Content-Language: am የሰላሌው ልዑል ራሰ ካሣ ኃይሉ ዳርጌ
header image

ልዑል ራሰ ካሣ ኃይሉ ዳርጌ



የልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ ዳርጌ
የአርበኝነትና የሕይወት ዘመን ታሪክ















1. ትውልድና የሕይዎት ጉዞ

Leul Ras Kassa Hailu
ልዑል ራሰ ካሣ ኃይሉ ዳርጌ
የሸዋ መኳንንት የሆኑት ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ ዳርጌ፤ በሰሜን ወሎ የላሊበላ ከተማ በምትገኝበት በላስታ ወረዳ ህዳር 3 ቀን 1873 ዓ.ም ተወለዱ፡፡
ወላጅ አባታቸውም ከላስታ የገዥዎች ሀረግ የሚመዘዙት ደጃዝማች ኃይሌ ወልደ ኪሮስ ናቸው፡፡
የልዑል ራስ ካሣ እናት ወይዘሮ ትሰሜ ዳርጌ ሲሆኑ እርሳቸውም የዳግማዊ አፄ ምኒልክ አጎት የሆኑት የራስ ዳርጌ ሣህለ ሥላሴ ልጅ ናቸው፡፡
ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ፤ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ አያት የሆኑት፤ የሸዋው ንጉሥ ሳህለ ሥላሴ የልጅ ልጅ፣ ልጅ ናቸው፡፡
የልጅነት ዘመናቸውን የቤተ ክህነት ትምህርት እየተማሩ አድገዋል፡፡
ልዑል ራስ ካሣ በልጅነታቸው ዓለምን ጠልተው የምንኩስና ህይወትን በመመኘት፣ የታጨችላቸውን ልጃገረድ አልቀበልም እስከ ማለት ደርሰው ነበር።
ሆኖም የመጀመሪያው ግሳጼ ከዳግማዊ ምኒልክ ሲደርሳቸው፤ ምንኩስና የሚሉትን ትተው፣ ለወግ ለማዕረግ እንዲበቁና የታጨችላቸውንም ወይዘሪት አሜን ብለው እንዲቀበሉ ተነገራቸው፡፡
ይህንን ንጉሣዊ ግሳጼ መግፋት ያልሆነላቸው ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ፤ በ1895 ዓ.ም የመረሐቤቴዋን ተወላጅ ልዕልት ጽጌማሪያም በሻህን ሊያገቡ ችለዋል፡፡
የልዕልት ጽጌ ማሪያምን ድርጊት ለማስታወስ ያህል፤
Prince Tsige Mariam Beshah
የልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ
ባለቤት ልዕልት ጽጌ ማሪያም በሻህ

Photo credit to:  ESAADFS
ከስልጣን የተባረሩት ልጅ እያሱ በልዕልት ጽጌ ማሪያም ባለቤት በልዑል ራስ ካሣ ቁጥጥር ስር በነበሩበት ወቅት፤ ልጅ ኢያሱ በሚመገበው ምግብ ላይ መርዝ ጨምሮ ሊገለው የሚችል ሰው ሊኖር ይችላል ብለው ስለሰጉ፣ የልጅ እያሱ ምግብ በሙሉ በልዕልት ጽጌ ማርያም እጅ ብቻ እንዲዘጋጅ ከባለቤታቸው ጋር ተስማምተው ነበር፡፡ ልዕልት ጽጌ ማሪያም ምግቡን ለማዘጋጀት ሽንኩርት ከመክተፍ ጀምሮ በእሳት ላይ ድስት ጥዶ ወጥ እስከመስራት ድረስ ያለውን ዝግጅት በሙሉ ራሳቸው ይሠሩ ነበር፡፡ ምግቡም ከተዘጋጀ በኋላ በሳጥን ቆልፈው ልጅ እያሱ ወደሚኖርበት የቤታቸው ፎቅ ውስጥ ወደሚገኘው ክፍል ይልኩታል። የዚህን ሳጥን ቁልፍ የሚይዙት ልዕልት ጽጌ ማርያም እና ልጅ እያሱ ብቻ እንደነበሩ ተዘግቧል፡፡ (የበለጠ ለማንበብ --> Ethiopian History )

ካሣ ሃይሉ፤ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱና በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት፤ በ1902 ዓ.ም. የደጃዝማችነት ማዕረግ፣ ጥቅምት 7 ቀን 1908 ዓ.ም.፣ የራስነት ማዕረግ እና ጥቅምት 22 ቀን 1923 ዓ.ም. ደግሞ የልዑልነት ማዕረግ ማግኘት ችለዋል፡፡
ከፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ በፊት የበጌምድር ገዥ ሆነው ከዱበር እስከ መተማ ያለውን ሰፊ ሀገር አስተዳድረዋል፡፡
በእርግጥም ልዑል ራስ ካሳ፤ ክብራቸውን የጠበቁና ግርማ ሞገስ የነበራቸው፣ በጣም የረጉና ዝምታን የሚወዱ፤ የአገራቸውን ባሕልና አስተዳደር ጠንቅቀው የተረዱ፣ ምክር አዋቂና ባለበሳል አዕምሮ ስለነበሩ የሚሰጡት አስተያየት ሁሉ ተደማጭነትና ከፍ ያለ ዋጋ የሚሰጠው እንደነበረ ይነገራል፡፡
ሰፔንሰር የተባለው ጸሐፊ ስለ ልዑሉ ሲጽፍ፤
“ልዑል ራስ ካሳ በባህሪያቸው ዝምተኛ ሲሆኑ፤ በአለባበሳቸውም ባህላዊ ልብስ ያዘወትራሉ፡፡
ረዘም ያለ ፂማቸውን ዠርገግ አድርገው፤ በወርቅ ክፈፎችና በአንበሳ ምስል በተሠሩ ቁልፎች ያጌጠውን ጥቁር ካባቸውን ደርበው፣ በወርቅ ፍሬም የተሠራ የዐይን መነፅራቸውን ጣል አድርገው ሲታዩ ከሌሎቹ መኳንንቶች ሁሉ ይለያሉ፡፡”

በማለት ገልጿቸዋል፡፡

ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ አራት ወንዶችና ሦስት ሴት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፤ በእድሜያቸው ቅደም ተከተል፤
  1. ወንድወሰን ካሣ
  2. አበራ ካሣ
  3. አስፋወሰን ካሣ
  4. አስራተ ካሣ
  5. ብዙነሽ ካሣ
  6. ማንአህሎሽ ካሣ እና
  7. ትሰሜ ካሣ
ይባላሉ፡፡

Leul Ras Kassa Hailu
ወንድወሰን ካሣ ታህሣሥ 1 ቀን 1929 ዓ.ም.፣ የወንድወሰን ካሣ ወንድሞች፤ አበራ ካሣ እና አስፋወሰን ካሣ ታኅሣሥ 12 ቀን፣ እንዲሁም ራስ እምሩ ታኅሣሥ 6 ቀን በፋሽስት ወታደሮች ተያዙ።
ሦስቱም ወንድማማቾች፤ ደጃዝማች አበራ ካሣ፣ ደጃዝማች አስፋወሰን ካሣ እና ደጃዝማች ወንድወሰን ካሣ ጠላትን በጀግንነት በመፋለም ላይ እያሉ ፋሽስት ባደረገው የሠላም ጥሪ በመታለል እጃቸውን ከሰጡ በኋላ በፋሽስት ወታደሮች የተገደሉ ናቸው፡፡
ነገር ግን ራስ እምሩና ሌላው ባላባት ታዬ ጉልላት፣ በግራዚያኒ ልዩ ትእዛዝ የጦር እስረኞች ተደርገው ታኅሣሥ 26 ቀን 1929 ዓ.ም. ኢጣሊያ ወደሚገኘው አሲናራ ደሴት ውስጥ ተወሰደው ታስረዋል፡፡
የመጨረሻ ልጅ የሆነው አስራተ ካሣ በዚያን ጊዜ ገና ከ13 ዓመት የማይበልጥ ታዳጊ ልጅ ነበር፡፡
ደጃዝማች አበራ ካሣ እና ደጃዝማች አስፋወሰን ካሣ አዲስ አበባ በመሸገው የፋሽስት ጦር ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሰዋል፡፡
ደጃዝማች ወንድወሰን ካሣ ግን ወደ ላስታ በመሸሽ ጠላትን እየተዋጉ ጥራር የተባለው ወንዝ ላይ ሲደርሱ በፋሽስት ወታደሮች ተይዘው ከተረሸኑ በኋላ በቅዱስ ሃርቤ ቤተ ክርስቲያን እንደተቀበሩ ይነገራል፡፡
ኩል መስክ ከተማ የሚገኘው በጥርብ ድንጋይ የተሠራው ህንፃ የደጃዝማች ወንድወሰን ካሣ መኖሪያ ቤት ወደ ትምህርት ቤት ተቀይሮ የሙሉ ሳይክል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደሆነ ይነገራል፡፡
በዚህ ገጽ ላይ የሚታየው የመጀመሪያው የልዑል ራስ ካሣ ፎቶ፤ ልዑል ራስ ተፈሪ መኮንን ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም. የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው ሲነግሡ በንግሥ ስነሥርዓቱ ላይ የለበሱት የማዕረግ ልብስ ነው፡፡

2. በማይጨው ጦር ግንባር የነበራቸው ተሳትፎ

ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ፤ በመሐል የሠፈረውን የልዑል ራስ ስዩም መንገሻን ጦር ለማገዝ በግምት 40 ሺህ የሚደርስ ጦራቸውን ይዘው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ዘምተዋል፡፡
ተንቤን ላይ የሠፈረው በልዑል ራስ ካሣ የሚመራው ጦር ከጠላት ጋር ውጊያ ሲጀምር ሌላ እርዳታ እንዳይደርስለት፤ የጠላት ጦር አስቀድሞ የሸለቆ መተላለፊያወችን ሁሉ ዘጋ፡፡
በልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ እና በነልዑል ራስ ሥዩም መንገሻ የሚመራው የኢትዮጵያ ሠራዊት ግን ሩቅ ለሩቅም ሆነው በመድፍ ጠላትን ይደበድቡ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ጦር፤ ከመሸገበት ሥፍራ እየለቀቀ ወደ መቀሌ የሚወስደውን መንገድ ይዘው በጀግንነት እየተዋጉና በሩጫ እየፎከሩ ጠላት ምሽግ ውስጥ በመግባት በጐራዴ ጠላትን ሲጨፈጭፉ ሳለ፤ መቀሌ የመሸገው የጠላት ጦር ተስፋ ቆርጦ፤ ስንቃቸውንና የጦር መሣሪያቸውን ጭነው ሊሸሹ ሲሉ የኢጣሊያ አውሮፕላኖች ደርሰው፤ በጀግንነት እየተዋጋ ድልን ይጠባበቅ በነበረው በጀግናው የኢትዮጵያ ጦር ላይ በጄኔቫ ኮንቬንሽን ጥቅም ላይ እንዳይውል የተከለከለውን መርዛማ የሙስታርድ ጋስ (mustard gas) እንደ ዝናብ ያለማቋረጥ በኢትዮጵያ ሠራዊትና በቀይ መስቀል አመቡላንሶችና ሆሰፒታሎች ላይ ሳይቀር እየተመላለሱ አርከፈከፉበት፡፡

ጀግናው የኢትዮጵያ ሠራዊት ያ ሁሉ የሙስታርድ ጋዝ የቦንብ ዝናብ ያለማቋረጥ እየዘነበበት፤ ለሦስት ቀንና ለሦስት ሌሊት ጠላትን ፊት ለፊት እየተጋፈጠ ይዋጋ ነበር፡፡

3. የመጨረሻ የሕይዎት ዘመን

Debretabore Hospital
ልዑል ራስ ኃይሉ ዳርጌ
በደብረ ታቦር ያሠሩት ሆስፒታል

Photo Link
ልዑል ራስ ካሣ በህይወት ዘመናቸው አስራ ሁለት የተለያዩ መጻሕፍትን እና በተጨማሪም የአማርኛ፣ የእንግሊዝኛ፣ የፈረንሳይኛና፣ የአረብኛ የንግግር መማሪያ መጽሐፍትን ጽፈዋል፡፡ ...የበለጠ ለማንበብ addisadmassnews ይመልከቱ
በ 1928 ዓ.ም. ልዑል ራስ ካሣ ለድሃ ታካሚወች የሚውል ህንጻ በሆስፒታሉ ግቢ እንዲሠራ በማሰብ በወቅቱ በነበረው ገንዘብ፤ ከራሳቸው 10 ማሪያ ተሬዛ እርዳታ በመሰጠት ለድሃ ታካሚወች የሚውል ህንጻ በሆስፒታሉ ግቢ እንዲሠራ አድርገዋል፡፡ ...የበለጠ ለማንበብ: AmharaNetwork ይመልከቱ

ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ፤ ጥልቅ ሃይማኖተኛ ሰው ስለነበሩ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ክህነት መቀበላቸው ካላቸው ክብር ሁሉ የበለጠ አድርገው ይመለከቱት ነበር፡፡
በዚህም መሠረት በአዲስ አበባ ፈረንሣይ ለጋሲዮን የሚገኘውን የፈርንሣይ እየሱስ ቤተ ክርስቲያንን አሠርተዋል፡፡

ልዑል ራስ ካሣ፤ በ1951 ዓ.ም. በተወለዱ በ78 ዓመታቸው ኪዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም በደብረ ሊባኖስ ገዳም ተፈፅሟል፡፡



ምንጭ፤
  1. ምስጋና፤ ለብሩክ አበጋዝ አባቦና፤ AmharaNetwork
  2. ምስጋና፤ ለኢትዮጵያዊነት፤ Ethiopiawinet
  3. ከዊኪፒዲያ የተተረጎመ
  4. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ