Content-Language: am እቴጌ ጣይቱ ብጡል
header image





Etege Taitu
The image is digitally edited by the webmaster

እቴጌ ጣይቱ ብጡል



የእቴጌ ጣይቱ የአመራር ብልሀትና በዐድዋ
ጦርነት ወቅት ያበረከቱት ጉልህ አስተዋጽዖ















Etegie Tayitu
Photo credit to: UNESCO
 (The image is retouched by the webmaster)
አብዛኛዎቹ ምሁራን እነደሚስማሙበት ከሆነ፤ለቤተሰባቸው ሦስተኛ ልጅ የሆኑት እቴጌ ጣይቱ የተወለዱት ግንቦት 3 ቀን 1843 ዓ.ም. ነው፡፡
አባታቸው ራስ ብጡል ኃይለማሪያም የየጁና የጎንደር ሰው ናቸው፡፡
እናታቸው ጎጃም ክፍለ ሀገር የተወለዱት ወይዘሮ የውብዳር ይባላሉ፡፡
እቴጌ ጣይቱ በልጅነታቸው አማርኛ ማንበብና መጻፍ ተምረዋል፡፡
በገናም የመደርደር ችሎታ ነበራቸው፡፡
እቴጌ ጣይቱ ግእዝን በደንብ የተረዱ ከመሆናቸውም በላይ፤ የዲፐሎማሲ፣የፖለቲካና የኢኮኖሚ ትምህርትም እንዳገኙ ይታመናል፡፡
የእቴጌ ጣይቱ ወላጆች በጊዚያቸው፤ የጎጃም፣ የየጁ፤ የወሎና የቤገምድር ገዥዎች እንደነበሩ ይነገራል፡፡
የወላጆቻቸው ባላባታዊ የዘር ሐረግ ወደኋላ ሲቆጥር፤ ትውልዳቸው ከጎጃም ከሆነው በ17ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነግሠው እስከነበሩት እስከ አፄ ሱስኒዮስ ዘመነ መንግስት ድረስ ይዘረጋል፡፡
አጎታቸው (የአባታቸው ወንድም) ደጃዝማች ውቤ ኃይለማሪያም የትግራይ ገዥ ነበሩ፡፡
እቴጌ ጣይቱ በአፍሪካ ሀያልና ድንቅ ሴት እንደነበሩ ጸሐፍት ያወሳሉ፡፡
እቴጌ ጣይቱ በተፈጥሮ ድንቅ የአመራር ጥበብን የተቀዳጁ ስለነበረ አሰተዳደራዊ ፖለቲካቸው እንዲሰምርላቸው በማሰብ ተሿሚዎችን በጋብቻ የማሰተሳሰር ዘይቤ ነበራቸው፡፡
በተለይ የኢትዮጵያን ድንበር የሚነካ ማናቸውም ውይይት ላይ ጠንካራ ተቃውሞ በማሳየት የማይበገሩና የቀረበላቸውን አስተያየት ሁሉ ሳይመረምሩ እንደወረደ የማይቀበሉ፤ አስተዋይና ድንቅ ሴት ነበሩ፡፡
አዲስ አበባን የቆረቆሩ እሳቸው ናቸው፡፡
በአጠቃላይ ንግሥት ጣይቱ፤ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ለተከናወኑት አበይት ተግባራት ሁሉ ግንባር ቀደም አስተወጽዖ በማድረግ ከፍተኛውን ድርሻ ያበረከቱ እጅግ ጠንካራና የአመራር ጥበብን የተካኑ ንግሥት እንደነበሩ በሰፊው ተዘግቧል፡፡
Taytu Hotel
በ 1998 ዓ.ም. የተሠራው እና በተሠራበት ዘመን
የነበረውን ገጽታ የሚያሳይ፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪው
ሆቴል የሆነው የእቴጌ ጣይቱ ሆቴል
Photo courtesy of: mereja.com
እቴጌ ጣይቱ፤ ዳግማዊ ምኒልክ ሐረር ዘመቻ ላይ እንዳሉ የመንግስታቸው መቀመጫ የነበረውን እንጦጦን ለቀው፤ ከእንጦጦ በሰተደቡብ ወደሚገኘው የተንጣለለ ሜዳ ላይ ማእከላዊ ግዛታውን ማለትም የአሁኗን አዲስ አበባ በ1879 ዓ.ም. ቆረቆሩ፡፡
በሌላም በኩል እቴጌ ጣይቱ፤ በስማቸው የተሰየመውን በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውንና አዲስ አበባ የሚገኘውን “እቴጌ ጣይቱ ሆቴል” የተሰኘውን ፒያሳ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ በ 1898 ዓ.ም. ከዳግማዊ ምኒልክ ጋር በመሆን አቋቋሙ፡፡

የሆቴሉንም ሥራ እራሳቸው እያሰተናገዱና በነፃም እየጋበዙ እንዳለማመዱት ይነገራል፡፡
አዲስ አበባ በማእከላዊ ከተማነት ፀንታ እንድትመሠረት ካደረጓት ምክንያቶች መካከል፤
    Addis Abeba Arada City
    በ1928 ዓ.ም. የአዲስ አበባ የንግድ ማዕከል
    የነበረው የአራዳ ከተማ ገጽታ
  1. በእንጦጦ ሠፋሪዎች ዘንድ በሙቀቱና በፈዋሽነቱ ይዘወተር የነበረው ፍልውሀ መኖር፣
  2. ግቢ ተብሎ የሚታወቀው የአሁኑ የምኒልክ ቤተመንግሥት መታነፅ፣ በኋላም የመናገሻ ካቴድራል ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶና በአካባቢው የአራዳ ገበያ መድራት፣
  3. የዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች ሰፋፊ መሬቶችን ይዘው መደላደላቸው፣
  4. ምኒልክ ከአውስትራሊያ ያስመጡት የባሕርዛፍ ተክል፤ የነበረውን የሕንፃና የማገዶን ችግር ማቃለሉ፣
  5. የከተማ ቦታዎች እየተመዘገቡ የባለንብረትነት ካርታ መታደሉና፣
  6. እንዲሁም በሌሎችም ምክንያቶች የአዲስ አበባ ከተማ የኢትዮጵያ ዋና ከተማነቷ ለዘለቄታው ሊረጋገጥ ችሏል፡፡

Tayitu
እቴጌ ጣይቱ የውጫሌን ውል በተመለከተ ጠንካራ አመራር የሰጡና ወሳኝ ሚና የተጫወቱ መሪ ነበሩ፡፡
እቴጌ ጣይቱ፤ የውጫሌን ውል በተመለከተ ሲወያዩ የኢጣሊያ ተወካይ የሆነው የአንቶኒሊ ንግግር ስለአበሳጫቸው፣ ወዲያውኑ የእርሱን ንግግር አቋርጠው፤
“ያ አንቀጽ የሚለውን ነገር እኛም ለኃያላን መንግሥታት አሳውቀናል፡፡
…እንዳንተ ሁሉ እኛም ክብራችንን እንጠብቃለን፡፡
እናንተ የምትመኙት፤ ኢትዮጵያ በእናንተ ስልጣን ስር እንድትሆን ነው፡፡
ይህ ለምን ጊዜም የማይሆን ነገር ነው፡፡”
በማለት መልስ ሰጥተውታል፡፡
አንቶኒሊ፤ የውጫሌን ውል፤ የኢጣሊያ መንግሥት በጦር ኃይል እንደሚያስከብር በተናገረ ጊዜ፣ ይህን ንግግር የሰሙት እቴጌ ጣይቱ እየሳቁ፤
“የዛሬ ሳምንት አድርገው፡፡ በዚህ የሚደነግጥልህ የለም፡፡ ሂድ የፎከርክበትን አድርግ፡፡
እግሩን ለጠጠር፣ ደረቱን ለጦር ሰጥቶ አገሩን የሚያድን ሰው በዚህ የሌለ አይምሰልህ፡፡
የገዛ ደሙን ገበሮ ለገዛ አገሩ መሞት ጌጥ ነው እንጅ ሞት አይባልም፡፡
አሁንም ሂድ አይምሽብህ፤ የፎከርክበትን በፈቀድህ ጊዜ አድርገው፡፡
አኛም ከዚህ እንቆይሀለን፡፡”
ካሉት በኋላ፤
“…እኔ ሴት ነኝ፡፡ ጦርነት አልወድም፡፡ ግን እንዲህ መሳዩን ውል ከመቀበል፣ ጦርነትን እመርጣለሁ፡፡”
በማለት ቁርጥ ያለ የአገር ወዳድ የጀግና መልስ ሰጥተዉታል፡፡

በመጨረሻም በኢትዮጵያና በኢጣሊያ መንግሥት መካከል የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሻክሮ ወደማይቀረው የአድዋ ጦርነት ሲያመራ በራሳቸው የሚመራ ጦር አደራጅተው ከባለቤታቸው ከምኒልክ ጎን ለውጊያ የተሰለፉ ቆራጥ ሴት ነበሩ፡፡
እቴጌ ጣይቱ ለማይቀረው የአድዋ ጦርነት ከአፄ ምኒልክ ጋር መቀሌ ከደረሱ በኋላ የጦር አለቆች የሆኑትን እነ ራስ መኮንንን ሰብስበው፤
“…አንድ የኢጣሊያ ሹም እናንተን ሁሉ ንቆ እስኪመሽግ ድረስ ዝም ብላችሁ በመቆየታችሁ አፈርኩባችሁ፡፡” ብለዋቸዋል፡፡
የመቀሌ የጠላት ምሽግ በወንዶች ጀግንነት አልፈታ ሲል በሴት ብልሀት ተተካ፡፡
እቴጌ ጣይቱ ከመቀሌ የጠላት ምሽግ በግምት 75 ሜትር ርቀት የሚገኘውን የውሀ ጉድጓድ፤ ጣሊያኖች ውሀ እንዳይቀዱ ለማድረግ 500 በሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች እንዲያዝና እንዲጠበቅ አዘዙ፡፡
በዚህም መሠረት በምሽጉ ያሉት የኢጣሊያ ወታደሮችና እንስሳት ሳይቀሩ በውሀ እጦት እጅግ ተሰቃዩ፡፡
በኢጣሊያ ያሉ ጋዜጦችም፤
“…ታላቅ ምሽግ ነው የተባለውንም የመቀሌ ምሽጋችንን ደግሞ በውሀ እጦት ለቀቅን፡፡ ይህ የኢጣሊያን መንግሥት ውድቀት ስለሚያሳይ፤ መንግሥታችን ድል መደረጉን አምኖ ከአበሻ ምድር ለቆ መውጣት አለበት፡፡”
በማለት ጽፈዋል፡፡
በመጨረሻም በእኝህ ጀግና ሴት ብልሀት፤ ጠላት ውሀ ጥሙን መቋቋም ባለመቻሉ ምክንያት ጠንካራ ምሽጉን ለቆ ለመውጣት ተገዷል፡፡
የኒውዮርክ ታይምስ፣ የፈርንሳዩ ጋዜጣ ለፐቲት ጆርናል፣ እና ሐርፐርስ ዊክሊ የተባሉት ዓለም አቀፍ ጋዜጦች ስለአድዋ ድል ሲተርኩ፤ እቴጌ ጣይቱን በ3ኛው ክፍል ዘመን በኢጣሊያ የፓልምሪን ኢምፓየር ንግሥት ከነበረችው ከንግሥት ዜኖቢያ፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ51ኘው እስከ 30ኛው ዓመተ ዓለም፤ የግብፁ የፕቶሎሚክ ሥርወ መንግሥት የመጨረሻዋ ንግሥት ከነበረችው ከክሊዎፓትራና እንዲሁም በ18ኛው ክፍለ ዘመን የሩሲያ ንግስት ከነበረችው ከታላቋ ካትሪን ጋር እያመሳሰሉ ኃያልነቷን በመግለፅ ዘግበዋል፡፡

ሐምሌ 8 ቀን 1888 ዓ.ም. ቴምፕስ የተባለው ጋዜጣ፤
“…ጣይቱ በግቢያቸው ውስጥ ባለው ሜዳ ላይ ምረኮኞቹን ይጋብዙ ነበር፡፡
…ከጀነራል አልቤርቶኒ ጀምሮ ሁሉም በአንድነት በአውሮፓውያን ደንብ መሠረት ይጋበዛሉ፡፡
...በሚመገቡበት ጠረጴዛ ላይ፤ ሰሀን፣ ሹካ፤ ማንኪያ፤የአፍ መጥረጊያ ፎጣ፤ አበባና የሚጠጡት ቪኖ ሳይቀር ይደረገልቻው ነበር፡፡”
በማለት ሰለ እቴጌ ጣይቱ ትህትናና ጥበብ ዘርዝሮ ጽፏል፡፡

ከዚህ በታች የቀረበው ስዕል፤ ከአድዋ ድል በኋላ ‘የእቴጌ ጣይቱ መታሳቢያ ይሁን’ በማለት በኢጣሊያ አገር የሚገኝ አንድ የጣፋጭ ከረሜላ አምራች ፋብሪካ፤'VIVIDENT' በተሰኘው የፋብሪካው ብራንድ ምርት ላይ የእቴጌ ጣይቱን ምስልና ስም በማውጣት ለ 60 ዓመታት ያህል በተከታታይ ለሽያጭ አቅርቦት እንደነበር ተረጋግጧል፡፡
Italian confectionery company product in the name of Taitu
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በታመሙባቸው የመጀመሪያ ዓመታት የእቴጌ ጣይቱ ሥልጣን እያደገ መጥቶ ብዙዎቹን የሸዋ መኳንንት ሥጋት ላይ ጣላቸው፡፡
ቀድሞውንም ቢሆን ጣይቱ ጠንካራ ባሕርይ የነበራቸው በመሆኑ፤ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥትም ለተከናወኑት ዐበይት ተግባራት ግንባር ቀደም አስተዋፅዖ ማድረግ የቻሉ ጥበበኛና ታላቅ ሴት ነበሩ፡፡
የአዲስ አበባ ዋና መሥራችም እቴጌ ጣይቱ ናቸው፡፡
የኢጣሊያኖችን መሰሪ ተግባር በመረዳት የውጫሌን ውል በአስተዋይነታቸው ጠንቅቀው በመረዳታቸው ውሉን በይፋ ያፈረሱት እቴጌ ጣይቱ ናቸው፡፡
በዓድዋ ጦርነትም ቢሆን የሠራዊቱን ሞራል በማበረታታት እና የጦር ዘዴና መላ በመፍጠር የተጫዎቱት ሚና ቀላል ስላልነበረ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ አኩሪ ገድል በመሆን ሲዘከር ይኖራል፡፡
የምኒልክ ጤንነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ በሄደበት ወቅት፤ እቴጌ ጣይቱ አገሪቱን የማስተዳደሩን ድርሻ ለመረከብ ፍላጎት ስለነበራቸው፤ ባለቤታቸውን ወክለው በመሰላቸው መንገድ ባለሥልጣናትን ሹም ሽር ማድረግ ሲጀምሩ፤ በሚሰጧቸው ውሳኔዎች ላይ የእርሳቸው የሥልጣን ተቀናቃኞች ደስተኞች አልነበሩም፡፡
ይህ የእቴጌ ጣይቱ በሥልጣን እየገነኑ መምጣታቸውና ሹም ሽር ማድረጋቸው፤ የሸዋ መኳንንትን በጣም አስደነገጣቸው፡፡
ትውልዳቸው ከጎንደር የሆነው እቴጌ ጣይቱ፤ ምንም እንኳን ለፖለቲካው ቁልፍ የሆኑ ባለሥልጣናትን ከነገሥታት ቤተሰቦች ጋር ማስተሳሰሩ በኢትዮጵያ የነገሥታት ታሪክ እንግዳ ነገር ባይሆንም፤ እንደ እቴጌ ጣይቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያደረሰው ሰው ግን አለ ተብሎ አይታመንም፡፡
እቴጌ ጣይቱ፤ ለዳግማዊ አፄ ምኒልክ አልጋ ወራሽነት ያጩት ልጅ እያሱን ሳይሆን፤ የራሳቸው ፖለቲካዊ የአመራር እድላቸው እንዲሰምር በማሰብ፤ የወንድማቸው ልጅ የሆኑትን ራስ ጉግሳ ወሌን ለእንጀራ ልጃቸው ለንግሥት ዘውዲቱ አጯቸው፡፡
በእቴጌ ጣይቱ ላይ የተነሳውን አድማ ከበስተጀርባ ሆነው የሚመሩት የጦር ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ እና አገሪቱን በሞግዚትነት የማስተዳደሩ ሥልጣናቸው አደጋ ላይ የወደቀው ራስ ተሰማ ናደው በአንድነት ሆነው በማቀናበር አድማወን ይበልጥ እያጠነከሩት መጡ፡፡
በእቴጌ ጣይቱ ላይ የተነሳው ተቃውሞ ይበልጥ እየሰፋ መጥቶ የንጉሠ ነገሥቱም ጦር በአድማው መሳተፍ ጀመረ፡፡
በዚህም መሠረት ተቀናቃኞቻቸው እቴጌ ጣይቱን ከሥልጣናቸው ገለል ለማድረግ በሚያደርጉት ጥረት፤ ተክለሐይማኖት አደባባይ ተሰብስበው ባሳለፉት ውሳኔ፤ “ጣይቱ ከሥልጣን ተገላ ባሏን በማስታመም ብቻ እንድትወሰን” የሚለውን አሳባቸውን በአቡነ ማቴዎስ በኩል ለማስተላለፍ ሞክረው ነበር፡፡
ሆኖም እቴጌ ጣይቱ የአቡንን ሽምግልና በበጎ አይን እልተመለከቱትም፡፡
እቴጌ ጣይቱም በበኩላቸው ለአዲስ አበባ አድባራትና ለውጭ አገር ዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች የደረሰባቸውን ሁኔታ በመግለጽ ደብዳቤ ጽፈው እርዳታቸውን ተማፀኑ፡፡ በጻፉትም ደብዳቤ፤ “እርሳቸው ውድ ባለቤታቸውን እያስታመሙ ሳለ አድመኞች የተነሱባቸው መሆኑን“ በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ በተቀመመ ቃላት አስተዛዝነው ቢጽፉም ደብዳቤው ምንም ውጤት ሳያስገኝላቸው ቀረ፡፡
እቴጌ ጣይቱ በግዞት የተቀመጡበት
የእንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን

Photo credit to: tripadvisor
የእቴጌ ጣይቱ ደጋፊዎችና ተቆርቋሪዎችም ማለትም፤ የጎንደሩ ዘመዳቸው የደጃዝማች አያለው ብሩ፣ የወንደማቸው ልጅ የራስ ጉግሣ ወሌ እና ብርቱ ሠራዊት የነበራቸው የእቴጌ ጣይቱ ወንድም ራስ ወሌ ብጡል ነበሩ፡፡
የእቴጌ ጣይቱ ተቀናቃኝ በነበሩት የወሎው ራስ ሚካኤልና በእቴጌ ጣይቱ ወንድም በሆኑት በራስ ወሌ ብጡል መካከል ደም ሊያፋስስ የሚችል አደገኛ ፍጥጫ ስለነበረ፤ እቴጌ ጣይቱ ለሁለቱም ወገኖች በጻፉት ልብ የሚነካ ደብዳቤ አማካይነት ፀቡን ለማብረድና ጦርነት ተካሂዶ ደም እንዳይፈስ ማድረግ ችለዋል፡፡
ይህም ፖለቲካዊ ተግባራቸው የእቴጌ ጣይቱ፤ በመጨረሻው ዘመናቸው፤ በበጎነቱ ሲታወስ የሚኖር ርኅራኄ የተሞላበት ተግባር ሆኖ በታሪክ ተመዝግቦላቸዋል፡፡
እቴጌ ጣይቱ በተቀናቃኞቻቸው በመሸነፋቸው ቤተመንግሥቱን ለቀው ቀድሞ ወደሚወዱት ወደ እንጦጦ ማሪያም ቤተ ክርስቲያን ሄደው በግዞት እንዲቀመጡ ተገደዱ፡፡
እቴጌ ጣይቱ ከዳግማዊ ምኒልክ
አጠገብ የተቀበሩበት አዲስ አበባ
አራት ኪሎ የሚገኘው
ታዕካ ነገሥት ባዓታ ለማሪያም ገዳም
በመጨረሻም ወደ ትውልድ አገራቸው ወደ ጎንደር ሄደው ቀሪ እድሜኣቸውን እንዲያሳልፉ ቢጠይቁም ሊፈቀድላቸው አልቻለም፡፡
በዚህም ምክንያት በእንጦጦ ማሪያም ቤተ ክርስቲያን በግዞት እንደተቀመጡ በየካቲት ወር 1910 ዓ.ም. ሕይዎታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡

አስከሬናቸውም የደግማዊ አፄ ምኒልክ መታሰቢያ በሆነው በታዕካ ነገሥት ባዓታ ለማሪያም ገዳም ከባለቤታቸው ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጎን እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡






ምንጭ፤
  1. "አጤ ምኒልክ"  ደራሲ፡- ጳውሎስ ኞኞ የካቲት ወር 1984 ዓ.ም.
  2. "የኢትዮጵያ ታሪክ ከ 1847 እሰከ 1983"  ደራሲ፡- ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ
  3. "መራራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ "  ደራሲ፡- ታዬ ቦጋለ አረጋ 2011 ዓ.ም.
  4. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ