Content-Language: am ራስ አበበ አረጋይ
header image

ራስ አበበ አረጋይ (አባ ገስጥ)



የራስ አበበ አረጋይ (አባ ገስጥ) የሕይወትና የአርበኝነት ዘመን ታሪክ

በእያንዳንዱ አርዕስት ሥር የሚገኘውን የድምጽ ማጫወቻ በመጠቀም
ትረካውን ማዳመጥ ይችላሉ

ክፍል አንድ

ትውልድና የቤተሰብ ሕይወት

ክፍል ሁለት

የቅድመ አርበኝነት የሕይዎት ዘመን

ክፍል ሦስት

በአርበኝነት ዘመን የገጠማቸው ውጣ ውረድ

ክፍል አራት

የኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር መመስረት

ክፍል አምስት

ፋሽስት ኢጣሊያ ለራስ አበበ ስላቀረበው የዕርቅ ድርድር

ክፍል ስድሰት

ንጉሠ ነገሥቱ ከስደት ሲመለሱ የራስ አበበ አቀባበል

ክፍል ሰባት

የራስ አበበ የድህረ አርበኝነት የሕይዎት ዘመን

የመጨረሻ ክፍል

የመንግሥት ግልበጣ ሙከራና የራስ አበበ ህልፈተ ሕይወት


Ras Abebe Aregay
ራስ አበበ አረጋይ በአርበኝነት ዘመን
አበበ አረጋይ ነሐሴ ፲፬ ቀን ፲፰፻፺፮ ዓ.ም. (ነሐሴ 14 1896) በሸዋ ጠቅላይ ግዛት ጅሩ ወረዳ ውስጥ ተወለዱ፡፡
አባታቸው አፈ ንጉሥ አረጋይ በቸሬ ይባላሉ፡፡
እናታቸው ወይዘሮ አስካለ ማሪያም ጎበና ይባላሉ፡፡
ወይዘሮ አስካለ ማሪያም ጎበና፤ የራስ ጎበና ዳጨ ልጅ ናቸው፡፡
የአበበ አረጋይ አያት ራስ ጎበና፤ የዳግማዊ ምኒልክ የጦር አዝማች ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ በጊዜው የነገድና የጎሳ ብጥብጥ በነበረበት ወቅት ሁኔታውን ለማርገብና ሕዝቡን አንድ ለማድረግ ጥረት ያደረጉ ዝነኛ የጦር ሰው ናቸው፡፡
አበበ አረጋይ ወይዘሮ አድማሰወርቅ ሥዩምን በህግ አግብተው በ ፲፱፻፲፰ ዓ.ም (በ 1918) የተወለደው የበኩር ልጃቸው የሆነውን ዳንኤል አበበን እና በማስከተለም በ ፲፱፻፳ ዓ.ም. (በ 1920) የተወለደችውን ሶስና አበበን አፍርተዋል፡፡
የህግ ባለቤታቸው ወይዘሮ አድማሰወርቅ በሞት ሲለዩ፤ በ ፲፱፻፳፩ ዓ.ም. (በ 1921) ወንድወሰን አበበን የወለዱላቸውን ወይዘሮ ቆንጅት አብነትን አገቡ፡፡
አበበ አረጋይ፤ በፈረስ ስማቸው አባገስጥ ተብለው ይጠራሉ፡፡
በ1928 ዓ.ም. የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጣው ሠራዊት በሰሜንና በደቡብ ግንባር ተሰልፎ ከጠላት ጋር ሲዋደቅ፤ የመናገሻ ከተማይቱን ሰላምና ፀጥታ የማስከበሩ ግዳጅ የተሰጠው ለአራዳ ዘበኞች ነበር፡፡
የአራዳ ዘበኛ ቤተ ደንብ የተቋቋመውም፤ በ ፲፱፻፲፱ ዓ.ም. (በ1919) ነው፡፡
ቀደም ሲል ከተማው ይጠበቅ የነበረው ጥርምቡሊ ተብሎ በሚጠራው የጥበቃ ሠራዊት ነበር፡፡
በኋላ ግን የአዲስ አበባ ከተማ በማዘጋጃ ቤትነት ደረጃ የራሱ አስተዳደር እንዲኖረው ሲደረግ፤
ቢተወደድ ወልደ ፃድቅ ጎሹ በ ፲፱፻፩ ዓ.ም. (በ1901) የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው ተሾሙ፡፡
አበበ አረጋይ በ ፲፱፻፳፯ ዓ.ም.(በ1927) የባላምባራስነት ማዕረግ ተሰጥቷቸው፤ ለአዲስ አበባ ለግማሹ ክፍል ለፀጥታ ጥበቃ የአራዳ ዘበኛ አለቅነት ተሹመው ወደ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ተዛወሩ፡፡
በ1928 ዓ.ም. ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ሲዘምቱ፤ አባ ገስጥ አበበ አረጋይ የአራዳ ዘበኛ ጠቅላይ አዛዥነትን ተሾሙ፡፡
በሰሜንና በደቡብ ጦር ግንባር ከጠላት ጋር ወራትን የፈጀ ፍልሚያ ከተደረገ በኋላ፤ ንጉሠ ነገሥቱ ከማይጨው ጦር ግንባር በመመለስ በተሰበረ መንፈስ ሚያዝያ ፳፪ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. (ሚያዝያ 22 1928) ሐሙስ ከጧቱ ሦስት ሰዓት አዲስ አበባ ገቡ፡፡
የኢትዮጵያ ሠራዊት ጠላት ባዘነበበት የሙስታርድ ጋስ ቦምብ የተነሳና በሠራዊቱ ዘንድ በታየው በአንዳንድ የቅንጅት ጉድለት ምክንያት የጠላት ሠራዊት ድል ስለቀናው ለከተማው ነዋሪ ሐዘኑንና ድንጋጤውን ይበልጥ አከበደበት፡፡
የጠላት ጦርም ከሰሜን እና ከደቡብ ጦር ግንባር ወደ አዲስ አበባ መገሥገሥ ጀመረ፡፡
ከዚህ በኋላ መወሰድ ስለሚገባው እርምጃ ለመምከር ሚያዝያ ፳፫ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. (ሚያዝያ 23 ቀን 1928) ልዑላን መሳፍንቶች፣ መኳንንቶች፣ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና ታላላቅ የአርበኞች የጦር መሪዎች፣ ተሰብስበው ንጉሠ ነገሥቱ በተገኙበት በታላቁ ቤተ መንግሥት ከፍተኛ ጉባዔ ተደረገ፡፡
ጉባዔው ባደረገውም ሰፊ ክርክር፤ አንደኛው የጉባኤው ሀሳብ፤
“ቤተ መንግሥቱ ወደ ጐሬ ተዛውሮ በዚያ በኩል ጠላትን መከላከል፡፡” የሚል ሲሆን፤

ሁለተኛው ሀሳብ ደግሞ፤
“ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ዓለም መንግሥታት ማሕበር ሄደው እንዲያመለክቱ ሆኖ፤ እስከዚያው ድረስ ግን ጦሩ በየሥፍራው በአርበኝነት ተሠማርቶ አገሩን እየተከላከለ እንዲጠብቅ፡፡”
በሚሉ በሁለት የተለያዩ ሀሳቦች በመከፈሉ ምክንያት ጉባዔው ለሚቀጥለው ቀን ተላለፈ፡፡
በሚቀጥለው ቀን በተደረገው ጉባዔ፤ ከሁለቱ የተለያዩ ሀሳቦች መካከል፤
“ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ዓለም መንግሥታት ማሕበር ሄደው እንዲያመለክቱ ሆኖ፤ እንስከዚያው ድረስ ግን ጦሩ በየሥፍራው በአርበኝነት ተሠማርቶ አገሩን እየተከላከለ እንዲጠብቅ” የሚለው ሀሳብ በአብላጫ ድምፅ ተቀባይነት በማግኘቱ ንጉሠ ነገሥቱ ሚያዝያ ፳፬ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. (ሚያዝያ 24 ቀን 1928) ወደ አውሮፓ ለመሄድ በባቡር ወደ ጅቡቲ ተጓዙ፡፡
የንጉሠ ነገሥቱ ወደ ውጭ ሀገር መሄድ እንደተሰማ ቤተ መንግሥቱ ተዘረፈ፡፡
ዝርፊያውም በሌሎች የከተማይቱ አካባቢዎች ሳይቀር ተፋፍሞ ቀጠለ፡፡
ይህን ዝርፊያ ለማስቆም የአራዳ ዘበኛ ጠቅላይ አዛዥ ሆነው ለተሾሙት ለባላምባራስ አበበ አረጋይ ከባድ ፈተና ሆነባቸው፡፡
በተለይ የዘራፊዎቹ ከቀን ወደ ቀን መበራከት፤ ለአራዳ ዘበኞቹ ከአቅም በላይ ሆነባቸው፡፡
በወቅቱ የአዲስ አበባ ከንቲባ የነበሩት ብላታ ታከለ ወልደ ሐዋርያት የከተማውን ሹማምንት በመሰብሰብ ከመከሩ በኋላ ዝርፊያውን ለማስቆም መሞከር የከተማውን ሠላማዊ ሕዝብ ማስጨረስ እንደሆነ ከተወሳ በኋላ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ድል መሆንን አምኖ በመቀበል ከተማይቱን ለጠላት ማስረከቡ ህሊናን ለዘላለም የሚያቆስል ውርደት እንደሚሆን ታወቀ፡፡
ስለሆነም አዲስ አበባን ለቆ በመውጣት በዱር በገደሉ በመሰማራት የፋኖ ውጊያ እንዲደረግ ተወሰነ፡፡
አበበ አረጋይም ውሳኔውን ለበታች ሹማምንቶቻቸው ካስታወቁ በኋላ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ተመለሱ፡፡
Italian troops entering Addis Ababa
የኢጣሊያ ወታደሮች ሚያዝያ 28 ቀን
1928 ዓ.ም. አዲስ አበባ ሲገቡ

image link
ከዚህ በኋላም አበበ አረጋይ የወሰኑት ውሳኔ፤ የጠላት ጦር የጣርማ በርን አልፎ አዲስ አበባን መያዙ ስለሆነ የኢጣሊያ ጦር በእግሩ ሊረግጠው ቀርቶ በአይሮፕላኑ እንኳን ጥቃት ለማድረስ ወደማይችልበት ወደ ሰሜን ሸዋ ገደላ ገደል መሽጎ በአዲስ አበባ የተከማቸውን የጠላት ጦር ሠላም መንሳት ይኖርብኛል በማለት ወዲያውኑ፤ እናታቸውን፣ ባለቤታቸውን፣ ልጆቻቸውን ማለትም፤ 6 ወንዶችን እና 3 ሴቶችን አስከትለው ሚያዝያ ፳፰ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. (ሚያዝያ 28 ቀን 1928) ሰሜን ሸዋ ወደሚገኘው ግምቢቹ ወደተባለው ስፍራ ተጉዘው ግንቦት ፯ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. (ግንቦት 7 ቀን 1928) በቦታው ደረሱ፡፡
የጠላት ጦርም ሁኔታው ስለተመቻቸለት ንጉሠ ነገሥቱ ወደ አውሮፓ በተጓዙ በአራተኛው ቀን ሚያዝያ ፳፰ ቀን ዓ.ም.፲፱፻፳፰ ዓ.ም.(ሚያዝያ 28 ቀን 1928) አዲስ አበባ ገብቶ ከተማይቱን ተቆጣጠረ፡፡
Military Head Quarter of Ras Abebe Aregay
በአርበኝነት ዘመን በሰሜን ሸዋ የነበረው
የራስ አበበ አረጋይ የማዘዣ ጣቢያ
አበበ አረጋይ ግምቢቹ እንደደረሱ ነዋሪውን በመሰብሰብ የተፈጠረውን ሁኔታ ሁሉ ካስረዱ በኋላ በሀገራችን ላይ ጠላት ያደረሰውን ወረራ ለመመከት ያለው አማራጭ በአርበኝነት ተሰማርቶ ጠላትን መግቢያ መውጫ ማሳጣት እንደሚገባ ለሕዝቡ ከገለጹለት በኋላ ሁሉም በየፊናው ጠላትን ለመዋጋት በፈቃደኝነት ለመሰማራት ዝግጅቱን ገለፀ፡፡
በየቦታው ተበታትኖ የነበረው የክብር ዘበኛ ጦርና የአራዳ ዘበኞችም ተላልከው በመሰባሰብ ለአገራቸው መስዋዕት ለመሆን ከአባ ገስጥ አበበ አረጋይ ጋር ተቀላቀሉ፡፡
አባ ገስጥ አበበ አረጋይም ከተሰባሰቡት አርበኞች ውስጥ ልምድና ችሎታ ያላቸውን መልምለው በአለቃና ጭፍራ መልክ አደራጅተው የአርበኝነት ሥራቸውን ተያያዙት፡፡
ጠላት የባላምባራስ አበበን የአርበኝነት እንቅስቀሴ በመገደቡ ከ40 የማይበልጡ ተከታዮቻቸውን ብቻ ይዘው በተራራማው የመንዝ ምድር ብቻ ተወስነው ነበር፡፡
በኋላም አበበ አረጋይ ከመድረሳቸው አስቀድሞ ልጅ ኃይለ ማሪያም ማሞ ቀደም ብለው ሚያዝያ 13 ቀን 1929 ዓ.ም. ከጠላት ጋር ባደረጉት ጦርነት ጠላትን ድል አድርገው በሰሜን ሸዋ የሚገኘውን ጅሩና ሞረት የተባለውን ስፍራ ካስለቀቁ በኋላ ባላምባራስ አበበ አረጋይና ፊታውራሪ ዘውዱ አባኮራን ከጠላት ነፃ የሆነውን ስፍራ መረከብ ቻሉ፡፡
አባ ገስጥ አበበ አረጋይ ከጠላት ጋር ካደረጓቸው ጦርነቶች መካከል በአንዱ የጠላትን አይሮፕላን በእሩምታ ተኩስ ተመቶ እንዲወድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
አበበ አረጋይ ለፈፀሙት ለዚህ የጀብዱ ሥራቸው፤ በጀግኖች አርበኞቻቸው የሚከተለው ግጥም ተገጥሞላቸዋል፡፡
ጠላት በአይሮፕላን በአየር ሲንደረደር፣
የአርበኞቹ መሪ ደባለቀው ካፈር፡፡
አንተ አበበ አረጋይ እረስ፤ ገስጥ፣
የፋሽስትን አንጎል የሚበጠብጥ፡፡
አበበ አረጋይ በአንድ ስፍራ ብቻ ለረጅም ጊዜ ተወስነው ጠላትን የሚዋጉ ሳይሆን የተለያዩ ሥፍራዎችን በመቀያየር አመች ሥፍራ እየመረጡ በጠላት ላይ አደጋ ለመጣልና የጠላት ኃይል ሲበረታ ድግሞ ከቦታው ለመሰወር የሚያስችል እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር፡፡
በዚህም የተነሳ አባ ገስጥ አበበ አረጋይ በሰኔ ወር 1929 ዓ.ም. ወደ ግንደ ብረት ለመሄድ ከመረሐቤቴ ተነሱ፡፡
የሙገርን ወንዝ ተሻግረው ከወንዝ ማዶ እንደደረሱ፤ አብረዋቸው ይንከራተቱ የነበሩት ባለቤታቸውን ወይዘሮ ቆንጅት አብነት፤ በ10 ወሩ በአንቀልባ ታዝሎ በጅሩ በረሃ ሲንከራተት ከአዲስ አበባ በወጡ በ13ኛው ቀን ግንቦት 9 ቀን 1928 ዓ.ም. በድንገት ሕይወቱ ባለፈው ሕፃን ምትክ፤ ሰኔ 17 ቀን 1929 ዓ.ም. ከምሽቱ 12 ሰዓት ሲሆን ወይዘሮ ቆንጅት በግንደ ብረት በረሃ ወንድ ልጅ ተገላገሉ፡፡
ይህም የተወለደው ህፃን ለአባ ገስጥ አበበ አረጋይ አራተኛ ልጃቸው መሆኑ ነው፡፡
አበበ አረጋይ የአርበኝነት ተግባራቸውን ለመፈፀም ወደ ሌላ ስፍራ መሄድ ስለነበረባቸው ቤተሰባቸውን አንድ ቦታ ደብቀውና አስፈላጊውን ማስጠንቀቂያ ሰጥተው እርሳቸው አርበኞቻቸውን ይዘው ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡
Ras Abebe Aregay with his patriots
ራስ አበበ ለአርበኞቻቸው
የውጊያ ስምሪት ትዕዛዝ ሲሰጡ
ቤተሰቡም በረሀብ ተጎድቶ ነበርና ረሃቡ ሲጠናበት እህል ገዝቶ የሚያመጣ አንድ ሰው ልከው ኖሮ የተላከው ስው በድንገት በባንዳ እይታ ውስጥ ገባ፡፡ ከዚያም ተይዞ የኢጣሊያ አለቆች ዘንድ ቀርቦ በግርፋት ሲመረመር እውነቱን ስለተናገረ ጦር ታዞ ሴቶቹ ወደተደበቁበት ቦታ ወሰዳቸው፡፡
የጠላት ጦር እየተመራ እስፍራው እንደደረሰ ቤተሰቡን የሚጠብቁ ሁለት ወንዶች ከጠላት ጋር ተታኩሰው ሲወድቁ ያዩት ወይዘሮ ቆንጅት ህፃኑን እንደታቀፉ ተማረኩ፡፡
ሦስት ቀን ሙሉ ምንም ምግብ ሳይቀምሱ የቆዩት ወይዘሮ ቆንጅት፤ የኢጣሊያ ወታደር ደረቅ ዳቦ ቢጥልላቸውም እርሳቸው ግን በእልህ ዳቦውን መልሰው እንደወረወሩለት ተነግሯል፡፡
አበበ አረጋይ የቤተሰባቸውን ደህንነት ለማወቅ ሰው ቢልኩም በስፍራው እንደሌሉ ሲሰሙ ከፍተኛ ሐዘን ተሰማቸው፡፡
በጠላት እጅ የወደቁትም ወይዘሮ ቆንጅት ከነቤተሰባቸው ጣሊያን ሰራሽ በሆነውና ኤንትሬ በተሰኘው የእህል ማጓጓዣ መኪና ላይ ተጭነው ወደ አዲስ አበባ እና ከዚያም ወደ ደብረ ብርሐን ተወሰዱ፡፡
በኋላም ደጃዝማች ወዳጀ የተባሉ ሰው እንዲጠብቋቸው ተድርጎ አምስት ቀን ተቀመጡ፡፡
እንደገናም ይፈለጋሉ ተብለው ወደ አዲሰ አበባ ተወስደው በበጅሮንድ ለጥይበሉ ገብሬ ቤት በጨለማ ክፍል ውስጥ አምስት ቀናት፤ ቀጥሎም በደጃዝማች አባውቃው ቤት ለአምስት ወራት ያህል ታሰሩ፡፡
በመጨረሻም ወደ ሸኖ ተልከው በእስራት እንዲቆዩ ተደረገ፡፡

Daniel Abebe Aregay
የ13 ዓመቱ ዳንኤል አበበ
አረጋይ የተኩስ ልምምድ ሲያደርግ

ከፎቶው በስተቀኝ የሚገኙት ዶክተር
ዓለመወርቅ በየነ፤ በመሐል የ13
ዓመቱ ዳንኤል አበበ አረጋይ
ሲሆኑ በግራ ስሙ ካልታወቀ
አርበኛ ጋር በ1933 ዓ.ም.
የተነሱት ፎቶግራፍ




ምስግና ለ፤ ሲሳይት መኮንን
በፎቶው ላይ ከሶስቱ ሰዎች በስተቀኝ የሚገኙት ዶክተር ዓለመወርቅ በየነ በእንግሊዝ ሀገር የእንስሳት ሕክምና ትምህርት ተምረው ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ የጥቁር አንበሳ የአርበኞች ንቅናቄ ሊቀ መንበር ነበሩ፡፡
(ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ዶክተር ዓለመወርቅ በየነ፤ በዚያን ጊዜ ጥይት ቤት ይባል የነበረው እና በኋላ ወደ እስር ቤት የተቀየረው ውስጥ ታስረው ነበር፡፡ ዶክተር ዓለመወርቅ በየነ ደፋር እና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡
ታስረው በነበረበትም ወቀት በእስር ቤት የሞቱትን ይመዘግቡ ስለነበረ፤ የሞታቸውን ምክንያት፤ “ለአገራቸው ብለው የሞቱ” በማለት በጽሑፍ ይገልጹ ስለነበረ ይህን ድርጊታቸውን ፋሽስቶች አይተው ለምን እንደዛ ብለው እንደሚመዘግቡ ሲጠይቋቸው፤ “እስረኞቹ የሞቱበትን ምክንያት ስለማላውቅ፤ ትክክለኛው ነው ብየ በአሰብኩት መልክ መዝግቢያለሁ፡፡” በማለት መልስ ከሰጧቸው በኋላ ኖክራ ወደተባለው የዳህላክ ደሴት ተወስደው ለ5 ዓመታት ታስረዋል፡፡)
ስለ ዶ/ር ዓለመወርቅ የእንግሊዝኛውን ጽሁፍ ለማንበብ፤➝( ሊንክ )

አበበ አረጋይ የበኩር ልጃቸው የሆነውን ዳንኤል አበበን ገና በወጣትነቱ ውጊያ እንዲማርና እንዲሰለጥን በማለት በውጊያ ያሳትፉት እንደነበር ታውቋል፡፡
አንድ ቀን በአጋጣሚ አባቱ አጠገቡ ባልነበሩበት ወቅት ወጣቱ ዳንኤል በተካፈለበት ውጊያ እግሩ ላይ ቆስሎ በጠላት ከተማረከ በኋላ ወደ ደብረ ብርሃን ተወስዶ እስር ቤት ተጣለ፡፡
ወጣቱ አርበኛ ዳንኤል አበበ ምንም ሕክምና እንዳያገኝ ተከልክሎ ስለነበር ቁስሉ ቀስ በቀስ አመርቅዞ ነበር፡፡
የአበበ አረጋይ የቤተሰብ ፈተና በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ እንደገና በጦር ሜዳ ቆስለው የነበሩት እናታቸው ወይዘሮ አስካለ ጎበና በሌላ ውጊያ ላይ በጠላት ከተማረኩ በኋላ ያለምንም እርህራሄ እያዳፉ ወደ ጦር ሰፈራቸው ወሰዷቸው፡፡
ይህ ሁሉ ተደራራቢ ፈተና ቢገጥማቸውም አበበ አረጋይ ከአርበኝነት ተግባራቸው ዝንፍ አላደረጋቸውም፡፡
ጣሊያኖች የግንደ ብረት አገረ ገዥ ያደረጉትና መሣሪያ አምጡ እያለ ሕዝብ የሚያምሰውን የባንዳ ሹመኛ ለመውጋት አበበ አረጋይ ወደ ግንደ ብረት ዘመቱ፡፡
የግንደ ብረት አገረ ገዥ አበበ አረጋይን ለመውጋት 400 ጦር አሰልፎ እርሳቸው ወዳሉበት ሥፍራ ለሁለት ሰዓት ተጉዞ ሲጠባበቅ በአበበ አረጋይ ጦር ሰኔ 21 ቀን 1929 ዓ.ም. ድል ተመታ፡፡
ሐምሌ 18 ቀን 1929 ዓ.ም. ባላምባራስ አበበ ከብላታ ተክሌ ወልደ ሐዋርያት እና ከሻለቃ መስፍን ስለሽ ጋር በአንድነት በመሆን አዲስ ዓለም የሰፈረውን የጠላት ጦር ለማጥቃት አቀዱ፡፡
ሆኖም ከታሰበው ዒላማቸው በስተምሥራቅ በኩል የሚገኘው የጠላት ጦር፤ በአይሮፕላን የቦምብ ጥቃት ጭምር በመታገዙ ያቀዱት የውጊያ ስልት ግቡን ሳይመታ ስለቀረ ስፍራውን ለቀው ወደ መንዝ ለመመለስ ተገደዋል፡፡
ባላምባራስ አበበ አረጋይ በውጊያ ከስድስት ጊዜ በላይ በጥይት ተመተው ቢቆስሉም በሀገር ባህል መድኃኒት ታክመው ስለሚድኑ የአርበኝነት ተግባራቸውን አንድም ቀን አቋርጠው አያውቁም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቡልጋ መሪ የነበሩት ደጃዝማች ፍቅረ ማርያም ናደው በውጊያ ላይ መገደል የቡልጋ አርበኞች ያለመሪ በመቅረታቸው ምክንያት የልጅ እያሱ ልጅ የሆነውን በድበቅ ይኖር የነበረውን እንግዳሸት እያሱ የተባለውን የ15 ዓመት ልጅ ለማንገሥ በአርበኞች መካከል ተመክሮበት ስምምነት ስላገኘ ወጣቱ እንግዳሸት መላከ ፀሓይ ተብሎ በአርበኞች ፈቃድ ነገሠ፡፡
ወጣቱ ንጉሥ የቤተ መንግሥት አስተዳደግና ሥርዓት ስላልተማረ በእንደራሴ እንዲተዳደር ተወስኖ የእንደራሴነቱንም ተግባር አበበ አረጋይ እንዲረከቡ በአርበኞች ከተመረጡ በኋላ የራስነት ማዕረግ ተሰጥቷቸው የጦር አበጋዝ (የጦር አዛዥ) እንዲሆኑ ከተወሰነ በኋላ ራስ አበበ አረጋይ ተብለው መጠራት ጀመሩ፡፡
Ras Abebe Aregay and his troops
ራስ አበበ ከአርበኞቻቸው ጋር
ራስ አበበ አረጋይ ወጣቱ ንጉሥ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለአንድ ዓመት ያህል ጥረት ሲያደርጉና በአርበኞች ቁጥጥር ሥር የነበረውንም አገር ሲያስተዳደሩና የዳኝነትም ተግባር ሲያከናውኑ ከቆዩ በኋላ ወጣቱ ንጉሥ መስከረም 27 ቀን 1931 ዓ.ም. በሞት ተለየ፡፡
ለማያዛልቅ ጉዳይ በሕይወት ባሉና ለአቤቱታ ውጭ ሀገር በሄዱት ንጉሥ ላይ ደርበው ሌላ ንጉሥ ያነገሡት አርበኞች እስከመጨረሻው ሥጋት ሊፈጥርባቸው እንደሚችል ተገንዝበውታል፡፡
ከዚያ በኋላ ራስ አበበ አረጋይ ጋራና ሸንተረር ወደበዛበት ወደ መንዝ ምድር በማቅናት ከጅሩ ከመጣው የጠላት ክፍለ ጦር ጋር ውጊያ ገጠሙ፡፡
የጠላት ኃይል እጅግ ብርቱ ስለነበር በመድፍ በመደብደብ ከፍተኛ ዊጊያ ቢያካሂድም ልበ ሙሉና ቆራጥ የነበረው የአርበኞች ውጊያ ጠላትን ብትንትኑን አወጣው፡፡
የሚያነሳው አጥቶ በየቦታው የወደቀው የጠላት የእሬሳ ክምርም ቁጥሩ እጅግ ብዙ ነበር፡፡
ይህም ድል ለራስ አበበ አረጋይ አርበኞች ከፍተኛ ዝናን አስገኘ፡፡
ራስ አበበ አረጋይ በጦር አመራር ብቻ ሳይሆን አልሞ ተኳሽ ጀግና የጦር መሪ ስለነበሩ በውጊያ መሓል በወታደራዊ መነፅር አሻግሮ ይመለከት የነበረውን የኢጣሊያ የጦር አዛዥ አልመው በመተኮስ ድባቅ መተው የገደሉ እውቅ ተኳሽ ናቸው፡፡
ራስ አበበ የሚሸሸውንና የተደበቀውን የጠላት ጦር እየተከታተሉ የታጠቁትን ቦንብ እየፈቱ በመወርወር ሰባትና ሰምንቱን የጠላት ጦር በአንድ ቦንብ ፍንዳታ ሁሉንም የሚረፈርፉ ቆራጥ ጀግና ናቸው፡፡
በጠላት መሐል የራስ አበበ አረጋይ ስም ሲነሣ ሁሉም ይርበደበዳል፡፡
አንድ ቀን ጧት ራስ አበበ አረጋይ ፀሎት ላይ ሳሉ አንድ ሰው ገብቶ፤ “ጠላት አጠገባችን ደርሷል” እያለ ደጋግሞ ቢነግራቸውም ፀሎታቸውን ማቋረጥ ስላልፈለጉ ዝም ብለውት ከቆዩ በኋላ፤ ፀሎታቸውን አሳርገው ሲጨርሱ፤ “ታዲያ ይምጣ!...ሞተን አንጠብቀው፡፡” ማለታቸው ተነግሯል፡፡
የራስ አበበ አረጋይ የታሰሩት ባለቤታቸውና ቤተሰቦቻቸው ተፈትው ከመንከራተትና ከስቃይ ይድኑ ዘንድ እርሳቸው በእርቅ ለኢጣሊያ እንዲገቡላቸው በተደጋጋሚ ቢያባብሏቸውም ቤተሰባዊ ፍቅርን ከሀገራቸው ፍቅር እንደማያስበልጡ በቁርጠኝነት ነግረዋቸዋል፡፡
Ethiopian Patriots Association
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች መሥራች አባላት
    ከግራ ወደ ቀኝ፤
  1. ደጃዝማች ተስፋዬ ዕንቁ ሥላሴ፣
  2. አቶ ደሳለኝ ተክለ ወልድ፣
  3. ደጃዝማች ፀሐዩ ዕንቁ ሥላሴ፣
  4. አቶ ልሣኑ ሀብተ ወልድ እና
  5. ደጃዝማች አሉላ በቀለ
በሸዋ ክፍለ ሀገር፤ በመንዝ የአርበኞች ማህበር እንዲቋቋም በጥቂት አርበኞች ሀሳብ ቀርቦ በጥቅምት ወር 1931 ዓ.ም. በራስ አበበ አረጋይ ሰብሳቢነት ታላቅ የአርበኞች ስብሰባ ከተካሄደ በኋላ ማህበሩ በጽሁፍ ፀድቆ ተቋቋመ፡፡
በዚህም መሰረት ጥቅምት 23 ቀን 1931 ዓ.ም. ማህበሩ የ“ጥንታዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች ማህበር” በሚል ስያሜ ተቋቋመ፡፡
የማህበሩንም አመራሮች ለመምረጥ ታህሳስ 29 ቀን 1931 ዓ.ም. በተጉለት ስብሰባ ተደርጎ የማህበሩ መሪዎች ተመረጡ፡፡

በዚህም መሠረት፤
  1. ራስ አበበ አረጋይ የክብር ፕሬዚደንት፤
  2. ባሻ ኪሮስ ወልደ መስቀል (በኋላ ደጃዝማች) ሥራ አስኪያጅ፣
  3. አቶ ልሳኑ ሐብተ ወልድ (በኋላ ብላታ) ዋና ፀሐፊ፣
  4. አቶ ደሳለኝ ተክለ ወልድ (በኋላ ፊታውራሪ) ገንዘብ ያዥ፣
  5. አቶ ደምሴ ወልደ አማኑኤል (በኋላ ደጃዝማች) አባል፣
  6. አቶ ተስፋዬ ዕንቁ ሥላሴ (በኋላ ደጃዝማች) አባል፣
  7. አቶ ፀሐዩ ዕንቁ ሥላሴ (በኋላ ደጃዝማች) አባል፣
  8. አቶ ፈለቀ ዳኘ (በኋላ ፊታውራሪ) አባል፣
  9. አቶ ጽጌ ወልደ ማሪያም (በኋላ መቶ አለቃ) አባል፣
  10. አቶ ወልደ ዮሐንስ የምሩ (በኋላ ደጃዝማች) አባል፣
ሆነው ተመረጡ፡፡

the Ethiopian Flag during the Second Italo-Ethiopian War
በአርበኝነቱ ዘመን ክብር ዘበኞች
ወደ ማይጨው ጦር ግንባር
ሲዘምቱ ይዘውት የዘመቱት
ትልቁ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ
ክብር ዘበኞች ወደ ማይጨው ጦር ግንባር ሲዘምቱ ይዘውት የዘመቱት ትልቁ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ በአርበኝነቱ ዘመን በሰሜን ሸዋ በአርበኞች እጅ ስለነበረ፤ የንጉሠ ነገሥቱ የዘውድ በዓል በሚከበርበት ቀን በአርበኞች ማሕበር ምስረታ እለት ጥቅምት 23 ቀን ይህ በስዕሉ ላይ የሚታየው ሠንደቅ ዓላማ የውለበለብ ነበር፡፡
ቆየት ብሎም የአርበኞች ማሀበር ሰሙን አሻሽሎ የ“ጥንታዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች አርበኞች ማህበር” ተብሎ እንደገና ተሰየመ፡፡
የማህበሩ አባላትም ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሄዶ ከ 300 በላይ ደርሶ ነበር፡፡
Patriots Abebe Aregay and Tedla Mekonen
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች
አርበኞች ማህበር መስራች አባላት
በግራ ባላምባራስ አበበ አረጋይ፣
በቀኝ ባላምባራስ ተድላ መኮንን
የራስ አበበ አረጋይ አይበገሬነት ፈተና የሆነበት ፋሽስት ኢጣሊያ ለራስ አበበ አረጋይ የእርቅ ድርድር ማቅረብ ጀመረ፡፡
በዚህም መሠረት በራስ ኃይሉ ተክለ ሐይማኖት በኩል የእርቅ ድርድሩ እንዲደረግ ቀደም ብለው ሞክረው ነበር፡፡
ባቀረቡላቸውም የዕርቅ ደብዳቤ፤ ጣሊያኖች ለራስ አበበ አረጋይ ደመወዝ ቆርጦ፣ ያላቸውን ንብረት ሁሉ አስጠብቆ ሊያኖራቸው መወሰኑን ገለፁላቸው፡፡
ራስ አበበ ከጠላት ጋር በሚያደርጉት ድርድር ጠላትን ግራ በማጋባት ምንም ሊጨበጡለት አልቻሉም፡፡
በኋላም ጣሊያኖች ሌላ አካባቢ የሚገኙትን አርበኞችን በመግደላቸው ድርድሩ መቅረቱን ራስ አበበ ቢያስረዷቸውም ቅሉ እነርሱ ግን በአርበኞች ዘንድ ዝነኛ አርበኛ ወደ እነርሱ አሳምኖ ለማስገባት ጓጉተው ስለነበረ ጥረታቸውን ሳያቋርጡ ቀጠሉበት፡፡
በሌላ ጊዜ ደግሞ ጣሊያናዊው የደብረ ብርሃን አገረ ገዥ የሆነው ኮሎኔል ማሊቲ ለራስ አበበ አረጋይ የላከው የጽሁፍ መልዕክት፤

“---ባለቤትህና ልጅህ በክብር ተቀምጠዋል፡፡
ለሀገሬ እንዳትል አስካሁን የደከምከው የሚያኮራህና በቂም ነው፡፡
ምንም ትርፍ ላታገኝበት ለሸዋ ብለህ አትድከም፡፡
ይልቅስ ምክሬን ተቀብለህ ወደእኛ ብትገባ ይሻለሀል፡፡”

የሚል ነበር፡፡
ራስ አበበ አረጋይም ለተላከላቸው መልዕት ምላሹን ሲሰጡ፤
“...የባለቤቴና የልጄ በደህና መያዝ ከተቀደሰ ተግባሬ የሚያስተጓጉለኝ አይሆንም፡፡
እኔም ሆንኩ ሌሎቹ የኢትዮጰያ አርበኞች ከናንተ ጋር የምንታገለው ለውድ ሀገራችን ነፃነትና ክብር፤ እንዲሁም ለሕዝቧ ደህንነት መሆኑን እወቀው፡፡
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በኢጣሊያ ፋሽስት ኮቴ ሲረገጥ እንደማይኖር አረጋግጥልሀለሁ፡፡”
የሚል ቁርጥ ያለ መልስ ላኩለት፡፡
በደብረ ብርሃን እስር ቤት ምንም ህክምና ሳያገኝ ይሰቃይ የነበረው የራስ አበበ አረጋይ ልጅ ዳንኤል አበበም በኢጣሊያ አለቆች አማካይነት ወደ አዲስ አበባ ተወስዶ ሕክምና ከተደረገለት በኋላ ወደ ትምህረት ቤት ገብቶ እንዲማር ተደርጎ ነበር፡፡
ነገር ግን ራስ አበበ አረጋይ ለኢጣሊያ አልገባም በማለታቸው የተበሳጩት የኢጣሊያ ሹማምንቶች፤ ዳንኤልን ከትምህርት ቤቱ አቋርጠው አባቱን እንዲያሳምን ወደ አባቱ ላኩት፡፡
ዳንኤል፤ የአባቱ አቋም ምንም የማይለወጥ መሆኑን ሲረዳ እዚያው ቀርቶ ከአባቱ ጋር ሆኖ መታገሉን መረጠ፡፡
the Italian General Ciro Nasi
የሸዋ ገዥ የነበረው የኢጣሊያ
ጀነራል ሲሮ ናሲ
የኢጣሊያ ጦር አዛዥ ጀነራል ሲሮ ናሲ ከራስ አበበ አረጋይ ጋር እንደገና አዲስ ድርድር ለማድረግ፤ ወሰነ፡፡
በዚህም የድርደር መንፈስ መሠረት፤ አርበኞችን ለማግባባት ሲባል የኢጣሊያ ጦር በተጉለት፣ በቡልጋና ከአካባቢው ካሉት ምሽጎች እንዲነሳ ጀነራል ሲሮ ናሲ አዘዘ፡፡
በዚህም መሠረት አርበኞቹ እምሽጉ ድረስ መሄድ ስለቻሉ፤ የውስጥ አርበኞች በድብቅ ብዙ ጥይትና ቦምብ ሊሰጧቸው ቻሉ፡፡
ራስ አበበ የኢጣሊያ መልዕክተኞችን የሚቀበሉት ካሉበት ስፍራ ሆነው የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ሰቅለው በማውለብለብ ሲሆን፤ ጣሊያኖች ግን አርበኞች ጦር ሠፈር ድረስ ለመድረስ ሰባት የፍተሻ ኬላወችን ማለፍ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡
የደብረ ብርሃን አገረ ገዥ የሆነው የኢጣሊያ ኮሎኔል ማሊቲ ግን፤ ከራስ አበበ አረጋይ ጋር ለመገናኘት ያን ሁሉ የፍተሻ ጣቢያ ተፈትሾ ማለፍ ነበረበት፡፡
የእርቁ ድርደር ቀጥሎ ሳለ በኢትዮጵያ የኢጣሊያ ንጉስ እንደራሴ የሆነው ባለሥልጣን ለጉብኝት ወደ ሰሜን ሸዋ ሸኖ ሄዶ በነበረበት ወቅት፤ የራስ አበበ ባለቤት ምርኮኛዋ ወይዘሮ ቆንጅት አብነት በእስር ላይ መሆናቸውን አወቀ፡፡
ወደ እርሳቸውም ቀርቦ፤ “አንችን ያየሁባትን የዛሬን ቀን በጣም አከብራታለሁ፡፡ ለመሆኑ ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ” ብሎ ሲጠይቃቸው ከእስር እንዲያስፈታቸው ጠየቁት፡፡
ባለሥልጣኑም ጥያቄአቸውን ተቀብሎ “ከአሁን ጀምሮ ነፃ ናት ወደ ፈለገችበት መሄድ ትችላለች፡፡ ብቸኛ ሴት ናት፡፡ ምን ልታደርገን ትችላለች፡፡” በማለት ከእስር ቤት እንዲወጡ ፈቀደላቸው፡፡
ወይዘሮ ቆንጅት ከሰባት ወራት የእስር ቆይታ በኋላ አዲስ አበባ መግባት ቻሉ፡፡
አዲስ አበባም እንደደረሱ በመጀመሪያ የባለቤታቸው አክስት ከሆኑት ከወይዘሮ አዛለች ጎበና ቤት ካረፉ በኋላ በእንጦጦ ኪዳነ ምሕረት እና በመጨረሻም በቀጨኔ መድሐኔዓለም አካባቢ ቆይተዋል፡፡
ከዚያም በኋላ በታህሳስ ወር 1932 ዓ.ም. ባለቤታቸው ወደሚገኙበት ሥፍራ ሄደው ከባለቤታቸው ጋር ለመገናኘት ቻሉ፡፡
በእርቁ ድርድር ሳቢያ ባለቤታቸው ከእስር መፈታታቸው፤ በአርበኞች ዘንድ ራስ አበበ አረጋይ ከጠላት ጋር እርቅ እንደፈፀሙ ተደርጎ በመወሰዱ ይህን ጥርጣሬ ለማሶገድ ራስ አበበ ለአርበኞች መሪወች በጻፉት ደብዳቤ፤
“ያደረኩት እርቅ ፍጹም ዕርቅ መስሏችሁ እንዳትታለሉ፡፡
አበበ ለጠላት ሊገባ ነው ብላችሁ የምታስቡ ብትኖሩ በእግዚአብሔር ስም እምልላችኋለሁ፡፡
የእኔ ሀሳብ በጦር ሜዳ የቆሰሉትን ቁስላቸው እስኪሽር፣ በበሽታ የተጎዱት አርበኞች እንዲያገግሙ፣ የታረዙት ልብስ እንዲያገኙና በቆላውና በደጋው ሲንከራተቱ የተጎዱት ከብቶቻችን እንዲያገግሙ ነው ድርድሩን የጀመርኩት፡፡”
በማለት ለአርበኞች መልዕክት ላኩ፡፡
በዚህም መካከል በእርቅ ድርድሩ ምክንያት በተፈጠረው የተረጋጋ ሁኔታ የተወሰኑት የጅሩ የአርበኞች መሪዎች ከራስ አበበ ጋር ለመመካከር ሲጓዙ በጠላት ምሽግ በኩል ሲያልፉ በምሽጉ የሚገኘው የኢጣሊያ ጦር ኃላፊ ነገ እሸኛችኋለሁ ብሎ በሰላም የሚያስተናግድ መስሎ ወስዶ የጦር መሣሪያቸውን ተቀብሎ ካሳደራቸው በኋላ ከአለቃው ጋር ተነጋግሮ የያዛቸውን አርበኞች በሞት እንዲቀጡ አደረገ፡፡
የህን ዘግናኝ ወሬ የሰሙት ራስ አበበ፤ በአካባቢው የሚገኙትን አርበኞች ጥር 21 ቀን 1932 ዓ.ም. ሰብስበው ከተመካከሩ በኋላ አርበኞችን አታሎ በሞት እንዲቀጡ ያደረገው የኢጣሊያ ጦር ኃላፊ ለእነርሱ ተላልፎ እንዲሰጥ ጥያቄ እንዲቀርብ ተወሰነ፡፡
በዚህም መሠረት በአርበኞች አሟሟት ውሳኔ ለመስጠትና የእርቁንም ድርድር ፍጻሜ ለማድረስ የካቲት 30 ቀን 1932 ዓ.ም. ጀነራል ናሲ አርበኞቹ ድረስ እንደሚመጣ ራስ አበበ ለአርበኞቹ አስረዱ፡፡
በዚህን ጊዜ ጀነራሉ ከሚመጣበት ከሁለት ቀን በፊት ሰምምነት ተደርጎ ጀነራሉ በሚመጣበት ዕለት በደፈጣ ውጊያ እርምጃ እንዲወሰድበት ሰምምነት ላይ ተደረሰ፡፡
ይሁን እንጅ ጀነራል ናሲ ሀሳቡን ቀይሮ ሌሎችን ተወካዮችን ልኮ ዕርቃችን የፀና ይሁን የሚል መልዕክት በመላኩ የታቀደው ሁሉ ሳይሳካ ስለቀረ በዚህ የተበሳጩት ራስ አበበ፤ አርበኞቹን በግፍ በመግደላችሁ ዕርቁን ለመቀጠል ሌላ ቀጠሮ አልሰጥም፤ እርቁ እንዳይፈረስ ከፈለክ ወንጀለኞቹን አሳልፈህ ስጠኝ በማለት የተፈፀመውን የአርበኞች ግድያ ለእርቁ ማፍረሻ አድርገው በማቅረብ ቁርጥ ያለ መልስ ላኩለት፡፡
ይሁን እንጅ ጣሊያኖች የአበበ አረጋይን ሀሳብ ስላልተቀበሉት የዕርቅ ድርድሩ ፈርሶ ሁኔታዎች ሁሉ ወደቀድሞ ቦታቸው በመመለሳቸው አርበኞች እንደገና ተወያይተው ጠላትን በተለያዬ አቅጣጫ ተሰማርተው ለመውጋት በመስማማት የቀድሞ የአርበኝነት ተግባራቸውን ቀጠሉ፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ከስደት በመመለስ ከሱዳን ተነስተው ጎጃም ከሰነበቱ በኋላ በፍቼ በኩል አድርገው ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ሚያዝያ 22 ቀን 1933 ዓ.ም. ፍቼ ሲገቡ፤ ራስ አበበ አረጋይ ፍቼ ድረስ በመሄድ በሰልፍ ተቀበሏቸው፡፡
ራስ አበበ ከልጃቸው ከዳንኤል አበበ ጋር ሆነው ንጉሠ ነገሠቱ ጋ በመቅረብ ለጥ ብለው እጅ ከነሱ በኋላ፤
“እኔ የእርስዎ ታማኝ አሽከርዎ ለጠላት ሳልገዛ ቆይቻለሁ፡፡ ዳግመኛ በሕይወት አገኝዎታለሁ ብዬ ተስፋ አላደረኩም ነበር፡፡ እናም ፀሐይ ወጥታለን ለዚህ ቀን ስላደረሰን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።”
በማለት ንግግር አሰምተዋል፡፡
Ras Abebe and his patriots
ንጉሠ ነገሥቱ እንጦጦ ሲደርሱ
የራስ አበበ አረጋይ አርበኞች
በሽለላና በቀረርቶ ሞቅ ያለ አቀባበል ሲያደርጉላቸው
ጉዞውም ከፍቼ ወደ አዲስ አበባ ቀጥሎ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ጧት ንጉሠ ነገሥቱ እጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን በር ላይ ሲደርሱ ስመ ጥሩው ጀግና ክቡር ራስ አበበ አረጋይ ቁጥራቸው 10 ሺህ የሚደርስ አርበኞቻቸውን አሰልፈው እጅግ የደመቀና የጋለ አቀባበል አደረጉላቸው፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ከእንጦጦ ማርያም ተነስተው በግልጽ አውቶሞቢል ላይ ሆነው በነጭ ፈረስ ላይ በተቀመጠው በእንግሊዛዊው ኮሎኔል ዊንጌት፤ በጌድዮን ጦር እና በአርበኞች ታጅበው ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ለመቀጠል ተዘጋጁ፡፡
በዚህን ጊዜ በእንግሊዛዊው ጀነራል ካኒንገሃም አማካይነት በሞተር ብስክሌቶችና በቀላል ታንኮች ላይ በመሆንና፤ በተጨማሪም ንጉሠ ነገሥቱን የሚያጅቡ ከደቡብ አፍሪካ የመጡ ወታደሮችና የፖሊስ ሠራዊት ፈረሰኞች ወደ እንጦጦ ተልከው ንጉሠ ነገሥቱን እንዲያጅቡ ከተደረገ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ በደማቅ ንጉሣዊ ክብር ታጅበው ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ ዝግጅቱ ተጠናቀቀ፡፡
የጉዞውም ዝግጅት እንደተጠናቀቀም ከጀነራል ካኒንግሃም አንድ መልዕክት ለራስ አበበ አረጋይ ደረሰ፡፡
መልእክቱም፤ ቁጥራቸው 10 ሺህ የሚደርሰው የራስ አበበ አረጋይ የአርበኞች ጦር ንጉሠ ነገሥቱን አጅቦ ከሚሄድ ይልቅ እንጦጦ ላይ ሠፍረው ለ48 ሰዓት እንዲቆይ የሚል ነበር፡፡
ይህም የካኒንገሃም ሀሳብ ለራስ አበበ አረጋይ ተተርጉሞ ሲነገራቸው፤
“አልቀበልም! ንጉሠ ነገሥታችን በአገራችን በኢትዮጵያ ላይ የፋሽስት መንግሥት የሚፈጽመውን ግፍ ለዓለም መንግሥታት ማህበር ለማመልከት ወደ አውሮፓ ሲሄዱ፤ እኛም አዲስ አበባን ለቀን በየጫካውና በየገደሉ በመሰማራት ከጠላታችን ጋራ ለነፃነታችን ስንዋጋ አምስቱን ዓመታት አሳልፈናል፡፡
ዛሬ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ የወዳጅ አገር የእንግሊዝ መንግሥት እርዳታ ተጨምሮበት ንጉሠ ነገሥታችን የነፃነታችንን ችቦ እያበሩ ወደ መናገሻ ከተማቸው ሲያመሩ እኛ ተነጥለን እዚህ እንጦጦ እንድንቆይ የምንጠየቀውን አልቀበልም፡፡
አሁን የቆምነው ነፃ በሆነችው አገራችን መሬት ላይ ነው፡፡
ዛሬም ለመጓዝ የተዘጋጀነው ነፃ ወደሆነችው ወደ አዲስ አበባ ከተማችን ነው፡፡
ምናልባት የአዲስ አበባ ፀጥታ አስግቷችሁ እንደሆነ እኛ በቂ የሆነ ኃይል ሰላለን በቶሎ ደርሰን እንጋፈጥላችኋለን፡፡
ከዚህ ሌላ ባታስቸግሩን ይሻላል፡፡ እኛ ውለታችሁን ማሰብ፤ እናንተም ምስጋናችንን መቀበል የሚገባ ነው፡፡
ከዚህ ውጭ የምንጠይቃችሁ ነገር የለም፡፡”
የሚል መልስ ሰጡ፡፡
ዊንጌትም በራስ አበበ መልስ ተማረከ፡፡ ወዲያውኑም ዊንጌት ለካኒንግሃም ባስተላለፈው ቃል፤
የታወቀው የአርበኞች መሪ አበበ አረጋይ፤ ከጃንሆይ ተለይተን እንጦጦ ለመቆየት ጨርሶ የማይታሰብ ነው ብሏል፡፡ የንጉሠ ነገሥቱም አቋም ይህንኑ የመሠለ ስለሆነ ሀሳቡን ከመቀበል በስተቀር ምርጫ የለንም፡፡
ሲል አስታወቀ፡፡
ካኒንጋሃምም ሌላ ታሪክ መፍጠር ስላልፈለገ በጉዞው ፕሮግራም መሠረት፤ ንጉሠ ነገሥቱ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ታጅበው ከታላቁ ቤተ መንግሥት ደረሱ፡፡
Ras Abebe Aregay
የአዲስ አበባ ገዥ፣ የጦር ሚኒስትር፣
በሌፍትናንት ጀነራልነት ማዕረግ
የመከላከያ ሚኒስትርና
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር
ሆነው ያገለገሉት አበበ አረጋይ

credit to: ENKSSM
የቀድሞው የአራዳ ዘበኛ አለቃና የሸዋው እውቅ አርበኛ ራስ አበበ አረጋይ የሜጀር ጀነራልነት ማዕረግ ተሰጥቷቸውና የአዲስ አበባን ገዥነት ተሹመው ወደ ድሮ መኖሪያ ቤታቸው ገቡ፡፡
የሜጀር ጀነራልነት ማዕረግ ያገኙት አበበ አረጋይም ሹመቱ እንደተሰጣቸው ቅድሚያ ሥራቸው ያደረጉት የአዲስ አበባን ፀጥታ ማስከበር ነበር፡፡
የራስ አበበ አረጋይ ፀጥታን የማስፈንና የማረጋጋት ችሎታ ለሌላም ሥፍራ በማስፈለጉ፤ አዲሰ አበባን ለጥቂት ወራት ካስተዳደሩ በኋላ በነሐሴ ወር 1933 ዓ.ም. የሲዳሞ፣ የቦረናና የወላይታ አገረ ገዥ ሆነው ተሾሙ፡፡
በተሾሙባቸውም ሀገራት ለጥቂት ጊዚያት ከሰሩ በኋላ የጦር ሚኒስቴር መስሪያ ቤት እንደገና ሲቋቋም የመጀመሪያው የጦር ምኒስትር ሆነው የካቲት 16 ቀን 1934 ዓ.ም. ተሾሙ፡፡
ይህም ያገኙት ሹመት በአርበኝነቱ ዘመን በእርሳቸው ጠቅላይ አዛዥነት የታገሉትንና ሌሎችን አርበኞችን በመንግሥት መደበኛ ጦር ሠራዊት ውስጥ ተመድበው እንዲያገለግሉ ለማድረግ አስችሏቸዋል፡፡
ከ 1933 ዓ.ም. እስከ 1934 ዓ.ም. ድረስ የሲዳሞ ጠቅላይ ገዥ በመሆን ተሹመዋል፡፡

LIbrary in the name of Ras Abebe Aregay at Debre Berehan
በደብረብርሐን ከተማ በራስ አበበ አረጋይ
ስም የተሠየመው ቤተ መጽሐፍት

credit to: mezemirethiopia
በ 1934 ዓ.ም. በትግራይ ምድር የበቀለው የወያኔ አማፂ ቡድን በአካባቢው የፈጠረውን ሁከት ለመቆጣጠር እና ፀጥታ ለማስከበር፤ አበበ አረጋይ ወደ ስፍራው ተልከው ከእንደርታው ወዲ ወልዳይ ጋር በመሆንና በእንግሊዞች የአየር ኃይል በመታገዝ ጥቅምት 6 ቀን 1936 ዓ.ም. ውቅሮ በሚገኘው የወያኔ ማዘዣ ጣቢያ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አድርገዋል፡፡
በመቀጠልም፤ ንጉሠ ነገሥቱ፤ የትግራይን ፀጥታ ለማስከበር አበበ አረጋይን የትግራይ ገዥ በማድረጋቸውና እርሳቸውም በወሰዱት ቆፍጠን ያለ እርምጃ መረጋጋትን ለማስፈን ችለዋል፡፡

አበበ አረጋይ፤
  1. ከ1939 ዓ.ም. እስከ 1941 ዓ.ም. ድረስ ለሁለት ዓመታት ለሁለተኛ ጊዜ የጦር ሚኒስትር ሲሆኑ በድምሩ ለ 7 ዓመታት የጦር ምኒስትር፣
  2. ግንቦት 27 ቀን 1941 ዓ.ም. በሌፍትናንት ጀነራልነት ማዕረግ የመከላከያ ሚኒስትር፣
  3. ሰኔ 30 ቀን 1941 ዓ.ም. የአገር ግዛት ምኒስትር፤
  4. ከ 1941 እስከ 1947 ዓ.ም. ድረስ ለ 6 ዓመታት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር፣
  5. ከ ህዳር 18 ቀን 1950 እስከ ታህሳስ 8 ቀን 1953 ዓ.ም. ድረስ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር
በመሆን በታማኝነት አገልግለዋል፡፡
በ1952 ዓ.ም. መጨረሻዎቹ አካባቢ፤ የመንግሥት አመራር በሁለት ጎራ ተከፍሎ፤ አንደኛው ጎራ ንጉሠ ነገሥቱን የሚደግፍ ሲሆን ሌላው ጎራ ደግሞ መንግሥቱን ለመገርሰስ የፈለገ ቡድን ነበር፡፡
ንጉሠ ነገሥቱን የሚደግፈው ቡድን እነ ራስ አበበ አረጋይ ያሉበት ሲሆን የአማፂው ቡድን ደጋፊዎች ደግሞ፤ የፖሊስ ሠራዊት ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ጽጌ ዲቡና የሀገሪቱ የደህንነት መሥሪያ ቤት አዛዥ፤ ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ ይገኙበታል፡፡
የመፈንቅለ መንግሥቱ ዋና ጠንሳሹ ግርማሜ ነዋይ ሲሆን መፈንቅለ መንግሥቱ በጦር ኃይል እንዲታገዝ ስለፈለገ፤ የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘበኛ ዋና አዛዥ የሆነውን ወንድሙን መንግሥቱ ነዋይን አግባብቶና አሳምኖ፤ የአመጹ ዋና አስተባባሪ አደረገው፡፡
በተጨማሪም፤
  1. አቶ መኮንን ሐብተ ወልድን (የአቶ አክሊሉ ሐብተ ወልድ ወንድም)፣
  2. ራስ አንዳርጋቸው መሣይን (የንጉሠ ነገሥቱ የመጀመሪያ ልጅ የልዕልት ተናኘወርቅ ባለቤት) እና፣
  3. ሜጀር ጀነራል ሙሉጌታ ቡሊን (ከ1933 ዓ.ም. እስከ 1947 ዓ.ም. ድረስ ለ14 ዓመታት የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘበኛ አዛዥ የነበሩ)፣
  4. ራስ አበበ አረጋይን፤ የሀገሪቱ ጠቅላይ ምኒስትር፣
በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት አስሮ በመያዣነት በቁጥጥሩ ሥር አዋላቸው፡፡
ይህ የ1953ቱ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ሲከሽፍ፤ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት በእስር ላይ በነበሩት የመንግስት ምኒስትሮችና ከፍተኛ ኃላፊዎች ላይ እርምጃ ከመወሰዱ በፊት ግርማሜ ነዋይ በአመጹ የተካፈሉትን የጦር መኮንኖች ሰብስቦ፤
“ሁሉም ነገር እንደአቀድነው አልሄደም፡፡ ነገር ግን ተልዕኮአችን ስላልተሳካ፤ ቢያንስ ኢትዮጵያን ከእነዚህ ደም ጠጭዎች ማጽዳት አንዱ የተቀደሰ ተግባራችን ስለሆነ በምንወስደው እርምጃ እንዳታዝኑ፡፡” የሚል ንግግር ተናግሯል፡፡

ግርማሜ ነዋይ ላይ፤ የግድያ እርምጃው ከመወሰዱ አስቀድሞም ሆነ ከእርምጃው በኋላ በገፁ ላይ የመደንገጥ፣ የመጸጸት ወይም የማመንታት ምልክት አልታየበትም ነበር።
ከዚህ በኋላ ራስ አበበ አረጋይን ጨምሮ በመያዣነት የያዟቸውን ሦስቱን ባለሥልጣኖችና ያሠሯቸውን ከ20 የማያንሱ ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ ሹማምንቶችን ሰብስበው በመትረየስ ጥይት ደብድበው ገለዋቸዋል፡፡
1ኛ፡- ከሜክሲኮ አደባባይ እስከ ብሔራዊ ትያትር ድረስ ያለው ዋናው የአስፋልት መንገድ በስማቸው ራስ አበበ አረጋይ መንገድ (Ras Abebe Aregay Street) ተብሎ ተሰይሟል፡፡
2ኛ፡- በስማቸው የተሰየመው፤ ፒያሳ ከመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ እና አዲስ አበባ የምግብ አዳራሽ አጠገብ ይገኝ የነበረው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ ትምህርት ቤቱ ባልታወቀ ምክንያት ለጊዜው መዘጋቱ ተነግሯል፡፡
3ኛ፡- በደብረ ብርሐን ከተማ የሚገኝ መጽሐፍት ቤት ሲሆን፤ ይህም መጽሐፍት ቤት የሚያስገርም ታሪክ አለው፡፡
Ras Abebe Aregay Liberary - Debre Berehan
በመዘምር ግርማ የግል ጥረት እና በራሱ ወጭ
በደብረ ብርሃን ከተማ የተቋቋመው መጽሐፍት ቤት
credit to: africanstorybook.org
መጽሐፍት ቤቱ የተቋቋመው መዘምር ግርማ በተባለው በጎ አድራጊ ሲሆን፤ ይህ ወጣት በራሱ ተነሳሽነት በደብረ ብርሐን ከተማ በግሉ ወጭ ቤት ተከራይቶ በራስ አበበ አረጋይ ስም የተሰየመ መጻሕፍት ቤት (Ras Abebe Aregay Library, RAL) ለማቋቋም ያደረገው ጥረት እጅግ የሚያበረታታና ለወጣቱና ለቀረው ህብረተሰብ መልካም አርዓያ ያለው ተግባር ሆኖ ስላገኘው፤ አፍሪካን ስቶሪ ቡክ (African Storybook (ASB)) የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት የመዘምርን ሥራ ለማበረታታት እ.ኤ.አቆጣጠር ከ2015 ጀምሮ አብሮ እየሠራ እንደሆነ ታውቋል፡፡
አፍሪካን ሰቶሪ ቡክ፤ በአፍሪካ ቋንቋዎች ለቅድመ ንባብ በግልፅ ፈቃድ ያላቸው የስዕል መጽሃፎችን በማሳተም ከአስተማሪዎች እና ከልጆች ጋር በብዙ የአፍሪካ ቋንቋዎች ማንበብና መጻፍን ለማበረታታት አልሞ የሚሠራ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡
መዘምር ግርማ፤ እውቀትን ለማጋራት እና በስነ-ጽሁፍ ላይ ያለውን ቁርጠኝነት በደብረ ብርሃን ከተማ በግሉ ተነሳሽነት አንድ ክፍል ተከራይቶ አነስተኛ የማህበረሰብ ቤተመፃህፍት እንዴት እንዳቋቋመ እና የንባብ ባህልን በማስፋፋት የደብረ ብርሃን ማህበረሰብ ልጆችን እና ወጣቶችን ለመደገፍ የፈፀመው ትግባር የሚደነቅ ነው።
Ras Abebe Aregay Liberary - Debre Berehan
ይህ በፎቶው ላይ የሚታየው መዘምር ግርማ ይባላል

credit to: africanstorybook.org
በመጽሐፍት ቤቷ መጽሐፍት የሚቀመጡት በቀርቀሀ በተሰሩ ማሰሮዎች ውስጥ ነበር፡፡ ነገር ግን ቀስ በቀስ በብዙ እገዛና ድካም የመጻሕፍት መደርደሪያ ያለው ወደ መደበኛ መጽሐፍት ቤት በማደግ ከ20 በላይ ለሆኑ የትምሕርት ቤት ማህበረሰቦችን እና የነዋሪውን የንባብ ፍላጎት ለማርካት ጥረት መደረጉን የመጽሐፍት ቤቱ መስራች የመዘምር ዘገባ ያስረዳል፡፡
በመዘምር ዘገባ መሰረት፤ እ.ኤ.አ. በጥር እና ሜይ መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ 367 የአፍሪካ ታሪክ መጽሐፍት ለልጆች እና ለጎልማሶች ጥቅም ላይ ውለዋል። በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ እና በትግርኛ ቋንቋዎች የተተረጎሙ በቁጥር 162 የሚደርሱ የተረት መጽሐፍት እና እንዲሁም የእንግሊዝኛ ቅጂዎቻቸው ተነበዋል።
...ስለመጽሐፍት ቤቱ የበለጠ ለማንበብ፤ → (africanstorybook.org) ይጎብኙ




ምንጭ፤
  1. "ቀሪን ገረመው" ደራሲ፤ ቀኝአዝማች ታደሰ ዘወልዴ 2008 ዓ.ም.
  2. "የታሪክ ማስታወሻ" ደራሲ፡- ደጃዝማች ከበደ ተሰማ 1962 ዓ.ም.
  3. ምስግና፤ ለሸገር ራዲዮ “ለትዝታ ዘአራዳ ፕሮግራም” አቅራቢ ለተወዳጁ ጋዜጠኛና ተራኪ ለተፈሪ ዓለሙ
    --› “ትዝታ ዘአራዳ ፕሮግራም ክፍል 1-ራስ አበበ አረጋይ (አባገስጥ)”
    --› “ትዝታ ዘአራዳ ፕሮግራም ክፍል 2-ራስ አበበ አረጋይ (አባገስጥ)”
  4. peoplepill.com
  5. ethiopiaobserver.com
  6. ከዊኪፒዲያ የተተረጎመ
  7. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ጎራው - በኦርኬስትራ ኢትዮጵያ   ዩቲውብ
  8. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ