Content-Language: am ልጅ ኃይለ ማሪያም ማሞ
header image




ልጅ ኃይለማሪያም ማሞ



የልጅ ኃይለማሪያም ማሞን
የአርበኝነት ዘመን ታሪክ ያዳምጡ














1. ትውልድና ዕድገት

Lij-Hailemariam Mamo
ልጅ ኃይለ ማሪያም ማሞ
ኃይለማሪያም ማሞ በሸዋ ጠቅላይ ግዛት በሰላሌ አውራጃ ያያ ኩኩማ በተባለው ቀበሌ በ 1896 ዓ.ም. ተወለደ፡፡
ትምህርቱን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ከመጀመሩ አስቀድሞ በመንደሩ በሚገኘው ቤተ ክርስቲያን መሰረታዊ ትምህርት ተምሯል፡፡
ኃይለማሪያም ማሞ የጀግናው የደጃዝማች ኃይሌ አንዳርጋቸው የልጅ ልጅ ልጅ ነው፡፡
ኃይለማሪያም ማሞ በወጣትነት እድሜው በግብርና ሥራ ተሰማርቶ ሰርቷል፡፡
ስሙ ዘውዴ የተባለ ልጅም ወልዷል፡፡

2. የአርበኝነት ዘመን

ኃይለማሪያም ማሞ ሚያዝያ 26 ቀን 1928 ዓ.ም. በ32 አመት ዕድሜው ከደብረ ብርሃን ጫጫ ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ እየገሠገሠ በነበረው የፋሽስት ጦር ላይ ጦርነት ገጥሞ 170 የፋሽስት ወታደሮች ሲማረኩ ከተማረኩት ውስጥ 2ቱ የህክምና ዶክተሮች ሲገኙበት ከተያዙ ከጥቂት ቀናት በኋላም ምርኮኞቹ ተለቀዋል፡፡
ኃይለማሪያም ማሞ በፋሽስት ጦር ላይ የተቀዳጀው ይህ ድል፤ ከሸዋ አርበኞች መካከል የቀዳሚነት ስፍራውን ይዣለሁ ብሎ እንዲያምን ያደረገው ድል መሆኑን የታሪክ ፀሐፊው ሰለሞን ገብረ እግዚአብሔር ያስረዳል፡፡

ኃይለማሪያም ማሞ ይህን ጥቃት በጠላት ላይ በፈጸመ በማግስቱ የፋሽስት ጦር አዲስ አበባን መቆጣጠር ችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ወታደራዊ አመራሮች አዲስ አበባን ለቀው እንደወጡ ኃይለማሪያም ማሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ የደፈጣ ውጊያውን ቀጠለ፡፡
በተጨማሪም ኃይለማሪያም ማሞ፤ በሰላሌ ሙገር፣ በደብረብርሃን፣ በመንዝና ተጉለት፣ በቡልጋ እና በሰሜን ሰላሌ አርበኞችን በማስተባበር ጠላትን መፋለም ተያያዘው፡፡
በሐምሌ ወር 1928 ዓ.ም. አንዳንድ የአርበኞች ግንባር መሪዎች እጃቸውን ለጠላት መስጠታቸውን ተከትሎ ኃይለ ማርያም የትግል ስፍራውን ወደ ተጉለት አዛወረ።
የኃይለ ማርያም የደፈጣ ውጊያና የአርበኝነት እንቅስቃሴ በፋሽስት ኢጣሊያ ዘንድ ከፍተኛ ብስጭትን ፈጠረ።
የኃይለ ማርያምን ጦር በውጊያ ለመቋቋም በማሰብ የደብረብርሃን ጦር አዛዥ የሆነው የፋሽስት ጄኔራል ሩጌሮ ትራሺያ በአካባቢው የሚገኙትን የእርሱን ወታደሮች በማሰባሰብ ጦሩን ማጠናከር ጀመረ፡፡
በዚህ መልኩ ኃይለ ማሪያምን በተለያዩ የውጊያ አውዶች የገጠመው የፋሽስት ጦር ድል አልቀናውም፡፡
Lij-Hailemariam Mamo
በደብረ ብርሃን ከተማ በ 1934 ዓ.ም.
የተሠራው ኃይለ ማሪያም ማሞ ከፍተኛ
መሰናዶ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት

ምስጋና፤ ለሳሙኤል ጌታቸው  Photo Link
ጀግኖቹ የኃይለ ማሪያም ተዋጊ አርበኞች በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የጠላት ወታደሮችን በመግደልና የተለያዩ መሣሪያዎችንም በመማረክ ከፍተኛ ድል አስመዝግበዋል፡፡

በሰኔ ወር 1930 ዓ.ም. የፋሽስት ወታደሮች በክልሉ ያለውን ተቃውሞ ለማረጋጋት ሲሉ አንኮበርን እና በዙሪያው ያሉትን ደጋማ አካባቢዎች ከበው ነበር።
በዚህን ጊዜ ኃይለ ማርያም ማሞ 500 የሚሆኑ ወታደሮችን አሰልፎ የጠላት መመላለሻ ስፍራን (ኮሪዶር) ሰብሮ ለመግባት ከፍተኛ ውጊያ አድርጎ ነበር፡፡
በቡልጋ ጎርፎ ከተባለው ስፍራ በተደረገው በዚህ ከባድ ውጊያ ላይ ኃይለ ማርያም ማሞ ሰኔ 6 ቀን 1930 ዓ.ም. በጥይት ተመቶ ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ ስለደረሰበት የአንበሶች አንበሳ፣ የጀግኖች ጀግና ሆኖ ስሙን በወርቅ ቀለም እስመዝገቦና እጅግ የላቀና ገናና የአርበኝነት ታሪክ ሠርቶ ገና በወጣትነት እድሜው በተወለደ በ34 ዓመቱ ሕይወቱን ለእናት ሀገሩ አሳልፎ ሰቷል፡፡

ለልጅ ኃይለማሪያም ማሞ ጀብድና ጀግንነት ከተገጠሙ ግጥሞች መካከል፤
ሀይለማሪያም ማሞ የጦሩ ገበሬ፣
ፈረሱን እንደሰው አስታጠቀው ሱሬ፡፡

ኃይለማርያም ማሞ የጦሩ ገበሬ፣
እያላጋው መጣ ነጬን ከነጭ በሬ፡፡

ኃይለማርያም ማሞ የጦሩ ገበሬ፣
ይኸንን ሶላቶ ነዳው እንደበሬ።

መተኮሱንማ ማንም ይተኩሳል፣
ኃይለማርያም ማሞ አንጀት ይበጥሳል።

ተብሎ ተገጥሞለታል፡፡

የጀግናው የኃይለማሪያም ማሞ የአርበኝነት ገድል መታሰቢያ፤

  1. ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት፤ ከተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እና ከእቴጌ መነን የልጃገረዶች ትምህርት ቤት ቀጥሎ በአንጋፋነቱ ሦስተኛ የሆነው የኃይለ ማሪያም ማሞ ከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በደብረ ብርሃን ከተማ በሚያዝያ ወር 1934 ዓ.ም. ተሰርቶ በስሙ ተሰይሟል፡፡
  2. በአዳማ (ናዝሬት) ከተማ፤ የልጅ ኃይለማሪያም ማሞ መታሰቢያ ሆሰፒታል ተሰርቷል፡፡






ምንጭ፤
  1. "ቀሪን ገረመው" ደራሲ፤ ቀኝአዝማች ታደሰ ዘወልዴ 2008 ዓ.ም.
  2. ከውኪፒዲያ የተተረጎመ
  3. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ