Content-Language: am ልጅ እያሱ
header image

ልጅ እያሱ



የልጅ እያሱን የሕይዎት ዘመን ታሪክ ያዳምጡ















Lij Eyasu
ልጅ እያሱ በልጅነት እድሜ
ልጅ እያሱ ከአባታቸው ከወሎው ገዥ ከንጉሥ ሚካኤል እና የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ልጅ ከሆኑት ከእናቱ ከወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክ በወሎ ጠቅላይ ግዛት ተወለዱ፡፡
ልጅ እያሱ የተወለዱበት ቀን በትክክል ባይታወቅም ጥር 28 ቀን 1887 ዓ.ም እንደሆነ ይገመታል፡፡
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በሕመም እየተዳከሙ በመጡበት ሰዓት፤ ከእርሳቸው የተወለደ ወንድ ልጅ ባለመኖሩና፤ የዙፋን ውርስ ለሴት ልጅ ማስተላለፍ በነበረው ባላባታዊ ሥርዓት የተለመደ ባለመሆኑ፤ ዙፋናቸውን ማን እንደሚወርሰው ለመወሰን ተቸግረው ነበር፡፡
በመጨረሻም ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሕመማቸው ፀንቶ ወደ ደብረ ሊባኖስ ለመሄድ በተዘጋጁበት ወቅት፤ ልጅ እያሱ አልጋ ወራሻቸው መሆናቸውን ለሚኒስትሮቻቸው ነገሯቸው፡፡
ልጅ እያሱም፤ በሞግዚታቸው በራስ ተሰማና በቤተ ክርስያን ልቃውንት ምክር አማካኝነት፤ እድሜአቸው በሰል እስኪልና ከባለቤታቸው ጋር ያለው ጋብቻ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት እስኪፈጸም ድረስ ንግሥናቸው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲተላላፍ ተወሰነ፡፡
ይሁን እንጅ ልጅ እያሱ፤ ንግሥናቸው እንዲተላለፍ የተወሰነባቸውን ውሳኔ ችላ በማለት በራሳቸው መንገድ መጓዛቸው፤ የሚያሳዩት ያለተረጋጋ ባሕርይና ወደ እስልምናውም ሐይማኖት ያደላሉ ተብለው ይወቀሱ ስለነበረ፤ በመኳንንቱና በመሳፍንቱ ዘንድ ተግባራቸው ሁሉ አልተወደደላቸውም ነበር፡፡
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በታመሙባቸው የመጀመሪያዎቹ አመታትም፤ የእቴጌ ጣይቱ ሥልጣን እያደገ በመምጣቱ፤ የሸዋንና የትግራይን ንጉሣዊ ቤተሰብ ለማስተሳሰር ይረዳል በሚል እምነት፤ ከእቴጌ ጣይቱ ጋር ዝምድና የነበራትን የራስ መንገሻ ዮሐንስ የሰባት ዓመት ህፃን ልጅ የሆነችውን ሮማነወርቅ መንገሻን፤ ልጅ እያሱ እነዲያገቡ ተደርጎ ነበር፡፡ ግን ጋብቻው ብዙም ሊዘልቅ አልቻለም፡፡
እቴጌ ጣይቱ ግን፤ የራሳቸውን የፖለቲካ መስመር ለማስተካከል ያመቻቸው ዘንድ፤ ለምኒልክ አልጋ ወራሽነት ያጩት ልጅ እያሱን ሳይሆን የዳግማዊ አፄ ምንሊክን ሴት ልጅ ዘውዲቱን ነበር፡፡
በሸዋ መኳንንቶችና መሳፍንቶች ዘንድ፤ በእቴጌ ጣይቱ ላይ ቅሬታውና ማጉረምረሙ እየበረታ መጥቶ በካቲት ወር 1902 ዓ.ም. ይፋ ወጣ፡፡
በዚህም በተነሳው ተቃውሞ ምክንያት፤ እቴጌ ጣይቱ ወደ እንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን እንዲሄዱና በዚያ በግዞት መልክ እስከ ዕለተሞታቸው ድረስ እንዲቆዩ ተገደዱ፡፡
የልጅ እያሱ ሞግዚት የነበሩት፤ ቢተወደድ ራስ ተሰማ ናደው ሲሞቱ ደግሞ የ16 ዓመቱን ወጣቱን ልዑል የሚገስፀው ሰው ጠፋ፡፡
እቴጌ ጣይቱ ከሥልጣን ሲገለሉ፤ ለወጣቱ አልጋ ወራሽ ለልጅ እያሱ የተመቸ ሁኔታን ፈጠረላቸው፡፡
ልጅ እያሱን ሙሉ ስልጣን እንዳይዙ ያገዳቸው፤ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ አስትንፋስ ለሁለት ዓመት ያህል ሳይቋረጥ መቆየቱ ነበር፡፡
ይሁን እንጅ ልጅ እያሱ ንጉሠ ነገሥት ባይባሉም፤ የሥልጣን ዘመናቸው ለአራት ዓመታት ያህል ቆይቷል፡፡
የልጅ እያሱ ታናሽ እህት ዘነበ ወርቅ፤ ገና በለጋ እድሜያቸው ከጎጃሙ ራስ በዛብህ ጋር ከተጋቡ በኋላ በወሊድ ምክንያት ህይወታቸው አለፈ፡፡
Woizero Seble Wongel Hailu
የልጅ እያሱ ባለቤትና የልዑል ራስ ኃይሉ
ተክለ ሐይማኖት ልጅ የሆኑት
ወይዘሮ ሰብለወንጌል ኃይሉ ከልጃቸው
ከዓለም ፀሐይ እያሱ ጋር
በኋላም በአባታቸው በንጉሥ ሚካኤል ፈቃድና በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ምርጫ፤ የጎጃሙ የራስ ኃይሉ ተክለ ኃይማኖት ልጅ የሆኑትን ወይዘሮ ሰብለ ወንጌል ኃይሉን በ 14 አመት ዕድሜዋ ለ15 ዓመቱ ለልጅ እያሱ ዳሩላቸው፡፡
ልጅ እያሱም፤ ከሕጋዊ ሚስታቸው ከወይዘሮ ሰብለ ወንጌል ኃይሉ፤ ዓለም ፀሐይ እያሱ የምትባል፤ (ከፎቶው በስተቀኝ በኩል የምትታየውን) ሴት ልጅ ከወለዱ በኋላ በተጋቡ በስድሰተኛ ዓመታቸው ተለያይተዋል፡፡

በ1920 ዓ.ም የተወለደችው የልጅ ኢያሱ ብቸኛና ህጋዊ ልጅ ወይዘሮ አለም ፀሐይ እያሱ፤ በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ፈቃድ የእመቤት-ሆይ ማዕረግ ተሰጥቷቸወል።
ልጅ እያሱ፤ ከአምባሰል ባላባት ከጃንጥራር አስፋው ጋር ትዳር የመሰረቱ የንጉሥ ሚካኤል ልጅ ወይዘሮ ስህን ሚካኤል የሚባሉ ታላቅ እህት አላቸው፡፡
የወይዘሮ ስህን ሴት ልጅ እቴጌ መነን አስፋው ደግሞ የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ባለቤት ናቸው፡፡
ከልጅ እያሱ አባት ከንጉሥ ሚካኤል የሚወለዱት ወይዘሮ ተዋበች ደግሞ፣ የትግራዩ ገዥ የለዑል ራስ ስዩም መንገሻ ዮሐንስ ሚስት ነበሩ።

የልጅ እያሱ የልጅ ልጅ
ፕሮፌሰር ግርማ ዮሐንስ እያሱ

Photo Credit to: Africa University
ልጅ እያሱ፤ በእናታቸው በወይዘሮ ሸዋረገድ ምኒልክ የንጉሠ ነገሥትነት የዘር ሐረግ በኩል የሰሎሞናዊው ስርዎ መንግስት ዘር ነኝ ማለት እየቻሉ፤ እርሳቸው ግን በአባታቸው በንጉሥ ሚካኤል (የቀድሞ ስማቸው ራስ መሐመድ ዓሊ) በኩል፣ የመሐመድ ዘር ነኝ ብለው መናገር ይቀናቸው ነበር፡፡
ልጅ እያሱ፤ ቁጥራቸው ቢያንስ 13 የሚደርሱ በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጡ ሚስቶች እና ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ የአብራካቸው ክፍይ የሆኑ ልጆች እንዳላቸው ይነገራል፡፡
ከነዚህም መካከል የንጉሠ ነገሥት ዙፋን ወራሾች ነን የሚሉ፤ ለምሳሌ እንደ ፕሮፌሰር ግርማ ዮሐንስ ያሉ የልጅ እያሱ የልጅ ልጆች ይገኛሉ፡፡
ፕሮፌሰር ግርማ ዮሐንስ እያሱ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ዚምባቡዌ በሚገኘው የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ፤ በማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ የስነ መለኮት ሂውማኒቲስ እና ትምህርት ዲን ሆነው ተሹመው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡
የልጅ እያሱ ዘመነ መንግሥት በእንቆቅልሽ የተሞላ ዘመን ነበር ማለት ይቻላል፡፡
በኢያሱ የታሪክ መጻህፍት በተደጋጋሚ የሚነሳው መልካም ገፅታው ሳይሆን፤ በተቃራኒው ነው፡፡
ሕዝቡ ለልጅ እያሱ አዎንታዊ አመለካከት ነበረው ማለት ይቻላል፡፡
በልጅ እያሱና በንጉሥ ተፈሪ ዘመን የነበረውን የኑሮ ሁኔታ በማነጻጸር ህዝቡ፤
በኢያሱ ዳቦ ነው ትራሱ፣
በተፈሪ የለም ፍርፋሪ፤

እያለ ግጥም ገጥሞላቸዋል፡፡
የልጅ እያሱ መልከ ቀናነት፣ የንግግር ችሎታና እስፖርተኛነት የሕዝቡን ሕሊና ይማርከው እንደነበር ይነገራል፡፡
ልጅ እያሱ ከወሰዷቸው አዎንታዊ ከሆኑ እርምጃዎች መካከል፤
  1. የግል ንብረትን ማስከበር፣
  2. አሥራትን (ግብርን) በወቅቱ ለመሰብሰብ ማስችል፣
  3. ከሳሽና ተከሳሽ አብረው ታሥረው ይማቅቁ የነበረውን የቁራኛ ሥርዓት መሻር፣
  4. የመንግሥትን ሂሳብ ኦዲት በማስደረግ፤ አላግባብ የመንግሥት ገንዘብ ባባከኑት ላይ እርምጃ መውሰድ፣
  5. ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የጀመሩትን ኢትዮጵያን የማዘመን ሥራ ለማስቀጠል ከታቀዱት ውስጥ፤ በራስ ተሰማ ናደው አጋዥነት የመጀመሪያውን የፖሊስ ኃይል ማቋቋም፣
የሚሉት ይገኙበታል፡፡
  1. በ 1ኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የነበረውን የኃይል አሰላለፍና ሚዛን ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ ከጀርመን መንግሥት ጋር መተባበራቸው፤
  2. አንድ የኢትዮጵያ ንጉሥ ሊፈጽማቸው ከሚገቡት ሥርዓቶች መካከል፤

    • አንዲትን ሴት በሥርዓተ ተክሊል አግብቶ መቀመጥን፤
    • በኢትዮጵያ ፀንቶ የኖረውን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሐይማኖትን ጠብቆ መኖርን፤
    • ለንጉሥነት የተገባውን ክብርና ሞገስ በግልጽም ይሁን በስውር መጠበቅን፤
    የሚሉትን ንጉሣዊ ተግባራት ተላብሰው ያለመገኘታቸው፤
  3. የጠሉትን ሰው በሐሰት እያሶነጀሉ ማሰራቸው፣
  4. የግል ባሕርያቸው ተቃርኖ የሞላበትና ቀጣይነት የሌለው መሆኑ፣
  5. የከተማ ዘበኛ አቋቁመው፤ ራሳቸው ግን የሰዓት ዕላፊ ገደቡን እየጣሱ ከነርሱ ጋር መታኮሳቸው፣
  6. ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ ከዐድዋ ድል በኋላ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የተደላደለውን ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ መስተጋብር ማናጋቱ ትልቁን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ለዚህም ማረጋገጫው፤ መኳንንቱ አርፈው እንዲቀመጡ በይፋ ከተናገሯቸው ውርደትና ንቀት የተሞላባቸው ቃላት መካከል፤
    “እኔ፤ ጎልማሶችን አስከትየ አገር ለመጎብኘትና ያልቀናውን አገር ለማቃናት በተነሣሁ ጊዜ፤ ያለፈቃዴ መከተል የለባችሁም፡፡
    ወፍራችኋል፣ ሸምግላችኋል፡፡ በዘመናችሁ አባቴን ተከትላችሁ አገር አቅንታችኋል፡፡
    አሁን ግን ሸሽታችሁ አታመልጡም፤ አባራችሁ አትጨብጡምና ተመልሳችሁ በየሥራችሁ ጠንክሩ፡፡”
    የሚሉ ይገኙበታል፡፡

    ይህ የልጅ እያሱ ተግባር በምኒልክ ዘመነ መንግሥት ታፍረውና ተከብረው የኖሩትን መሳፍንቶች የነበራቸውን የፖለቲካ የበላይነት ለማሳጣት ያለመ እንደነበረ የታሪክ ምሁራን አበክረው ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
    ከላይ የተገለፀው የልጅ እያሱ ንግግር በቀና መልኩ ቢተረጎም፤
    “እናንተ በተራችሁ ሠርታችኋል፡፡ አሁን ማረፊያ ጊዚያችሁ ነውና እረፉ፡፡ አሁን ተራው የእኛ የወጣቶች ነው፡፡”
    ለማት ፈልገው ነው፤ ብሎ መውሰድ ይቻላል ይሆናል፡፡

    በመኳንንቶቹ በኩል ግን የልጅ እያሱን ንግግር የተረጎሙት በተለየ መልኩ ነው፡፡ አልፎ ተረፎ ተናገሩ የተባለው ከዚህም የባሰ ነበር፡፡
    መኳንንቶችን እናንተ “የአባቴ ሙክቶች” በማለት ያፌዙባቸው እንደነበር ይነገራል፡፡
  7. ሌላው የምኒልክ በሕይዎትና በሞት መካከል ተንጠልጥሎ መቆየት የልጅ እያሱን ትዕግሥት ስለተፈታተነው፤ ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ የግቢ ዘበኞች ጋር ግጭት ፈጥረው ተኩስ ተከፍቶ አስራ ሰባት ሰዎች ከሞቱ በኋላ በመጨረሻ አቡነ ማቴዎስ በመሐል ገብተው የግቢው ዘበኞች እጃቸውን እንዲሰጡና ግጭቱ እንዲበርድ ተደረገ፡፡
  8. የልጅ እያሱን በመጥፎ ካስነሱት ተግባራት አንዱ፤ የጊሚራ ዘመቻ የተባለውን መርተው እጅግ በርካታ ዜጎችን ለሞትና ለባርነት መዳረጋቸው ይጠቀሳል፡፡
  9. Lij Iyassu
    ልጅ እያሱ ከአባታቸው ከንጉሥ ሚካኤል ጋር
  10. የሸዋን መኳንንቶች የማዳከሙ የልጅ እያሱ ፖሊሲ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው፤ አባቱን ንጉሥ ሚካኤልን የወሎና የትግራይ ንጉሥ አድርጎ በደሴ ከተማ በተከናወነው የንግሥ ሥርዓት ላይ መሾማቸው ነው፡፡
    ለዘውዱ ክብረ በዓሉም ሞገስ ለመስጠት ሲባል፤ ልጅ እያሱ ከምኒልክ ቤተ መንግሥት ዘውድ፣ ሉልና የሥርዓተ ንግሥ ልብስ ይዘው ለአባታቸው ለንጉሥ ሚካኤል ወስደዋል፡፡
  11. የታወቁ የሸዋ መኳንንትን ከሹመት ለመሻርና የቆየውን የአያታቸውን የሸዋን አገዛዝ ሥርዓት አፍርሶ በራሳቸው በመሰላቸው መንገድ እንደሚለውጡት መናገራቸው ይበልጥ ተቀባይነታቸውን እያሳጣው መጣ፡፡
  12. ሞግዚታቸው ራስ ተሰማ ናደው ታመው ሲሞቱ፤ ገና በእድሜ ያልበሰሉ ስለነበሩ፤ በምትካቸው ማን ይመደብልዎ ተብለው በሸዋ መኳንንቶች ሲጠየቁ፤ “ማንንም አልፈልግም፡፡ ራሴ እመራለሁ፡፡” በማለት ያለማንም አማካሪ በራሳቸው መንገድ አገሪቱን ለመምራት ማሰባቸውና በዚህም ምክንያት የሚፈጽሟቸው ተግባራት ሁሉ የነበረውን የአስተዳደር ሥርአትና ዘይቤ የሚቃረን በመሆኑ በሸዋ መኳንንቶች ዘንድ ግራ መጋባትንና ቅሬታን አስከተለ፡፡
  13. በ1923 ዓ.ም. የተደነገገውን ህገ መንግሥት በዋናነት የጻፉት ምሁርና ፖለቲከኛ የነበሩት ፊታውራሪ ተክለ ኃዋሪያት ተክለ ማሪያም፤ ሰለልጅ እያሱ ከተናገሩት ውስጥ፤
    Lij Eyasu
    ልጅ እያሱ የሙስሊም ተርባን ልብስ ለብሰው
    ድሬዳዋ በሚገኝ በአንድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፤ የእምነቱ ተከታዮች ተሰብስበው የፀሎት ሥነ ሥርዓት በሚያከናውኑበት ወቅት፤ ልጅ እያሱ፤ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ገብተው ላይተር አውጥተው በመለኮስ ሲጋራ ማጨሳቸው ለክርስቲያን ሐይማኖት ያላቸውን ንቀት ያሳያል በማለት ገልጸውታል፡፡
    አስተያየታቸውንም ሲያጠቃልሉ፤ ልጅ እያሱ የአባታቸውን የዘውድ አገዛዝ ለመረከብ በፍጹም የማይበቁ ሰው ከመሆናቸውም በላይ የኢትዮጵያን የግዛት ሉአላዊነትና የሕዝቡን አነድነት ለማስጠበቅ፤ እያሱ ከሥልጣን ከነጭራሹ መወገዳቸው እሰፈላጊ ነው በማለት በአጽኖት አስረድተዋል፡፡
  14. ልጅ እያሱ፤ ማንም ሰው እንዳይከተላቸውና እንዳይገዛላቸው በጳጳሱ ተወግዘው ከሥልጣናቸው እንዲወገዱ መደረጋቸውን ሐረር ሆነው ሲሰሙ፤ በተወሰነባቸው ውሳኔ ተበሳጭተው በከተማው ረብሻ እንዲነሳ ማድረጋቸው ተነግሯል፡፡
እቴጌ ጣይቱ ከሥልጣን መወገድ በኋላም ቀስ በቀስ ካልተጠበቀ አቅጣጫ የልጅ እያሱን ሥልጣን የሚቀናቀን ኃይል እየበዛ መምጣት ጀመረ፡፡
ልጅ እያሱም፤ ዘውዲቱን የሥልጣን ተቀናቃኛቸው አድርገው ስለወሰዷቸው፤ እቴጌ ጣይቱንና ወይዘሮ ዘውዲቱን ከአዲስ አበባ ቤተ መንግሥት አሶጥተዋቸው ነበር፡፡
የመንግሥት መኳንንቶች ከነሠራዊታቸው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ፤ ካሕናቱ እና ሕዝቡ በቤተ መንግሥቱ ግቢ መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም የመስቀል በዓል ቀን እንዲሰበሰቡ ተደረገ፡፡
በስብሰባውም መካከል፤ ልጅ እያሱ ፈፀሙት የተባለው ወንጀል ከተነበበ በኋላ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፤ ልጅ እያሱ ባሳዩት ሐይማኖታቸውን የመካድ ተግባር ምክንይት የነበራትን ግንኙነት ማቋረጧን በመግለጽ ከመንግሥት ሥልጣናቸው ተሽረው እንዲሰናበቱ ተወሰነ፡፡

Lij Iyasu and Dejazmach Teferi
ልጅ እያሱና ደጃዝማች ተፈሪ
በኋላም ወይዘሮ ዘውዲቱ በግዞት ከነበሩበት ቦታ ወደ አዲስ አበባ ተጠርተው፤ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ተብለው የአባታቸውን ዙፋን እንዲወርሱ ሲደረግ፤ በተጨማሪም ደጃዝማች ተፈሪ፤ አልጋ ወራሽና ባለ ሙሉ ስልጣን እንደራሴ እነዲሆኑ ታወጀ፡፡
ልጅ እያሱ ከሥልጣን ተሽረው ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ የአባታቸውን የዳግማዊ አፄ ምኒልክን በትረ ሥልጣ እንዲወርሱ ሲደረግ፤ በዘመኑ ከነበሩ መኳንንቶች ውስጥ ደጃዝማች አብረሃም አርአያ የተባሉ፤ ልጅ እያሱ ግቢ ገብተው የልጅ እያሱን መሻርና የንግሥቲቱን በዙፋን መቀመጥ በመቃወም ብጥብጥ ለመፍጠር ሞክረው ነበር፡፡
ነገር ግን የማያዋጣቸው መሆኑን ሲረዱ ለፀጥታ አስከባሪዎች እጃቸውን ሰጥተዋል፡፡

ልጅ እያሱ ከሥልጣን ተሸረው ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ሥልጣኑን ከተረከቡ በኋላ፤ የራስ ጉግሣ ወሌ ወደ ማዕከላዊ ሥልጣን እየቀረቡ መምጣትና የልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን (በኋላም ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ) አልጋ የመውረስ ጽኑ ፍላጎት መካከል የስልጣን ሽኩቻው ተጋግሎ ብዙ ውጣ ውረዶች ተከስተዋል፡፡
King Mikael of Wollo
የወሎው ንጉሥ ሚካኤል
የልጅ እያሱን ከዙፋን መውረድ የሰሙት የልጅ እያሱ አባት ንጉሥ ሚካኤል፤ የወሎን ሠራዊት አስከትለው ወደ ሸዋ በመጓዝ ከደብረ ብርሃንና ከአንኮበር መካከል በሚገኘው ቶራ መስክ በተባለው ቦታ ላይ ጥቅምት 7 ቀን 1909 ዓ.ም. ከሸዋ ከመጣው ጦር ጋር ጦርነት ገጥመው በሸዋ በመጣው ጦር ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡
ከ10 ቀናት ቆይታ በኋላም ጥቅምት 17 ቀን 1909 ዓ.ም. በሸዋው ጦርና በንጉሥ ሚካኤል መካከል በድጋሚ ጦርነት ተጀመረ፡፡
8 ሺህ የሚደርሰው የንጉሥ ሚካኤል የወሎ ሠራዊት፤ የንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ የጦር ሠራዊት ጠቅላይ አዛዥ ከሆኑት ከልዑል ራስ ተፈሪ መኮንን ጋር፤ ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ብርሃን በሚወስደው መንገድ 87 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘውና ሰገሌ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ ጦርነት ተደርጎ በዚሁ ዕለት ንጉሥ ሚካኤልና ሠራዊታቸው ድል ሆኖ ንጉሥ ሚካኤል ተማረኩ፡፡
አባታቸው መሸነፋቸውን የሰሙት ልጅ እያሱ፤ ከነበሩበት ከሐረር ወደ አዲሰ አበባ ለውጊያ ሲመጡ 15 ሺህ ከሚደርስ ከሸዋ ከተላከ ጦር ጋር ጦርነት ገጥመው ሲሸነፉ ሸሽተው ወደ ወሎ ተጓዙ፡፡
ልጅ እያሱ ወሎ ከገቡ በኋላ እንደገና ጦር በማደራጀት ላይ መሆናቸው ተሰማ፡፡
ልጅ እያሱን ለመያዝ፤ በፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ መሪነት ወደ ወሎ ዘመቻ ተደርጎ ከልጅ እያሱ ጋር ጦርነት ገጥመው ሁለቱም ወገኖች በብርቱ ከተዋጉ በኋላ፤ ልጅ እያሱ ድል ሆነው እንደገና ወደ መቅደላ ሸሹ፡፡
Fitawrari Habte Giorgis Dinegde
ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ
Leul Ras Seyoum Mengesha
ልዑል ራስ ሥዩም መንገሻ
በኋላም ልጅ እያሱ የነበራቸው ኃይል ስለተዳከመ፤ በ26 ዓመት እድሜያቸው ወደ ትግራይ በመሄድ ግብፅያ በሚባለው ገዳም ውስጥ ገብተው እንደተደበቁ ተሰማ፡፡
የትግራዩ ገዥ ለልዑል ራስ ስዩም መንገሻ ዮሐንስ ለማስታረቅ ሙከራ አድርገው ሰለአልተሳካ፤ ልጅ እያሱ ከግዛታቸው ወጥተው እንዲሄዱ አደረጓቸው፡፡
ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ፤ የልጅ እያሱ እህት የሆኑትን ወይዘሮ ተዋበችን አግብተው ስለነበረ፤ ልጅ እያሱ በትግራይ በነበረቡበት ጊዜ ለዑል ራስ ስዩም መንገሻ ዮሐንስ በቤታቸው ለበርካታ ጊዚያት ደብቀዋቸው እንደቆዩ ይነገራል፡፡
ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ፤ ልጅ እያሱን አሳልፎ ላለመስጠት እንደመነሻነት ከሚነገሩት ሌሎች ምክንያቶች መካከል፤
አንደኛው፤ በሰሜኑ ክፍል የነበረው ባላባታዊ ሥልጣን፤ ማለትም የእቴጌ ጣይቱና የራስ ወሌ ብጡል (የእቴጌ ጣይቱ የወንድም ልጅና የንግሥት ዘውዲቱ ባል) በሸዋ መኳንንቶች ከሥልጣን መገፋት ያስነሳው ቅሬታ ሲሆን፤
ሁለተኛው፤ ልጅ እያሱ የአባታቸውን ዘውድ ወርሰው ሙሉ ሥልጣን ባይቀዳጁም ቅሉ፤ ህዝቡ ለዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከነበረው ከፍተኛ አክብሮትና ፍቅር የተነሳ፤ ልጅ እያሱን ለሸዋ መኳንንት አሳልፎ አልሰጣቸውም፤
የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
Lij Eyasu
ልጅ እያሱ እጃቸው ሲያዝ
ልጅ እያሱን አድነው የያዟቸውና ወሎ ድረስ ሄደው ለልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ያስረከቧቸው፤ የአፄ ዮሃንስ የልጅ ልጅ የሆኑት ራስ ጉግሳ አርአያ ናቸው፡፡
ራስ ጉግሳ ልጅ እያሱን ከመያዛቸው አስቀድሞ፤ ተንበርክከው የልጅ እያሱን ጫማ መሳማቸው ይነገራል፡፡
ይህ የራስ ጉግሳ አድራጎት የሚያመለክተው፤ በወቅቱ በነበረው ዘውዳዊ ሥርዓት፤ በተዋረድ ተላልፎ ለተሰጠ ንጉሣዊ ሥልጣን፤ ያሳዩት የነበረው ክብር ምን ያህል እንደነበረ ያስረዳል፡፡
በኋላ ላይ ልጅ እያሱ እጃቸው ተይዞ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ፤ በሰሜን ሸዋ፤ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ የአጎት ልጅ ለሆኑት ለሰላሌው ገዥ ለልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ ዳርጌ እስረኛ ሆነው ተላልፈው ተሰጡ፡፡
ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉም፤ መኖሪያቸው በሆነው በፍቼ ከተማ ውስጥ፤ ልዩና ምቹ የሆነ የመኖሪያ ክፍል ተዘጋጅቶላቸው እንዲቀመጡ አደረጉ፡፡
Tsigemariam Beshah
ልዕልት ጽጌ ማሪያም በሻህ

Photo credit to: ESAADFS
ልጅ እያሱ ታስረው በነበረበት በዚህ ወቅት፤ የልዑል ካሣ ኃይሉን ባለቤት የልዕልት ጽጌ ማሪያም በሻህን ድርጊት ለማስታወስ እንሞክር፡፡
ከስልጣን የተባረሩት ልጅ ኢያሱ በልዑል ራስ ካሣ መኖሪያ ቤት ውስጥ በቁጥጥር ስር በነበሩበት ወቅት፤ ልጅ እያሱን በሚመገበው ምግብ ላይ መርዝ ጨምሮ ሊገለው የሚችል ሰው ሊኖር ይችላል ብለው ስለሰጉ፣ የልጅ እያሱ ምግብ በሙሉ በልዕልት ጽጌ ማርያም እንዲዘጋጅ ከባለቤታቸው ጋር ተስማምተው ነበር፡፡
ልዕልት ጽጌ ማሪያምም ምግቡን ለማዘጋጀት ሽንኩርት ከመክተፍ ጀምሮ በእሳት ላይ ድስት ጥዶ ወጥ እስከመስራት ድረስ ያለውን ዝግጅት በሙሉ ራሳቸው በመስራት እና ምግቡ ከተዘጋጀም በኋላ በሳጥን ቆልፈው ልጅ እያሱ ወደሚኖርበት የቤታቸው ፎቅ ውስጥ ወደሚገኘው ክፍል ይልኩታል። የዚህን ሳጥን ቁልፍ የሚይዙት ልዕልት ጽጌ ማርያም እና ልጅ እያሱ ብቻ እንደነበሩ ተዘግቧል፡፡ የበለጠ ለማንበብ ---> Ethiopian History
Emperor Haile Selassie
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ

photo credit to:  blackwash.blog
ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ከአረፉ በኋላ፤ በምትካቸው ራስ ተፈሪ መኮንን “ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው በንግሥቲቱ ዙፋን ተተክተው በትረ ስልጣኑን ሙሉ ለሙሉ ተረከቡ፡፡
ንግሥት ዘውዲቱ በሞቱ በዓመቱ፤ ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ፤ የልዑል አልጋ ወራሽ አስፋወሰን ኃይለ ሥላሴን ሠርግ ለመታደም ወደ አዲሰ አበባ በሄዱበት ወቅት፤ ልጅ እያሱ ከራስ ኃይሉ በተላከላቸው ገንዘብ ጠባቂያቸውን አባብለው ከእሥር ቤት ከአመለጡ በኋላ ወደ ጎጃም ቢሸሹም እንደገና ተይዘው ወደ አዲስ አበባ ተላኩ፡፡
በኋላም ሐረር ወደሚገኘው ወደጋራሙለታ ተወስደው እንዲታሱሩና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ደጋፊዎች እንዲጠብቋቸው ተደረገ፡፡
ራስ ኃይሉ ተክለ ሐይማኖትም ከልጅ እያሱ ጋር ማደማቸው በብዙ ምስክር ከተረጋገጠባቸው በኋላ ፍርድ እንዲፈርዱ የተሠየሙት መኳንንቶች ሞት ፈረዱባቸው፡፡
ሆኖም ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ የሞት ፍርዱን ሽረው በእስራት እንዲለወጥላቸው ከወሰኑ በኋላ ገንዘባቸው እንዲወረስ አዘው ታሰሩ፡፡
Ras Hailu Tekle Haimanot of Gojjam
የጎጃሙ ልዑል ራስ
ኃይሉ ተክለ ሐይማኖት
የልጅ እያሱ ባለቤት ወይዘሮ ሰብለወንጌል ኃይሉ፤ የራስ ኃይሉ ተክለ ሐይማኖት ልጅ መሆናቸው ይታወሳል፡፡
በ1928 ዓ.ም. ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ከወረረች በኋላ በአይሮፕላን ለሕዝቡ በበተኑት ወረቀት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በኃይለ ሥላሴ ላይ እንዲያምጽና እውነተኛ አልጋ ወራሽ የሆነውን እያሱን እነዲደግፍ በማነሳሳትና እርሳቸውን እንደመሣሪያ በመጠቀም ኢትዮጵያን ለመበታተን አቅዶ እንደነበር ይነገራል፡፡
በመጨረሻም ልጅ እያሱ በእሥር ላይ ሳሉ በህዳር ወር 1927 ዓ.ም. በተወለዱ በ40 ዓመታቸው መሞታቸው እንደተሰማ፤ በአዲስ አበባ በቤተ መንግሥት ኀዘን እንደተደረገላቸው ታውቋል፡፡




ምንጭ፤
  1. "የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እሰከ 1983"  ደራሲ፡- ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ
  2. "የኢትዮጵያ ታሪክ - ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ"  ደራሲ፡- ተክለ ጻድቅ መኩሪያ 1961 ዓ.ም.
  3. “የታሪክ ማስታዎሻ”  ደራሲ፡- ደጃዝማች ከበደ ተሰማ   2ኛ ዕትም ሐምሌ 2007 ዓ.ም.
  4. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ