Content-Language: am ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ
header image



ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ




የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ የሆነው
የልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስን ታሪክ ያዳምጡ














ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ
የአፍሪካው ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ

Photo credit to:  blackoutdoors
ዓለማየሁ ቴዎድሮስ፤ የአፄ ቴዎድሮስ እና በኋላም የአፄ ዮሐንስ 4ኛ መቀመጫ እና የጎንደር ዋና ከተማ በነበረችው በደብረ ታቦር ከተማ ሚያዝያ 5 ቀን 1853 ዓ.ም. ተወለደ፡፡
አፄ ቴወድሮስ ከሞቱ በኋላ እናቱም ወይዘሮ ጥሩወረቅ አከታትለው ስለሞቱ ብቻውን ቀረ፡፡
ወይዘሮ ጥሩወርቅ የሰሜኑ ገዥ የነበሩት የደጃዝማች ውቤ ልጅ ናቸው፡፡
ይሁን እንጅ የአለማየሁ እናት ሊሞቱ አቅራቢያ ካፒቴን እስፒዲን አስጠርተውና እጁን ይዘው፤
“...ልጄ አባት የለውም፡፡
እኔም እናቱ ልሞት ነው፡፡
ዘመድ ስለሌለው አንተ ዘመድ ሁነው፡፡
አባት ስለሌለው አንተ አባት ሁነው፡፡
ያልኩህን ሁሉ እንደምታደርግ ቃል ግባልኝ፡፡ ሲሉኝ፣ 'የጠየቁኝን ሁሉ እፈጽማለሁ ብየ ማልኩላቸው'፡፡”
በማለት አስፒዲ የተናገረውን ጽፏል፡፡
ካፒቴን እስፒዲ የልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ሞግዚት እንዲሆን በእንግሊዝ ጦር መሪ በጀነራል ናፒየር የተመደበ የህንድ የጦር መኮንን ነበር፡፡
አፄ ቴዎድሮስ፤ እጃቸውን ለእንግሊዝ ወታደሮች ላለመስጠት ብለው ሽጉጣቸውን ጠጥተው በራሳቸው ላይ እርምጃ ከወሰዱ በኋላ የእንግሊዝ ወታደሮች የንጉሠ ነገሥቱን የአፄ ቴዎድሮስን ንብረቶች ዘርፈው ከመቅደላ ሲወስዱ ልዑል ዓለማየሁንም ከዘረፏቸው ንብረቶች ጋር አብረው ወደ እንግሊዝ አገር ወሰዱት፡፡
ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ከንግሥት ቪክቶሪያ ጋር
ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ
ከንግሥት ቪክቶሪያ ጋር

Photo Link
ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ በ 7 ዓመት ዕድሜው ከአዲስ አሳዳጊው ከካፒቴን እስፒዲ ጋር ወደ እንግሊዝ ሀገር ለመጓዝ ሰኔ 4 ቀን 1860 ዓ.ም. በመርከብ ተሳፈረ፡፡
ዓለማየሁ ከአንድ ወር የመርከብ ጉዞ በኋላ ሐምሌ 5 ቀን 1860 ዓ.ም. እንግሊዝ አገር ከገባ በኋላ ካፒቴን ሰፒዲ ወደቤቱ ወሰደው፡፡
የእንግሊዝ ንግሥት ቪክቶሪያ ዓለማየሁን በቅርብ ይቆጣጠሩት ስለነበር እስፒዲም ንግሥቲቱ ጋ በመውሰድ ከንግሥቲቱ ጋር እንዲገናኙ አደረገ፡፡
ንግሥቲቱም ለልዑል ዓለማየሁ አስፈላጋው ጥንቃቄ ሁሉ እንዲደረግለት አዘዙ፡፡
አስፒዲም ዓለማየሁን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማስተማር ጀመረ፡፡
ንግሥት ቪክቶሪያ ዓለማየሁን እያገኙ ባነጋገሩበት ጊዜ ስለዓለማየሁ በጻፉት ማስታወሻ፤
“...ጨዋና ውብ ልጅ ነው፡፡ ኬክ መብላት ይወዳል፡፡
የሰጠሁትን ኬክ ሁሉ ደስ እያለው በፈገግታ በላ፡፡
ዛሬ ከዓለማየሁ ጋር አብረን ምሳ በላን፡፡
ዓለማየሁ እኔ ጋ ሲመጣ የሀገሩን የሀበሻ ልብስ ለብሶና ከሀገሩ በመጡለት ጌጣጌጦች አጊጦ ነው፡፡
ምሳ በልተን ከጨረስን በኋላ ለዚህ ለተከበረ ትንሽ ልጅ በእጁ ላይ ሰዓት አሰርኩለት፡፡
በወገቡም ላይ የወርቅ ሰንሰለት አስታጠኩት::”
በማለት ገልፀውታል፡፡
ንግሥት ቪክቶሪያ፣ አብዛኛውን ጊዜ፤“ለዚህ እናት ለሌለው ህፃን እናቱ እኔ ነኝ፡፡” ይሉ ነበር፡፡
አለማየሁ በእንግሊዝ ሀገር መኖር ከጀመረ አንድ ዓመት ሞላው፡፡
Prince Alemayehu with Capitain Spedy
ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ
ከሞግዚቱ ከካፒቴን ሰፒዲ ጋር

Photo credit to: fanos.masho
ሰፒዲ በሥራው ሹመት አግኝቶ ወደሀገሩ ተመድቦ እንዲሄድ ሲወሰን ዓለማየሁ ስፒዲ አንገት ላይ ተጠምጥሞ እያለቀሰ፤
“...አባ፣ አባዬ፣ አባቴ አንተ ነህ፣ ያለአንተ መኖር አልችልም፤ ፤ከአንተ አትለየኝ፣ ያለበለዚያ እሞትብሀለሁ... ::” በማለት ተማጸነው፡፡
እሰፒዲ ለሁለት ዓመታት ዓለማየሁን እንዲያሳድግ ተፈቅዶለት ስለነበር የ 8 ዓመቱን ዓለማየሁንና ሚስቱን ይዞ ወደ ተሾመበት ወደ ሕንድ ሀገር ተጓዘ፡፡
እሰፒዲ በሁለት ዓመት የሕንድ ሀገር ቆይታው ስለ ዓለማየሁ በጻፈው ሪፖርት፤
“...በትምህርቱ ጎብዟል፡፡
ከትምህርቱ ሌላ የውጭ ስፖርት ይወዳል፡፡
በተለይ ፈረስ ግልቢያ ይወዳል፡፡
የአዕምሮ ህመም አንድ አንዴ ይነሳበታል፡፡
ለጠየቀኝ ጥያቄ ሁሉ እውነቱን እነግረዋለሁ፡፡”
በማለት ተናግሯል፡፡
Alemayehu Tewodros


Photo courtesy of:   Royal Collection Trust
ዓለማየሁ ቴዎድሮስ በትምህርቱ ባይገፋም ከሁለት ዓመት የሕንድ ሀገር ቆይታው በኋላ ወደ እንግሊዝ ሀገር ተመለሰ፡፡
ዓለማየሁ እንግሊዝ ሀገር እንደተመለሰ ጮሌና ስነምግባር ያለው ስለነበረ ዘመናዊ የውትድርና ትምህርት እንዲከታተል ተወስኖ 18 ዓመት እንደሞላው፤ በ1733 ዓ.ም. በተቋቋመውና ዓለም ዓቀፍ እውቅና ባለው በሮያል ሚሊተሪ አከደሚ በሳንድኸርስት ገብቶ እንዲሰለጥን ተደረገ፡፡

የዓለማየሁን ጤንነት እንዲከታተሉ የተመደቡት ሰዎች፤ ዓለማየሁ በትውልድ ሀገሩ ላይ ማተኮርና ማሰብ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ሀገሩም ሁለት አክስቶችና አንድ ወንድም እንዳሉት ይናገር ነበር፡፡
Prince Alemayehu Monument at Windsor Castle
በዊንድሶር የነገሥታት መካነ መቃብር
በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን
የሚገኘው የልዑል ዓለማየሁ የመቃብር ሐውልት

Photo courtesy of:   mfaethiopia
ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ በጥቅምት ወር 1871 ዓ.ም. 17 ዓመት ከ7 ወር እንደሞላው በሳንባ ምች ሕመም በመጠቃቱ ምክንያት ከፍተኛ የደረት ህመምና የመተንፈስ ችግር ስላጋጠመው በጠና ታመመ፡፡
ህክምና ቢደረግለትም ሕመሙ ስለጸናበት ምግብና መድሐኒት መውሰድ አልቻለም፡፡

የእንግሊዝ ንግሥት ቪክቶሪያ መታመሙን ሰምተው የማጽናኛ ደብዳቤ ቢጽፉለትም በህመሙ ምክንያት የተላከለትን ደብዳቤ ለማንበብ ጀምሮ ሳይጨርሰው ቀረ፡፡
ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ያስታማሚዎቹን ሁለት እጆች እንደያዘ ሕዳር 5 ቀን 1872 ዓ.ም. ከጧቱ 10 ሰዓት ከ 10 ደቂቃ ሲሆን
በተወለደ በ19 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡

አስከሬኑም በንግሥት ቪክቶሪያ ትዕዛዝ ዊንድሶር በሚገኘው የነገሥታት መካነ መቃብር በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡
በመቃብሩም ላይም፤
"የአበሻው ልዑል ዓለማየሁ
ኤፕሪል 13 1861 ተወለደ::
ኖቬምበር 14 1879 አረፈ::“
የሚል አረፍተ ነገር በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተጻፈበት፡፡
ንግሥት ቪክቶሪያ ግን ከጽሁፉ በታች፤
ዕንግዳ ሆኜ መጣሁ:: ተቀበላችሁኝም::
የሚል የወንጌል ቃል እንዲጨመርበት አዘው እንዲጻፍ ተደርጓል፡፡

ወደ ...( ቤተ ድረ ገጽ ይመለሱ )



ምንጭ፤
  1. "አጤ ቴዎድሮስ" ደራሲ፡- ጳውሎስ ኞኞ ግንቦት ወር 1985 ዓ.ም.
  2. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ