንስ ለመንገሥ ወደ አክሱም ጽዮን ማርያም ለመሄድ ሲንቀሳቀሱ፤ ቀሳውስቱ ተሰብስበው፤
“ሚስት ሳይኖርዎት እንዴት እናነግስዎታለን?” ብለው ሲጠይቋቸው፤
“ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፈውን አላነበባችሁምን? ሚስት ያለው በሙሉ ልቡ እግዚአብሔርን ሊያገለግል አይችልም ብሎ የለምን?...”
ብለው መልስ ከሰጧቸው በኋላ ሚስት ሳያገቡ ብቻቸውን “አፄ ዮሐንስ 4ኛ ንጉሠ ነገሠት ዘ ኢትዮጵያ” ተብለው ነገሡ፡፡



የአፄ ዮሐንስ የአስተዳደር ዘይቤ በአፄ ቴወድሮስ ተጀምሮ የነበረውን ጠንካራ ንጉሣዊ አገዛዝ እንደገና የመመሥረት ፍላጎት የወረሰ ቢሆንም የተከተለው የአገዛዝ መንገድ ግን በእጅጉ የተለየ ነበር፡፡
አፄ ዮሐንስ የበላይነቱ እስከታወቀላቸው ድረስ ኢትዮጵያን ከአቻ መሳፍንት ጋር ለመጋራት ዝግጁ ነበሩ፡፡
ይህ የአገዛዝ ዘይቤ ብልኅነት የተመለባት ቢመስልም የማታ ማታ ግን ለራሳቸው ለንጉሡ ጦስ እንደነበረ መገንዘብ ተችሏል፡፡
እርስ በርስ ባላንጣዎች በነበሩት በጎጃሙ ንጉሥ ተክለሐይማኖት እና በሸዋው ንጉሥ ምንይልክ መካከል ያለውን የኃይል ሚዛን ለማስጠበቅ አፄ ዮሐንስ ብዙ ቢደክሙም ሳይሳካላቸው ስለቀረ ሁለቱ ንጉሦች እርስ በራሳቸው ይቅር ለእግዚአብሔር ተባብለው በንጉሠ ነገሥቱ ላይ የአመፅ ግንባር ፈጠሩ፡፡

ንጉሠ ነገሥቱ፤ በአንድ በኩል በጣሊያኖች፣ በሌላ በኩል በማህዲስቶች ስለተወጠሩ በንዴትም ይሁን በሌላ ሁኔታ ተነሳስተው በጎጃም ሕዝብ ላይ ዘግናኝ የሆነ የቅጣት ማዕበል አዘነቡበት፡፡
በጎጃም ላይ ያደረሱትን ጥፋት በማመንም ለራስ ዳርጌ በጻፉት ደብዳቤ፤
“በድሀው ኃጢያት እንደሆነም አይታወቅም፤ አገሩን ሳጠፋ ከረምኩ፡፡”
በማለት ሀሳባቸውን አስፍረዋል፡፡
የአፄ ዮሐንስ የአንድነት ስልት ሐይማኖታዊ ገጽታ ነበረው፡፡
ዓላማቸው የእምነት ብቻ ሳይሆን የሐይማኖትም አንድነት መመስረት ነበር፡፡
የእስልምና ሐይማኖት በአፄ ዮሐንስ ርዕዮት ዓለም ውስጥ ምንም ስፍራ አልነበረውም፡፡
አፄ ዮሐንስ በፖለቲካው መስክ ያሳዩትን ሆደ ሰፊነት በሐይማኖት ረገድ ሊያሳዩ አልፈቀዱም፡፡
ይህም በመሆኑ በተለይ የወሎ ሙስሊሞች የእስልምና ሐይማኖታቸውን ለውጠው ክርስትናን እንዲቀበሉ፤ ያለበለዚያ ግን ንብረታቸውን እንዲያስረክቡ ታዘዙ፡፡
የፖለቲካ መሪወች የነበሩት እንደነ መሐመድ ዓሊ (በኋላ የወሎ ንጉሥ ሚካኤል) ሐይማኖታቸውን ለውጠውና ክርስትናን ተቀብለው ሚካኤል ሲባሉ ሌላውም ህዝብ መስሎ ለማደር እሽ በማለት ለይስሙላ ተቀበለ፡፡ ቀን ቀን ለእግዚአብሔር፣ ማታ ማታ ደግሞ ለአላህ መፀለዩን ተያያዙት፡፡
ሌሎቹም በሐይማኖታቸው ምክንያት መኖር የተቸገሩ ደግሞ ወደ አርሲ እና ወደ ጉራጌ ሀገር ተሰደው ብዙ መከራ ተቀብለዋል፡፡

አፄ ዮሐንስ ቦሩ ሜዳ በተባለው ቦታ ላይ ትልቅ የሐይማኖት ጉባኤ አድርገው ነበር፡፡
በዚህም ጉባኤ ላይ ንጉሠ ነገሥቱ ይደግፉት የነበረው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ብቸኛው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እምነት ሆኖ እንዲቀጥልና የሌሎች እምነት ተከታዮችም በጉባኤው በተደረገው ክርክር እንደተረቱ ተቆጥረው የተዋህዶ ቤተክርስቲያንን እምነት እንዲቀበሉ ደነገጉ፡፡
ቀደም ሲል የነበረው የዘመነ መሳፍንት ርዕዮት መሠረት የነበረው የዕምነት ልዩነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማሳረጊያውን አግኝቶ ጉባኤው ተጠናቀቀ፡፡
ድንጋጌውን አንቀበልም ብለው በድሮው እምነታችን እንጸናለን ያሉት የህብረተሰብ ክፍሎች ግን መከራና ስደት ጠበቃቸው፡፡
ይሁን እንጅ የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዲጠበቅ በማድረጋቸው፤ በግብጾችም ላይ ባገኙት ድልና እንዲሁም ለዘመናት በአንድ ጳጳስ ተወስና ለቆየችው ቤተ ክህነት ከግብጽ አራት ጳጳሳት በማስመጣታቸው በቤተክርስቲያን አባቶችና በህዝቡ ዘንድ ከበሬታን አስገኝቶላቸው ነበር፡፡



ከአፄ ቴዎድሮስ መንግሥት መውደቅ በኋላ፤
"እንግሊዞች እንዲህ በቀላሉ ኢትዮጵያ እምብርት መድረስ ከቻሉ እኛስ ምን ያቅተናል? አይበገሬ የተባለው የአበሻ ህዘብ ለካ እንዲህ በቀላሉ የሚንበረከክ ነው?"
የሚል ከንቱ ሀሳብ በአንዳንድ የውጭ መንግሥታት ኃይሎች ውስጥ መስረፅ ጀመረ፡፡
ለዚህም ስሜት መፈጠር ጉልህ ድርሻ ያበረከተው በምፅዋ የፈረንሳይ ቆንስል (counseller) የነበረው ስዊዘርላንዳዊው ቅጠረኛ ቨርነር ሙዚንገር ነበር፡፡
ይህ ሰው በኢትዮጵያ ምድር ከረንን ከያዘ በኋላ የግብፅ የግዛት የመስፋፋት ፖሊሲ ቀያሽ በመሆን ሠርቷል፡፡
በዚህም መሠረት ሙዚንገር 2ሺህ ወታደሮቹን ይዞ ወደ ጎንደር ለመሄድ ሲያቀና፤ የሙዚንገር ጦር የኢትዮጵያን ድንበር መሻገሩን የሰሙ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን የሙዚንገርን ጦር ጥቅምት 29 ቀን 1867 ዓ.ም. ጠብቀው በደፈጣ ውጊያ ፈጁት፡፡
ሙዚንገር፣ ራስ ካሳ ምርጫ (በኋላ አፄ ዮሐንስ) የካቶሊኮችን እንቅስቀሴ ለማገድ የሚያደርጉትን ጥረት አስመልክቶ በጻፈው ደብዳቤ፤ “ካሣ ፀባዩን ያላሳመረ እንደሆነ የቴዎድሮስ ፅዋ ይጠብቀዋል::” በመላት ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር፡፡
የኦቶማን ቱርኮች፤ ግብፅን ለ350 ዓመታት በቅኝ ግዛትነት ተቆጣጥረው በነበረበት ወቅት ግብፅና ሱዳንን 16 ዓመት ገዝቶ የነበረው ቱርካዊው እስማኤል ፓሻ፣ የአያቱን የሙሀመድ ዓሊ ፓሻን የተስፋፊነት ፈለግ በመከተል፤
የግብፅ እድገትና ብልጽግና የተመሠረተው በአፍሪካ ላይ መሆኑን ተግንዘቦ የዓባይን ፈለግ ተከትሎ ወደ አፍሪካ ምድር መስፋፋት ቀጠለ፡፡
በዚህም መሠረት የዛሪዋን የደቡብ ሱዳንን ግዛት ወደ ክልሉ አስገባ፡፡
የእስማኤል እቅድ ባጭሩ ነጭ አባይንና ጥቁር ዓባይን ያቀፈ፣ ማለትም ሱዳንንና ኢትዮጵያን ከግብፅ ጋር በመደባለቅ "የግብፅ-አፍሪካ ግዛት" የተሰኘ ሰፊ የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ግዛት ለመፍጠር ነበር፡፡
በነገራችን ላይ ግብፆች በርካታ የቅኝ ገዥዎች ተፈራርቀውባታል፡፡

በግብፅ ላይ የተፈራረቁባት ቅኝ ገዥዎች

  1. በኦቶማን ቱርኮች ለ 350 ዓመታት፣
  2. በፈረንሳዮች ለ 3 ዓመት፣
  3. በኋለኛው ዘመን በተነሳው የኦቶማን ቱርክ በሞሀመድ ዓሊ ሥርዎ መነግሥት ለ 148 ዓመታት፤
  4. በኦቶማን ቱርክ ገባር መንግሥት ለ 47 ዓመታት፣
  5. በእንግሊዞች ለ 40 ዓመታት፤
በጠቅላላው ለ 588 ዓመታት በቅኝ ገዥዎች ተገዝተዋል፡፡
ግብፅ ከቅኝ ግዛትነት ወጥታ ራሷን በነፃነት ማስተዳደር የጀመረችው በ 1945 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡
አፄ ዮሐንስ የክርስቲያን መንግሥት በእስላም ሲጠቃ ያውሮፓ ክርስቲያን መነግሥታት አጋርነታቸውን እንዲገልጹ ቢጥሩም ውጤት አላመጡም፡፡
በአውሮፓ የወዳጅነት መመዘኛው ሐይማኖት ሳይሆን ቁሳዊ ጥቅም ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ይልቅ ግብፅ ለአውሮፓ ኢኮኖሚያዊና ስትራተጅካዊ ጠቀሜታ ሰላላት አውሮፓውያን ግብፅን የመርዳት ዝንባሌ ማሳየት ጀመሩ፡፡
ግብፆች በሰሜን በኩል ምጽዋ፣ ዙላና አንፈላ የተባሉ የቀይ ባሕር ወደቦችን ከተቆጣጠሩ በኋላ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ በማምራት ወደ ተሟላ አገራዊ ወረራ ተሸጋገሩ፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን በመስከረም ወር 1868 ዓ.ም. የግብጽ ጦር እየገፋ ሲመጣ ከግብፆች ጋር ሰላም ለመፍጠር በማለት አፄ ዮሐንስ የሐማሴንና የሠራዬ አውራጃ ሠራዊታቸው ወደ አድዋ እንዲያፈገፍግ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡



አፄ ዮሐንስ በግብፅ ወራሪ ጦር ላይ የክተት አዋጅ ያወጁት የግብጽ ጦር ሐማሴን ከደረሰ በኋላ ነው፡፡
ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ የግብፅን ወራሪ ጦር ለመግጠም 20 ሺህ ጦር አሰልፈው የክተት አዋጅ አወጁ፡፡
አፄ ዮሐንስ ያወጁት የክተት አዋጅ፤
“ክርሰቲያን የሆንክ ሁሉ ቄሶች ጭምር ወደመጣው ጠላት እንድትዘምቱና እስላሞችን እንድታጠፉ፡፡” የሚል ነበር፡፡
አፄ ዮሐንስ ኤርትራ በሚገኘው ጉንደት ላይ የገጠሙት ጦርነት ወሳኝ ጦርነት ነበር፡፡
የግብፅ ጦር ከኢትዮጵያ ጋር ሲዋጋ ብቻውን አልተዋጋም፡፡
Battle of Gundent
ኤርትራ የሚገኘው የጉንደት
ጦርነት የተካሄደበት የግብፆች ምሽግ
የግብፅ ጦር፤ ግብፅን በቀኝ ግዛትነት ተቆጣጥሮ ይገዛ የነበረ የኦቶማን ቱርክ ተስፋፊ ኃይል ሲሆን፤ በአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ወቀት የተሳተፉ በርካታ ቁጥር ያላቸው የአሜሪካ የጦር መኮንኖችና እነዲሁም ከአውሮፓ ከተላኩ ቅጠረኛ የጦር መኮንኖችና ወታደሮች ጋር ቅንጅት በመፍጠር የተካሄደ ጦርነት ነበር፡፡
አፄ ዮሐንስ ጉንደት በተባለው ሥፍራ በተካሄደው ውጊያ በግብፆች ላይ ድል ተቀዳጅተዋል፡፡
ጉንደት ላይ በተካሄደው ጦርነት፤ በኢትዮጵያ በኩል፤ በአፄ ዮሐንስ፣ በራስ አሉላ እንግዳ እና በራስ ወልደ ሚካኤል ሰለሞን የጦር መሪነት፤ 50 ሺህ ጦር ሲሰለፍ፤
በጉንደት ጦርነት የጀግና
ሴቶች አጋርነት ሲታይ

ምስጋና:- ለይርጋዓለም አበበ ኃይሌ
በግብፅ በኩል ደግሞ፤ በዴንማርኩ አዛዥ በኮሎኔል አረንድሩፕና በአሜሪካ የጦር መኮንኖች የሚመራ 5 ሺህ ጦር ተሰልፎ ህዳር 8 ቀን 1869 ዓ.ም. ጦርነት ተካሂዶ በአራትና በአምስት ሰዓታት ውስጥ እጅግ በሚደንቅ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሠራዊት የግብፅን ጦር ሙሉ በሙሉ በመደምሰስ ከፍተኛ ድልን ተቀዳጅቷል፡፡

የግብፅ ጦር አዛዥ የነበረው ኮሎኔል አረንድሩፕም በዚሁ ቀን ተገሏል፡፡
በጉንደት ጦርነት የግብፅ ጦር አዝማች ሆኖ ተሰልፎ የነበረው አሜሪካዊው ኮሎኔል ስለ ግብፆች መሸነፍ ሲጽፍ፤
በጦር ተወግተው የተጋደሙ፣ እጃቸው የተቆረጠ፣ አንገታቸው የተቀነጠሰ አካላት፣ ድል አድራጊውን ጠላት ማረኝ ማረኝ ይላሉ፡፡ ግን ማን ሊሰማ፡፡ ጭፍጨፋውን የሚያቆም ምንም ኃይል አልነበረም፡፡
በመላት ምስክርነቱን ሰቷል፡፡
ይህን በግብፅ ጦርና በቅጥረኛ ወታደሮች የደረሰውን ከፍተኛ ሽንፈት የግብፅ ሕዝብ ቢሰማው የኦቶማን ቱርክ የገዥነትን ክብር ያዋርዳል ብለው ስላሰቡ ወሬው ሳይነገር ተዳፍኖ ቀርቷል፡፡



በኤርትራ ምድር የሚገኘው የጉራ ጦርነት የተካሄደበት ምሽግ

  (Image modified by: the webmaster)
የግብፅ ወራሪ ጦር በጉንደት በደረሰበት ሽንፈት ከአራት ወራት በኋላ በቁጭት ተነሳስቶ ለሁለተኛ ጊዜ በአሜሪካዊው የጦር ጀነራል መሪነት ከ 15 ሺህ ጦር ውስጥ 5 ሽውን ለውጊያ አሰልፎ ነበር፡፡
በጉራ ጦርነት ብዙ የውጭ አገር የጦር መሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ፤ የዴንማርኩ የጦር አዛዥ ኮሎኔል አረንድሩፕና የስዊዘርላንዱ አሳሽ ዋርነር ሙዚንገር ይገኙበታል፡፡
ሆኖም በኢትዮጵያዊው የመረብ ምላሽ (የአሁኗ ኤሪትራ) ገዥና የጦር መሪ በራስ አሉላ የተመራው የኢትዮጵያ ሠራዊት የግብፅን ጦር ከቦ መፈናፈኛ በማሳጣት ከፍተኛ ጉዳት ሰላደረሰበት በሶስት ቀናት ውጊያ አብዛኛው የግብፅ ወራሪ ጦር ተገድሎና ተማርኮ በኢትዮጵያ ሠራዊት ድል አድራጊነት ድጋሚ ሽንፈትን ተከናነበ፡፡
በዋርነር ሙዚንገር የሚመራውም የግብፅ ጦር፤ በአፋር የአውሳ ሱልጣን በሆነው በመሐመድ ኢብን ሀንፋድ የሚመራው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከበባ አድርጎ ስለደመሰሰው ዋርነር ሙዚንገርም በዚህ ውጊያ ተገድሏል፡፡

ግብፆች፤ በጉንደትና በጉራ ጦርነት ተደጋጋሚ ሽንፈት ስደረሰባቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የመስፋፋት አላማቸው ተጨናግፎ ቀረ፡፡

አፄ ዮሐንስ ግብፆች የወሰዷቸውን የኢትዮጵያ ግዛቶች ለማስመለስና ለኢትዮጵያ ነፃ የባሕር ወደብ ለማግኘት እንዲችሉ መልክተኛ ቢልኩም ግብፆች የአፄ ዮሐንስን መልክተኛ ሁለት ወር አስረው ያለምንም ውጤት መልሰውታል፡፡



እንግሊዞች የአፄ ዮሐንስን የነፃ የባሕር ወደብ ጥያቄን ለማስተናገድ አልፈለጉም፡፡
እንግሊዞች፣ ቀይ ባሕር በግብፆች፤ ካልሆነም በሌላ በእንግሊዝ ወዳጅ በሆነ መንግሥት ቁጥጥር ስር መቆየት አለበት ብለው ወስነዋል፡፡
በዚህም መሰረት የግብፅ መንግስት እየተዳከመ ሲሄድ እንግሊዞችም ግብፅን በቁጥጥር ስር አደረጉ፡፡
ቀደም ብላ የአሰብ ወደብን ይዛ ለነበረችው ኢጣሊያም፣ እንግሊዞች የምጽዋን ወደብን እንድትቆጣጠር ፈቀዱላት፡፡
በዚያን ወቅትም የአሰብ ወደብ የኢጣሊያ መንግስት ንብረት እንዲሆን ተወስኖ ነበር፡፡
ጣሊያንም አንድ ጥይት ሳትተኩስ ወደ መሀል ኢትዮጵያ የምትንደረደርበትን የምጽዋን ወደብን በእንግሊዝ ቡራኬነት በነፃ አገኘች፡፡
እንግሊዝ የምፅዋን ወደብ ለኢጣሊያኖች ስትሰጥ የራሷ ስሌት ነበራት፡፡ ምክንያቱም፣ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረች፣ የቅኝ ግዛቱን በአፍሪካ ምድር ለማስፋፋት ያሰፈሰፈው የፈረንሳይ መንግሥት ወደ አባይ ድርሽ እንዳይል ኢጣሊያ ትከላከልልኛለች በሚል ስሌት ነበር፡፡

አፄ ዮሐንስ በየዋህነት በገቡት ውልና ቃል መሰረት እንግሊዞች የሚሰሩትን ሸፍጥ ባለመረዳት ከልክ ያለፈ ትብብር በማድረግ ሁለት ጊዜ በጦርነት ድል ባደረጓቸው ደካማ የግብፅ መንግስት ምትክ ሁለት ጠንካራ ጠላቶችን (ኢጣሊያ እና መሀዲስቶችን) ተክተው አረፉት፡፡

ጣሊያኖች በአሰብና በምፅዋ ወደብ ብቻ ተወስነው መቅረት ስላልፈለጉ ይልቁንም ወደ መሀል ኢትዮጵያ ዘልቀው ለማያዝ ከፍተኛ ፍላጎት አደረባቸው፡፡
Ras Alula
ራስ አሉላ ዕንግዳ
የመረብ ምላሽ ገዥ የሆኑት ራስ አሉላ ጣሊያኖች የያዙትን የእትዮጵያ ምድር እንዲለቁ በደብዳቤ ትዕዛዝ ቢሰጡም ጣሊያኖች ስላልተቀበሉት ጀግናው ራስ አሉላ ፈረሳቸውን ጭነው ጥር 20 ቀን 1879 ዓ.ም. መሽጎ በተቀመጠው የኢጣሊያ ጦር ላይ ዘምተው ውጊያ ከፈቱባቸው፡፡
የኢጣሊያ ጦር ውጊያውን ስለመከተ፣ ራስ አሉላ ወደኋላ በማፈግፈግ እነደገና የጦራቸውን ኃይል አሰባስበው በመዋጋት፤ ዶግአሊ በተባለው ስፍራ ላይ መሽጎ የነበረውን 500 የኢጣሊያ ጦር ገድለው ድልን በመቀዳጀት ስፍራውን ከጠላት ለማስለቀቅ ችለዋል፡፡
በዚህም ሽንፈት የተነሳ በኢጣሊያ አገር ታላቅ ሽብር ሆነ፡፡
ይህን የተፈጠረውን ጠብ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አፄ ዮሐንስ እና ኢጣሊያ በየግላቸው የእንግሊዝን እርዳታ ጠየቁ፡፡
እንግሊዞች የላኩት አስታራቂም በምላሹ ዮሐንስ በዶግአሊ ላደረሰው እልቂት ኢጣሊያ ይቅርታ እንዲጠይቁ፤ ጣሊያኖች የያዙዋቸውም የኢትዮጵያ ግዛቶች ፀንተው እንዲቀጥሉና ይህንኑ እንዲቀበል የሚል ሆኖ አረፈው፡፡
ይሁን እንጅ እነደዚህ ዓይነቱን ሀሳብ ማንም የተቀበለው አልነበረም፡፡
በዚህን ወቅት ነበር ጀግናው ራስ አሉላ፣ ለተላከው አስታራቂ መልክተኛ፤
“ጣሊያኖች ኢትዮጵያ ምድር ላይ የሚሰፍሩት፤ እኔ የሮማ አገረ ገዥ መሆን የቻልኩ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡”
በማለት በታሪክ ሲታወስ የሚኖረውን ድንቅ ንግግር የተናገሩት፡፡

ለጥቂት ዓመታት በርትቶ የነበረው የአፄ ዮሐንስ ኃይል ከ 1877 ዓ.ም. በኋላ መዳከም ጀመረ፡፡
አፄ ዮሐንስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመጋቢት ወር 1880 ዓ.ም. 80 ሺህ ጦር አሰልፈው ጣሊያኖች ላይ ቢዘምቱም የጣሊያኖችን ምሽግ ማስለቀቅ አልቻሉም፡፡
የጦራቸውም ደጀን (ከኋላ የተሰለፈ ተጠባባቂ ጦር) የሳሳ እንደነበር ይነገራል፡፡
ከቀድሞ ምሁራን አንዱ የሆኑት ብላታ ገብረ እግዚአብሔር ጊላ የተባሉ ፀሀፊ አፄ ዮሐንስ የተናገሩትን ሲጠቅሱ፤
“እንግዲህስ የሰው አገር እንገዛለን ብለው መጥተው ከምሽግ መሀል ከተሸሸጉ እኔ ምን አደርጋለሁ ብለው ተመለሱ፡፡”
በማለት ጽፈዋል፡፡



Ethiopian Warrios with Mehadists
አፄ ዮሐንስ በጦር ሜዳ
ላይ የተገደሉበት የያኔው
መተማ በሰዓሊው እይታ

Image courtesy of: Ethiopian warriors
ከመሀዲስቶች ጋር የነበረው ዋናው የጦርነት ፍልሚያ መተማ ላይ ነበር፡፡
ሱዳኖች ‘ጋላባት’ ብለው የሚጠሯት መተማ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ለረጅም ጊዜ የሰላምም ሆነ የጠብ መገናኛ መድረክ ሆና ቆይታለች፡፡
የእስልምና ተሐድሶ ብሎ የተነሳው ይህ የመሀዲስቶች ንቅናቄ ሰሜንንና ማእከላዊ ሱዳንን አጥለቀለቀው፡፡
በዚህ ወቀት ግብፅ በእንግሊዝ ቁጥጥር ስር ወድቃ ነበር፡፡
ግብፆች በኢትዮጵያ ላይ ጀምረውት የነበረውን የመስፋፋት ፖሊሲ በመመርኮዝ ነው የኢጣሊያም ሆኑ የግብፆች ቀንደኛ ጠላቶቹ የሆኑት መሀዲስቶች የተነሱት፡፡
መሀዲሰቶች ግብፆችን ለማሳደድ የተነሱት ከሱዳን ምድር ነው፡፡
የመሀዲሰቶች ንቅናቄ አነሳስ ዋናው ምክንያት የእስልምና ተሀድሶን ለማስፋፋትና የሚጠሉትን የግብፅ አገዛዝ ለማሶገድ ነበር፡፡
ተቆርጦ ሱዳን የቀረውን የግብፅን ጦር ከመሀዲስቶች ለማዳን የሚቻለው በኢትዮጵያ ምድር አቋርጦ ማለፍ ከቻለ ብቻ ስለነበረ ይህን ለማስፈጸም እንግሊዞች የግድ ከኢትዮጵያ ጋር በመስማማት እርዳታዋን መጠየቅ ስለነበረበቻው መልክተኛ በመላክ ከአፄ ዮሐንስ ጋር ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
አፄ ዮሐንስም የገቡትን ውል አስፈጽማለሁ በማለት የግብፅ ወታደሮች የኢትዮጵያን ምድር አቋርጠው እንዲያመልጡ በመርዳታቸው መሀዲስቶች ተበሳጭተው፤ የጠላቴ ወዳጅ ከጠላቴም በላይ ጠላት ነው በሚል መርህ ኢትዮጵያን የመሀዲስቶች ቁጣ ማሳረፊያ አደረጋት፡፡
ግብፆች አካባቢውን ለቀው ከወጡ በኋላ መሀዲስቶች ወደ ኢትዮጵያ ምድር ዘልቀው በመግባት ዘረፋወችን በመፈፀም መተናኮል ጀመሩ፡፡
በጥር ወር 1879 ዓ.ም. መሀዲስቶች ደምቢያን ከወረሩ በኋላ አከታትለው መተማን አቃጥለው ተመለሱ፡፡
በዓመቱ እንደገና ወደ ጎንደር ሲጓዙ 200 የሚደርሱ አብያተ ክርስቲያናትንና እንዲሁም ጎንደር ከደርሱም በኋላ በተጨማሪ 47 አብያተ ክርስቲያናትን አቃጥለዋል፡፡
ይህም መሀዲስቶች በጎንደር የፈፀሙት ተግባር እስከ ዛሬ ድረስ በጎንደር ሕዝብ ዘንድ በአሰቃቂነቱ ሲታወስ የሚኖር ከባድ ጥፋት ያደረሰ አሳዛኝ ታሪክ ትቶ አልፏል፡፡
በኢትዮጵያና በመሀዲስቶች ጦር መካከል የመጀመሪያው ውጊያ በኤርትራ ውስጥ ተደርጎ በኢትዮጵያ በኩል የጦር መሪው ራስ አሉላ ዕንግዳ ድል ቀንቷቸው አሸንፈዋል፡፡

ግብፆች ቀደም ሲል ተቆጣጥረውት የነበረውን ቤኔሻንጉልንና አሶሳን፣ እንዲሁም ምእራብ ወለጋን፣ አልፎ ተርፎም ወደ ኦሮሞ ምድር በመዝለቅ መሀዲስቶች በግብፆች እግር ስር ተተክተው ግዛቶችን ተቆጣጥረው ነበር፡፡
ይሁን እንጅ አፄ ምንይልክ የጦር መሪያቸውን ራስ ጎበና ዳጨን ልከው መሀዲስቶችን በጦር ሜዳ ፍልሚያ ድል አድርገው ከኢትዮጵያ ግዛት አስወጥተዋቸዋል ፡፡



አፄ ዮሐንስ ደርቡሾችን ለመውጋት፤ልጆቻቸውን ትልቁ ራስ አርአያንና እንዲሁም ራስ መንገሻንና ሌሎች የጦር አለቆችን በማሰለፍ ገስግሰው ወደ መተማ ተጓዙ፡፡
እቅዳቸውም መተማ ላይ ደርቡሾችን ከመቱ በኋላ እምዱርማን ድረስ ዘልቀው ጠላቶቻቸውን ለመደምሰስ ነበር፡፡
የዘመተው ሠራዊታቸውም፤ 130 ሺህ የእግረኛ ጦርና 20 ሺህ የፈረሰኛ ጦር ነበር፡፡
በደርቡሾች በኩል ያለው የሠራዊት ቁጥር 85 ሺህ ይደርሳል፡፡
ዜኩ የተባለው የደርቡሾች ጦር መሪ ስለ አፄ ዮሐንስ የጦር ብዛት ሲናገር፤
“ወደ አበሾች ሰላይ ልኬ ነበርና ብዛታቸው እንደ ሰማይ ኮከብ፣ እንደ ባህር አሸዋ ነው፡፡ ሲጓዙም ከብዛታቸው የተነሳ የምድሩ ትቢያ እንደ ደመና ሆኖ ፀሐይን ይከልላታል፡፡”
በማለት ተናግሯል፡፡
The_Battlefield_Where_king_John_was_killed
አፄ ዮሐንስ በጦር ሜዳ ላይ
የተገደሉበት የያኔው መተማ
የአፄ ዮሐንስ ጦር ከመሀዲስቶች ጋር መጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም. መተማ ላይ ጦርነት ጀመረ፡፡
ጦርነቱ እንደተጀመረ ከሠራዊቱ ብዛት የተነሳ አቧራው እነደ ደመና ሆኖ ሰውና ሰው ለመተያየት እስኪያቅት ድረስ ደርሶ ነበር ይባላል፡፡
በዚህ ታላቅ ውጊያ የአፄ ዮሐንስ ሠራዊት የደርቡሾቹን ምሽግ ጥሶ ገባ፡፡
ከዚያም የከተማውን ህዝብ በማስወጣት ከተማውን አቃጠሉት፡፡
የአፄ ዮሐንስ ሠራዊት ድል ለማድረግ ትንሽ ሲቀራቸው አፄ ዮሐንስ በጥይት ቆስለው ወደቁ፡፡
የአፄ ዮሐንስ በጥይት መመታት ወሬው ቀስ በቀስ ወደ ተዋጊው ሠራዊት ተዛመተ፡፡
በዚህም ያልተጠበቀ ክስተት ሠራዊታቸው ተደናግጦ እንዲበተን ምክንያት ሆነ፡፡
በጦርነቱ ተሸንፎ ይሸሽ የነበረው የመሀዲስቶች ጦር ሁኔታውን በማየት የልብ ልብ አግኝቶ የሸሸውን የአፄ ዮሐንስን ሠራዊት በተራው ለማባረር በቃ፡፡
ድርቡሾች በውጊያው ዕለት በጦር ሜዳ የወደቀውን የኢትዮጵያውያንን የጦር አለቆች ሬሳ እየፈለጉና ራሳቸውን እየቆረጡ የምስራች እያሉ ለአለቃቸው ላኩለት፡፡
ንጉሠ ነገሥቱም በዚህ ሽሽት መሀል ሕየወታቸው አለፈ፡፡
መሀዲስቶችም የአፄ ዮሐንስን ሬሳ እንዳገኙ በጭካኔ ራሳቸውን ቆርጠው በእንጨት ላይ ሰቅለው ለግብፆች ማስፈራሪያና መሳለቂያ አደረጉት፡፡

ይህ ድርጊት በኢትዮጵያ የውጊያ ታሪክ አሳዛኝና ዘግናኝ ታሪክ ሆኖ አልፏል፡፡




የአፄ ዮሐንስ የዘር ሐረግ

Family Tree of Emperor Yohane





ምንጭ፤
  1. "አጤ ቴዎድሮስ"  ደራሲ፡- ጳውሎስ ኞኞ ግንቦት ወር 1985 ዓ.ም.
  2. "የኢትዮጵያ ታሪክ ከ 1847 እሰከ 1983"  ደራሲ፡- ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ