Content-Language: am ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ገጽ ሁለት
header image



(ድረ ገጽ ሁለት)


ዳግማዊ አፄ ምኒልክ





ፋሽስት ኢጣሊያ የኢትዮጵያ መሬት የሆነችውን ኤርትራን በቅኝ ግዛትነት ልትይዝ ከቻለችባቸው ምክንያቶች ውስጥ፤
  • አንደኛ
    ኢትዮጵያውያን መኳንንት በማዕከላዊው መንግሥት ላይ እየሸፈቱ ጠላት ለሆነው ለፋሽስት ኢጣሊያ መንግሥት ድጋፍና እገዛ በማድረጋቸው ነበር፡፡
    በተለይ አፄ ዮሐንስ ከሞቱ በኋላ በትግራይ የተፈጠረውን የሥልጣን ሽኩቻ ብንመለከት፤
    በመጀመሪያ፤ አፄ ዮሐንስ ዙፋናቸውን እንዲወርሱ የተናዘዙላቸው ለልጃቸው ለራስ መንገሻ ዮሐንስ ነበር፡፡
    ነገር ግን የትግራይና የሐማሴን መኳንንቶች፤ የትግራይ ገዥ በሆኑት በራስ መንገሻ ላይ የስልጣን ተቀናነቃኝ ሆነው ተነሱ፡፡
    ይህን ሰበብ በማድረግ በማዕከላዊው መንግሥት ላይ በመሸፈት፤ አገራቸውን ኢትዮጵያን ከድተው ጠላታቸው በሆነው በኢጣሊያ መንግሥት ሥር ለመተዳደርና እነርሱን ለመርዳት ወሰኑ፡፡
    እነዚህ በማእከላዊው መንግስት የሸፈቱና ለኢጣሊያ መንግሥት ታማኝነታቸውን ለመግለጽ ሲሉ የኢትዮጵያን መሬት እንደቡራኬ እየቆረሱ ለኢጣሊያ በገፀ በረከትነት አቀረቡላቸው፡፡
    ከነዚህም በወቅቱ የኢጣሊያንን መንግሥት ገዥነት አምነውና ተቀብለው የኢትዮጵያ መሬት የሆነውን ኤርትራን በመሸንሸን ለኢጣሊያ ከሰጡት ሀገር ከሀዲዎች መካከል፤
    1. ደጃዝማች ደብብ የተባሉት፣ አሥመራንና አካባቢዋን፤
    2. ደጃዝማች ባህታ ሐጎስ፣ አካለ ጉዛይን፤
    3. ባላምባራስ ክፍለየሱስ፣ ከረንንና በጎስ የተሰኙትን ክፍለ ሀገሮች ለኢጣሊያ መንግሥት ካስረከቡ በኋላ፣ ራሳቸው ባላምባራስ ክፍለየሱስ ለኢጣሊያ በሰጡት መሬት ላይ ተመልሰው የከረን አገረ ገዥ ሆነው በፋሽስቶቹ ተሸሙ፡፡

    • ሁለተኛው
      ፋሽስቶቹ በኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው የየመኳንንቱ (የአካባቢ ገዥዎች) አማካሪና የኢትዮጵያ ወዳጅ በመምሰል ለአገራቸው ይሰልሉና መኳንንቱን እርስ በርሱ ያጋጩት ነበር፡፡

      ሦስተኛው
      ከ1880 አስከ 1884 ዓ.ም. ለአምስት ዓመታት በተለይ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ላይ የተንሰራፋው እና “ክፉ ቀን” ተብሎ ይጠራ የነበረው የረሀብ መቅሰፈት ያስከተለው የኢኮኖሚና ማህበራዊ መናጋት ለኢጣሊያ ወደ ሰሜን ደጋማው ክፍል ለመስፋፋት አመች ሁኔታ ፈጠረለት፡፡
      በዚያ ዘመን ተከስቶ የነበረው መጠነ ሰፊ ረሀብ በሕዝብ ሕሊና ውስጥ የማይጠፋ ጠባሳ ትቶ እንዳለፈ ይተረካል፡፡


አፄ ዮሐንስ በመተማ ከደርቡሾች ጋር ተዋግተው ከሞቱ በኋላ፣ የኢጣሊያ መንግሥት የያዘው የቅኝ ግዛት ወሰን እንዲረጋለት በማሰብ፣ ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጋር መዋዋል ፈለገ፡፡
ይህንንም ውል ለማስፈጸም በኢጣሊያ መንግሥት በኩል የተመረጠው፣ የኢትዮጵያ መኳንንቶች ወዳጅ የሆነውና በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ዘንድ ተወዳጅ የነበረው ኢጣሊያዊው አማርኛ ተናጋሪ ኮንት አንቶኒሊ ነበር፡፡
Conte Antonili
ኮንት አንቶኒሊ
ኮንት አንቶኒሊ ሸዋ ገብቶ መቀመጥ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ኢትዮጵያዊት ሴትም አግብቶ ሁለት ልጆች ወልዷል፡፡
በተለይ ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ባለቤት ከእቴጌ ጣይቱ ጋር ጥሩ ወዳጅነት ሰላለው፤ ለማታለልም ሆነ ለመስበክ አመችቶት ነበር፡፡
ይህ ሰው ወዳጅ መስሎ ቀርቦ፤ አሥመራ ውስጥ በጣሊያኖች የተረቀቀውን ውል አምጥቶ ለዳግማዊ አፄ ምኒልክ በማቅረብ፤ ለመንግሥታቸው ያሰበ በማስመሰል ከኢጣሊያ መንግሥት ጋር እንዲዋዋሉ አደረገ፡፡
አንቶኒሊ ውሉን ይዞ ሲመጣ ምኒልክ አዲስ አበባ አልነበሩም፡፡
በውሉ መፈረም የተቻኮለው አንቶኒሊ ምኒልክ ያሉበት አገር ድረስ ሄዶ ውሉን አቅርቦና ሰብኮ ሚያዝያ 25 ቀን 1881 ዓ.ም. ምኒልክን አስፈረማቸው፡፡
ውሉም፤ በተዋዋሉበት ስፍራ ስም የውጫሌ ውል ተብሎ ተሰየመ፡፡
የውጫሌ ውል የተፈረመው፤ ኢጣሊያ አሰብን በቅኝ ግዛትነት ከያዘች ከ 20 ዓመት በኋላ እና በሐማሴን ግዛቷን አስፋፍታ ከያዘች በኋላ ነበር፡፡
የውጫሌ ውል በ 21 አንቀጾች የተከፋፈለ ሲሆን፤ ለአድዋ ጦርነት መነሻ የሆነችው የውሉ 17ኛዋ አንቀጽ ነበረች፡፡
የውጫሌ ውል አንቀጽ 17 የአማርኛው ትርጉም እነደሚከተለው ይነበባል፤
“የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮፓ መንግሥታት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በኢጣሊያ መንግሥት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል፡፡”

በኢጣሊያ ቋንቋ የተጻፈው ውል ደግሞ፤
“የኢትዮጵያ መንግሥት ከውጭ አገር መንግሥታት ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግሥት አማካይነት ማድረግ ይገባዋል፡፡”
ይላል፡፡
የአማርኛውና የጣሊያንኛው ትርጉም ልዩነት አለው፡፡
የጣሊያንኛው ትርጉም ላይ፣ ኢትዮጵያ፤
ማናቸውም የውጭ ግንኙነቷ በኢጣሊያ መንግሥት ፈቃድ ብቻ እንዲፈጸም
የሚያመለክት ነው፡፡

አቶ ግርማይ ገብረ ጻድቅ የተባሉ ጸሀፊ የካቲት 20 ቀን 1980 ዓ.ም. በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ባቀረቡት ጽሁፍ፤
“...በአፄ ዮሐንስ ሞት ምክንያት፣ የኢትዮጵያ መኳንንት በሥልጣን ይገባኛል ምክንያት ሲራኮቱ፣ ለጠላት ይበልጥ አመች ሁኔታዎችን ፈጠረ፡፡
መኳንንቶቹንም እንደመሣሪያ በመጠቀም ጭምር ባሕረ ነጋሽን ‘ኤርትራ’ ብሎ ሰየመ፡፡
እንደገናም ወደ ትግራይ ጭምር በመዝለቅ፣ ለአዲሱ ንጉሥ ዳግማዊ ምኒልክ ታላቅ ራስ ምታት ሆነ፡፡
የኢጣሊያ ጦር መረብን ተሻግሮ ትግራይን ሲወር ዳግማዊ ምኒልክ ከነገሡ 6 ወራት እንኳን ስላልሞላቸው፣ ጣሊያኖችን ለመቋቋም አስተማማኝ የኢኮኖሚ መሠረትና ወታደራዊ ኃይል አልነበራቸውም፡፡
ታላላቆቹ የአገሪቱ መሳፍንቶች ለዳግማዊ ምኒልክ ጀርባቸውን በመስጠት፣ ከጠላት ጋር ተሰልፈው ሊወጓቸው እያሴሩባቸው ነበር፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፤ አገሪቱ በታሪኳ ውስጥ አጋጥሟት በማያውቅ “ታላቅ ረሀብ” ውስጥ ስለነበረች፤ በአገሪቱ በሞላ ህዝቡ እንደቅጠል በመርገፍ ላይ ነበር፡፡
በዚህን ወቀት ዳግማዊ ምኒልክ፤ ጠላቶቻቸውን የሚወጉበትን ስልት ከመለወጥ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡
በመሆኑም ዳግማዊ ምኒልክ ሌላ አማራጭ ስላልነበራቸው፤ ያለማንም ተከላካይ ወደ መሐል አገር ይገሠግሥ የነበረውን ጠላት፣ ውጫሌ ላይ በፈረሙት ውል አማካይነት፣ ከመረብ ምላሽ እልፍ እንዳይል በማድረግ፤ ለማይቀረው ጦርነት ሁለገብ ዝግጅት ማድረግ ጀመሩ፡፡
ብዙ የታሪክ ጸሐፊዎች እንደተስማሙበት፤
“ዳግማዊ ምኒልክ በዚህ ወቅት የተጠቀሙበት ስልት፤ የዲፕሎማሲ ብስለታቸውን፣ አርቆ አሳቢነታቸውን፤ ተጨባጭ ሁኔታን የማመዛዘንና የመገምገም ችሎታቸውንና የአመራር ብቃታቸውን በሚገባ አረጋግጧል፡፡”
የሚል ነበር፡፡

ጣሊያኖች የውጫሌን ውል ከተዋዋሉ በኋላ፣ ለአሥራ ሁለት የአውሮፓ መንግሥታትና ለአሜሪካ ጭምር ጥቅምት 2 ቀን 1882 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ፤
“ኢትዮጵያ፣ በኢጣሊያ ስር ነች” እያሉ ማሳወቅ ጀመሩ፡፡
በትምህርት ቤት የመማሪያ ደብተሮቻቸው ላይ ሳይቀር፣ “ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ጥገኝነት ሥር ናት” የሚል ጽሁፍ አሳትመው ያሰራጩ ጀመር፡፡
ዳግማዊ ምኒልክም፣ የውጫሌው ውል አልገባቸውም ነበርና፣ እርሳቸውም በበኩላቸው የኢትዮጵያ ንጉሥ መሆናቸውን ለማሳወቅ፤ ለጀርመን ንጉሠ ነገሥት የጻፉት ደብዳቤ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ለውጫሌ ውል ብጥብጥ መነሻ ሆነ፡፡
በዚያን ጊዜ፣ልዑል ራስ መኮንን በኢጣሊያ ጉብኝት ላይ ስለነበሩ ጉዳዩን ሰምተው ኖሮ፣ መቃወማቸውን ለኢጣሊያ መንግስት ካሰሙ በኋላ፣ አገራቸው ሲመለሱ የውሉን መበላሸት ለዳግማዊ ምኒልክ ነገሯቸው፡፡
በዚያም ወቀት የአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት የባሪያ ንግድን ለማስቀረት በብራስልስ ጉባኤ እያደረጉ ሳለ፤ የጉባኤው ተሳታፊ የሆነው የኢጣሊያ መልክተኛ፤
“ኢትዮጵያ በኢጣሊያ መንግሥት ጥገኝነት ሥር ስለሆነች ዛሬ በጉባኤው ላይ የተገኘሁት የኢትዮጵያንም መንግሥት ወክየ ነው፡፡”
በማለት ንግግር ሲያደርግ ለጊዜው ጉባኤው የታወከ ቢመስልም፣ የተወካዩን ንግግር ከደገፉት የተስፋፊነት ምኞት ከነበራቸው መንግሥታት መካከል፤
እንግሊዝጀርመንፈረንሳይና ቱርክ ይገኙበታል፡፡
ይህን ሁሉ ዝርዝር ጉዳይ ዳግማዊ ምኒልክ ከወዳጆቻቸውና፣ ከጠላቶቻቸው ሰምተዋል፡፡
ነገር ግን አቅማቸው ደካማ በመሆኑ ምንም ማድረግ ባለመቻላቸው በጣም ተበሳጩ፡፡

ዳግማዊ ምኒልክ ፣ የተሳሳተውን የውሉን አንቀጽ 17 በማሻሻል ጉዳዩን በሠላም ለመጨረስ ስለፈለጉ፣ ለኢጣሊያው ንጉሥ ለቀዳማዊ ኡምቤርቶ በጻፉት ደብዳቤ፤
  1. የውጫሌው ውል የአማርኛውና የጣሊያንኛ ትርጉም እንደማይስማማ፣
  2. ውሉን የተፈራረሙት ለወዳጅነት እንጅ፣ በእንደዚህ አይነት ውል ግዴታ ውስጥ የሚገቡ ሰው እንዳልሆኑ፣
  3. በውሉ አንቀጽ 17 የተሳሳተው ተስተካክሎ ለመንግሥታቱ ሁሉ እንዲገለጽላቸው፤
በማለት አቋማቸውን አስታወቁ፡፡
የዳግማዊ ምኒልክ ደብዳቤ የደረሰው የኢጣሊያ መነግሥትም፤ ጉዳዩ በሰላም እንዲያለቅ ቀደም ሲል ውሉን ያስፈረመው ኮንቲ አንቶኒሊን እንደገና ወደ አዲስ አበባ ላከ፡፡
ኮንቲ አንቶኒሊንም ዳግማዊ ምኒልክ ችሎት ቀርቦ፤
“የኢጣሊያ መንግሥት 17ኛው አንቀጽ ተሳስቷል የሚባለውን አንቀበልም፡፡ በዚህ ጉዳይ ማንም ኃያል መንግሥት ሊያስገድድ አይችልም፡፡ ምክንያቱም፣ ኢጣሊያ ክብሯን የምትጠብቅ ታላቅ መንግሥት ናት፡፡”
በማለት የጉራ ንግግር ተናገረ፡፡
በችሎቱ ላይ የነበሩት እቴጌ ጣይቱ፤ የአንቶኒሊ ንግግር ስለአበሳጫቸው፣ ወዲያውኑ የእርሱን ንግግር አቋርጠው፤
“ያ አንቀጽ የሚለውን ነገር እኛም ለኃያላን መንግሥታት አሳውቀናል፡፡
በአማርኛ ቋንቋ የተጻፋውን ምን እንደሚልም ነግረናል፡፡
እንዳንተ ሁሉ እኛም ክብራችንን እንጠብቃለን፡፡
እናንተ የምትመኙት፤ ኢትዮጵያ በእናንተ ሥልጣን ሥር እንድትሆን ነው፡፡
ይህ ለምን ጊዜም የማይሆን ነገር ነው፡፡”
የሚል ቁርጥ ያለ መልስ ሰጡት፡፡
በጨረሻም ከብዙ ውይይት በኋላ ውሉ ተቀይሮ፤
“17ኛው አንቀጽ ተሰርዟል፡፡”
የሚል በአማርኛ ብቻ በሁለት ቅጅ ተጽፎ አንዱ ቅጅ ለአንቶኒሊ ተሰጠው፡፡
በማግስቱም አንቶኒሊ የተሰጠውን የአማርኛ ቅጅ ወደ ጣሊያንኛ ሲያስተረጉመው፤
Empress Taitu
ቆራጧና ብልኋ መሪ እቴጌ ጣይቱ

17ኛው አንቀጽ የነበረው ቃል ተሠርዟል፡፡ ለመቸውም ተፍቋል፡፡” የሚል ሆኖ አገኘው፡፡
በዚህም ጽሁፍ የተደናገጠው ኮንት አንቶኒሊ በቀጥታ ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ሄዶ፣
ዳግማዊ ምኒልክ፣ እቴጌ ጣይቱ እና መኳንንቶች ሁሉ ባሉበት ገብቶ፤ ለምን ተሠርዟል የሚል ቃል ተጻፈ? በማለት ጠየቀ፡፡
ዳግማዊ ምኒልክም፤
“ሁለታችንም ተነጋግረን የተጻፈ ነው እንጅ እኛ የጨመርነውም ሆነ የቀነስነው ነገር የለም፡፡”
ብለው መለሱለት፡፡
አንቶኒሊም ድጋሚ የተጻፈውን ውል ለማስቀየር ብዙ ቢናገርም የሚሰማው ስላላገኘ ተበሳጭቶ የተጻፈውን የማሻሻያ ውል ቀዳዶ ጥሎ፤ ውሉን የኢጣሊያ መንግሥት በጦር ኃይል እንደሚያስከብር በተናገረ ጊዜ፣ ይህን ንግግር የሰሙት እቴጌ ጣይቱ እየሳቁ፤
“የዛሬ ሳምንት አድርገው፡፡
በዚህ የሚደነግጥልህ የለም፡፡
ሂድ የፎከርክበትን አድርግ፡፡
እግሩን ለጠጠር፣ ደረቱን ለጦር ሰጥቶ አገሩን የሚያድን ሰው በዚህ የሌለ አይምሰልህ፡፡
የገዛ ደሙን ገብሮ ለገዛ አገሩ መሞት፤ ጌጥ ነው እንጅ ሞት አይባልም፡፡
አሁንም ሂድ አይምሽብህ፤ የፎከርክበትን በፈቀድህ ጊዜ አድርገው፡፡
እኛም ከዚህ እንቆይሀለን፡፡”
በማለት ወኔ የተሞላው የጀግንነት መልስ መለሱለት፡፡

እቴጌ ጣይቱ ቀጥለውም፤
“...እኔ ሴት ነኝ፡፡ ጦርነት አልወድም፡፡
ግን እንዲህ መሳዩን ውል ከመቀበል፣ ጦርነትን እመርጣለሁ!”
በማለት ተናገሩ፡፡
በአቶኒሊ ንግግር የተናደዱት ዳግማዊ ምኒልክም፤ ውሉን በተዋዋሉ በአራተኛው ዓመት ለአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት ሁሉ የውጫሌን ውል ማፍረሳቸውን ገልፀው ጻፉ፡፡
የዳግማዊ ምኒልክ ደብዳቤ ከደረሳቸው መንግሥታት መካከል፤
የምኒልክ ወዳጅ የሆኑት፤ የእንግሊዝ ንግሥት ቪክቶሪያ ለዳግማዊ ምኒልክ በጻፉት ደብዳቤ፤ "ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በቀላሉ መያዝ ስለምትችል፤ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ጥገኝነት ስር ብትቆይ ይሻላል፡፡" በማለት ገለፁላቸው፡፡
የጀርመኑም ንጉሠ ነገሥት፤ "በኢጣሊያ ጥገኝነት ስር መቆየቱ ስለሚሻል ጉዳዩን እንደገና አስቡበት፡፡" የሚል የምክር ደብዳቤ ለዳግማዊ ምኒልክ ጻፉላቸው፡፡
በዚህ ምክንያት ዳግማዊ ምኒልክ፤ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ጣሊያኖች በሙሉ አገራቸውን ለቀው እንዲወጡ አዘው፤ ወደፊትም ማንኛውም ኢጣሊያዊ ሰው ወደአገራቸው እንዳይመጣ ለኢጣሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቁ፡፡
የኢጣሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የዳግማዊ ምኒልክ ደብዳቤ እንደደረሰው፤ ዳግማዊ ምኒልክን አባብሎ ውሉን እንዲቀበሉ ለማድረግ፤ ሁለት ሚሊዮን ጥይት ገፀ በረከት አስይዘው ላኩ፡፡
ዳግማዊ ምኒልክም ውሉን የኢጣሊያ መንግሥት ባለመቀበሉ ማዘናቸውን ገልፀውና፣ የተላከውን ስጦታ ተቀብለው፣ እግዚአብሔር ይስጥልኝ ብለው አሰናበቱት፡፡
ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ፤ በ 1887 ዓ.ም. የኢጣሊያ ጦር አድዋ ገብቶ አገሩን ያዘ፡፡ በማከታተልም፤ አዲግራትና መቀሌን ተቆጣጠረ፡፡
እሰከ አክሱም ድረስ ዘልቆ በመግባትና ለሕዝቡም ልብስና ማባብያ በመስጠት፤ “ከምኒልክ አገዛዝ ነፃ ላወጣችሁ ነው የመጣሁት፡፡” የሚል የሀሰት ፐሮፓጋንዳ መንዛቱን ቀጠለ፡፡
በማከታተለም ጣሊያኖች፤ ወደፊት እየገፉ አጋሜን፣ እንደርታንና አምባላጌን ያዙ፡፡
ምንም እንኳን በወቅቱ በአገሪቱ ላይ አምስት አመት የቆየ ከባድ ረሀብ የደረሰ ቢሆንም፤ ምኒልክ ያንኑ ረሀብተኛ ሕዝብ ለማዝመት ወስነው ከዚህ የሚከተለውን የክተት አዋጅ አወጁ፡፡
Menilk Proclamation
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ለዐድዋ ጦርነት ያወጁት አዋጅ



ቀደም ብለው ወደ ኢትዮጵያ የገቡት የኢጣሊያ
ሰላዮች ኢትዮጵያን ከፋፍሎ ለመግዛት አጥብቀው ሰርተዋል

በተለይ ትልቅ ተደማጭነትና የመሪነት ስብዕና አላቸው ብሎ ያመነባቸውን ኢትዮጵያዊ መሳፍንትን ከንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በመነጠልና ንጉሠ ነገሥቱንም አሶግዶ አላማቸውን ለማሳካት የዐድዋ ጦርነት ከመጀመሩ ሁለት ዓመት በፊት፤ በነሐሴ እና መስከረም ወር 1886 ዓ.ም. የኢጣሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ብላክ ሆነው ለጀነራል ባራቴየሪ መመሪያ ሰጥተው ነበር፡፡
ባራቲየሪም፤ በተሰጠው መመሪያ መሰረት፤ የተነደፈውን መርሃ ግብር ለመተግበር፤ በኢትዮጵያ ሁለት የተለያዩ መንግሥታት ለመፍጠር እንዲቻል የራሱን ሰዎች አሰማራ፡፡
በእቅዳቸውም መሰረት፤ ሰሜናዊው የኢትዮጵያ ክፍል፤ በራስ መንገሻ ዮሐንስ ስር እንዲሆንና፣ እንዲሁም በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል ደግሞ በልዑል ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል ስር ሆነው፣ ነገር ግን ሁለቱም መንግሥታት በኢጣሊያ አስተዳደርና ጥበቃ ስር እንዲሆኑ ለማባበል ከፍተኛ ጥረት አድርገው ነበር፡፡
ሌላው ቀርቶ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ አጎት የሆኑትን ራስ ዳርጌ ሳህለ ሥላሴን ሳይቀር ወደ ኢጣሊያ እንዲገቡ ለማባበል ሞክረው ነበር፡፡ ይሁን እንጅ የኢጣሊያኖች ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡...የበለጠ ለማንበብ-->ሊንክ
ናሬቲ የተባለው የኢጣሊያ ተወላጅ፤ አፄ ዮሐንስን፣ አንቶኒሊ የተባለው የኢጣሊያ ተወላጅ ደግሞ፤ ለንጉሥ ምኒልክ ወዳጅ መስለው እየቀረቡ፤ አፄ ዮሐንስንና ንጉሥ ምኒልክን በከፋፍለህ ግዛው አስተሳሰብ ነገር እየጎነጎኑ እርስ በርስ ያጣሏቸው ነበር፡፡
አፄ ዮሐንስ መተማ ላይ ከሞቱ በኋላም፤ እነዚህ ወዳጅ መስለው የሚቀርቡት ጣሊያኖች፤ የትግራይ ገዥ የነበሩትን ራስ መንገሻንም እንዲሁ፤ ከጣሊያን ጋር ከተባበሩ፣ ዙፋን ላይ እንደሚያሰቀምጧቸው ቃል በመግባት እስከማስከዳት ደርሰው ነበር፡፡
በሐረርጌም የራስ መኮንን ወዳጅ መስሎ የቀረበው የኢጣሊያ ሰላይም በበኩሉ፤ ራስ መኮንን ጉብኝት ላይ በነበሩበት ወቅት፤ ሰለኢጣሊያ ጦር ብዛትና ዘመናዊነት እያስረዳ፤ ከመዋጋት ይልቅ የኢጣሊያንን ጥያቄ መቀበሉ እንደሚያዋጣ በመንገር ፍርሀት ለማሳደር ጥረት ቢያደርግም፣ አልተሳካለትም፡፡
ለኢጣሊያ ሰላዮች ያልተበገሩት፤ የመረብ ምላሽ ገዥ የነበሩት ራስ አሉላ እንግዳ ነበሩ፡፡
ራስ አሉላ፤ የኢጣሊያ ሰላዮችን ተግባር ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ትግራይን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ ያሉትን የኢጣሊያ ሰላዮች ሁሉ እየለቀሙ ያስሩ ነበር፡፡
ሆኖም በኢጣሊያ ሰላዮች የማባበሉ ተግባር ራስ አሉላም ጋ እንደደረሰ ለንጉሥ ምኒልክ ሲያጫውቱ፤
“...ጃንሆይ፤ እነዚህ ጣሊያኖች ዓይናቸው ታውሯል ልበል? እኔንም እኮ አባበሉኝ፡፡”
በማለት ነግረዋቸዋል፡፡
አፄ ዮሐንስም በበኩላቸው፤ በራስ አሉላ የታሰሩትን የኢጣሊያ ሰላዮች ፍታ እያሉ ስለሚያስፈቷቸው ራስ አሉላ በጣም ይበሳጩ ነበር፡፡
ጣሊያኖች፤ የወሎውን ራስ ሚካኤልንም በኋላ (ንጉሥ ሚከኤል) ወደ እነርሱ ለማሰለፍ ሲሉ፤
“እንደገና ወደ ጥንት ሐይማኖትዎ ተመልሰው የእስላም ሐይማኖት ንጉሥ ይሆናሉ::”
እያሉ ስለሰበኳቸው፣ ወደ ጣሊያኖች ሊገቡ በቋፍ እንደነበሩ ተነግሯል፡፡
የኢጣሊያ ሰላዮች ኢትዮጵያ ገብተው የመከፋፈል ተግባር መፈፀማቸውንና የኢትዮጵያ መንግሥት ደካማ መሆኑን ለማስረዳት፤ ጀነራል ባራቴሪ ለኢጣሊያ የውጭ ጉዳይ በጻፈው ድበዳቤ፣
“- የኢትዮጵያ ራሶች ሁሉ ተለያይተዋል፡፡
- ሁሉም የሚሠራውና የሚያስበው የየግሉን ጉዳይ ብቻ ነው፡፡
- የጎጃሙ ንጉሥ ለምኒልክ የውስጥ ጠላት ነው፡፡
- የትግራዩ ራስ መንገሻ አሁንም እያንገራገረ ነው፡፡
- የወሎው ራስ ሚካኤል ከኛ ጋር እየተነጋገረ ነው፡፡
- ራስ መኮንንም ጦርነቱ እንዳይካሄድ የተቃውሞ ተንኮል እየሠራ ስለሆነ፣
ጦርነቱ ሲጀመር በንጉሡ ላይ ይሸፍታል፡፡”
በማለት ጽፏል፡፡
አንዳንድ ሰዎችም፤ የኢጣሊያ መንግሥትን ገናናነትና፣ ከኢጣሊያ ዘመናዊ መሣሪያ ጋር ጦርነት ለመግጠም ያለመቻሉን የሚያስተማምን ማስረጃ እያቀረቡ የኢጣሊያ መንግሥት በሚፈልገው መንገድ ብንታረቅ ይሻላል እያሉ ዳግማዊ ምኒልክን በመምከር ለማግባባት ሞክረዋል፡፡
ይህን በመሳሰለው ግርግር ግራ የተጋቡት ዳግማዊ ምኒልክ፣ መኳንንቱን ሁሉ ሰብስበው፤
“...አንፍራ፡፡ እኔ እንደሆንኩ መዝመቴን አልተውምና ሰለ ኢጣሊያ ዘመናዊ መሣሪያና ገናናነት አትንገሩኝ፡፡
ኃይል የእግዚአብሔር ነውና እጋጠማለሁ፡፡
ብትዘምቱም፣ ብትቀሩም፣ ሬሳዬን ከጦር ሜዳ ፈልጉት፡፡
ጠላትን ከኋላ አስቀምጦ መዝመት አይቻልምና በየግዛታችሁ ያሉትን ጣሊያኖች አባሩ…፡፡”
በማለት ትእዛዝ ሰጡ፡፡

ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር ባቀደችበት ወቅት፤
በዳግማዊ ምኒልክ ላይ ሸፍተው የነበሩት ደጃዝማች ጓንጉል ዘገየ የተባሉ ሰው፤ በአገሬ ላይ የውጭ ጠላት ሊወራት ሲመጣ ዝም አልልም በማለት፤
“የእርስዎና የእኔ ጉዳይ ቀርቶ ይማሩኝና መጥቸ ከእርስዎ ጋር ሆኘ ጠላትን እየተዋጋሁ ልሙት፡፡” ብለው ዳግማዊ ምኒልክን አስፈቅደው ከሠራዊቱ ጋር መቀላቀላቸው፤
ኢትዮጵየውያን በተለያዬ ጉዳይ እርስ በርስ ባይስማሙም፤ የውጭ ጠላት ሲመጣ ግን ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው፤ በጠላት ላይ አንድ ሆነው እንደሚቆሙ
የሚያሳይ ተግባር ነው፡፡


ልዑል ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል፤ ለአምባላጌ ውጊያ የኢትዮጵያ ሠራዊት የጦር አበጋዝ (አዛዥ) በመሆን፤
  1. ራስ ወሌን፣
  2. ራስ ሚካኤልን፣
  3. ራስ መንገሻ አቲከምን፣
  4. ራስ አሉላን፣
  5. ደጃዝማች ወልዴን፣
  6. ፊታውራሪ ገበየሁን
  7. ፊታውራሪ ተክሌን፣
  8. ሊቀ መኳስ አድነውን እና፣
  9. ቀኛዝማች ታፈሰን
ይዘው ጣሊያን ወደመሸገበት የአምባላጌ ምሽግ ደረሱ፡፡

Ras Mekonnen at the battle of Amba Alage
ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል
በአምባላጌ ውጊያ ላይ ያሳዩትን
የጦር መሪነትና ያደረጉትን የጀግንነት
ተጋድሎ የሚያሳይ ስዕል ለትሪቡን
የተባለው የፈረንሳዩ ጋዜጣ ታህሳስ
20 ቀን 1888 ዓ.ም. አትሞ አውጥቶታል
ይህ የተፈጥሮ ምሽግ የሆነው አምባላጌ፣ በኢጣሊያ የጦር አዛዥ በሻለቃ ቶዞሊ የሚመራው የኢጣሊያ ጦር ቀድሞ ተቆጣጥሮት ስለነበረ፤ የኢትዮጵያ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ራስ መኮንን የኢጣሊያ ጦር ሥፍራውን ለቆ እንዲወጣ በመደራደር ላይ ነበሩ፡፡
የኢጣሊያ ጦር በሰላም ቦታውን እንዲለቅ በደብዳቤ ቢጠየቀም፤ ቦታውን በመልቀቅ ፈንታ ተጨማሪ ጦር ጠይቆ ራሱን ካጠናከረ በኋላ አለቀም የሚል መልስ ሰጠ፡፡
ከዚህ በኋላ የጦር አዛዡ ራስ መኮንን ከእርሳራቸው ጋር የዘመቱትን የጦር አበጋዞች ከምሽጉ ግራና ቀኝ አቅራቢያ አሰልፈው አና ራሳቸውም በመሐል ሆነው የአምባላጌ ተራራን ከበቡት፡፡
በዚህም መሰረት፤ በኢጣሊያና በኢትዮጵያ መካከል የመጀመሪያው ውጊያ ህዳር 29 ቀን 1888 ዓ.ም. አምባላጌ ላይ ተጀመረ፡፡

Battle of Amba Alage
በአምባላጌው ምሽግ የጣሊያን
ወታደሮች አዛዥ የሆነው
ሻለቃ ቶዜሊ በኢትዮጵያ ወታደሮች
ሲገደል የሚያሳየውን ስዕል
ለትሪቡን የተባለው የፈረንሳዩ ጋዜጣ
ህዳር 28 ቀን 1888
ዓ.ም. አትሞ አውጥቶታል
የግንባር ቀደም የጦር መሪው ጀግናው ፊታውራሪ ገበየሁ (አባ ጎራው)፤ የታመሙት ህመም ሳይገታቸው፤ ሠራዊታቸውን እየመሩ ሊታሰብ በማይችል ድፍረትና ወኔ የአምባላጌን አቀበት እየተዋጉ ወጥተው አምባላጌ ምሽግ ዘንድ ደረሱ፡፡
ስለምሽግም ሆነ ዘመናዊ የጦር ትምህርት የሌለው የኢትዮጵያ ሠራዊት አምባላጌ የመሸገውን የኢጣሊያ ጦር ምሽጉ ድረስ እየሄደ በያዘው አሮጌ ጠመንጃ የጠላትን ወታደር ይቆላው ጀመር፡፡
የፋሽስት ኢጣሊያ ጦር በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ የመድፍ ጥይት በተከታታይ አዘነበበት፡፡

የኢትዮጵ ሠራዊት ግን፤ ጠላትን እየገደለ፤ እራሱም እየወደቀ ውጊያውን ያለማቋረጥ በጀግንነት ቀጠለ፡፡

ውጊያው ለሁለት ሰዓት ያህል ተፋፍሞ ከተካሄደ በኋላ፤ የኢጣሊያ ወታደሮች ቦታቸውን እየለቀቁ መሸሽ ጀመሩ፡፡
የኢትዮጵያ ሠራዊትም የሚሸሸውን የጠላት ጦር እየተከታተለ ሲወጋ የኢጣሊያ ጦር አዛዥ ሻለቃ ቶዞሊ ወታደሮቹን አስከትሎ ሲሸሽ በሰባት ጥይት ተመቶ ተገደለ፡፡

አንድ የኢጣሊያ የጦር አዛዥ ስለውጊያው ሲናገር፤
“...ጦርነቱ ዋጋ ያለው አይመስለኝም፡፡
...መድፎቻችን ያለማቋረጥ ሲተኮሱ፤ ጠላቶቻችን ሲወድቁ፤ ሲቆስሉና ሲሞቱ እናያለን፡፡
...ግን ጠላቶቻችን ብዛታቸው ሳይቀንስ እንዳሉ ሆነው ወደፊት ይመጡብናል፡፡
...እጅግ በጣም ብዙ ናቸው፡፡
…ግራና ቀኝ እንደቀለበት ከበውናል፡፡”
በማለት ጽፏል፡፡
ጣሊያኖች የሚቆስሉባቸውን ወታደሮች ወደ መቀሌ ማጓጓዝ ቀጥለዋል፡፡
ራስ አሉላ እንግዳ ጦር የተወሰነውን የኢጣሊያ ምሽግ በመቆጣጠሩ፤ የኢጣሊያ ወታደሮች ስቃይ እየበዛ ሄዶ ወደ መቀሌ የመሸሻ መንገዳቸውም ተዘጋ፡፡
ከአምባላጌ ምሽግ የኢጣሊያ ወታደሮችን ሽሽት በተመለከተ፤ መሐመድ የተባለው ሶማሊያዊው የኢጣሊያ ወታደር፤
“...በቅሎ ጭነው ከሚጓዙ ሰዎች ጋር ተደባልቄ ስጓዝ፤
... አበሾች በጥይት ተቀበሉን፡፡
ከየድንጋዩ ኋላ አበሾች ተደብቀው ኖሮ፤ ከላያችን ይተኩሳሉ፡፡
ከፊታችንም ይተኩሳሉ፡፡
ከጎናችንም ይተኩሳሉ፡፡
መድረሻ አሳጡን፡፡
...በዚያ ላይ በቅሎዎች እየረጋገጡን ያልፋሉ፡፡
በግራና በቀኝ የኛ ወታደሮች ሬሳና ቁስለኛ ተከምሯል፡፡
የቆሰሉት ሰዎቻችን እርዱን! እርዱን! እያሉ ይጮሃሉ፡፡ ግን የሚሰማቸው የለም፡፡
በየትኛውም ቦታ አበሾች እየተከታተሉ ያለማቋረጥ ይተኩሱብናል፡፡
የእኛ መድፍ ተኳሾች ከእኛ ጋር ሲሸሹ ሳይ ተሰፋ ቆረጥኩ፡፡
...በጉዞዬ ላይ አንድም የኛን መኮንኖች አላየሁም፡፡
እኔም አንድ ቦታ ተደብቄ ራሴን አዳንኩ፡፡”
በማለት ተናግሯል፡፡
በዚህ አይነት የአምባላጌው ጦርነት በኢትዮጵያውያን ድል አድራጊነት ተጠናቀቀ፡፡

በአምባላጌው ጦርነት፤ 1ሺህ 300 የኢጣሊያ ጥቁር ወታደሮችና 20 የጦር መኮንኖች መሞታቸውን ራሳቸው ጣሊያኖቹ አምነዋል፡፡
ከአምባላጌ ምሽግ ከሞት የተረፈው የኢጣሊያ ጦር ከ15 ቀናት በኋላ መቀሌ ላይ ተሰበሰበ፡፡
ከተረፉትም መሀል፤ አንዳንዱ፤ ራሱ በሰይፍ የተገመሰ፣ ትከሻው የተቆረጠና በጥይት የቆሰለ ይገኙበታል፡፡



Battle of Mekele Fort
ጣሊያን የተቆጣጠረውን የመቀሌን
ምሽግ ለማስለቀቅ የኢትዮጵያ
ጀግኖች በቆራጥነት ሲዋጉ
የሚያሳይ ስዕል
ከአምባላጌ ጦርነት የተረፈው የኢጣሊያ ሠራዊት ወደ መቀሌ ሸሽቶ ምሽግ ሰርቶ ታጎረ፡፡
የኢጣሊያ ሠራዊት ጉድ የሆነውና ድል ተደርጎ የአምባላጌ ምሽጉን ለቆ የወጣው፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት በባዶ እግሩ ምሽጋቸውን ሰብሮ ገብቶ በጀግንነት በመዋጋቱ ነበር፡፡
ከአምባላጌ ውድቀታቸው ተምረው፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት ለእግሩ ጫማ እንደሌለው ስለሚያውቁ፤ የመቀሌ ምሽጋቸውን በግንብ፣ በሽቦና በተሰባበረ ጠርሙስ አጠናክረው እንደማይደፈር አድርገው ሠሩት፡፡
እዚህ ላይ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት፤ አገር ወዳዱ የትግራይ ሕዝብ ለ5 ተከታታይ ቀናት፤ ማንም ሳያዘው በራሱ ፈቃድ እየወጣ፤ በኢጣሊያ ምሽግ ላይ ሲተኩስ እንደነበረ ተዘግቧል፡፡
ታህሳስ 29 ቀን 1988 ዓ.ም. ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ መቀሌ ከደረሱ በኋላ፤ የጦር አለቆች የሆኑትን እነ ራስ መኮንንን ሰብስበው፤
“...አንድ የጣሊያን ሹም እናንተን ሁሉ ንቆ እስኪመሽግ ድረስ ዝም ብላችሁ በመቆየታችሁ አፈርኩባችሁ፡፡”
በማለት ተናግረዋቸዋል፡፡
የመቀሌ የጠላት ምሽግ በወንዶች ጀግንነት አልፈታ ሲል በሴት ብልሀት ተተካ፡፡
እቴጌ ጣይቱ፤ ከመቀሌ የኢጣሊያኖች ምሽግ በግምት 75 ሜትር ርቀት የሚገኘውን የውሀ ጉድጓድ፤ ጣሊያኖች ውሀ እንዳይቀዱ ለማድረግ 500 በሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች እንዲያዝና እንዲጠበቅ አዘዙ፡፡
የኢጣሊያ ወታደሮች የውሀው ጉድጓድ ይያዛል ብለው አላሰቡም፡፡
እቴጌ ጣይቱም ውሃውን ለሚጠብቁት ወታደሮች፤ እንጀራ በወጥ እየተፈተፈተ በመሶብ ሆኖ፣ ፍሪዳው ታርዶ፣ ሥጋው ተዘጋጅቶና ጠጁ በብዙ የቀንድ ዋንጫ እየተሞላ በየቀኑ ሌሊት ሌሊት ይልኩላቸው ነበር፡፡
የኢጣሊያ ወታደሮች የሚጠጡት ውሀ ካለማግኘታቸውም በላይ፤ የልዑል ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤልና የራስ አሉላ ሠራዊት በጥይት ይደበድባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሠራዊት የመቀሌን ምሽግ ስብርባሪ ጠርሙስ እያለፉና የሽቦውን አጥር በጎራዴ እየበጣጠሱ ሊያልፉ ሲሞክሩ የጣሊያን ወታደር በጥይት ይመታቸው ነበር፡፡
ጣሊያኖች ራሳቸው እንደጻፉት፤
“...አንድ ኢትዮጵያዊ ወታደር፤ የምሽጉን የሽቦ አጥር ለማለፍ ሲሞክር ገላው በሽቦው ተበሳስቶ፤ ደሙን እያዘራ ግንቡ ሥር ሆኖ ግንቡን አፍርሶ ለመጣል፣ የግንቡን መሠረት ሲቆፍር በጥይት ተገደለ፡፡
...ይህ እንዴት አይነት ጀግንነት ነው?”

በማለት ምስክርነታቸውን ሰተዋል፡፡
በመቀጠልም ሲጽፍ፤
“ በምሽጉ ውስጥ ያሉ የጋማና የቀንድ ከብቶች በውሀ እጦት መሞት ጀመሩ፡፡ በሕይዎት ያሉትም እንሰሳት፤ የውሀ ማጠራቀሚያውን ገንዳ ከበው ውሀውን ሰዎች እንዳይቀዱ ከለከሉ፡፡
...እኛ የኢጣሊያ መኮንኖች ፊታችንን የታጠብነው፤ የሌሊቱን ውርጭ ጤዛ በፎጣችን እየጠረግን በማበስ ነበር፡፡

በማለት ተናግሯል፡፡
የገንዳው ውሀ ተቆጣጣሪ የሆነው የኢጣሊያ ወታደር በምሽጉ ያሉትን ወታደሮች ሰበስቦ፤
“...የውሀ ነገር አከተመ፡፡ ዛሬ የሚታደላችሁ ውሀ ለመጨረሻ ጊዜ ነው፡፡
...ዛሬ የሚታደላችሁን ውሀ በጥንቃቄ ያዟት፡፡
...አንዲት ጠብታ ከመሬት ጠብ እንዳትል ተጠንቀቁ፡፡
...ውሀው ይሸታል፡፡ በጣም የቆሸሸ ነው፡፡ ወደ ቢጫነት ተቀይሯል፡፡
...ወታደሮቹ ግን የሚታደላቸውን ውሀ እንደብርቅ ይመለከቱት ነበር፡፡”

በማለት ተናግሯል፡፡
ፊልተር የተባለው ኢጣሊያዊ እንደጻፈው፤
“...ምኒልክ አሰጠርተውኝ ከድንኳናቸው ገባሁ፡፡ እነደገባሁም እንዲህ አሉኝ፤
...እናንተ እኛን ለማሸነፍና ድል ለማድረግ መታችኋል፡፡
የኢትዮጵያንም ሕዝብ ከባርነት አገዛዝ እናወጣሃለን ትላላችሁ፡፡
ነገር ግን እንኳን የኢትዮጵያን ሕዝብ፣ እነዚያን በምሽጋቸው የታፈኑትን ወገኖቻችሁን እንኳን ለማውጣት አልቻላችሁም፡፡
...የእናንተ ሰዎች በውሀ ጥም እንዲሞቱ ማድረግ እችላለሁ፡፡ ይህን ለባራቴሪ ንገረው፡፡
ቅዱሳን መላእክት ግን፤ ጠላቶቻችንን እንድንወድ ይነግሩናል፡፡
አኔ ክርስቲያን ነኝ፡፡ የአረመኔ ሕዝብ ንጉሥ አይደለሁም፡፡
ስለዚህ እነዚህ ክርስቲያኖች አይሞቱም፡፡
ሰዎችን ላኩና ይውሰዷቸው፡፡
ልትወጉን የምትፈልጉ ከሆነ፤ ባንድነት ሆናችሁ ጠብቁኝ፡፡ እመጣለሁ አሉኝ፡፡”
በማለት ጽፏል፡፡
ምንም እንኳን ምሽጉን በሰላም ለመልቀቅ የዳግማዊ ምኒልክ ፈቃድ ገና ያላገኙ ቢሆንም፤ በምሽጉ ውስጥ ያሉት የጣሊያን ወታደሮች ከጣሊያን መንግሥት፤ ምሽጉን ልቀቁ የሚል ደብዳቤ ሲደርሳቸው፤ደስታቸው ከልክ ያለፈ ነበር፡፡
በኢጣሊያ ያሉ ጋዜጦች፤

“አምባላጌ ላይ ተዋርደንና በጦር ኃይል ተሸንፈን ለቀቅን፡፡
ታላቅ ምሽግ ነው የተባለውንም የመቀሌ ምሽጋችንን ደግሞ በውሀ እጦት ለቀቅን፡፡
ይህ የኢጣሊያን መንግሥት ውድቀት ስለሚያሳይ፤ መንግሥታችን ድል መደረጉን አምኖ ከአበሻ ምድር ለቆ መውጣት አለበት፡፡”

በማለት ጽፈዋል፡፡
በኢጣሊያኑ ንጉሥ ኡምቤርቶ ስም ጀነራል ባረቲየሪ በጻፈው ደብዳቤ፤ የመቀሌን ምሽግ ለአበሻው ንጉሥ እነዲያስረክቡ ታዘዘ፡፡ ከምሽጋቸውም መውጣት የሚችሉት ነጭ ባንዲራ ሲሰቅሉ መሆኑን ተነገራቸው፡፡
በመጨረሻም በጅሮንድ ባልቻ ሳፎ (በኋላ ደጃዝማች) ጣሊያኖች ተቆጣጥረውት በነበረው የመቀሌ ምሽግ ውስጥ ገብተው የኢትዮጵያን ባንዲራ ተከሉበት፡፡
የኢጣሊያ ወታደሮች ምሽጉን ለቀው ሲወጡ በደስታ ተውጠው፣ ግራና ቀኝ ቆመው በሚሰድባቸው የኢትዮጵያ ሠራዊት መሀል ሲያልፉ፤ የኢትዮጵያ ሠራዊትን ክልል ለማቋረጥ አራት ሰዓት ፈጅቶባቸዋል፡፡
የኢጣሊያ መንግሥት፤ መቀሌ ላይ ስለተያዙት የኢጣሊያ ወታደሮች ጉዳይ በዕርቅ ለመጨረስ ስብሰባ ተቀምጦ ነበር፡፡
የኢጣሊያ ጦር፤ በአምባላጌና በመቀሌ በተደረጉት በሁለቱም ውጊያዎች ድል በመደረጉ፤ ልታረቅ ማለቱ አሳፋሪ ነገር ሆነባቸው፡፡
በዚህ ላይ የኢጣሊያ ጋዜጦች፤ ሽንፈታቸውን አሳፋሪ ተግባር ነው እያሉ መንግሥታቸውን ይወቅሱና ሕዝቡን ይቀሰቅሱ ስለነበር፤ ሕዝቡም፤

“ሁለት ጊዜ በጥቁሮች በመሸነፋችን ታላቁ የኢጣሊያ መንግሥት በዓለም ፊት ተዋረደ፡፡ ...ክብራችን ይመለስ፡፡ ...እንዋጋ፡፡”

እያለ መጮሁን ቀጠለ፡፡
የኢጣሊያ መንግሥትም ውጊያውን እንዳይቀጥል፤ የኢትዮጵያ ጦር የማይበገር ሆነበት፡፡
በዚህም መሠረት፤ የሕዝቡን ጩኸት ለማብረድ ሲል የኢጣሊያ የሚኒስትሮች ካቢኔ ጉዳዩ በዕርቅ እንዲያልቅ ወሰነ፡፡
በኢትዮጵያ ጦር ከመቀሌ ምሽግ ከተማረኩት የኢጣሊያ መኮንኖች ውስጥ፤ አስር መኮንኖች በመያዣነት ቀርተው፤ የዕርቁን ጉዳይ እንዲያስፈጽም፤ አንድ የጣሊያን የሻለቃ መኮንን ወደ ጀነራል ባራቴሪ ተላከ፡፡
ለዕርቁ የተላከው የኢጣሊያ መኮንንም፤ ጣሊያኖች ያቀረቡትን የዕርቅ ድርድር ይዞ ዳግማዊ ምኒልክ ዘንድ ቀርቦ፤ የመጣበትን ጉዳይ እንዲናገር ታዘዘ፡፡
የተላከው የኢጣሊያ መኮንን ካቀረበው የዕርቅ ሀሳብ በጥቂቱ ሲገለጽ፤
  1. በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት ያሉ ሹሞች ሁሉ የኢጣሊያን የበላይነት ማወቅ አለባቸው፡፡
  2. እስከ ተከዜ ወንዝ ድረስ ያለው የኢጣሊያ ግዛት ይሆናል፡፡
  3. ጠቅላላ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ጥገኝነት ሥር ትሆናለች፡፡
  4. የውጭ አገር ሰው ኢትዮጵያ ገብቶ ማንኛውንም ሥራ ለመሥራት ቢፈልግ በቅድሚያ ከኢጣሊያ መንግሥት ማስፈቀድ አለበት፡፡
  5. የቀረጥና የግብር ጉዳይ በኢጣሊያ ሕግና ደንብ መሠረት ይሆናል፡፡
  6. ጣሊያኖች በኢትዮጵያ ውስጥ መሬት ለመግዛት ኃይል አላቸው፡፡
  7. ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ንጉሦችና ራሶች ሁሉ የኤርትራውን የኢጣሊያ ገዥ ትእዛዝ ይቀበላሉ፡፡
የሚል ይገኝበታል፡፡



ከትግራይ ገዥ ከራስ መንገሻ ጋር በመጣላት ከድተው ወደ ጣሊያኖች ገብተው የነበሩት፤ ራስ ስብሐትና ደጃዝማች ሐጎስ ተፈሪ፤
‘ከጠላት ጋር በማበር ወንድሞቻችንን አንወጋም’ በማለት ተከታዮቻቸውን ከነመሣሪያቸው ይዘው፤ ጣሊያኖችን ከድተው ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ገቡ፡፡
ዳግማዊ ምኒልክም ሁለቱን መኳንንቶች በፍቅር ተቀብለውና ሸልመው፤ አገራችሁን ጠብቁ ብለው አሰናበቷቸው፡፡
ሁለቱም መኳንንቶች ከተሰናበቱ ከሶስት ቀን በኋላ፤ ከአዲግራት ከሚመጣው የኢጣሊያ ጦር ሠራዊት ጋር ጦርነት ገጥመው 360 የኢጣሊያ ወታደሮችን መግደላቸውን ለዳግማዊ ምኒልክ መልእክት ልከዋል፡፡








ምንጭ፤
  1. "አጤ ምኒልክ"  ደራሲ፡- ጳውሎስ ኞኞ የካቲት ወር 1984 ዓ.ም.
  2. "የኢትዮጵያ ታሪክ ከ 1847 እሰከ 1983"  ደራሲ፡- ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ
  3. "የኢትዮጵያ ታሪክ - ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ"  ደራሲ፡- ተክለ ጻድቅ መኩሪያ 1961 ዓ.ም.
  4. "መራራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ "  ደራሲ፡- ታዬ ቦጋለ አረጋ 2011 ዓ.ም.