በላይ ዘለቀ ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት በጎጃም ጠቅላይ ግዛት የአርበኝነት ተግባር ከጀመሩት ከመጀመሪያዎቹ እረድፍ ከሚጠቀሱት ውስጥ በ 25 ዓመት ለጋ ዕድሜው ከወራሪው ፋሽስት ኢጣሊያ ጋር አርበኛ ሆኖ ለመፋለም የቆረጠ ወጣት ነው፡፡
ወራሪው ፋሽስት ኢጣሊያ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ እንደነበረ በላይ ዘለቀ ያውቅ ነበርና ከእለታት አንድ ቀን በብቸና የገበያ ቀን ሳይታሰብ አራት እርሱን መሰል ተከታዮችን አስከትሎ ከገበያው አጠገብ በሚገኝ ጉብታ ሥፍራ ላይ ቆሞ ገበያተኛውን ሲመለከት ሳለ፤ “አስጨናቂ! ሽፍታ! ሽፍታ! በላይ!” የሚል ድምፅ ከገባያተኛው ሲሰማ አስጨናቂ ኮስተር ብሎ፤
“የአገሬ ሰው ስማኝ!!”
“ጣሊያን የሚሉት ነጭ አገራችንን ሊወር፣ ሚስትህን፣ ልጅህን ሊደፍር፤ ሐብትህን ሊወርስ መቷል፡፡
ይኸው ብቸና ገብቶ መሣሪያ አስረክቡ ብሏል፡፡
መሣሪያውን ለጣሊያን የሚያስረክብ ሰው ካላ ቤቱን አቃጥልበታለሁ፡፡”
በማለት ንግግር አድርጎ ሕዝቡ መሣሪያውን ለጠላት እንዳያስረክብ አስጠነቀቀ፡፡
እነአስጨናቂም (በላይ ዘለቀ) የሄዱበት ሳይታወቅ ወዲያውኑ ከሥፍራው ተሰወሩ፡፡
ቀስ በቀስም የኢጣሊያ ጦር ከደብረ ማርቆስ ተነስቶ ወደየአውራጃዎች ለማምራት መንቀሳቀስ መጀመሩን አስጨናቂ እንደሰማ፤ ልክ እንደርሱ በተመሳሳይ ምክንያት ሸፍተው የነበሩትን ባለጦር መሣሪያዎችንና ጀሌዎችን ለምክር ሰብስቦ፤
“ጎበዝ! አገራችን በጠላት ስትደፈር ዝም ብለን ብንመለከት፤ ለአገር ነፃነት፣ ለመንግሥት ክብር እና ለሐይማኖት ጽናት ሲሉ በየጦር ሜዳው ደማቸውን ያፈሰሱትና አጥንታቻውን የከሰከሱት የአባቶቻችን አጥንት ስለሚወቅሰን የተቻለንን ሁሉ ማድረግ አለብን፡፡”
በማለት ወኔ ተናንቆት ሲናገር ተመሳሳይ ሀሳብና ዓላማ ያላቸው ቁጥራቸው ከ 30 እስከ 50 የሚደርሱ የአንድ አያት ልጆች ከተሰባሰቡ በኋላ በአስጨናቂ መሪነት አገር ወራሪውን ጠላት ለመውጋት በአንድነት ተስማሙ፡፡
ከዚያ በኋላ በእርሱ የጎበዝ አለቃነት በምሥራቅ ጎጃም በ25 ዓመት ለጋ ዕድሜው የአርበኝነት ሥራውን ጀመረ፡፡
ግንቦት 12 ቀን 1928 ዓ.ም. በግምት ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ 6 የጠላት ኮንቮዮች ከደብረ ማርቆስ ተነስተው የሚሄድበትን አቅጫ የሚያሳዩ በገንዘብ በተደለሉ ባንዳዎች እየተመሩ ወደ ብቸና አቅጣጫ በመጓዝ ላይ ነበሩ፡፡ እነ በላይ ዘለቀም ጥቅጥቅ ያለ ጫካ በሚገኝበት ረባዳ ሥፍራ ላይ አድፍጠው ስፍራ ስፍራቸውን ይዘው ሲጠባባቁ ሳሉ፤ አራቱ የጠላት መኪኖች ተከታትለው አልፈው አምስተኛው መኪና እንደደረሰ በላይ ዘለቀ በሰጠው የተኩስ ትእዛዝ በኮንቮዮቹ ላይ በአንድነት የጥይት እሩምታ አዘነቡባቸው፡፡
በመጀመሪያው መኪና ላይ የነበሩት 4 የኢጣሊያ ወታደሮችና ሁለት ባንዳዎች ሲሞቱ ከወገን በኩል አንድ ሰው ሲሞት አንዱ ቁስለኛ ሆኗል፡፡
ከዚህ ፈጣን ከሆነ የደፈጣ ውጊያ በኋላ እነበላይ ዘለቀ የማረኩትን ቦምብና መሣሪያ ይዘው በጫካው ውስጥ ከደበቁት በኋላ ከስፍራው በፍጥነት ተሰወሩ፡፡
በብልህነቱ፣ በአዳማጭነቱና በአስተያየት ጥልቀቱ በላይ ዘለቀ የሚተማመንበት የልጅነት ጓደኛው ቢሰውር፤ ከከተማ ወደ ገጠር፣ ከገጠር ወደ ከተማ በመመላለስ ጠቃሚ መረጃ ያቀርብለት ስለነበር፤ አባኮስትር በላይ ድል በድል ላይ ይቀዳጅ ስለነበር በልጅነት ጓደኛው ይመካበት ነበር፡፡
አባኮስትር በላይ ታማኝ የሆኑ የውስጥ አርበኞችም ነበሩት፡፡
ባንዳ መስለው የጠላትን መሣሪያ ዓይነትና ብዛት፣ የወታደሩን ቁጥርና የጦሩን መሪ፣ የሚዘምቱበትን ቀንና ቦታ የሚሰልሉለት ታማኝ የውስጥ አርበኞች ነበሩት፡፡
በአንድ ወቅት ታናሽ ወንዱሙን እጅጉ ዘለቀን ደጃዝማች ብሎ ሲሾም፣ እጅጉ ዘለቀም በበኩሉ፤
“ጋሸ፣ ስሙን ሁሉ ጨረስከው፤ አንተ ማን ልትባል ነው?” ብሎ ሲጠይቅ፤
በላይም፤
“ለእኔ ሌላ ስም ምን ያስፈልጋል፤ እናቴ በላይ ብላኝ የለም እንዴ?”
በማለት እንደመለሰ ተነግሯል፡፡
በአካባበቢው የነበረው ሕዝብም በላይን፤ ልዑል በላይ የሚል የማዕረግ ስም አውጥቶለት እንደነበር ይነገራል፡፡
አባኮስትር በለምጨን በረሃ መሽጎ ለኢጣሊያ መንግሥት አልንበረከክም በማለቱ፣ ሕዝቡም ለኢጣሊያ ባለሥልጣኖች እንዳይገዛ በማድረጉና ጠላትን መግቢያ መውጫ በማሳጣት ፋታ ስለነሳው “አፄ በጉልበቱ” የሚል የሙገሣም ስም ሕዝቡ አውጥቶለት ነበር፡፡