Content-Language: am ደጃዝማች አፈወርቅ ወልደ ሰማያት
header image





ደጃዝማች አፈወርቅ ወልደ ሰማያት



የቆራሔው ጀግና የደጃዝማች አፈወርቅ
ወልደ ሰማያትን የአርበኝነት ታሪክ ያዳምጡ















1. ትውልድና የትዳር ሕይዎት

Dejazmach Afework Woldesemait
የቆራሄው ጀግና ደጃዝማች
አፈወርቅ ወልደ ሰማያት
አፈወርቅ ወልደ ሰማያት ከአባታቸው ከመምህር ወልደሰማያት በ1898 ዓ.ም. አቃቂ በሰቃ በተባለ ሥፍራ ተወለዱ፡፡ በልጅነታቸው የአማርኛ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡
አቶ አፈወርቅ ገና በጎልማሳ ዕድሜያቸው ወይዘሮ ተዋበች ካሴ ከተባሉት ሴት ጋር በትዳር ተጣምረው አምስት ልጆችን አፍርተዋል፡፡፡ ሦስቱ ልጆቻቸው በልጅነት ዕድሜያቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ሻለቃ ጌታቸው አፈወርቅ የተባለው ልጃው የክብር ዘበኛ ሠራዊት መኮንን በመሆን አገራቸውን በቅንነት አገልግለው በጡረታ ላይ እንዳሉ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
ትንሹ ልጃቸው አቶ ኃይሉ አፈወርቅ ግን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በተለያዩ አገሮች በዲፕሎማትነት አገራቸውን ሲያገለግሉ ቆይተው በጡረታ ላይ እንዳሉ በደረሰባቸው ሕመም ምክንያት በአገር ቤትም ሆነ በውጭ አገር ሕክምና ቢደረግላቸውም ሕመማቸው ስለጸና መጋቢት 8 ቀን 2001 ዓ.ም. በተወለዱ በ78 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

2. በኦጋዴን የፈፀሙት የጀግንነት ገድል


በሶማሌያ ጠረፍ በቆራሔ በኩል የነበረውን የኢጣሊያ ጦር ከወታደሮቻቸው ጋር ሆነው ከአንድ ዓመት በላይ መሽገው ይከላከሉ የነበሩት ስመ ጥር አርበኛ ግራዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት ነበሩ፡፡
ከፋሽስት የኢጣሊያ ጦር ጋር በኦጋዴን ግንባር ለተደረገው ጦርነት ቁልፍ የስትራተጂክ ቦታው ቆራሄ የተባለው ሥፍራ ነበር፡፡
ይህን በመረዳትም ደጃዝማች አፈወርቅ፤
“የኢጣሊያ ወታደሮች ቆራሄን ከያዙ፤ መላ ኦጋዴንን እንደያዙ ይቆጠራል፡፡”
በማለት ተናግረው ነበር፡፡
በቆራሄ የግራዝማች አፈወርቅ ምሽግ ዘመናዊ ነው ባይባልም የዓይን ምስክሮች እንዳረጋገጡት ከአውሮፕላን ለሚዘንበው ቦምብ በቂ መከላከያ ነበረው፡፡
በየምሽጎቹም ውስጥ 1 ሺህ 500 የሚሆኑ ወታደሮች እንደነበሩ በታሪክ ተዘግቧል፡፡
ግራዝማች አፈወርቅ የጠላት አውሮፕላን ከሩቅ ቦታ ሆኖ ቦምብ ሲወረውር፤ ኦርሊኮን (Oerloikon) የተሰኘውን ፀረ አውሮፕላን መሣሪያ ይዘው ከሩቁ ሆነው የሚተኩሱ እሳቸው ብቻ በመሆናቸው ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ጠላትን የተፋለሙ ጀግና ነበሩ፡፡
በአካባቢውም የነበረው ፀረ አውሮፕላን መሣርያ የእርሳቸው ብቻ ነበር፡፡
ጥቅምት 6 ቀን 1928 ዓ.ም. የጠላት አውሮፕላን ቦምብ እንደዝናብ ሲያወርድባቸው አፈወርቅ ኦርሊኮኑን በመተኮስ አውሮፕላኖቹን ሲያባርሩ እንደነበር ጂ ኤል ሰቲር የተባለው እንግሊዛዊው ጋዜጠኛ የምስክርነት ቃሉን ሰጥቷል፡፡
ከጠላት ጋር በቆራሄ በተደረገው ጦርነት አፈወርቅ ወልደሰማያት በምሽጋቸው ሆነው በጀግንነት እየተከላከሉ ብዙ የኢጣሊያ ወታደሮች ላይ ጉዳት ካደረሱ በኋላ በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ የኢጣሊያ ወታደሮች ቆራሄን መያዝ ችለዋል፡፡
የግራዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት የጀግንነት ዝና በግንባሩ በነበሩት የኢጣሊያና የሶማሌ ወታደሮች ዘንድ በጣም ገኖ ይወራ ነበር፡፡
በግንባሩ የኢጣሊያ ጦር አዛዣ የነበረው ግራዚያኒ፤ ወደ ጦር ግንባር ብዙ የኢጣሊያ እግረኛ ሠራዊት ሲልክ፤ አፈወርቅ ወልደሰማያት ድል እያደረጉ ሰለሚመልሱት፤ በሶማሌ የነበረውን አይሮፕላን በሙሉ አስነስቶ መሽገው የነበሩትን የኢትዮጵያ ወታደሮች ያስደበድብ ጀመር፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ጀግናው አፈወርቅ ወልደሰማያት፤ የሚዋጉበትን መሣሪያ አስቀምጠው፤ በምትኩ የመድፍ መሣሪያ ይዘው እየተንከባለሉ በቆራጥነት ሲዋጉ በአይሮፕላን ቦምብ ተመተው ቆሰሉ፡፡
ጀግናው አፈወርቅ ወልደሰማያት ቆስለውም ቢሆን በቆራጥነት እየተዋጉ ሳላ ቁስላቸው የበረታ ስለነበረ ወታደሮቻቸው አይተው፤ ከነበሩበት ቦታ አንስተው ወደ ሌላ ከተማ እንውሰድዎት ሲሏቸው አሻፈረኝ ካሉ በኋላ፤

“...እስካሁን ድረስ ከጠላት ጋር በጽኑ ተከላክለን ባቆየነው ምሽግና እናንተ የጦር ጓደኞቸ በምትዋጉበት መካከል አስቀምጡኝ፡፡ ስሞትም ከአይሮፕላን አደጋ ለመከላከያ በተቆፈረው ጉድጓድ ቅበሩኝ እንጅ አደራችሁን ከዚህ ስፍራ ወደ ሌላ እንዳትወስዱኝ፡፡”


በማለት ለወታደሮቻቸው ነገሯቸው፡፡

የግራዝማች አፈወርቅ ወታደሮች የተጠቀሙባቸው መሣሪያዎች ዓይነትና የነበራቸው የመከላከል አቅም የኢጣሊያ ወታደሮችን እጅግ ስላስገረማቸው፤ የኢጣሊያ ፀሐፊዎች ግራዝማች አፈወርቅ 60 የሚጠጉ ፀረ ታንክ መሣሪያዎችና መትረየሶች ነበራቸው በማለት አስመስለውና አጋነው እስከመጻፍ ደርሰዋል፡፡
እውነታው ግን የኢጣሊያ ወታደሮች እንደጻፉት ሳይሆን፤ ስቲር የተባለው የእንግሊዝ ጋዜጠኛ ምስክርነቱን ሲሰጥ፤ ከአንድ ኦርሊኮን ከተሰኘ ፀረ አይሮፕላን መሣሪያና ከአራት ሻል ያሉ መሣርያዎች በስተቀር የተቀሩት ግን ዘመን ያለፈባቸው ኋላ ቀር እንደነበሩ ዘግቧል፡፡
በአንጻሩ፤ ፋሽስት ኢጣሊያ በግራዝማቹ ላይ እና በአካባቢው ያዘመተው የጦር ኃይል ደግሞ፤ ስድስት ባታሊዮን ጦር፣ 150 ተሽከርካሪዎች፣ 9 ታንኮችና 20 ብረት ለበስ መኪናዎች እንደነበሩ ተዘግቧል፡፡
የኢጣሊያ ኃይል በርካታ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች የታጠቀ መሆኑን አፈወርቅ ቀደም ብለው በስለላ ስለደረሱበት ተጨማሪ ጦር ከዘመናዊ የጦር መሣርያ ጋር እንዲላክላቸው ጠይቀው 600 የሚሆኑ ተጨማሪ ወታደሮች ተልኮላቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጅ የተላከላቸው ተጨማሪ ኃይል ቀድሞ ከነበረው ኃይል ጋር ተደምሮም ቢሆን ኢጣሊያ ያሠለፈውን የጦር ኃይል ፈጽሞ ሊመክት የሚችል አልነበረም፡፡

የደጃዝማች አፈዎርቅ የመጨረሻ ፍልሚያ

ጥቅምት 23 ቀን 1928 ዓ.ም. ቁጥራቸው ሃያ የሚደርስ የጠላት አውሮፕላኖች ቦምባቸውን በኢትዮጵያውያ ወታደሮች ላይ ማዝነብ ጀመሩ፡፡ እነዚህን አውሮፕላኖች ከአካባቢው ለማባረር አፈወርቅ የወሰደባቸው ጊዜ 30 ደቂቃ ብቻ ነበረ ሲል በጦር ግንባር የነበረ ስቲር የተባለው የእንግሊዝ ጋዜጠኛ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን አፈወርቅ በወታደሮቻቸው መሀል እየተዘዋወሩ የወታደሮቻቸውን መንፈስ ለማነቃቃት ካደረጓቸው ንግግሮች መካከል፤

“…አብረን እንደበላን አብረን እንሞታለን እንጂ እኔን ጥለህ የት ትሄዳለህ?
በሰላሙ ቀን ከወደድከኝ በዚች ቀውጢ ቀን ብቻዬን ጥለህ የት ትሄዳለህ?
ብቻዬን ጥለኸኝ እንደማትሄድ አውቃለሁ፡፡ እንደምትወዱኝ እወዳችኋለሁ፡፡
በሰላሙ ጊዜ ጭብጦና በሶ ተካፍለን በልተን አሁን እንዴት ይርበናል?
ስንቄን አካፍዬ እንዳበላሁህ የመከራዬም ተካፋይ ሁነኝ፡፡
አፈወርቅ እጁን ለጠላት አይሰጥም!
አንተ የአፈወርቅ ነህና የተቀደሰ እጅህን ላልተቀደሰ ጠላት አትሰጥም፡፡”

በማለት የተለመደ ንግግራቸውን ለወታደሮቻቸው ያሰሙ ነበር፡፡

ጥቅምት 23 ቀን በአንድ በተጣለ ቦምብ አፈወርቅ ቅልጥማቸውንና ቁርጭምጭሚታቸው ላይ ክፉኛ ቆሰሉ፡፡
የደረሰባቸውን ከባድ የሆነ የመቁሰል አደጋ ለመታከም ወደ ደጋሀቡር በመሄድ በቀይ መስቀል የሕክምና ማዕከል ዕርዳታ ማግኘት ይችሉ ነበር፡፡
እርሳቸው ግን ከዓላማቸው ዝንፍ የማይሉ መንፈሰ ጠንካራና የማይበገር ጽናት ስለነበራቸው ለሕክምና ብለው ከወታደሮቻቸው ርቀው ቢሄዱ፤ ጦራቸው የመበተን አደጋ ይደርስበታል ብለው ስለሰጉ መሄዳቸውን ሰርዘው ያለምንም ህክምና ቁስላቸውን አሳስረው ከወታደሮቻቸው ጋር ጠላትን መፋለም ቀጠሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ጥቅምት 24 ቀን 1928 ዓ.ም. በግራዝማች አፈወርቅ የጦር ሰፈርና በአካባቢው የጠላት አውሮፕላን ድብደባው በተጠናከረ መልኩ ቀጥሎ ዋለ፡፡
የግራዝማች አፈወርቅን ምሽግ ለመያዝ ከአውሮፕላኑ ድብደባ በተጨማሪ አንድ ባታሊዮን የኢጣሊያ እግረኛ ጦር፣ አንድ የታንክ ቡድንና በተጨማሪም የዓረብና የሱማሌ የጦር ወታደሮች ያሉበት ወደ ቆራሄ በመገስገስ ላይ ነበር፡፡

የአፈወርቅን መሞት በተመለከተ፤
“ጥቅምት 25 ቀን 1928 ዓ.ም. ግራዝማች አፈወርቅ ቁስላቸውን ስላልታከሙ ህመማቸው እየጠና አካላቸው እየዛለ ሄዶ የጠላትን አውሮፕላን ከሚያሸብሩበት ኦርሊኮናቸው ላይ ዘፍ ብለው ወደቁ፡፡ ይተኩሱትም የነበረው የመሣሪያ ድምፅ ፀጥ ሲል፤ አፈወርቅ መሞታቸው በሠራዊታቸውና በነዋሪው ሕዝብ ዘንድ ታወቀ፡፡”
በማለት በሥፍራው የነበው ስቲር የተባለው ጋዜጠኛ የምስክርነት ቃሉን ሰቷዋል፡፡፡

የጦር ሜዳ ጀግናው አፈወርቅ ወልደ ሰማያት ገና በለጋ እድሜያቸው በተወለዱ በ30 ዓመታቸው ከጠላት ጋር በጀግንነት ሲፋለሙ ሕይወታቸው አለፈች፡፡ ጠላትም እፎይታ አገኘ፡፡ ወታደሮቻቸውም እምባ በእምባ ተራጭተው በዚያው ሕይዎታቸው ባለፈበት ሥፍራ ቀበሯቸው፡፡

ለደጃዝማች አፈወርቅ የተደረገላቸው መታሰቢያ

Tomb of Dejazmach Afework Woldesamyit
ንጉሠ ነገሥቱ በወቅቱ ለደጃዝማች
አፈወርቅ ወልደ ሰማያት በጂጂጋ
ከተማ አሠርተውላቸው የነበረው ሐውልት
በቆራጥ የአመራር ብቃታቸውና የከፈሉትን መስዋዕትነት በመገንዘብ፤ መስዋዕት በሆኑ በ14ኛው ቀን፤ የግራዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያትን የጀግንነት ገድል የሰሙት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጂጂጋ ድረስ ሄደው ለነበረው የኢትዮጵያ ሠራዊት የማበረታቻ ንግግር ካደረጉ በኋላ፤ በፊታውራሪ ጓንጉል ኮላሴ መሪነት ተዋግተው አራት ታንክና በመኪና ላይ የተጠመደ መትረየስ የማረኩትን የኢትዮጵያ ወታደሮችና በውጊያ ወደቆሰሉት ወደ ፊታውራሪ ጓንጉል ሄደው ሽልማት በመሸለም አበረታቷቸዋል፡፡
ከዚያም ግራዝማች አፈወርቅ ወደተቀበሩበት ሥፍራ ድረስ በመሄድ በመቃብሩ ላይ የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል፡፡
ግራዝማች አፈወርቅ፤ ለዚህ ታላቅ ክብር የበቁ የመጀመርያው ጀግና ኢትዮጵያዊ የጦር ወታደር ናቸው፡፡
ግርማዊ ጃንሆይም በማስከተል፤ ለግራዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት የደጃዝማችነት ማዕረግ፤ ለደጃዝማች አፈወርቅ ልጅና ለሌሎች በጦርነቱ የጀግንነት ሥራ ለሠሩ ወታደሮች ሁሉ የማዕረግ ስምና ሽልማት ሰጥተው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል፡፡

የግራዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት መሞት ለኢጣሊያ ሠራዊት እፎይታን ስለሰጠው፤ አዲስ ጦር ልኮ በአይሮፕላን ቦምብ እየደበደበ በመጨረሻ ሥፍራውን ለመያዝ ቻለ፡፡

በቆራጥ የአመራር ብቃታቸውና የከፈሉትን መስዋዕትነት በመገንዘብ በጂጂጋ በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መልካም ፈቃድና ትዕዛዝ አንድ ትምህርት ቤትና አንድ ሆስፒታል በደጃዝማች አፈወርቅ ስም እንዲሰየምና በቆራሄ ላይ ደግሞ ምስላቸውን በያዘ ቅርፅ ሐውልት ተሠርቶ ንጉሠ ነገሥቱ በተገኙበት እንዲመረቅ ተደርጓል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በወታደራዊው ደርግ ዘመነ መንግሥት በጂጂጋ ከተማ ሐውልት እንዲቆምላቸው ተደርጓል፡፡
ቆራሄ ላይ የነበረው ሐውልታቸው በፀረ ሕዝብና በፀረ አንድነት ኃይሎች መፍረሱ በወቅቱ ለነፃነትና ለአገር ክብር ተቆርቋሪ የሆነውን የኢትዮጵያን ሕዝብ እጅግ አሳዝኖ አልፏል፡፡



ምንጭ፤
  1. …ምስጋና፤ ለ ታሪክን ወደኋላ፤  የጽሁፍ ሊንክ
  2. …ምስጋና፤ ለአዲስ አድማስ ኒውስ፤  የጽሁፍ ሊንክ
  3. …ምስጋና፤ ለ አዲስ 1879፤  ዩቲውብ ሊኒክ
  4. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ