1. ልዕልት አይዳ ደስታ
የክቡር ራስ ደስታ ዳምጠው የመጀመሪ ልጅ የሆኑት ልዕልት አይዳ ደስታ መጋቢት 30 ቀን 1919 ዓ.ም. አዲስ አበባ ተወለዱ፡፡
ፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ በፈፀመበት ወቅት ንጉሠ ነገሥቱ ወደ እንግሊዝ አገር ሲጓዙ ልዕልት አይዳም አብረው ተጉዘዋል፡፡
ልዕልት አይዳ እና ሶስት እህቶቿም በሰሜን ዌልስ በሚገኘው ክላሬንደን የሴቶች ልጆች ትምህርት ቤት ገብተው ተምረዋል።
በ1937 ዓ.ም. የማትሪክ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡
በኋላም ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ የትግራይ ልዑል ከሆኑት እና የ
አፄ ዮሐንስ የልጅ፤ ልጅ፤ ልጅ ከሆኑት ከልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ጋር በጥር ወር 1941 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ጋብቻ በመፈፀም አምስት ወንድና አንዲት ሴት ልጅ አፍርተዋል።
ልዕልት አይዳ በአያታቸው በ
በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በበጎ አድራጎት እና በባህላዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ አድርገዋል።
በ1966 ዓ.ም. ደርግ ባለቤታቸውን ለማሰር በተላኩ አብዮታዊ ወታደሮች አማካይነት በመቀሌ ቤተ መንግስት ተይዘው ታስረዋል።
ልዕልት አይዳ በደርግ ጊዜ ለ14 ዓመታት ከታሰሩት የንጉሠ ነገሥቱ የሴት ቤተሰቦች መካከል አንዷ ነበሩ፡፡
ልዕልት አይዳ ከእስር ከተፌ በኋላ የተቋረጠውን የቤተሰብ ህይወታቸውን ከባለቤታቸው እና ከልጆቻቸው ጋር በስደት ቀጠሉ፡፡
ከደርግ ውድቀት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ እና ወደ አዲስ አበባ በመመላለስ ጊዜያቸውን አሳለፉ።
በመጨረሻም ጥር 7 ቀን 2005 ዓ.ም. በተወለዱ በ86 ዓመታቸው በአሌክሳንድሪያ ቨርጂኒያ ሕይወታቸው አልፏል።
2. ልዕልት ሂሩት ደስታ
ልዕልት ሂሩት ደስታ ሚያዝያ 12 ቀን 1922 ዓ.ም. አዲስ አበባ ተወለዱ፡፡
ናትናኤል ቲ ኬኒ የተባለው ጋዜጠኛ በሚያዝያ ወር 1957 የናሽናል ጂኦግራፊክ እትም ላይ፤ “እሷ፤ ሰራተኛ ሲሰራ ስታይ፤ የሚሰራበትን መሳሪያ ወስዳ እንዴት እንደሚጠቀምበት ሰርታ የምታሳይ በጣም ዲሞክራሲያዊ የሆነች፤ የልዕልቶች ልዕልት ነች፡፡” በማለት ገልጿታል።
ልዕልት ሂሩት ደስታ በለንደን ለረጅም ጊዜ በሕክምና ከቆዩ በኋላ በተወለዱ በ84 ዓመታቸው ለንደን በ2006 ዓ.ም. ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡
የቀብር ስነ ሥርዓታቸውም በአዲስ አበባ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።
3. ልዕልት ሰብለ ደስታ
ልዕልት ሰብለ ደስታ ነሐሴ 26 ቀን 1923 ዓ.ም. አዲስ አበባ ተወለዱ፡፡
ልዕልት ሰብለ ደስታም ልዕልት ሶፊያ ደስታ በተሰረጉበት በተመሳሳይ ቀንና ቦታ የወለጋ ጠቅላይ ግዛት የሌቃ ቄለም ሥርዎ መንግስት አልጋ ወራሽ ከሆኑት ከጆቴ ከሚወለዱት ከደጃዝማች ካሣ ወልደ ማሪያም ጋር ተጋብተው አምስት ልጆችን እና 6 የልጅ ልጆችን አፍርተዋል፡፡ የልጆቻቸው ስምም፤
- አምሃ ካሣ
- እመቤት ካሣ
- የሽመቤት ካሣ
- ደብሪቱ ካሣ
- ኮከብ ካሣ
ይባላሉ፡፡
ልዕልት ሰብለ ደስታ ትምህርታቸውን እንግሊዝ አገር በሚገኘው በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ አጠናቀዋል፡፡
እንደ እናቷ ሁሉ ልዕልት ሰብለም የኢትዮጵያ ሴቶች የበጎ አድራጎት ማህበር ፕሬዝዳንት ነበሩ፡፡
በእርሳቸው ጊዜ አዲስ አበባ ላይ ወጣት ሴቶች በሰላም ሠርተው እንዲኖሩ ለማስቻል ለማህበሩ ገቢ የሚያስገኝ እጅግ ዘመናዊ ህንፃ ገንብተው ነበር።
የልዕልት ሰብለ ደስታ ባለቤት ደጃዝማች ካሣ ወልደ ማሪያም በአሜሪካ በፖለቲካል ሳይንስ የማስተርስ ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡
ልዕልት ሰብለ ደስታ ልጃቸው አምሀ ካሣ ተወልዶ አንድ ዓመት ሳይሞላው በደርግ በቄጥጥር ስር ውሎ ለ 13 ዓመታት በእስር ላይ ከቆየ በኋላ በ1980 ዓ.ም. ከእስር ተለቋል፡፡
ካሣ ወልደ ማሪያም በጣም አስተወይ፤ በአስተሳሰብ የበሰሉ፣ አገራቸውን መወከል የሚችሉ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ጠንቅቀው የተረዱና ጠንካራ እምነት የነበራቸው መሆኑን የተማሩበት የተምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ይናገራሉ፡፡
ደጃዝማች ካሣ ወልደ ማሪያም በ1952 ዓ.ም. የንጉሠ ነገሥቱ ልዩ ፀሓፊና የጽሕፈት ሚኒስቴር ምክትል ምኒስትር በመሆን ከተሾሙ በኋላ በሚቀጥለው ዓመት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ፕሬዝደንት ሆነው ተሸሙ፡፡
ካሣ ወልደ ማሪያም የዩኒቨርስቲው ፕሬዚደንት በነበሩበት ጊዜ በቁርጠኝነት እና በትጋት ለስኬት የሚሰሩ ምሁር እንደነበሩ አሜሪካ የተማሩበት የሲያትል ፓሲፊክ ኮሌጅ ፕሬዘደንት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለጉብኝት መጥተው መስክረዋል፡፡
ካሳ ወልደ ማሪያም በፕሬዘዳንትነት በቆዩባቸው ሰባት አመታት ውስጥ፣ ዩኒቨርሲቲው ሰፊ እድገት አሳይቷል። የትምህርት፣ የህክምና እና የህግ ፋከልቲዎችን አቋቁሟል። በኢትዮጵያ ኮሌጅ የገባ ተማሪ ሁሉ ከሞላ ጎደል ያውቋቸዋል።
በአሜሪካም ሆነው በሌላወም የዓልም ክፍል ተቀባይነትን አግኝተዋል፡፡
በ 1961 ዓ.ም. ካሣ ወልደ ማሪያም የወለጋ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመዋል፡፡
ደርግ በ1966 ዓ.ም. ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ክቡር ደጃዝማ ካሣ ወልደ ማሪያም በቁጥጥር ስር ውለው በምኒልክ ቤተ መንግሥት ከታሠሩ በኋላ ሐምሌ 7 ቀን 1971 ዓ.ም. ከታሰሩበት ክፍል ተጠርተው በእስር ላይ ከሚገኙት ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ ዘንድ ተንበርክከው ይፍቱኝ ብለው ፍታትን ከተቀበሉ በኋላ ተወስደው በደርግ ተገለዋል፡፡ አማሟታቸውም እርሳቸው እና ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ ታንቀው እንደተገደሉ ይታመናል፡፡
4. ልዕልት ሶፊያ ደስታ
ልዕልት ሶፊያ ደስታ ጥር 17 ቀን 1926 ዓ.ም. በጅማ ተወለዱ፡፡
ልዕልት ሶፊያ ጥር 23 ቀን 1951 ዓ.ም. የዕውቁ አርበኛና የጦር መሪ የ
ኃይለ ማሪም ማሞ ልጅ ከሆነው ከካፒቴን ደረጀ ኃይለ ማሪያም ጋር አዲስ አበባ ተጋብተው ትዳር መስርተዋል፡፡
ካፒቴን ደረጀ የተወለዱት በ1929 ዓ.ም. ነው፡፡
ካፒቴን ደረጀ እንግሊዝ አገር ከሚገኘው ከሳንደርስት ሮያል አካዳሚ በ1947 ዓ.ም. ተመርቀዋል፡፡
ካፒቴን ደረጀ ከልዕልት ሶፊያ ደስታ ጋር በ1951 ዓ.ም. ከተጋቡ በኋላ ልዑል ደረጀ ኃይለ ማሪያም ተብለው መጠራት ጀመሩ፡፡
ልዑል ደረጀ ኃይለ ማሪያም በ1953 ዓ.ም. በመንግስቱ ነዋይ ተጠንስሶ የነበረውን የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ለማክሸፍ በተደረገው ውጊያ ውስጥ ሕይዎታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡
ልዕልት ሶፊያ ደስታ ከሰሯቸው ሥራዎች ውስጥ፤
- ልዕልት ሶፊያ ደስታ እንጦጦ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት የተሰኘውን የግል ትምህርት ቤት በማቋቋም ራሳቸው በመምራት የደሀ ቤተሰብ የሆኑት ልጆች ጥራት ያለው ትምህርት አግኝተው እንዲማሩ የስኮላርሽፕ ዕድል እንዲሰጥ አድርገዋል፡፡
- ቸሻየር ኢትዮጵያን እና የወጣት ሴቶች ክርስቲያናዊ ማህበር ያሉትን YWCA (Young Womens' Christian Association) የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን በማቋቋም አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡
በአጠቃላይ ልዕልት ሶፊያ፤ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆኑ፣ ለጋስ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በበጎ አድራጎት ስራ በመሰማራት ለኢትዮጵያ ልጆች ብቻ ሳይሆን ለመላው ህጻናት ሳይቀር ትምህርት እንዲያገኙ እና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ከፍተኛ ፍላጎት የነበራቸው ሴት ነበሩ፡፡
ልዕልት ሶፊያ ደስታ በደርግ ቁጥጥር ስር ውለው ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ ለ14 ዓመታት በእስር ቤት ከቆዩ በኋላ በ 1980 ዓ.ም. ከእስር ቤት ሲፈቱ ወደ ጄኔቫ ሄደው ከቆዩ በኋላ ከዚያም ወደ ስዊትዘርላንድ፣ በመጨረሻም ወደ ለንደን ሄደው እዛው መኖር ጀመሩ፡፡ ከጥቂት ጊዚያት ቆይታ በኋላ ህዳር 2 ቀን 1914 ዓ.ም. በተወለዱ በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸውም በለንደን ተፈጽሟል፡፡
ልዕልት ሶፊያ ደስታ እና ልዑል ደረጀ ኃይለ ማሪያም፤ እመቤት ሆይ ሃና ማርያም ምህረተ ሥላሴ ደረጄ የምትባል አንድ ሴት ልጅ ብቻ ሲያፈሩ፤ ደስታ አስፋው የሚባል የልጅ ልጅም አላቸው፡፡
እመቤት ሆይ ሃና ማርያም በ1953 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተወለደች፡፡
እመቤት ሆይ ሃና ማርያም እንግሊዝ አገር በሚገኘው ክላርንደን በሚባለው የልጃገረዶች ትምህርት ቤት ተምራለች፡፡ እመቤት ሆይ ሃና ማርያም፤ የኮሎኔል አስፋው እና የወይዘሮ ዳርምየለሽ ልጅ ከሆነው ከልጅ አክሎግ አስፋው ጋር ተጋብተው ልጅ ደስታ አክሎግ የሚባል ወንድ ልጅ አፍርተዋል፡፡
እመቤት ሆይ ሃና ማርያም ምህረተ ሥላሴ ደረጄ፤ በአስተዳደጓ ወቅት በአዲስ መልክ ያጋጠማትን ችግር፤ ለውጥ እና ጥርጣሬን እንዴት በብቃት ሕይወቷን እንደመራች ልዩ ግንዛቤዎችን የሚያስጨብጥ
"ትናንት ብቻ ነበር" በሚል ርዕስ መፅሃፍ ጽፋ አሳትማለች፡፡
5. ሪር አድሚራል እስክንድር ደስታ
ሪር አድሚራል እስክንድር ደስታ ሐምሌ 30 ቀን 1926 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተወለዱ፡፡
ፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ በፈፀመበት ወቅት ንጉሠ ነገሥቱ ወደ እንግሊዝ አገር ሲጓዙ እስክንድር ደስታ የአንደ ዓመት ህፃን ሆኖ አብረው ተጉዘዋል፡፡
እስክንድር ደስታ በእንግሊዝ አገር ሳለ መሰረታዊ ትምህርታቸውን ከተከታተሉ በኋላ በ1944 ዓ.ም. በ18 ዓመቱ በብሪታንያ የሮያል የባህር ኃይል ኮሌጅን በመቀላቀል ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በባህር ኃይል ኦፊሰርነት ተመርቀዋል፡፡
በኋላም በ1947 ዓ.ም. አዲስ በተቋቋመው በኢትዮጵያ የባህር ኃይል ውስጥ በምክትል መቶ አለቅነት ከተመደቡ ከ3 ዓመት በኋላ በ1950 ዓ.ም. በ24 ዓመታቸው የኢትዮጵያ የባህር ኃይል ምክትል አዛዥ በመሆን ተመደቡ፡፡
በ1966 ዓ.ም. ደርግ መፈንቅለ መንግሥት እንዳካሄደ እስክንድር ደስታ ከምጽዋ ጠፍተው ወደ ጅቡቲ በመጓዝ እዛው ቆዩ፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ከሥልጣናቸው ሲወርዱ እስክንድር ደስታም በደርግ ቁጥጥር ስር ውለው ከታሰሩ በኋላ በተወለዱ በ40 ዓመት ዕድሜያቸው በደርግ ከተረሸኑት 60ወቹ ባለስልጣናት ጋር አብረው ተረሽነዋል፡፡