በወቅቱ የአሜሪካ መንግሥት፤ የኤርትራን በፌዴሬሽን የመተዳደር ሀሳብ በበጎ አይን መመልከቷ ለውሳኔው መጽደቅ እገዛ አድርጓል፡፡

ከግራ ወደ ቀኝ ሁለተኛው፤ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣ ሦስተኛው የልዑካን ቡድኑ ተጠሪ፤ ራስ ቢተወደድ ተሰማ ናደውና አራተኛው፤ ከንቲባ ገብሩ ደስታ ይገኙበታል
Photo credit to:
face2faceafrica
የኢትዮጵያና የአሜሪካ ኦፊሴላዊ ግንኙነት የጀመረው በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በ1896 ዓ.ም. ሲሆን፤ ይህም አሜሪካ ኢትዮጵያን እንዲጎበኝ በላከችው የልዑካን ቡድን አማካኝነት ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጋር በተፈራረሙት የወዳጅነትና የንግድ ውል አማካይነት ነው፡፡
አቶ ሊበን ኢብሳ ምስገና ይጋብውና በታዲያስ መጋዚን ላይ እንደአቀረበው ጽሁፍ ከሆነ፤
በአሜሪካው ፕሬዝደንት ቴዎዶር ሩዝቬልት ፕሬዝደንታዊ ዘመን፤ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፤ በ 1896 ዓ.ም ከአሜሪካ ጋር የተዋዋሉትን የወዳጅነትና የንግድ ውል መሠረት በማድረግ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት በልዑል ራስ ተፈሪ የእንደራሴነት ሥልጣን፤ ሐምሌ 4 ቀን 1911 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አሜሪካ አንድ የአቢሲንያ የልዑካን ቡድን ተጉዞ ነበር፡፡
ከተጓዙትም አራት የልዑካን ቡድኑ አባላት መካከል፤
- ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ
- ራስ ቢተወደድ ተሰማ ናደው የልዑካኑ ቡድኑ ተጠሪ እና
- ከንቲባ ገብሩ ደስታ
ይገኙበታል፡፡
የልዑካን ቡድኑ ኋይት ሀውስ ጥሪ ተደርጎለት በክብር በተገኙበት ወቅት፤ የአሜሪካ አምባሳደር ካፒቴን ሞሪስ፤ “ማወቅ ከምንፈልገው ዋናው ጉዳይ አንዱ፤ አቢሲንያ ከዓለም እጅግ ጥንታዊ የክርስቲያን ሐይማኖት ያላት ሀገር ናት፡፡” በማለት ተናግረዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑ ተጠሪ ቢተወደድ ተሰማ ናደውም በማከታተል፤ “ንጉሥ ሰለሞንን የጎበኘችው ንግሥት ሳባ የእኛ ንግሥት ነበረች፡፡ አሁን ያሉት መሪያችንም ከንግሥተ ሳባ ዘር ሲወርድ ሲዋረድ የተገኙ ናቸው፡፡” በማለት ንግግር አሰምተዋል፡፡
ከኋይት ሀውስ ጉብኝት በኋላም የልዑካን ቡድኑ የኒውዮርክ፣ የዋሽንግተን ዲሲ፣ የችካጎንና ሳን ፍራንሲስኮን ከተሞች ጎብኝቷል፡፡
የእንግሊዝኛውን ጽሁፍ የበለጠ ለማንበብ፤
--->( ከምስጋና ጋር ለ፤ Tadias Magazine)

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፊርማ
እስከ 1928 ዓ.ም. ድረስ የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ይቆጣጠሩ የነበሩት ሦስቱ አጎራባች የቅኝ ገዥ አገሮች ማለትም እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ጣሊያን ሲሆኑ፤ የአሜሪካ ሚና እየጎላ የመጣው ግን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ በኋላ ነበር፡፡
በኢትዮጵያም የረዥም ዘመን ቅኝ ገዥነት ያደከማቸው እንግሊዞች ሳይወዱ በግድ ስፍራቸውን በትኩስ ኃይል ለምትንቀሳቀሰው አሜሪካ መተው ነበረባቸው፡፡
በሌላ በኩል እንግሊዞች ንጉሠ ነገሥቱን በስደታቸው ጊዜ መጠጊያ የሰጧቸውና ወደ አገራቸውም በክብር ለመመለስ ባለውለታቸው ቢሆኑም ቅሉ፤ የእንግሊዞች
በአገሪቱ አስተዳደር ያለገደብ ጣልቃ እየገቡ ሥልጣን መሻማታቸውን ንጉሠ ነገሥቱ ዝም ብሎ መመልከት አላስቻላቸውም፡፡
እንግሊዞች፤ በኢትዮጵያ ላይ በገንዘብና በሐብት ረገድ ለሚያደርጉት ጥብቅ ቁጥጥር መፍትሔ ለማግኘት ይቻል ዘንድ አገሪቱ ፊቷን ወደ አሜሪካ በማዞር ከአሜሪካ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖራት ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ ጀመረች፡፡
ስለሆነም ከእንግሊዞች መዳፍ ለመላቀቅ የነበረው አማራጭ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ከአሜሪካ ጋር በአዲስ ምዕራፍ ማደስ ነበር፡፡

ክቡር አቶ ይልማ ደሬሳ
Photo credit to:
alchetron.com
በመጨረሻም አስር አመት ሙሉ ኢትዮጵያን ትቆጣጠር የነበረችው እንግሊዝ ዘወር እንድትል ተደርጋ፤ በምትኩ አሜሪካ ወደ መድረኩ ብቅ በማለት የኢትዮጵያ ዋና አጋዥ መሆን ጀመረች፡፡
በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል የጠበቀ ግንኙነት ለመመስረት በመጀመሪያ የተጉት ከአሜሪካኖች ይልቅ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነታቸውን በአዲስ ምዕራፍ መጻፍ የጀመሩት በ1935 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር ምክትል ሚኒስትር የነበሩት ክቡር አቶ ይልማ ደሬሳ አሜሪካንን በጎበኙበት ወቅት ነበር፡፡
ክቡር አቶ ይልማ ደሬሳ፤ እንግሊዝ አገር በሚገኘው በእውቁ የለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ተምረው እንደጨረሱ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ ለ13 ዓመታት ያህል በገንዘብ ምኒስትርነት እና በውጭ ጉዳይ ምኒስትርነት፣ የህግ መወሰኛ (ሴኔት) ምክር ቤት አባልነትና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ያገለገሉ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን የነበራቸውና እውቅናን ያተረፉ ምሁር ነበሩ፡፡
በጉብኝቱም ወቅት በኢትዮጵያ በኩል የቀረበው ጥያቄ፤ ወታደራዊ እርዳታ እንዲሰጣት፤ የገንዘብና የሕግ አማካሪዎች እንዲመደቡላት ነበር፡፡
አሜሪካም ወደ ኢትዮጵያ የቴክኒክ ቡድን በመላክ ሁኔታውን ካስጠናች በኋላ በ1936 ዓ.ም. ስምምነት በመፈረም የኢትዮጵያና የአሜሪካ ተራድኦ መሠረት ተጣለ፡፡
የአሜሪካ የቴክኒክ ኮሚቴ ጥናት ውጤትም በ1944 ዓ.ም. በሁለቱ አገሮች መካከል የ“ፖይንት ፎር” ስምምነት እንዲፈረም ተደረገ፡፡
የፖይንት ፎር ሰምምነት ካከናወናቸው ተግባራት ውስጥ፤
- የእርሻና የጤና ጥበቃ ትምህርት ማስፋፋት
- አንበጣ መከላከያን ማቋቋም
- የሕዝብ አስተዳደር (ፐብሊክ አድምኒስትሬሽን) ሥልጠና መስጠትና
- ኢትዮጵያውያንን ለትምህርት ወደ ውጭ አገር መላክ
የሚሉት ይገኙበታል፡፡
የፖይንት ፎር ስምምነት ለኢትዮጵያ የእድገት መሠረት የሚጥሉ መሆናቸው ግልጽ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ዋና ፍላጎት፤ ወታደራዊ እርዳታ ማግኘትና የእንግሊዞችን አምባገነንነት ለመቋቋም እንዲቻል አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ እንድትሰጣት ነበር፡፡

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የካቲት 6 ቀን 1937 ዓ.ም. በግብፅ ጉብኝት በማድረግ ከአሜሪካው ፕሬዚደንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት ጋር በአሜሪካ የጦር መርከብ ላይ ተገናኝተዋል፡፡ ከንጉሠ ነገሥቱ ጀርባ ይከተሉ የነበሩት ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ ዳርጌ ናቸው
Photo link
የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሠት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፤ በ1937 ዓ.ም. ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት ጋር በግብፅ ተገናኝተው ለኢትዮጵያ ወሳኝ በሆኑት፤ በኤርትራ፣ በኦጋዴንና በኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር ጉዳዮች ላይ መነጋገር ቻሉ፡፡
በኦጋዴን ያለውን የእንግሊዞችን ጫና ለመቋቋም በሚል የፖለቲካ ስሌት መሠረት፤ ኢትዮጵያ ለአሜሪካው የፔትሮሊየም ኩባንያ ለሆነው ለሲንክለር በኦጋዴን የነዳጅ ፍለጋ ጥናት እንዲያካሂድ ፈቃድ ሰጠች፡፡
ከ 1943 ዓ.ም. በኋላ፤ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ስትተሳሰር፤ አሜሪካም አሥመራ ባላት የመገናኛ ጣቢያ ምክንያት የምሥራቅ አፍሪካን እስትራተጅካዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ስትል ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቷን አጠናከረች፡፡
መስከረም 5 ቀን 1945 ዓ.ም. የእንግሊዝ ተራድኦ ቡድን ጓዙን ጠቅልሎ ከኢትዮጵያ ሲወጣ፤ ዘመናዊ ሥልጣኔን በማስተዋወቅ በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካሳደሩት መሪዎች አንዱ በሆኑት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዲፕሎማሲዊ ጥረት፤ ኢትዮጵያም የአሜሪካንን ወታደራዊ እርዳታ ለማግኘት ቻለች፡፡
በ1945 ዓ.ም. በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት፤ አሜሪካ በአዲስ ስያሜው “ቃኘው” የተባለውን በአሥመራ የሚገኘው የመገናኛ ጣቢያ ላይ የነበራትን ይዞታ አረጋገጠች፡፡
አሜሪካም በአጸፋው ለኢትዮጵያ ሰፊ የወታደራዊ እርዳታ ፕሮግራም ለመጀመር ተስማማች፡፡
“ማግ” በተባለው የአሜሪካ እርዳታ ፕሮግራም ቡድን አማካይነት፤ ኢትዮጵያ አምስት ሚሊዮን ዶላር ወጭ አድርጋ፤ 60 ሺህ ወታደሮች የያዘ ባለ ሦስት ክፍለ ጦር ሠራዊት ማቋቋም ቻለች፡፡
በዚህ የእርዳታ ፕሮግራም አማካይነት በተከታታዮቹ ዓመታት እየተሰጠ ቀጥሎ፤ አሜሪካ ለአፍሪካ አገራት ከምትሰጠው ወታደራዊ እርዳታ ውስጥ 60 በመቶው የሚመደበው ለኢትዮጵያ ነበር፡፡
ስለሆነም ከ1945 ዓ.ም. በኋላ በነበሩት ዓመታት ውስጥ፤ አሜሪካ በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት መድረክ ዋና ተዋናይ በመሆን፤ በተለይ የጦር ሠራዊቱን ክፍል በማደራጀት ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውታለች፡፡
ዘመናዊ ሥልጣኔን በማስተዋወቅና በዲፕሎማሲው በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካሳደሩት መሪዎች አንዱ የሆኑት
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፤ ቀደም ሲል የኢትዮጵያን አየር ኃይል ለማቋቋም ከፍተኛ ምኞት ስለነበራቸው፤ ንጉሠ ነገሥት ከመሆናቸው አንድ ዓመት በፊት በአፍሪካ ምድር ብቸኛ የሆነውን "ኢምፔሪያል ኢትዮጵያን አቪየሽን" የተሰኘ የአየር ኃይል በ1922 ዓ.ም. በነፃይቱ የኢትዮጵያ ምድር ማቋቋማቸው ይታወሳል፡፡ ( ---> የእንግሊዝኛውን ጽሁፍ የበለጠ ለማንበብ፤ ምስጋና ለ፤ adf-magazine.com)

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በ1942 ዓ.ም. ወደ አገራቸው ያሰገቡት የአየር ኃይል የጦር አይሮፕላን ላይ ቆመው ይታያሉ
Photo credit to:
adf-magazine
ቀደም ሲል በስዊድን ቁጥጥር ሥር የነበረውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል እና በኖርዌጅያኖች ይተዳደር የነበረው የኢትዮጵያ የባሕር ኃይልም ወደ አሜሪካኖች ተዛወረ፡፡
በዓለም እውቅና ባገኘው በእንግሊዙ የሳንድኸርስት የጦር አካዳሚ አምሳያ የተፈጠረውና የተደራጀው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጦር አካደሚም፤ እንግሊዛውያኑ በብቃትና በጥራት ባሰለጠኗቸውና ባደራጇቸው የሕንድ አማካሪዎች አማካይነት ከተቋቋመ በኋላ በንጉሠ ነገሥቱ በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መስከረም 21 ቀን 1951 ዓ.ም. ተመርቆ ሥራወን በይፋ ሲጀምር የአሜሪካ የሰውና የማቴሪያል እርዳታ አልተለየውም ነበር፡፡
የኢትዮጵያ የፖሊስ ሠራዊትም የሠለጠነውና የተቋቋመው በጀርመንና በእስራኤል ሲሆን፤ የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘበኛ ደግሞ የሠለጠነው በስዊድኖች ነበር፡፡
ከ1938 ዓ.ም. እስከ 1964 ዓ.ም. ድረስ አሜሪካ ለ26 ዓመታት ለኢትዮጵያ ያደረገችው ወታደራዊ እርዳታ፤ 180 ሚሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ይገመታል፡፡
ከ1945 ዓ.ም. እስከ 1960 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ፤ በአሜሪካ አገር 2,500 ኢትዮጵያውያን ወታደራዊ ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡
የሚሊተሪ መሣሪያዎችንና ሎጂስቲክስን በተመለከተም ለምሳሌ፤
- የጦር ጀቶች
- ፀረ አውሮፕላን መቃወሚያዎች
- ለባሕር ኃይል የሚያገለግሉ መርከቦችና ጀልባዎች
- ለእግረኛው ጦር የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች እና
- ወታደራዊ ዩኒፎርም
ሳይቀር የሚመጣው ከአሜሪካ ነበር፡፡
አሜሪካ ከምታበረክተው ወታደራዊ እርዳታ ውስጥ፤ በትጥቅም ሆነ በሥልጠና አቢይ ስፍራ የያዘው፤ በዘመናዊነቱና በቅልጥፍናው ዝናን ያተረፈው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ነበር፡፡
በ 1938 ዓ.ም. የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ለማቋቋም በተጠራው ጉባኤ ለመሳተፍ አሜሪካ ሄዶ የነበረው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን፤ በኢትዮጵያ የአየር መንገድ ለማቋቋም የአሜሪካንን ዕርዳታ ጠየቁ፡፡
በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ፤ Trans-contentental and Western Airline (TWA) ከተባለው የአሜሪካ አየር መንገድ ጋር፤ በአሜሪካ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ አማካሪ በነበሩት በጆን ሰፔንሰር አማካይነት በተደረገው ስምምነት መሰረት ታህሳስ 12 ቀን 1938 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቋቋመ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲቋቋም፤ በ 2.5 ሚሊዮን ብር የመነሻ ካፒታል በአክሲዮን መልክ በኢትዮጵያ መንግሥት ሙሉ ወጭ የተቋቋመ ሲሆን፤ አስተዳደሩ ግን ሙሉ በሙሉ በአሜሪካኖች ይመራ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተቋቋመ በኋላ፤ በስምምነቱ መሰረት ለ 30 ዓመታት ያህል አሜሪካ፤ ሥራ አስኪያጆችንና የቴክኒክ ተቆጣጣሪዎችን በመላክ ለአየር መንገዱ ሲመድቡ ቆይተዋል፡፡

በ1938 ዓ.ም. ይበር የነበረው C-47 የተሰኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይሮፕላን
Photo credit to:
selamtamagazine
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራውን የጀመረው የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ቅርስ በሆኑትና ለወታደራዊ ትራንስፖርት አገልግሎት ይውሉ በነበሩት ቁጥራቸው አምስት በሚደርሱ C-47 በተሰኙ ዳኮታ አውሮፕላኖች ሲሆን፤ ሦስቱን አይሮፕላኖች፤ DC-3 የሚል ስያሜ በመስጠት ለመንገደኞች አመች እንዲሆን አሻሻሏቸው፡፡
ቆይቶም DC-6 የተሰኙ ባለ አራት ሞተር አውሮፕላኖችን በማስመጣት አገልግሎቱን ካሰፋ በኋላ፤ በ 1952 ዓ.ም. ወደ ጄት አውሮፕላኖች በመሸጋገር ሁለት ቦይንግ 720B በመግዛት ስራውን ጀመረ፡፡
በመጨረሻም በ 1964 ዓ.ም. የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮሎኔል ስምረት መድሃኔ ሲሾሙ፤ አየር መንገዱ ከአሜሪካኖች የአስተዳደር ቁጥጥር ወጥቶ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በኢትዮጵያውያን ቁጥጥር ሥር መሆኑ በውል ተረጋገጠ፡፡

Photo credit to: face2faceafrica


Photo credit to: alchetron.com

Photo link

Photo credit to: adf-magazine

Photo credit to: selamtamagazine
































