Content-Language: am ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ ዮሐንስ
header image



ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ ዮሐንስ



የልዑል ራስ ስዩም መንገሻ ዮሐንስ
የማይጨው ጦርነት የአርበኝነት ታሪክ













1. ትውልድና የሕይዎት ጉዞ

Leul Ras Seyum Mengesha
ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ
ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ በጎጃም ጠቅላይ ግዛት ዝምብሪ በምትባል የአገው ምድር ከተማ ውስጥ ሰኔ 17 ቀን 1878 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡
አባታቸው፤ የአፄ ዮሐንስ 4ኛ ልጅና አልጋ ወራሻቸው የሆኑት ራስ መንገሻ ዮሐንስ ሲሆኑ፤ እናታቸው የትግራይ ምክትል ገዥ የነበሩት የራስ ወሌ ብጡል ልጅ ወይዘሮ ከፈይ ይባላሉ፡፡
ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ፤ አፄ ዮሐንስ ከሞቱ በኋላ የዳግማዊ ምኒልክ ተቀናቃኝ ነበሩ፡፡
የልዑል ራስ ስዩም መንገሻ የመጀመሪያ ሚስታቸው የወሎው ንጉሥ ሚካኤል ልጅና የልጅ ኢያሱ እህት ወይዘሮ ተዋበች ናቸው፡፡
ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ ከወይዘሮ ተዋበች የልዑል አሰፋወሰን ኃይለ ሥላሴን ባለቤት የሆኑትን ልዕልት ወለተ እስራኤል ስዩምን ወልደዋል፡፡

2. የማይጨው ጦርነት

Leul Ras Seyum Mengesha with his troops
ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ ከወታደሮቻቸው ጋር
ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ በማይጨው ዘመቻ፤ በሰሜን ጦር ግንባር የትግራይ ጦር አዛዥ ሆነው ተሰልፈዋል፡፡
ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የጦር ማዘዣ ጣቢያቸውን ህዳር 20 ቀን 1928 ዓ.ም. ወደ ደሴ ካዛወሩ በኋላ በትግራይ የሰፈረውን የወራሪው የፋሽስት ኢጣሊያ አዲሱ የጦር አዛዥ ማርሻል ባዶሊዮ ያለውን ኃይል ለመገመት አስበው ታህሳስ 5 ቀን የኢትዮጵያ የሰሜን ግንባር የጦር ኃይሎች ተቀናጅተው ማጥቃት እንደዲጀምሩ ትእዛዝ አስተላለፉ፡፡
የዚህ የማጥቃት ዋና ዓላማ፤ የትግራይን የተለያዩ ስፍራዎች የተቆጣጠረውን የፋሽስት ጦር በተለያየ አቅጣጫ ማለትም፤ በመሐል፣ በግራና በቀኝ አቅጣጫ በማጥቃትና ኃይሉን ለሁለት ከፍሎ በማዳካም፤ በተለይ በግራ አቅጣጫ ያለው የኢትዮጵያ ጦር ኤርትራን ለመቆጣጣር ዕቅድ ነበረው፡፡
በዚህም መሠረት በልዑል ራስ ስዩም መንገሻ የሚመራው 30 ሺህ ጦር ቀደም ሲል በጠላት እጅ ተይዛ የነበረችውን አቢ አዲን ለማስለቀቅ ታህሳስ 12 ቀን በከፈተው ጥቃት ጠላትን አሸንፎ መልሶ ተቆጣጥሯል፡፡
ይሁን እንጅ የጠላት አይሮፕላን ያለማቋረጥ የሚያዘንበው የሙስታርድ ጋስ ቦምብ እጅግ ብዙ የኢትዮጵያ ሠራዊት ስለጨረሰና ጦርነቱን በዚህ ሁኔታ መቀጠሉ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን በመሆኑ፤ የሚዋጋበትን ሥፍራ ለቆ ወደኋላ በመመለስ ከ ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ ጦር ጋር ሠራዊታቸውን ይዘው ወደ ኋላ በመመለስ ከንጉሠ ነገሥቱ ጦር ጋር ለመቀላቀል ተገደዱ፡፡

3. የልዑል ራስ ስዩም መንገሻ የመጨረሻ ፍጻሜ

በ1953 ዓ.ም. በተደረገው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወቅት፤ የመፈንቅለ መንግሥት ጠንሳሾቹ የመንግሥት ልዑላንን፣ መሳፍንትን፣ መኳንንትን እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጠርተው አሁን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሆነው በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ውስጥ አስረዋቸው ነበር፡፡
ከታሰሩትም ውስጥ ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ አንደኛው ስለነበሩ የታሰሩት በሙሉ ያለምንም ምህረት በጥይት ሲረሸኑ እርሳቸውም አብረው ተረሽነዋል፡፡
በመጨረሻም አስከሬናቸው ወደ አክሱም ተወስዶ በአክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡





ምንጭ፤
  1. "የታሪክ ማስታወሻ"  ደራሲ፡- ደጃዝማች ከበደ ተሰማ 1962 ዓ.ም.
  2. "የኢትዮጵያ ታሪክ - ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ"  ደራሲ፡- ተክለ ጻድቅ መኩሪያ 1961 ዓ.ም.
  3. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ