Content-Language: am ፊታውራሪ ሐብተ ጊዮርጊሰ ዲነግዴ (አባ መላ)
header image




ፊታውራሪ ሐብተ ጊዮርጊሰ ዲነግዴ (አባ መላ)




የፊታውራሪ ሐብተ ጊዮርጊሰ ዲነግዴን (አባ መላ)
የአርበኝነት ዘመን ታሪክ ያዳምጡ










1. የልጅነት ዘመን

Fitawurari Habte Giorgis
ፊታውራሪ ሐብተጊዮርጊሰ ዲነግዴ (አባ መላ)

Photo credit to: allaboutethio.com
ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ በምትገኘው ካቦ በተባለችው ሥፍራ በ1843 ዓ.ም. እንደተወለዱ ይገመታል፡፡
ከገበሬ አባታቸው ከአቶ ዲነግዴ ቦተራና ከእናታቸው ከእመት ኢጁ የተወለዱት ሀብተጊዮርጊስ፤ በተለያዩ መጻሕፍት ላይ እንደተገለጸው የጉራጌ ወይም የኦሮሞ ወይም ደግሞ የሁለቱ ቅልቅል እንደሆኑ ተመዝግቧል፡፡
የሀብተ ጊዮርጊስን እድገትና ትውልድ በተመለከተ ብዙ የተጻፉ መዛግብቶች አምብዛም ባይገኙም ከደህና ቤተሰብ እንደተወለዱ ግን ይነገራል፡፡
ዳግማዊ አፄ ምኒልከ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ በነበራቸው ዓላማ ወደ ጅባት እና ሜጫ አውራጃ ባደረጉት ዘመቻ የራስ ጎበና ዳጨ ከፊል ጦር ባደረገው እንቅስቃሴ አንድ ቤት ውስጥ ተሸሽገው የነበሩት ሀብተ ጊዮርጊስን ሲማርኩ፤ ሀብተ ጊዮርጊስ በእድሜ ገና ለጋ ነበሩ፡፡
ከተማረኩም በኋላ ኑሯቸውን አቶ አይተንፍሱ በተባለው በማረካቸው ወታደር ቤት አደረጉ፡፡ አቶ አይተንፍሱም ሀብተ ጊዮርጊስን እንደልጃቸው ተንከባክበው ለማሳደግ ወሰኑ፡፡
ሀብተ ጊዮርጊስ በየጊዘው የሚያሳዩት፤ የእርሻ ሥራ ጥንካሬ፣ የጦር አወራወር ስልትና እንዲሁም የፈረስ ግልቢያና የጋሻ ምከታ ችሎታቸው አሳዳጊያቸውን ያስደሰተ በመሆኑ ዳግማዊ አፄ ምኒልክም በምርኮ የተያዙት ሰዎች በሙሉ ለእርሳቸው ተላልፈው እንዲሰጡ በአስነገሩት አዋጅ መሰረት ምርኮኞች ሲላኩ አቶ አይተንፍሱም ሀብተ ጊዮርጊስን ወስደው ለምኒልክ አስረከቧቸው፡፡
ሀብተ ጊዮርጊስ ወደ ምኒልክ ዘንድ ሲሄዱ ገና የ18 ዓመት ወጣት ነበሩ፡፡

2. የሀብተ ጊዮርጊስ ወደ ንጉሡ ዘንድ መቅረብ

አሳዳጊያቸው አቶ አይተንፍሱ ሰለ ሀብተ ጊዮርጊስ መልካም ፀባይና ችሎታ ለንጉሡ ስለነገሯቸው ምኒልክም የፈረስ ቤት አለቃ የባልደረሱ እረዳት ሆነው እንዲያገለግሉ ሾሟቸው፡፡
የሀብተ ጊዮርጊስ መልካም ፀባይና ችሎታም ባልደራሱን ስላስደሰተ ከበሬታንና ሽልማትን ለማግኘት ቻሉ፡፡
ከዚህ በኋላ ምኒልክም ሀብተ ጊዮርጊስን የቤተ መንግሥታቸው የእልፍኝ አስከልካይ (በአሁኑ አጠራር ፐሮቶኮል) ሹም አድርገው ሾሟቸው፡፡
ሀብተ ጊዮርጊስ በየዕለቱ የሚያሳዩት ቅልጥፍና እና ብቃት ንጉሡን ስላስደሰታቸው በአንዳንድ ወታደራዊ መስኮችም ያሰማሯቸው ጀመር፡፡
በእንባቦ ጦርነት ወቅት ያሳዩት የውጊያ ችሎታና ብቃት በንጉሡ ዘንድ የበለጠ ተወዳጅ አደረጋቸው፡፡ (የእንባቦ ጦርነት፤ ግንቦት 30 ቀን 1874 ዓ.ም. በዳግማዊ አፄ ምኒልክና በጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሐይማኖት መካካል የተደረገ ጦርነት ነው፡፡)
ከዚህ በኋላም ሀብተ ጊዮርጊስ የበቾንና የጨቦን ግዛት እንዲያስተዳድሩ ሹመት ተሰጣቸው፡፡

3. በዐድዋ ዘመቻ ያደረጉት ተሳትፎ

Fitawurari Habte Giorgis
ሀብተ ጊዮርጊስ በዐድዋ ዘመቻ ወቅት ዳግማዊ አፄ ምኒልከ 120 ሺህ ሠራዊት በዐድዋ ግንባር ሲያሰልፉ ከሠራዊቱ ዋና ዋና የጦር መሪዎች መካከል ማለትም፤
  1. ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ
  2. እቴጌ ጣይቱ
  3. ከራስ መንገሻ ዮሐንስ
  4. ራስ አሉላ እንግዳ
  5. ወሎው ራስ ሚካኤል
  6. ጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሐይማኖት
  7. ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል

ጋር ሆነው የራሳቸውን ጦር ይዘው በጋራ በመሰለፍ በውጊያ ጥበባቸውና የጦር አመራር ብቃታቸው አኩሪ ገድሎችን ፈጽመዋል፡፡
የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የጦር አለቃ የነበሩት ፊታወራሪ ገበየሁ በዐድዋ ጦርነት ላይ ከሞቱ በኋላ ሀብተ ጊዮርጊስ ባሳዩት መልካም ፀባይ፣ የጦር አመራር እና የውጊያ ችሎታ የተነሳ የፊታውራሪነት ማዕረግ ተሰቷቸው ፊታውራሪ ገበየሁን በመተካት የጦር አለቃ ሆኑ፡፡

4. ጠንካራ የአመራር ችሎታዎች

Fitawurari Habte Giorgis
የጦር ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ
ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጦር ጋር ተጣምረው ብዙ የደቡብ ኢትዮጵያን ግዛቶችን ወደ አንድነት ለማምጣት ይቻል ዘንድ የፊታወራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ጦር ከራስ ጎባና ዳጬ፣ ከወሎው ከራስ ሚካኤል አሊ እና ከባልቻ አባ ነፍሶ ጦር ጋር በመተባበር ከፍተኛ አስተወፅፆ አበርክተዋል።
ፊታወራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ የቦረናን ግዛት በሚያስተዳድሩበት ወቅት 15 ሺህ የሚደርስ ሠራዊት ካሰባሰቡ በኋላ በሰኔ ወር 1889 ዓ.ም. ከምእራብ ሸዋ ተነስተው ወደ ቦረና ተጓዙ፡፡
ሐምሌ 25 ቀን 1881 ዓ.ም. የፊታወራሪ ሀብተጊዮርጊስ ሠራዊት ቦረና ደርሶ ሶጊዳ በተባለ ቦታ ላይ ምሽግ ገነባ።
የቦረና አባ ገዳ፤ አዲ ዶዮ በአካባቢው የገዳ ጉባኤ መሠረት ከፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ጋር ጦርነት መግጠም እንደማያስፈልግ በማመን ውሳኔውን አሳለፈ፡፡
ዳግማዊ አፄ ምኒልክም በቦረና ካደረጉት የተሳካ ዘመቻ በኋላ ለፊታወራሪ ሀብተጊዮርጊስ፤ ከቦረና ግዛት በተጨማሪ የሜጫ እና ጅባት ግዛቶችን እንዲያስተዳድሩ ሾሟቸው።
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የመንግስትን ስራ ዘመናዊ ለማድረግ በማሰብ በንጉሠ ነገሥቱ አስተዳደር ዘመን በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በማቋቋም፤ በብዙ የታመኑና የተከበሩ መኳንንቶችን መርጠው የሚኒስተርነት ሹመት ሲሰጡ ከነዚህ ምኒስትሮች መካከል ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ የጦር ሚኒስቴር ምኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡
የጦር ምኒስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላም ጦሩ በትጥቅ እንዲደረጅና በዲሲፕሊን የታነፀ እንዲሆን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡
በጦር ምኒስትርነት ከሚያዙት መንግስታዊ ጦር በተጨማሪ በግላቸው የሚያዙትና የሚመሩት 15 ሺህ ጦር እንደነበራቸው ይነገራል፡፡

ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ፤ ከ1901 ዓ.ም. እስከ 1919 ዓ.ም. ድረስ ለ10 ዓመታት ያህል የምኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ (በአሁኑ አጠራር ጠቅላይ ምኒስትር) በመሆን አገልግለዋል፡፡
ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ በውጊያ ጥበብ ሠልጥነው በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በሀገሪቱ ንጉሣዊ አስተዳደር ውስጥ ካገለገሉ በኋላ በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ከፍተኛውን ወታደራዊ ሹመት አግኝተዋል፡፡

ልጅ እያሱን በራስ ተፈሪ የመተካት ሂደት የተሳካው ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ባሳደሩት ብልሀት የተሞላበት አመራር በመስጠታቸው እንደሆነ በሰፊው ይታመንበታል፡፡
ዳግማዊ ምኒልክ በሕመም ምክንያት አቅም እያነሳቸው በመጣ ጊዜ ማዕከላዊ ሥልጣኑን እቴጌ ጣይቱ ለመቆጣጠር ሲጥሩ እቴጌይቱን ከስልጣን በማስወገድ ረገድ ለተወሰደው እርምጃ እና እንዲሁም በ1908 ዓ.ም. ልጅ እያሱን ከስልጣን አውርዶ በምትካቸው ልዕልት ዘውዲቱን ስልጣን ላይ ለማውጣት በተካሄደው የፖለቲካ ውሳኔ ዋናው ተዋናይ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ነበሩ።
ልጅ እያሱም ከስልጣን እንደተነሱ ድርጊቱን በፅኑ በተቃዎሙት በወሎው ንጉሥ ሚካኤል እና በሸዋ መኳንንቶች መካከል በተካሄደው የሰገሌ ጦርነት ላይ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ግንባር ቀደም የጦር አዝማች ነበሩ፡፡

Fitawurari Habte Giorgis
ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ፤ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ፣ በልጅ ኢያሱ 5ኛ፣ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ማለትም በአራቱም የመነግሥታት ዘመናት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት እና የጦር ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ፤ በወታደራዊ አዛዥነት እና በዳኝነት በነበራቸው ከፍተኛ ችሎታቸው የተነሳ ብዙ ጊዜ የሚጠቀሱ እና በኢትዮጵያ የግዛት አስተዳደር (ኢምፓየር) ውስጥ ትልቅ ስፍራ የነበራቸው ከመሆናቸውም በላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥም ትልቅ ሚና የተጫወቱ፣ አስተዋይ እና ነገር አዋቂ እንደነበሩ ታሪክ መስክሮላቸዋል።
ይህም ነገር አዋቂነታቸውና አስተዋይነታቸው “አባ መላ” ተብለው እንዲጠሩ አስችሏቸዋል፡፡
በዚህም የተነሳ ዳግማዊ ምኒልክ በውስጥም ሆነ በውጭ ለተፈጠሩት ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ወደ አባ መላ በመላክ አስተያየታቸውን የመጠየቅ ልማድ ነበራቸው፡፡
በአንድ ወቅት ሁለት እንግሊዛውያን ያለመግቢያ ፈቃድ ከኬንያ ወደ ኢትየጵያ ቦረና ግዛት ገብተው በመገኘታቸው ተገድለው ነበር፡፡ ተቀማጭነቱ በኢትዮጵያ የነበረው የእንግሊዝ መንግሥት ቆንስላም ዜጎቻችን ያለአግባብ ተገድለውብናል ብሎ አቤቱታውን ለንጉሠ ነገሥቱ አቅርቦ ነበር፡፡
ንጉሠ ነገሥቱም በጉዳዩ ላይ መክረን እንነግርሀለን ብለው መልስ ከሰጡ በኋላ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስን አስጠርተው የእንግሊዝ ዜጎች ለምን እንደተገደሉ ሲጠይቋቸው፤ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስም ቆንስሉን ወደ እኔ ላኩትና መልሱን በቶሎ አሳውቅወታለሁ ብለው መለሱላቸው፡፡
የእንግሊዝ ቆንስሉም (consul) ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዘነድ ከቀረበ በኋላ፤
“የዜጎቻችን ደም በከንቱ ስለፈሰሰ፤ ደማቸው የፈሰሰበት መሬት ለእኛ ይሰጠን፡፡” በማለት ጠየቃቸው፡፡ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስም በምላሹ፤ “ግን በሀገራችሁ የዚህን አይነት ደንብ አለን?”
በማለት ጠየቁት፡፡ ቆንስሉም አዎ ብሎ መለሰ፡፡
ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስም፤
“እንግዲያውስ መልካም፤ የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ እንግሊዝ አገር ሄዶ ሞቷልና ለንደንንም ለእኛ ስጡን፡፡ እናንተም የጠየቃችሁትን ውሰዱ፡፡” በማለት በጽሁ አርቅቀውና ፈርመው፤ “በል አንተም ለመስማማትህ እዚህ ወረቀት ላይ ፈርም፡፡”
ሲሉት አልፈርምም ብሎ ምንም ሳይተነፍስ ተመልሶ ሄዷል፡፡
ዳግማዊ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱም ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ለቆንስሉ ብልሀት የተሞላበት መልስ በመስጠታቸው ንጉሡና ንግሥቲቱ ፊታውራሪን አንገታቸውን አቅፈው ስመዋቸዋል፡፡

5. ሕልፈተ ሕይዎት

Fitawurari Habte Giorgis
አዲስ አበባ የሚገኘው የፊታውራሪ
ሀብተ ጊዮርጊስ መኖሪያ ቤት
ሀብተ ጊዮርጊስ በዐድዋ ዘመቻ ወቅት ዳግማዊ አፄ ምኒልከ 120 ሺህ ሠራዊት በዐድዋ ግንባር ሲያሰልፉ ከሠራዊቱ ዋና ዋና የጦር መሪዎች መካከል ማለትም፤
የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዕለተ ሞተ ዓርብ ታህሳስ 3 ቀን 1906 ዓ.ም ነበርና የንጉሠ ነገሥቱ የቅርብ ወዳጅና ታማኝ አገልጋይ የነበሩት የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴም ዕለተ ሞት በዕለተ ዓርብ ታህሳስ 3 ቀን ስለነበረ ቀኑ በመገጣጠሙ ምክንያት ለሰው ሁሉ ግርምትን የፈጠረ እንደነበረ ይነገራል፡፡
ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ለረጅም ጊዜ ታመው ከቆዩ በኋላ ዓርብ ታህሳስ 3 ቀን 1919 ዓ.ም. በተወለዱ በ76 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
የቀብራቸው ሥነ ሥርዓትም ግርማዊት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እና ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን በተገኙበት መድፍ እየተተኮሰ፣ ነጋሪት እየተጎሰመ በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡
የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ባለቤት ወይዘሮ አልታየ ወርቅ የባለቤታቸውን ግምጃ ሱሪና ራስ ወርቅ ይዘው ሲያለቅሱ ለሀዘኑ የተሰበሰበውን ሁሉ አስለቅሰውታል፡፡
በቀብር ሥነ ሥርዓቱም እለት የቅኔ አዋቂው ነጋድራስ ተሰማ እሸቴም፤
ከምኒልክ ይዞ እከአሁን ድረስ
የአልታየ ሞት ሆነ የሀብተ ጊዮርጊስ፤
በማለት ሰምና ወርቅ ግጥም አቅርበዋል፡፡

ለእኒህ ታላቅ ሰው መታሰቢያ የሚሆን በአዲስ አበባ በመርካቶ በስማቸው ድልድይ ተሰይሞላቸዋል፡፡
እንዲሁም በቱሉ ቦሎ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተሠርቶ በስማቸው ተሰይሞላቸዋል፡፡፡፡





ምንጭ፤
  1. allaboutethio   allaboutethio.com
  2. Ethio FM 107.8   ዩቲውብ ሊንክ
  3. ከዊኪፒዲያ የተተረጎመ
  4. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ