Content-Language: am ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ
header image

ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ (ባልቻ አባ ነፍሶ)



የዐድዋው ጀግና የደጃዝማች ባልቻ ሳፎን
(ባልቻ አባ ነፍሶ) የአርበኝነት ታሪክ ያዳምጡ













1. ትውልድና ዕድገት

Dejazmach Balcha Saffo
ባልቻ በወጣትነት ዘመናቸው

credit to: EthioHeritage
ባልቻ ሳፎ በ1854 ዓ.ም ወሊሶ አካባቢ በሚገኝ አገምጃ ተብሎ በሚጠራ ቦታ ተወለዱ።
ባልቻ ኑሯቸውን በዳግማዊ ምኒልክ ቤተመንግስት ሲጀምሩ እድሜያቸዉ ገና የ14 ዓመት ልጅ ነበሩ።
በአባታቸው ኦሮሞ፣ በእናታቸው የጉራጌ ተወላጅ የሆኑት ባልቻ በመጀመርያ በእልፍኝ አሽከርነት ቀጥሎም በጅሮንድ ተብለው የግምጃ ቤት ሀላፊ ሆነው ተሾሙ።
ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ብዙ ሰው የሚያውቃቸው በፈረስ ስማቸው ባልቻ አባነፍሶ በሚል መጠሪያ ነው።

2. የደጃ/ ባልቻና የንጉሥ ተፈሪ ፍጥጫ

የንጉሠ ተፈሪ የዘመናዊነት አካሄድ ያልጣማቸው የዳግማዊ ምኒልክ ቀኝ እጅ የነበሩት ባልቻ፤ ከንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጋር ግልጽ ፍጥጫ ውስጥ ገቡ፡፡
በፖለቲካው ሳይሆን በጦር ብልሀታቸው የታወቁት ባልቻ፤ የሸር መንገድ መርጠው ንጉሡን ከመጥለፍ ይልቅ ፊት ለፊት መጋፈጥን መረጡ፡፡
በተለይ ንጉሥ ተፈሪ የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክን ሥልጣን ቀስ በቀስ እየገዘገዙት እንደሆነ በማሰባቸው ቁጣቸው ገንፍሎ ነበር፡፡
ሆኖም ብዙ መኳንንቶች ንጉስ ተፈሪን በመቃወም ባነሳሱት አድማ ተይዘው በእስራትና በንብረት መወረስ ሲቀጡ፤ ባልቻ ግን ራሳቸውን ከአድማው ነፃ ለማውጣት ችለዋል፡፡
ባልቻ የሲዳሞ ገዥ በነበሩበት ጊዜ በ1920 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ንጉሥ ተፈሪ አስጠርተዋቸው ነበር፡፡
Balcha Safo
ባልቻ ትንሽ ጊዜ ወስደው ሲያቅማሙ ከቆዩ በኋላ ንግሥት ዘውዲቱ በላኩላቸው የማግባቢያ ጥሪ ወደ አዲሰ አበባ መጡ፡፡
Ras Teferi Mekonnen
ባልቻ ወደ አዲሰ አበባ ሲመጡ ብቻቸውን ሳይሆን የጦር መሣሪያ ያነገቡ ብዙ ጦር አስከትለው ስለነበረ ጭፍራቸውን ከአዲስ አበባ በስተደቡብ በሚገኘው ፉሪ ተራራ ላይ አስፍረው እርሳቸው ጥቂት ወታደሮችን አስከትለው ወደ ቤተ መንግሥት አመሩ፡፡
ባልቻ በንጉሡ ላይ ያላቸውን ጥላቻ በግልፅ ሲያሳዩ ንጉሥ ተፈሪ ደግሞ በበኩላቸው አርበኞች የለመዱትን ጮማ ሥጋና ጠጅ አቅርበው ግብዣ በማድረግ በመልካም ሁኔታ ከተቀበሏቸው በኋላ በባልቻ ላይ ስለሚወሰደው እርምጃ ውሳኔ አሳለፉ፡፡
Ras Biru Wolde Gebriel
ራስ ብሩ ወልደ ገብርኤል
በዚህም መሠረት በባልቻ ምትክ ደጃዝማች ብሩ ወልደ ገብርኤልን የሲዳሞ ገዥ ሆነው መሾማቸውን በአዋጅ ፉሪ ለሰፈረው ለባልቻ ጦር አስነገሩ፡፡
የባልቻ ጦርም አዋጁን ከሰማ በኋላ አዲሱን ገዥ ተከትሎ ተጓዘ፡፡
ደጃዝማች ባልቻ ራስ ተፈሪን ለመቃወም ያደረጉት ሙከራ ከከሸፈ በኋላ ብቻቸውን እንደቀሩ ስለተገነዘቡ፤ በቀጥታ ወደ አዲስ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ሸሽተው ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይቆዩ በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ታሰሩ፡፡

3. የአርበኝነትና የጀግንነት ታሪክ

Balcha Saffo
የዐድዋው ጀግና ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ (አባ ነፍሶ)

image link
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከተነገረላቸው ዋና ዋና ጀግኖች መካከል አንዱ ባልቻ ናቸው።
በጦርነት ላይ ባሳዩት ጀብዱ ሥራቸው በታሪክ ላይ ተወስቷል፣ ቆራጥነታቸው በስንኝ ተግጥሟል እንዲሁም በስማቸው ተዘምሯል።
በጅሮንድ ባልቻ ከአድዋ ጦርነት በፊት በ1874 ዓ.ም በእምባቦ፣ በ1879 ዓ.ም በሐረርጌ እንዲሁም በ1887 በወላይታ በተደረጉ ጦርነቶች በመሳተፍ ጀግንነታቸውን አስመስክረዋል።
በ1888 ዓ.ም፤ በ33 ዓመት ለጋ የወጣትነት ዕድሜያቸው 3 ሺህ ሠራዊታቸውን አስከትለው ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጋር ዐድዋ የዘመቱት በጅሮንድ ባልቻ፤ ከሊቀመኳስ አባተ ጋር በዐድዋ ዘመቻ ላይ በመድፎቻቸው አገርን የሚያኮራ ተግባር ፈጽመው ተመልሰዋል፡፡
በተለይ በመቀሌ ከዚያም በአድዋ ጦርነት ባሳዩት ጀብዱ ስማቸው ገኖ ከተጠሩት ታላላቅ የኢትዮጵያ ጀግኖች አንዱ ለመሆን በቅተዋል።


ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ነግሠው ኢትዮጵያን መግዛት በጀመሩ በስድስተኛው አመት ኢጣልያ ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን ለመውረር በተነሳችበት ወቅት 50 ዓመታት ሙሉ ያለእረፍት ያገለገሉትና የ68 ዓመት አዛውንቱ ባልቻ፤ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር ቅራኔ ውስጥ ስለነበሩ ይዘውት ከነበረው የመንግስት አስተዳደር እንዲገለሉ ተደርገው ነበር።
የፋሽስት ኢጣልያ በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ወረራዋን ስትጀምር፤ በአገራቸው መቼም የማይደራደሩት ባልቻ፤ ምንም እንኳን አዛውንት ቢሆኑም፤ ንጉሠ ነገሥቱ ጋር ቀርበው ጦርነት ሄደው ለመዋጋት ፍቃደኛ መሆናቸውን ነገሯቸው።
ንጉሠ ነገሥቱም ባልቻ ለአሳዩት ወኔ አድናቆታቸውን ከገለፁ በኋላ ጦርነቱ የሚፈቅደው ስልትና አወቃቀር ድሮ በአድዋ ጊዜ ከነበረው ጊዜ የተለየ መሆኑንና በእድሜያቸውም መግፋት ሊገጥማቸው የሚችለውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በጦርነቱ እንዳይካፈሉ ተደረጉ።
ፋሽስት ኢጣልያ በጦርነቱ አሸንፋ አዲስ አበባ ስትገባ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጋር ቅራኔ ውስጥ የነበሩትን ሁሉ እያባበለ በመውሰድ የወር ደመወዝ መድቦላቸው የተደላደለ ኑሮ ይኖሩ ነበር።
በዚህም የተነሳ ደጃዝማች ባልቻ ከእኛ ጎን ሊሰለፈፉ ይችላሉ የሚል ግምት በጣልያኖች ዘንድ ስለነበረ የኢጣሊያ መንግሥት “በሠላም ከገቡልኝ በደስታና በድሎት ይኖራሉ፡፡” ብሎ ቢልክባቸው፤
“...የጌታዬን መንግሥት ጠላት ወስዶት በሕይወት ልኖር አልፈልግም፡፡
ከጌታዬ ከምኒልክ ጋር በሰማይ ቤት ስገናኝ ምን ሠርቼ መጣሁ ለማለት እችላለሁ?"
ብለው መልስ በመስጠት፤ ባልቻ ቆራጥ አገር ወዳድ አርበኛ መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡
ወዲያዉም ጦራቸውን በማሰባሰብ በቀደምትነት የአርበኝነት ትግል ከጀመሩት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች መካከል አንዱ ሆኑ።
ባልቻ አባ ነፍሶ የጠላት ኃይል እርሳቸው ከገመቱት በላይ ሆኖ ስላገኙት በመጀመሪያ ወደ አገምጃ በመጨረሻም በቾ አበቤ ሄደው ተቀመጡ።
በቾ በነበሩበት ጊዜ ጄኔራል ግራዚያኒ፤
"ያገርዎ ንጉሥ የወረሰብዎትን ሀብት እንመልስልዎታለን፤ ወደ እኛ ይግቡ።"
ብሎ ቢፅፍላቸው ባልቻ ግን፤
"...ይድረስ ለግራዚያኒ፤ ገንዘቤን አንተ ከምትመልስልኝ ያገሬ ንጉሠ ነገሥት የወረሰኝ እሱ ይሻለኛል። አንተንም በሞት እንጂ በህይወት አላይህም።"
የሚል መልስ ከላኩለት በኋላ ግራዚያኒ፤ ኮሎኔል ፕሪንቺ ፖሊ የተባለውን የጠላት መኮንን በአባጆቢር አባዱላ መሪነት ብዙ ወታደር አስከትሎ ባልቻን እንዲወጋቸው አዘዘ።

4. የጀግናው የዐድዋ አርበኛ ህልፈተ ሕይወት

Statue of Dejazmach Balcha
በደቡብ ምእራብ ሸዋ ባንቱ ከተማ ውስጥ
የሚገኘው የደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ሐውልት

 image link
ጥቅምት 27 ቀን 1929 ዓ.ም. የጠላት ጦር ደጃዝማች ባልቻ ወደሚኖሩበት ቦታ ድረስ በባንዳ እየተመራ በመዝለቅ በእሳቸው ላይ ዘመተባቸው።
ደጃዝማች ባልቻም ከዘመተባቸው የጠላት ጦር ጋር በጀግንነት ከተዋጉ በኃላ አብረዋቸው ከነበሩት አንዳንዶቹ በውጊያው ላይ ሲሰው፣ አንዳንዶቹም ህይወታቸውን ለማትረፍ ሸሹ።
የኢጣልያ ጦር ባልቻን ከበባቸው። ወዴትም መሄድ አልቻሉም።
በመጨረሻም አንድ የኢጣሊያ ወታደር ወደ ደጃች ባልቻ ዘንድ ከቀረበ በኋላ፤
“...ደጃዝማች ባልቻ ማለት አንተ ነህ?” ብሎ ጠየቃቸው።
ደጃዝማቹም “አዎ እኔ ነኝ!” ሲሉት፤ “በሉ ይማረኩ። ሽጉጥዎትንም ያስረክቡኝ።” አላቸው።
ደጃዝማች ባልቻም ፤
“እኔ እጅ የምሰጥ ሰው አይደለሁም። ትጥቄንም አልሰጥህም!” ብለው ሽጉጣቸውን አውጥተው፤ የኢጣሊያ ጦር መኮንኑን ተኩሰው ገደሉት፡፡
በቦታው የነበሩት የጠላት ወታደሮችም በጀግናው አዛውንት ደጃዝማች ባልቻ ላይ የጥይት እሩምታ አዘነቡባቸው፡፡
የአድዋው አርበኛ ጀግናው ደጃዝማች ባልቻ ለሀገራቸው ነፃነት ሲሉ በሽምግልና ዕድሜያቸው ወራሪውን ፋሽስት ኢጣሊያን በቆራጥነት ተዋግተው በተወለዱ በ73 ዓመታቸው ለአገራቸው ክብር እና ነፃነት መስዋዕት ሆነው አልፈዋል፡፡

የደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ መታሰቢያዎች

ለደጃዝማች ባልቻ የጀግንነት ሥራዎች ክብር በመስጠት መታሰቢያ የሚሆኑ አዲስ አበባ ውስጥ፤ ሆስፒታል፣ መንገድ እና ትምህርት ቤት ተሰይሞላቸዋል፡፡
ከነዚህም መካከል፤
Dejazmach Balcha Hospital
ጌጃ ሰፈር ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አጠገብ የሚገኘው የደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ አጠቃላይ ሁለተኛ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት እና እንዲሁም ልደታ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ የሚገኘው በ1968 ዓ.ም የተቋቋመው የሶቪየት ቀይ መስቀል ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪም ከጦር ኃይሎች ወደ ሜክሲኮ የሚወስደው ዋና መንገድ በደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ስም ተሰይሞላቸዋል፡፡
ድምጻውያንም በበኩላቸው የእርሳቸውን የጦር ጀግንነትና ገድል እያወሱ በድምፃቸው አዚመውላቸዋል፡፡
በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ ደግሞ ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን ‹‹ባልቻ አባነፍሶ›› በሚል ታሪካዊ ተውኔትን ጽፈው በአገር ፍቅር ቲያትር ቤት እንዲታይና ትውልዱ ስለደጃዝማች ባልቻ የአገር ወዳድነትና የጀግንነት ታሪክ የበለጠ እንዲረዳ ከፍተኛ አስተወጽዖ አበርክተዋል፡፡


ምንጭ፤
  1. "የኢትዮጵያ ታሪክ ከ 1847 እሰከ 1983"  ደራሲ፡- ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ
  2. ምስጋና፤ ለስለሺ ሻውል dejazmachbalcha.com
  3. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ