Content-Language: am ፊታውራሪ ገበየሁ (አባ ጎራው)
header image



ፊታውራሪ ገበየሁ (አባ ጎራው)




የዐደዋው ጀግና የፊታውራሪ ገበየሁን (አባ ጎራው)
የአርበኝነት ዘመን ታሪክ ያዳምጡ










1. ትውልድ

የዐደዋው ጀግና ፊታውራሪ ገበየሁ (በፈረስ ስማቸው አባ ጎራው) ነሐሴ 12 ቀን 1836 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ፤ በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ በአንጎለላ አስታይ በምትባል ቀበሌ ተወልደው ከአፄ ምኒልክ ጋር አድገዋል፡፡
ፊታውራሪ ገበየሁ የአፄ ምኒልክ የልብ ወዳጅ እንደነበሩ ይነገራል፡፡

2. በአምባላጌ ውጊያ ያሳዩት ጀብዱ

Fitawurari Gebeyehu
ፊታውራሪ ገበየሁ (አባ ጎራው)
በኢትዮጵያና በፋሽስት ኢጣሊያ ጦር መካከል የመጀመሪያው ውጊያ አምባላጌ ላይ ሕዳር 29 ቀን 1888 ዓ.ም. ሲጀመር፤ ይህ የተፈጥሮ ምሽግ የሆነው አምባላጌ፤ በሻለቃ ቶሴሊ በሚመራ የጠላት ጦር ቁጥጥር ስር ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል (የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ወላጅ አባት)፤ ጠላት የያዘውን ቦታ በሠላም ለቆ እንዲወጣ በመደራደር ላይ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጅ፤
የኢትዮጵያ ሠራዊት የግንባር ጦር መሪ የነበሩት ፊታውራሪ ገበየሁ፤ የነበረባቸው ሕመም ሳይገታቸው ሊታመን በማይችል ድፍረትና ወኔ የኢትዮጵያን ሠራዊት ወደ ፊት እየመሩና ፊት ሊፊት እየተዋጉ የአምባላጌን አቀበት ወጥተው ሁለት ሰዓት ብቻ በፈጀ ውጊያ እጅግ የሚደንቅ እና ቅልጥፍና የተሞላበት ጀግንነት በመፈፀም ጦርነቱ በድል እንዲጠናቀቅ አሰችለዋል፡፡

Major Tossolli
በአምባላጌ ጦርነት ላይ
የሞተው ሻለቃ ቶሴሊ
በአምባላጌ ውጊያ የጠላት ጦር መሪ የነበረው ቶሴሊም በጦርነቱ በ 7 ጥይት ተመቶ ሲሞት፤ የቀረው የጠላት ጦርም ተበትኖ ወደ መቀሌ ሸሽቷል፡፡

ከአምባላጌው ድል በኋላም ፊታውራሪ ገበየሁ የመቀሌን የጠላት ምሽግ ለመስበር በተደረገው ውጊያ ቢቆስሉም ምርኩዝ ይዘው ጠላትን ከመውጋት ወደኋላ ያላሉ ቆራጥ ኢትዮጵያዊ ጀግና ነበሩ፡፡

3. በዐድዋው ጦርነት ያሳዩት ጀብዱ

ፊታውራሪ ገበየሁ በ52 ዓመት የሽምግልና ዕድሜያቸው ከአፄ ምኒልክ ጋር ዐድዋ የዘመቱ እውቅ አርበኛ ናቸው፡፡ በዐድዋው ጦርነትም የምኒሊክ ጦር ግንባር የፈረሰኛ ጦር መሪ ነበሩ፡፡
ፊታውራሪ ገበየሁ ወደፊት እየገሠገሡ ጠላትን በማጥቃት አመራር እየሰጡ ሳለ ጠላት፤ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ በሚመራው በሰፊው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ላይ እጅግ በርካታ የኢጣሊያ ወታደሮች የደፈጣ ውጊያ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተመለከቱ።
ይህን የተረዱት ፊታውራሪ ገበየሁ፤ ይህ የኢጣሊያ ወታደሮች ያጠመዱት የደፈጣ ውጊያ ወዲያውኑ አርምጃ ተወስዶበት ካልመከነ፤ በሰፊው የምኒልክ ተዋጊ ሠራዊት ላይ አስከፊ እልቂት እነደሚከሰት ስለተረዱ፤
Mekele Fort
ለማጥቃት እጅግ አዳጋች የነበረው
የመቀሌው የተጠናከረው የጠላት ምሽግ
ጊዜ ሳያባክኑ ወዲያውኑ የፈረሰኛ ጦራቸውን እየመሩ በቀጥታ የኢጣሊያ ጦር ወደ መሸገበት ጠንካራ የምሽግ ሥፍራ በማምራት ውጊያ በመጀመራቸው የምኒልክ ሠራዊት ጠላት ከደገሰለት አስከፊ እልቂት ያለምንም ጉዳት አምልጦ ወጥቶ ወደ ዋናው የዐድዋ ጦርነት ግንባር እንዲሄድ በማድረጋቸው ንቃት የተሞላበት ታላቅ ጀብዱ ፈጽመዋል፡፡

ከአምባላጌው ድል በኋላም የመቀሌን የጠላት ምሽግ ለመስበር በተደረገው ውጊያ ቢቆስሉም ምርኩዝ ይዘው ጠላትን ከመውጋት ወደኋላ ያላሉ ቆራጥ ኢትዮጵያዊ ጀግና ነበሩ፡፡

የዐድዋ ጦርነት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ማለዳ ላይ እነደተጀመረ፤ ጦሩን ሲመሩ ከነበሩት የጦር መሪዎች ውስጥ አንዱ የነበሩት ፊታውራሪ ገበየሁ፤ በጀነራል አልቤርቶኒ የሚመራውን የጠላት ጦር ፊት ለፊት የገጠሙት በዕንዳ ኪዳነ ምሕረት በኩል ነበር፡፡

4. ሕልፈተ ሕይወትና የቀብር አፈጻጸም

በዐድዋው ጦርነት አውደ ውጊያ ላይ የጠላት ጦር ጥቃት እየጨመረ ሲመጣና የኢትዮጵያ ሠራዊት ማፈግፈግ ላይ ሳለ፤ ፊታውራሪ ገበየሁ፤
“እንዴት ትሸሻላችሁ! እንዴት እንደምሞት ሂዱና ለንጉሡ ተናገሩ፡፡” ብለው ፈረሳቸውን በአለንጋ አስነስተው የጠላት መድፍና ጥይት በሚዘንብበት በተፋፋመ ውጊያ መሀል ተወርውረው ገቡ፡፡

በጠላት ውጊያ መበርታት ምክንያት ወደኋላ ሲያፈገፍግ የነበረው የኢትዮጵያ ሠራዊትም የእርሳቸውን የድፍረት ውጊያ በማየት ማፈግፈጉን ትቶ የጦር መሪውን ገበየሁን ተከትሎ ወደ ውጊያው መሐል ተንደርድሮ መግባት ጀመረ፡፡

ጀግናው የጦር መሪ ፊታውራሪ ገበየሁ እና ከእርሳቸው ጋር የነበሩ የተወሰኑ የጦር መሪወችና ተዋጊወች፤ ከጠላት ጋር በጀግንነት በመፋለም ላይ ሳሉ በጠላት ጥይት ተመተው ሕይወታቸው አለፈ፡፡

ፊታውራሪ ገበየሁ ገና ወደ ዐድዋ ሲዘምቱ፤
“ስሸሽ ከኋላየ ከተመታሁ አሞራ ይብላኝ፡፡ እኔ እንደ አባቶቸ አይደለሁም፡፡ ወግም አይገባኝም፡፡ ፊት ለፊት ስፋለም ከወደኩ ግን፤ ሬሳየን ወደ ትውልድ ቦታየ ውሰዱልኝ፡፡”
በማለት አስቀድመው ተናዘው ነበር፡፡

የአፄ ምኒልክ አበጋዝና የዐደዋው ጀግና ፊታውራሪ ገበየሁ (አባ ጎራው) የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. የዐድዋ ጦርነት በተደረገበት ዕለት ለእናት ሀገራቸው ነፃነት እና ክብር ሲሉ በቆራጥነት ተዋግተው በጀግንነት ወድቀዋል፡፡
አንጎለላ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን
አስከሬናቸውም በአድዋ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ለ 7 ዓመታት ተቀብሮ ከቆየ በኋላ ወደ አምባላጌ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተወሰደ፡፡
በኋላም በኑዛዜያቸው መሠረት አፅማቸው ወደ ሰሜን ሸዋ ተልኮ የትውልድ ስፍራቸው በሆነው፤ ከደብረ ብርሃን 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ባሶ ወራና ወረዳ፤ ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ባሰሯትና ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ክርስትና በተነሱባት አንጎለላ ኪዳነ ምህርት ውስጥ በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡
ይህ በስዕሉ ላይ የሚታየውን አፅማቸው ያረፈበትን የመታሰቢያ ሳጥን አቶ አብርሃም ደምሴ የተባሉ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የካቲት 16 ቀን 1989 ዓ.ም. አሰርተውላቸዋል፡፡
በትውልድ ስፍራቸው በአንጎለላ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን
በክብር ያረፈው የዐድዋው ጀግና የፊታውራሪ ገበየሁ አጽም
የአምባላጌን ምሽግ በመስበር የፋሽስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይልን ሽንፈት ቀድመው ያበሰሩት ፊታውራሪ ገበየሁ፤ በወቅቱ የፈረንሳይ ጋዜጦች፤ የአምባላጌው የኢትዮጵያ ጀግና! በማለት እንዳወደሷቸው ታሪክ ይነግረናል፡፡

በኢትዮጵያውያን ገጣሚዎች አንደበትም ከመሞታቸው በፊት ስለአሳዩት ጀብዱ የሚከተለው ግጥም ተገጥሞላቸዋል፡፡
አላጌ በሩ ላይ ማልዶ ቢገጥማቸው፣
ለምሳም ሳይደርሱ ቁርስ አደረጋቸው፡፡
የዐድዋ ስላሴን ጠላት አረከሰው፣
ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው፡፡


ምንጭ፤
  1. “የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983”  ደራሲ፤ ፐሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ 2003 ዓ.ም.
  2. “የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ” ደራሲ፤ ተክለፃድቅ መኩሪያ 1961 ዓ.ም.
  3. ምስጋና፤ ለኢቢሲ  ዩቲውብ ሊንክ
  4. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ