Content-Language: am ስለ ድረ ገጹ አዘጋጅ
header image


Tekletsadik Mekuria “...ያለፈን ታሪክ አጥርቶ ማወቅ በመጭው ጊዜ ለመጠንቀቅና ለማመዛዘን ይጠቅማል፡፡
ካለፉት ታሪካዊ ሥራ ከሠሩት ታላላቅ ሰዎች ጋር በታሪክ እየተዋወቅን፤ ከነዚህም ውስጥ ዛሬ አብረውን ያሉ ያህል የምንወዳቸውም፣ የምንጠላቸውም አሉ፡፡
የምንወዳቸውን የታላላቅ ሰዎች፤ ዝናቸውን በታሪክ ባነበብን ጊዜ፤ መንፈሳችን ይቀሰቀሳል፡፡
እኛም ኢትዮጵያውያን ልናውቅ ከምንፈልጋቸው ታሪኮች ውስጥ ቅድሚያ መስጠት የሚገባን፤ ለኢትዮጵያ ታሪክ ነው፡፡ ”


...የታሪክ ሊቁ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ


አባቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰውና በርካታ መስዋዕትነትን ከፍለው፣ ለዘመናት ኢትዮጵያን በጦር ኃይል አምበርክከው ለመግዛት ከተፈራረቁባት የተለያዩ የውጭ ወራሪ ኃይሎች ጋር በመፋለምና በመመከት የውድ ሀገራችን ኢትዮጵያን ዳር ድንበር ሳያስደፍሩ ነፃነቷንና አንድነቷን የጠበቀች አገር አቆይተውናል ፡፡
ይህን አኩሪ ገድል የፈፀሙ የቀደሙት የአገራችን መሪዎችን፤ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጀግኖች አርበኞች አባቶቻችንና አያቶቻችንን ውለታ ወጣቱ ትውልድ ሳይረሳ፤ ታሪካቸውን በማወቅና በመማር፤ አገራችን ኢትዮጵያ ተዝቆ የማያልቅ የታሪክ ሀብት ያላት የታላቅ አገር ኩሩ ትውልድ መሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል፡፡
የዚህ ድረ ገጽ ዋና ዓላማም፤ የተወሰኑትን የውድ ባለውለታዎቻችንን አኩሪ ታሪክ በጥቂቱም ቢሆን በመዘከርና ያበረከቱትን አስተዋጸኦ በማሳወቅ፤ አገር ተረካቢው ትውልድ የተሰበረውን የሀገር ፍቅር ስሜቱን ጠግኖና አጎልብቶ፤ ይበልጥ እያወቀ እንዲሄድ ፍንጭ ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
የተወሰኑትን የአገራችንን መሪዎችና አርበኞች አጫጭር ታሪኮችና ተጋድሎዎች በጥቂቱም ቢሆን ከተለያዩ የታሪክ መጽሐፍትና መጣጥፎች ቀንጭበን በአማርኛ ቋንቋ ስላቀረብን ማንኛውም ለማወቅ ፍላጎቱ ያደረበት ኢትዮጵያዊ ሁሉ፤ በተለይ ወጣቱ ትውልድ እንዲያነበው ተጋብዟል፡፡
ለዚህ ድረ ገጽ ግብአት እንዲሆኑ የተጠቀምኩባቸው መጣጥፎች ምንጫቸው በየድረ ገጹ መጨረሻ ላይ ተጠቅሰዋል፡፡
የተጠቀሱት የታሪክ መጽሐፍት ደራሲያንና የደራሲያኑ ቤተሰቦች፣ የተለያዩ መጣጥፎች አቅራቢዎችና የታሪክ ዘጋቢዎች ሁሉ፤ የተነሳሁበትን ቅን ዓላማ በመገንዘብ ትብብር እንደማይነፍጉኝ በመተማመን፤ በቅድሚያ ላቅ ያለ ምስጋናየን በአክብሮት ለማቅረብ እዎዳለሁ፡፡
በድረ ገፁ ያልተካተቱ ብዙ ሊዘከሩ የሚገባቸው ታላላቅ አርበኞች እንዳሉ ብረዳም፤ ሁሉንም ለማካተት ከአቅም በላይ በመሆኑ አስቀድሜ ታላቅ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡
ስለ ድረ ገጹም ሆነ ሰለጽሁፉ አስተያየት ወይም እርማት ለመስጠት ከፈለጉ በኢሜል አድራሻዬ ብትልኩልኝ ከምስጋና ጋር ደስታዬ የላቀ ነው፡፡
ይህን የድረ ገፅ ሥራ ለቤተሰቦቸ፤ ማለትም
ለውድ ባለቤቴ ለወይዘሮ ብስኩት ተሰማ፣ ለውድ ልጆቸ
ለፀጋ ስለሽ እና ለአቤል ስለሽ
ማስታዎሻ እነዲሆንልኝ አበርክቻለሁ


The Webmaster

የድረ ገጹ የዲዛይን፣ የፕሮግራም እና የጽሁፉ (content) ዝግጅት እና ቅንብር ሙሉ ሥራ ፈጣሪ፤
ስለሽ መንግሥቱ እጅጉ  |  2015 ዓ.ም. አዲስ አበባ ኢትዮጵያ


The Website is fully designed, developed, including content planning, management and editing by:
Seleshi Mengistu Ejigu  | © 2023  | Addis Ababa, Ethiopia