Content-Language: am ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ
header image




ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ



የደጃዝማች ገረሱ ዱኪን
የአርበኝነት ዘመን ታሪክ ያዳምጡ








1. ትውልድ እና የልጅነት የሕይዎት ዘመን

ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ
ገረሱ ዱኪ በሰኔ ወር 1897 ዓ.ም. አካባቢ በወሊሶ አወራጃ፤ ከአዲስ አበባ 104 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ማሩ በምትባለው ቦታ ከአባታቸው ከኦቦ ዱኪ ጉልማ እና ከናታቸው ከወይዘሮ ወርቄ ኤልሞ ተወለዱ፡፡
ደጃዝማች ገረሱ ‘አባ ቦራ‘ በሚል የቅጽል ስም ይጠራሉ፡፡
ገረሱ ዱኪ በልጅነት እድሜአቸው የቄስ ትምህርት ቤት ከመሄዳቸውም ባሻገር በቤተ ክርስቲያን የሐይማኖት ትምህርትም ተከታትለዋል፡፡
ወተዳር ሆነው አገራቸውን ለማገልገል በነበራቸው ጠንካራ ፍላጎት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የውትድርና ስልጠና አግኝተዋል፡፡
ገረሱ ዱኪ ጀግናና አገር ወዳድ መሆናቸውን የተመለከቱት ደጃዝማች ገብረ ማሪም ጋሪ ንጉሠ ነገሥቱ ጋ በማቅረብ፤ “በታማኝነት ሊያገለግልዎ የሚችል ይህን ደፋር ወጣት ልጅ፤ ከእርስዎ አጠገብ ቢሆን መልካም ነው፡፡” የሚል ንግግር አሰምተው አስተዋውቀዋቸዋል፡፡

2. በጦር ግንባር የነበራቸው ተሳትፎ

Dejazmach Geresu and his Family
ገረሱ ዱኪ ከቤተሰቦቻቸው ጋር
በ30 ዓመት የወጣትነት እድሜያቸው ከወራሪው የፋሽስት ኢጣሊያ ጋር የአረበኝነት ትግል የጀመሩት ገረሱ ዱኪ፤ ሀገራቸው በጠላት እግር እንድትረገጥ ከማይሹ እና ከፋሽስት ወረራ ነፃ እንድትወጣ በፅናት ከሚታገሉ ስመ ጥሩ አርበኞች መካከል አንዱ ነበሩ፡፡
ገረሱ ዱኪ በ1928 ዓ.ም. በንጉሠ ነገሥቱ ወደ ወሎ በተላኩበት ወቅት የነበራቸውን ወታደራዊ ችሎታ የተመለከቱት ልዑል አስፋወሰን ኃይለ ሥላሴ፤ የሻምበልነት ማዕረግ ሰጥተው አምባሰል የሚገኘውን ወታደራዊ ክንፍ እንዲመሩ ሥልጣን ተሰጣቸው፡፡
የሻምበል ገረሱ ዱኪን ውጤታማ ሥራ የተመለከቱት ልዑል አስፋወሰን፤ ገረሱ ዱኪን ወደ ሻለቅነት ማዕረግ አሳድገው የበለጠ ኃላፊነት በመስጠት ወሎ ጠቅላይ ግዛት የሚገኘውን ጦር እንዲመሩና ጦሩን ወደ አምባላጌ በመውሰድ ከልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ ሠራዊት ጋር በአንድነት ጠላትን እንዲወጉ በታዘዙት መሠረት ሠራዊቱን በፍጥነት አንቀሳቅሰው ወደ ሥፍራው ወስደዋል፡፡
በሰሜን ጦር ግንባር ከጠላት ጋር በተደረገው ጦርነት፤ የፋሺስት ወታደሮች በዘመናዊ መሣሪያዎች እስከ አፍንጫቸው ከመታጠቃቸውም በላይ በጄኔቫ ኮንቬንሽን የተከለከለውን መርዛማ የሙስታርድ ጋዝ ቦንብ በመጠቀማቸው ምክንያት በርካታ የኢትዮጵያ ወታደሮች ተሰውተዋል።
በዚህም መሠረት ለውጊያ የተሰለፈው የኢትዮጵያ ሠራዊት በኢጣሊያ ወታደሮች የተቃጣውን የአይሮፕላን ጥቃት መቋቋም አልቻለም።
ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ፤ የገረሱን ወታደራዊ ስትራቴጂ እና ጀግንነት ተመልክተው አድንቀዋል።
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም የገረሱ ዱኪን ጀግንነት በማወቅ ቤልጂየም የተሠራ ቤልጅግ የሚባል የመድፍ መሣሪያ በሽልማት ሰጥተዋቸዋል፡፡
በ1928 ዓ.ም. በሐገራችን ላይ በተፈፀመው የፋሽስት ኢጣሊያ የግፍ ወረራ ምክንያት፤ ከማይጨው እስከ ተንቤንና ሰቲት ሁመራ ድረስ እና እንዲሁም በየክፍለ ሐገሩ የዘመተው የኢትዮጵያ ሠራዊት በጦር ምኒስትሩ ሥር ሆኖ ባደረገው የጦርነት ግጥሚያ ታላላቅ የጀብዱ ሥራዎች ተፈጽመዋል፡፡
በዚህ ጦርነትም ታላላቅ የጦር ሜዳ ጀብዱ ከፈፀሙትም መካከል ባላምባራስ ገረሱ ዱኪ አንዱ ናቸው፡፡
እንዲያውም በጦሩ ግንባር ቀደም ሆነው በቃፊርነት በመሰልፍ የተንቤን ጦርነት ሲጀመር የመጀመሪያውን ተኩስ የተኮሱት ባላምባራስ ገረሱ ዱኪ ናቸው፡፡

3. የአምስት አመቱ የአርበኝነት ተግባር ሲዳሰስ

Geresu Duki
ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ በአርበኝነት ዘመን

Photo courtesy of: maddawalaabuupress
ባላምባራስ ገረሱ ዱኪ፤ ከሰሜኑ የጦርነት ዘመቻ መልስ ባላባት በሆኑበት ወደ ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ወደሚገኙት ወሊሶና ጅማ ሄደው ከማሩና ከአመያ ሕዝብ ጋር በመሆን አርበኝነታቸውን በቆራጥነት ጀመሩ፡፡
ባላምባራስ ገረሱ ዱኪ ከጠላት ጋር ይዋጉበት የነበረው ስፍራ ከአዲስ አበባ ያለው እርቀት 90 ኪሎ ሜትር ብቻ ነበር፡፡
በኋላ ላይ የፊታውራሪነት ማዕረግ ያገኙትና የ15 ዓመት እድሜ ያለውን ወንድ ልጃቸውን ተፈራ ገረሱን ሳይቀር በውጊያ ያሳተፉት ገረሱ፤ ቁጥሩ ከ50 ሺህ በላይ የሚደርስ የአካባቢውን ነዋሪዎች የፀረ ፋሽስት ትግሉ አጋር በማድረግ አንቀሳቅሰዋል፡፡
ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ፤ የገረሱን ወታደራዊ ስትራተጂ እና ጀግንነት ተመልክተው አድንቀዋል።
ገረሱ ዱኪ ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ በመሬት ላይ ያለውን እውነታና የጠላትን ክፉ ተግባር ለሕዝባቸው ሲያስረዱ፤
“ጠላታችን አገራችንን ቅኝ ገዝቶ ባሪያ ሊያደርገን የሚፈልግ ጠላት ነው።
ብቸኛ ፍላጎቱ ነፃነታችንን መንጠቅ ነው።
ባህሎቻችንን እና ሃይማኖቶቻችንን በመፃረር እየተዋጋን ነው።
በመካከላችን የከፋፍለህ ግዛን ሥርአት እየተገበረ ነው፡፡
አማራው ጠላትህ ነው ይላል። ነገር ግን ኦሮሞም አማራም የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው።
በጠላት ፕሮፓጋንዳ አንዳንድ ጨካኝ ኢትዮጵያውያንን ወደ እርሱ ለመሳብ በሚያቀርቧቸው ማባበያዎች ወደ ኋላ መመለስ እና መታለል የለብንም።
ለዘመናት በሃይማኖትና በጎሳ ስንከፋፈል የቆየነውን ያህል የግዛት አንድነታችን እንዳይከፋፈል ጠብቀን ማቆየት አለብን።
ጠላታችን ጅራቱን ቆልፎ ከአገራችን እንዲወጣ እናባርረው።”
በማለት ድንቅ ንግግር መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ለጠላት ገብረን አንኖርም ካሉ ጀግኖች አርበኞቻችን አንዱ ደጃዝማች ገረሱ ነበሩ፡፡
ገረሱ (አባ ቦራ) እሳቸው ካሉበት ከደቡብ ኦሮሚያ እስከ ኦሞ ወንዝ ድረስ ፋሽስት ኢጣሊያንን በደፈጣ ውጊያ ቁም ስቅሉን አሳይተውታል፡፡

በ15 ዓመቱ ከአባቱ ጋር የዘመታው
የደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ልጅ ተፈራ ገረሱ

Photo link
የእርሳቸው ጀግንነት ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ እስከ ጅማ ድረስ ብዙ ሺ ወጣቶችን ለውጊያ አነሳስቶ ጫካ አስገብቷል።
በ1929 ዓ.ም. በአንድ ከሀዲ ባንዳ የሚመራ ቁጥራቸው 100 የሚሆን በደንብ የታጠቁ የኢጣሊያ ወታደሮች ወደ ገረሱ ቤት መሄድ ጀመሩ።
ጠላት ወደ እርሳቸው መምጣቱን ገረሱ ዱኪ አስቀድመው መረጃውን አግኝተዋል።
የጦር መሣሪያ የታጠቁ የራሳቸውን 10 ወታደሮችን አስከትለው ቄሮ በሚባል ኮረብታ ላይ የመጣውን ጠላት አድፍጠው ጠበቁት።
የጠላት ወታደሮች በዒላማቸው ውስጥ መግባታቸውን ካረጋገጡ በኋላ ተኩስ ከፍተው ሁሉንም ማለት በሚቻል ደረጃ ረፈረፏቸው።
ከገረሱ ጋር የነበሩት አርበኞች ማለትም፤ ገነነ በዳኔ፣ በቀለ በንቲ፣ ደቻሳ ጉልማ፣ ሆርዶፋ ጉልማ እና መኩሪያ ተመቻቸው የተባሉት ጀግኖች በውጊያው ወቅት በተበታተኑት የጠላት ወታደሮች ላይ የጥይት ናዳ አዘነቡባቸው።
የማሩ ቀበሌ ነዋሪዎች ሳይቀሩ በያዙት ጦር እና ዱላ ሳይቀር ተዋግተው ብዙ ጠላትን መማረክ ችለዋል።
የጠላት ወታደሮች ብዙ ጠመንጃዎችን፣ መድፎችንና ጥይቶችን ጥለው ሄደዋል።
ይህን ድል የሰሙት፤ ከማሩ፣ ከሶዶ፣ ከዊሊሶ፣ ከጨቦ፣ ከአመያ እና ከዳዋ የመጡ ነዋሪወች የገረሱን ሠራዊት ተቀላቅለዋል፡፡
ይህን የገረሱ ዱኪን አመፀኝነትና እምቢተኝነት የሰሙት የፋሽስት ወታደሮች ገረሱን ለመክበብ ተዋጊ አውሮፕላኖችን ጨምሮ ወታደራዊ ኃይላቸውን ማጠናከር ጀመሩ።
ግን ይህ ሁሉ የጠላት ዝግጅት የማያዋጣቸው መሆኑን አውቀው ሌላ ዘዴ ቀየሱ፡፡
patriots crossing the omo river
የደጃዝማች ገረሱ ወታደሮች የኢትዮጵያን
ሠንደቅ ዓላማ ይዘው የኦሞ
ወንዝን አቋርጠው ወደ ጠላት
ይዞታ ለማምራት እየንተቀሳቀሱ ሳለ
ገረሱ ዱኪ ፊት ለፊት ቆመው ሲያስተባብሩ
ሙሴ ቀስተኛው የተባለውን በአድዋ ጦርነት ጊዜ ተማርኮ ለ40 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በመነኩሴ ስም የኖረ የኢጣሊያ ወታደር በሽምግልና ወደ ገረሱ ዘንድ ለመላክ አሰቡ፡፡
ይህ የአድዋ ምርኮኛው ሙሴ፤ ጠላት ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የኢጣሊያ ሰላይ ሆኖ ሲሠራ የቆየ ነበር፡፡
ሙሴም አርበኞች ጋ እየሄደ በወራሪዎች እና በእናንተ መካከል ሰላም እንዲፈጠር አደርጋለሁ እያለ ያታልል ነበር፡፡
ሙሴ፤ የአርበኞችን ቁልፍ እና ስትራተጂካዊ ይዞታዎችን እየሰለለ፤ እነ ደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ፣ እነ ራስ ደስታ ዳምጠው፣ እነ ራስ አበበ አረጋይ የመሳሰሉትን ጀግኖች የአርበኞች መሪዎች ይዞታ ሳይቀር በጠላት አይሮፕላን ያስደበድብ ነበር።
ሙሴ በተመሳሳይ መንገድ ገረሱና ተከታዮቹ ላይ ጉዳት ለማድረስ በተመሳሳይ ተልዕኮ ውስጥ በነበረበት ወቅት፤ በጀግናው አርበኛ ገረሱ ዱኪ እጅ ወደቀና ተይዞ ታሰረ።
በኋላም በችሎት ፊት ቀርቦ የሞት ቅጣት ተበይኖበት በሞት እንዲቀጣ ተደረገ፡፡
በሙሴ የሞት ቅጣት የተናደዱት ፋሽስቶች፤ ጀነራል ማርቲን በተባለ የጣሊያን ጦር መሪ አማካኝነት በጅባትና ሜጫ ግንባር የተጠናከረ ጥቃት ከፈቱ፡፡
Dejazmach Geresu Duki
ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ
የክብር ልብሳቸውን ለብሰው

Photo credit to፤ ENKSSM
ምንም እንኳን በዚህ ጠላት ባደረሰው ከባድ ውግያ ምክንያት በርካታ አርበኞች ላይ ጉዳት ቢደርስም ቅሉ፤ ጀግኖች አርበኞችም ጥቃቱን ተቋቁመው በጠላት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ ችለዋል፡፡
ይህ አንድ ቀን ሙሉ በተካሄደው ውጊያ የበላይነቱን ያገኘው የገረሱ ዱኪ ሠራዊት ነበር፡፡
በዚህ ውጊያ፤ ጠላት ስፍር ቁጥር የሌላቸው በርካታ የጦር መሣሪያዎችን ጥሎ ሲሸሽ ብዙ የጠላት ወታደሮችም ተማርከዋል፡፡
በሽንፈታቸው የተበሳጩት የጠላት ወታደሮች “እናንተ የገረሱ ሠላዮች ናችሁ” በሚል ሰበብ 18 ንፁሃን ኢትዮጵያውያንን ጨፍጭፈዋል፡፡
በዚህ ጠላት በፈፀመው የግፍ ጭፍጨፋ የተበሳጩት ኢትዮጵያውያን፤ ወንድ ሴት ሳይሉ የገረሱን ጦር ተቀላቅለዋል፡፡
በዚህም የተነሣ የገረሱ ሠራዊት ቁጥሩ እያደገ መጣ፡፡
በእግረኛ ጦር የፈረጠመው የገረሱ ሠራዊት ያለምንም ፍርሀት ይዋጋ ስለነበረ ገረሱ ዱኪ በአርበኞቹና በዜጎቹ ከፍተኛ ዝናና ክብርን ማግኘት ቻሉ፡፡
በገረሱ ዱኪ ጀግንነት የተደነቁት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለአርበኞች ባደረጉት ንግግር፤
“በአርበኛ ገረሱ ዱኪ የተመዘገበውን አኩሪ ድል በታላቅ ደስታ ነበር የተመለከትነው፡፡
ለዚህም ነበር በወሎ ግንባር የተሰማራውን ሠራዊት የመምራት ተግባር በአደራ የሰጠነው፡፡
ይህን አስደሳች ተግባርህን ወደፊት በመቀጠል ጅማን ከጠላት ነፃ ለማደረግ ጥረትህን ቀጥል፡፡ ለአንተ የጦርነት ጥበብ፤ እንደ ገና ጨዋታ፤ (እንደ ቼዝ ጨዋታ) እንደሆነ እናውቃለን፡፡”
በማለት አድናቆታቸውን ለገረሱ ዱኪ ገልፀውላቸዋል፡፡
ገረሱ ዱኪ ጅማ ከመድረሳቸው በፊት 1 ሺህ 700 የጠላት ወታደሮችን በውጊያ ማርከዋል፡፡
በውጊው በሠላም እጃቸውን የሰጡት የጠላት ወታደሮች እንዳይገደሉ ገረሱ ለወታደሮቻቸው ትእዛዝ ሰተዋል፡፡
እንዲሁም ጠላት ሲሸሽ ጥሎ የሄዳቸው 500 ተሽከርካሪዎች፣ ብዙ ሺህ ጠመንጃዎች እና 2o ከባድ እና መካከለኛ የጦር መሣሪያዎች በየቦታው ወድቀው ተገኝተዋል፡፡
ቀኛዝማች ገረሱ ዱኪ በድል አድራጊነት ጅማ ከገቡ በኋላ ጅማንና አካባቢዋን በሠላም ማስተዳደር ጀመሩ፡፡
በአምስቱ ዓመት የአርበኝነት ዘመን ከገረሱ ጎን ቆመው ከተጋደሉት እውቅ ጀግኖች አርበኘች መካከል፤ ደጃዝማች ገነነ በዳኔ፣ ደጃዝማች በቀለ ወያ እና ግራዝማች ተፈራ ገረሱ ይገኙበታል።

4. የገረሱ ዱኪ ሕልፈተ ሕይዎት

ጀግናውና ቆራጡ አርበኛ ቀኛዝማች ገረሱ ዱኪ ከነፃነት በኋላ የደጃዝማችነት ማዕረግ አግኘተው በተለያዩ የአስተዳደር ቦታዎችና እንዲሁም በሕግ አውጪው አካል ውስጥ ገብተው ሀገራቸውን በቅንነት አገልግለዋል፡፡
በመጨረሻም በ1956 ዓ.ም. በተወለዱ በ60 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ምንጭ፤
  1. "ቀሪን ገረመው - የአርበኞች ታሪክ"  ደራሲ፡- ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ 2008 ዓ.ም.
  2. …ምስጋና፤ ለገጣሚ፣ ጸሐፊና ጋዜጠኛ ለ ዓለም ኃይሉ ገብረ ክርስቶስ፤ tuckmagazine.com
  3. …ምስጋና ለ፤ Madda Walaabuu Press
  4. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ
  5. Rare WW2 Footage - No Music   youtube