ሶማ በብቸና አውራጃ በለምጨን ወረዳ የሚገኝ ሶስት በሮች ያሉት ትልቅ ኮረብታ ነው፡፡
አባ ኮስትርን በውጊያ አሸንፎ እጁን ለመያዝ መንግሥት፤ ከቤገምድር፣ ከወሎ እና ከጎጃም የተሰባሰበ ከ 3 ሺህ የማያንስ የፈረሰኛና የእግረኛ ጦር ልኮ የሶማ ተራራን ከቦ ከያዘ በኋላ ተኩስ በመክፈት ውጊያው ለ 8 ቀናት ቆየ፡፡ በኋላም ነገሩን በሰላማዊ መንገድ ለመጨረስ ተብሎ ለስምንት ቀናት የቆየ ተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረገ በኋላ ከንጉሠ ነገሥቱ በተላኩ መልእክተኞች አማካኝነት በውይይት ለመፍታት ቢሞከርም ሳይሳካ ቀረ፡፡
ውጊያው እንደገና ተፋፍሞ በመቀጠሉ የአባ ኮስትር ተዋጊዎች ጥይት ከመጨረሳቸውም በላይ የሚጠጡት ውሀ ስላጡና ስንቅም ስለጨረሱ በርሃብና በውሀ ጥም ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰባቸው ራሳቸውን መከላከል እንኳን ሳይችሉ ቀሩ፡፡
በሁለቱም ወገን የተካሄደው ውጊያ ከባድ ስለነበረ፤ የደጃዝማች እጅጉ ዘለቀ መቁሰልና የጦር አለቃው የጀግናው ሽፈረው ገርባና ሌሎችም ብዙ ተዋጊዎች በመሞታቸው ምክንያት የአባኮስትር ተዋጊ ሠራዊት በተፋፋመው ውጊያ እጅግ ስለተዳከመ ሠራዊቱ ለመንግሥት ጦር እጁን እንዲሰጥ ሲጠየቅ ሳይወዱ በግድ እጃቸውን ለመስጠት ተገደዱ፡፡
ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ሁኔታው እንደማያዛልቅ የተረዳው አባኮስትር በላይ፤ በተለይ የቆሰለ ወንዱሙን ለማዳን ሲል ከንጉሠ ነገሥቱ ከተላኩት መልክተኞች ጋር በመገናኘት የእርሱንና የተከታዮቹን መሣሪያ ካስረከቧቸው በኋላ የኢጣሊያ ጦር ያልበገረው ስመ ጥሩ ጀግና ደጃዝማች በላይ ዘለቀና ወንድሙ ደጃዝማች እጅጉ ዘለቀ የጊዜ ጉዳይ ሆኖ 3 ወራት ሙሉ በተከታታይ ከተካሄደ ውጊያ በኋላ ሳይወዱ በግድ እጃቸውን ለካቴና ሰጡ፡፡
ከለምጨን በረሃ እስከ ቦረና ሳይንት፣ ከእነብሴ አስከ ጨሞጋ፣ ከደራ እስከ ገብረ ጉራቻ ድረስ ጠላትን ድል እያደረገ አገሩን ያሰገበረው ጀግና በምቀኞች ወጥመድ ተጠመደ፡፡
በእርሱ መሪነት አምስት ዓመት ሙሉ የሞቀ ቤታቸውን ጥለው ከእርሱ ጋር በዱር በገደሉና በየበረሃው እንየተንከራተቱ ለአገራቸው ነፃነት ከጠላት ጋር የተጋደሉት የሠራዊቱ ሹማምንቶችና ወታደሮች፤ የፈረሰ እና የተቃጠለ ቤታቸውን መልሰው ሳያቋቁሙ፤ ለአገልግሎታቸው መታሰቢያ እንኳን ምንም ነገር ሳይደረግላቸውና አውቅና አንኳን ተነፍጓቸው፤ ያለማንም ጠያቂ የትም ተበትነው መቅረታቸው በላይ ዘለቀን እጅግ ከባድ ሀዘን ላይ ጥሎታል፡፡
ከቀናት በኋላም፤ ሁለቱ ወንድማማቾችና ግብረ አበሮቻቸው ወደ አዲሰ አበባ ተልከው ንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ ለፍርድ እስኪቀርቡ ድረስ ወደ እስር ቤት ተወረወሩ፡፡
ከጥቂት ወራት የእስር ቤት ቆይታ በኋላ፤ በንጉሠ ነገሥቱ የፍርድ ችሎት እንዲቀርቡ ተደርጎ የክሱ ጽሁፍ ከተነበበ በኋላ፤ በተባባሪነት የተከሰሱት 13 ተከሳሾችም በሰጡት ቃል፤ ከአልጋ ወራሽ ጋር ተላልከው አልጋ ወራሽ ጋ ለመሄድ ጉዞ ሲጀምሩ ተኩስ ተከፍቶባቸው ባልሞት ባይ ተጋዳይነት ተታኮሱ እንጅ መንግሥትን እንዳልከዱ ቃላቸውን ከሰጡ በኋላ ደጃዝማች በላይም በማስከተል፤
“መኳንንቱ አማልዱኝ፡፡ ጃንሆይም ይማሩኝ፡፡”
ብሎ ለምሕረት ልመና ለንጉሠ ነገሥቱ አንገቱን ጎንበስ አደረገ፡፡
ሌሎችም የእርሱ ተባባሪ ተከሳሾችም እነደዚሁ ከፍ ባለ ትህትና በችሎት ፊት ወድቀው ተማጸኑ፡፡
ይሁን እንጅ፤ ይህ ሁሉ ተማጽኗቸው እንደጠበቁት ውጤት ሳያስገኝ ቀረ፡፡
የአባ ኮስትር ተባባሪ ናቸው የተባሉት እስረኞችም ወደ እስር ቤት ከተመለሱ በኋላ ወንድማማቾቹ ደጃዝማች በላይ ዘለቀና ደጃዝማች እጅጉ ዘለቀ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ወንጀሉን ሠርተዋል በተባለው ስፍራ በብቸና በስቅላት እንዲቀጡ ፍርዱ በተሰጠ ማግሥት ከሁለት የጦር መኮንኖች ጋር ተቆራኝተው ወደ ጎጃም ጉዞ ጀምረው ነበር፡፡
ይሁን እንጅ አባይ ወንዝ እንደደረሱ ከንጉሠ ነገሥቱ በተላከ መልእክት እንደገና ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተደረገ፡፡
ታህሳስ 23 ቀን 1937 ዓ.ም. በልዩ ፍርድ ቤት ቀርበው ሁሉም ተከሳሾች በስቅላት እንዲቀጡ ተፈረደ፡፡
ጥር 4 ቀን 1937 ዓ.ም. ዓርብ ቀን በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት በተለመደው አዳራሽ ውስጥ ንጉሠ ነገሥቱ ለዙፋን ችሎት ተሰይመዋል፡፡
በተሰጣቸው ፍርድ ያላቸው ቅሬታ ምን እንደሆነ እንዲያስረዱ ንጉሠ ነገሥቱ ተከሳሾቹን ጠየቋቸው፡፡
ሁሉም ተከሳሾች በአንድ ላይ፤ የምንጠይቀው ምሕረት ነው አሉ፡፡
ከዙፋን ችሎቱ አካባቢ፤ “ስቅላት ይገባቸዋል! ስቅላት!” የሚል ድምጽ ከየአቅጣጫው አስተጋባ፡፡
በተከሳሾች ላይ የስቅላት ቅጣቱ እንዲሻሻልላቸው ሀሳብ ያቀረበ አንድም ሰው አልተገኘም፡፡
በመጨረሻም ፍርዱ እንደሚፀና ንጉሠ ነገሥቱ የመጨረሻውን ቃል ሲናገሩ ተከሳሾች ፍርዱን በጸጋ የተቀበሉ ይመስል፤ ንጉሠ ነገሥቱን እጅ ነስተው ከችሎቱ አዳራሽ ወጡ፡፡
ጥር 5 ቀን 1937 ዓ.ም. ጧት ላይ ጃንሜዳ ተብሎ በሚጠራው ሰፊ ሜዳ ውስጥ የጦር ሠራዊትና የክብር ዘበኛ ወታደሮች በተሰለፉበት፤ ተከሳሾቹ ማለትም፤
- ደጃዝማች በላይ ዘለቀ
- ደጃዝማች እጅጉ ዘለቀ
- ልጅ ማሞ ኃይለሚካኤል
- ፊታውራሪ ከበደ ኃይለ ሚካኤል
- ፊታውራሪ ገበየሁ አባይነህ እና በተጨማሪም
እስረኞችን ያስመለጡ አራቱ የክብር ዘበኛ ወታደሮች በተራ እየተራመዱ በሰልፈኞች ፊት እያለፉ እንዲታዩ ከተደረገ በኋላ አራቱ እስረኞችን ያስመለጡት ወታደሮች በጃንሜዳ በእንጨት ላይ ተሰቀሉ፡፡
ከላይ በተጠቀሰው ቀን የቀሩት አምስቱ እስረኞች ደግሞ የኢጣሊያ መንግሥት የአገር ተወላጆች ገበያ (መርካቶ ኢንዱጅኖ) ብሎ ወደሰየመው ሥፍራ በመኪና ተወሰዱ፡፡
ዕለቱ ቅዳሜ ቀን ስለነበረ የመርካቶ ገበያ በሰው ብዛት ተጨናንቋል፡፡
ወንድማማቾቹ ደጃዝማች በላይ ዘለቀና ደጃዝማች እጅጉ ዘለቀ መርካቶ በሚገኘው አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ አጠገብ ተወስደው ከመኪና እንደወረዱ የእጃቸው ካቴና ሲፈታ ለመጨረሻ ስንብት ይመስላል እርስ በርስ ተሳሳሙ፡፡
ሊሰቀሉ ሲሉም በጣም ከመዋደዳቸው የተነሳ እኔ ልቅደም እኔ ልቀደም ሲባባሉ የፍርድ አስፈጻሚው ዳኛ ታናሹ እንዲቀድም አዞ ደጃዝማች እጅጉ ዘለቀ ተሰቀለ፡፡
በመጨረሻም ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ለመሰቀል ወደ መሰላሉ ሲያወጡት፤
“አንች አገሬ ኢትዮጵያ! እውነት በድዬሽ ከሆነ ነፍሴን አይቀበላት፡፡ አልበደልኩሽ ከሆነም ወንድ አይብቀልብሽ!”
በማለት ከተናገረ በኋላ በታሰሩት በሁለት እጆቹ አማተበና ተሰቀለ፡፡
በጀግንነቱ ስሙ የገነነውን በላይ ዘለቀን ለማየት የተሰበሰበው የአብዛኛው ተመልካች ሕዝብ ፊቱ በእንባ ታጠበ፡፡
ገና በ25 ዓመት የወጣትነት ለጋ እድሜው ጀምሮ የግል ሕይወቱ ሳያሳሳው ለውድ እናት ሀገሩ ኢትዮጵያ በርካታ መስዋዕትነትን የከፈለውና የቁርጥ ቀን አርበኛ ሆኖ ጠላትን ያርበደበደው ጀግናው በላይ ዘለቀ፤ በተወለደ በ33 አመቱ ጥር 5 ቀን 1937 ዓ.ም. ቅዳሜ ጧት በአንገቱ ላይ ኒሻን ሳይሆን ገመድ በማጥለቅ እጅግ አሳዛኝ በሆነ መልኩ የሕይዎቱ ፍጻሜ ሆነ፡፡
ብላቴን ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ስለ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፤ “የሚያሳዝነው ነገር፤ ደጃዝማች በላይ መሞቱ ሳይሆን፤ ሞታቸው (ከባንዶች አለቃ) ከማሞ ኃይለማሪያም ጋር መሆኑ ነው፡፡” በማለት ተናግረዋል፡፡
በላይ ዘለቀ ከአምስቱ ዓመት የነፃነት ትግል መሪዎች ውስጥ ምናልባትም በጣም ተወዳጅ ሰው እንደነበረ በታሪክ ጸሐፊዎች ተዘግቧል፡፡
ይህ በሕዝብ ዘንድ የነበረው ተወዳጅነት ግን፤ ሥልጣናቸው ላይ እንደገና ለመደላደል በሚሞክሩት ንጉሠ ነገሥት ዘንድ አምብዛም አልተወደደለትም፡፡
የበላይ ዘለቀ ተወዳጅነትና ያለው ኃይል ከገነነበት ከራሱ አካባቢ ለማራቅ ይመስላል፤ ንጉሠ ነገሥቱ የራስነት ማዕረግ ሰጥተው በደቡብ ኢትዮጵያ አገረ ገዥ እንዲሆን ቢሾሙትም እርሱ ግን ተንኮል ያለበት መሆኑን ስለደረሰበት ይመስላል ሹመቱን ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል፡፡
የጎጃም አርበኛው ልጅ ኃይሉ በለው ራስ ተብለው የጎጃም ጠቅላይ ግዛት አገረ ገዥ ሆነው ሲሾሙ፣ ደጃዝማች መንገሻ ጀንበሬ የተባሉት ሌላው አርበኛ ደግሞ በቢተወደድነት ማዕረግ የጎጃም ጠቅላይ ግዛት ምክትል አገረ ገዥነት ሹመት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ለእነዚህ የጎጃም የአርበኞች መሪዎች ከፍተኛ ሹመትና ማዕረግ ተሰጥቶ፤ ለስመ ጥር ገናናው አርበኛ ለበላይ ዘለቀ ግን የሚገባው ክብርና ማዕረግ መነፈጉ ቅር እንዳሰኘው ብዙወቹ ያምናሉ፡፡
ሌላው ቀርቶ በአምስት ዓመቱ የአርበኝነት ዘመን፤ እርሱ ያዝባቸው የነበሩትን የሞጣና ከፊል የደብረ ማርቆስን አውራጃ ገዥነት ማጣቱም የበለጠ ሳያናድደው አልቀረም፡፡
በላይ ዘለቀ መጋቢት 16 ቀን 1933 ዓ.ም. በአዛዥ ከበደ ተሰማ በኩል ንጉሠ ነገሥቱ እንዲገነዘቡት በጻፈው ደብዳቤ ላይ፤
“…በጎጃም የቆዩ ባላባቶችና መኳንንቶች፤ አሁን ለንጉሠ ነገሥቱ ክብር አስመስለው ቢያሶሩ ሁሉም የጠላት ሹም መሆናቸውን ሰምተውታል፡፡
ስለዚህ እኔን በምቀኝነት ስለሚጣሉኝ የእኔን ድካም እንዳይረሱት ለክቡርነትዎ አስታውሳለሁ፡፡”
በማለት በጻፈው ደብዳቤ ላይ ለማስረዳት ሞክሮ ነበር፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ደብረ ማርቆስ ሳሉ የበላይ ዘለቀን የሠራዊት ሠልፍ ካዩ በኋላ በላይ ዘለቀን አስጠርተውት፤
“እኛ የማንንም ወሬ በአንተ ላይ አንሰማም፡፡
እንደአባትህ ቁጠረን፡፡
በዚህ በልጃችን በመኮንን ይሁንብን፡፡”
በማለት ለበላይ ዘለቀ ፊት ለፊት የገቡለት ቃል ሁሉ ከንቱ ሆኖ ሌላ ፍጹም ያላሰበውና ያልጠበቀው ድርጊት ተፈጸመበት፡፡
አባኮስትር በላይ ዘለቀ ከእስር ቤት ለማምለጥ የሞከረው፤ አምስት ዓመት ሙሉ ከጠላት ጋር በመዋጋት መስዋትነት የከፈለላትን አገሩንም ሆነ ንጉሠ ነገሥቱን በመክዳት የአመጽ ተግባር ለመፈፀም ሳይሆን፤ ለጊዜው ከእስር ቤት ስቃይ ወጥቶ ምሕረት ለመጠየቅ በማሰብ ነበር፡፡
- አባ ኮስትር በላይ ዘለቀ፤ በምግብ ሰዓት ከእኔ ይልቅ ለሠራዊቱ ይቅደም የሚል ነበር፡፡
እንጀራም ሆነ ጭብጦ፣ ንፍሮም ሆነ ቆሎ፣ የተገኘውን ከሠራዊቱ ጋር እኩል ተካፍሎ የሚበላ እንጅ ለእርሱ የተለየ ምግብ አይቀርብለትም፡፡
የምግብ እጥረት እንኳን ድንገት ቢፈጠርና ለእርሱ ብቻ ቢቀርብለት፣ “አንሱት፤ እኔ ብቻየን አልበላም” ብሎ ጦሙን ውሎ ጦሙን የሚያድር ሰው ነበር፡፡
- ፍቅረ ነዋይ ያላደረበት፣ ስለነገ የማይጨነቅ፣ የተቸገረን የሚረዳ፣ በሕዝብ ላይ በደል የሚያደርሱትን የሚቀጣ እና መነፈሳዊነት ያለው እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ነበር፡፡
- አባኮስትር በላይ፤ ለጦር መሪነት የተፈጠረ ሰው በመሆኑ ለትምሕርት ባይታደልም እግዚአብሔር በሰጠው ጥበብና የተፈጥሮ እውቀት እየተመራ፤ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሠራዊቱን በአለቃና በጭፍራ መድቦ፣ ለእያንዳንዱ ምድብ የአዣዥነትና የአዋጊነት ችሎታ ያላቸውን ጀግኖች ከሠራዊቱ መካከል መርጦ፤ ራስ፣ ቢተወደድ፣ አፈንጉሥ፣ ደጃዝማች፣ ቀኛዝማች፣ ግራዝማች፤ ፊታውራሪ የሚል ማዕረግ በመስጠት ሠራዊቱን እንዲመሩ ይሾም ነበር፡፡
እንዲሁም ከጠላት ቁጥጥር ውጭ የሆኑትን ግዛቶች ደግሞ ልዩ ልዩ ማዕረጎች ለሰጣቸው የጦሩ አዛዦች እንደየማእረጋቸው በተዋረድ አከፋፍሎ በመደልደል ሕዝቡን በሚገባ እንዲያስተዳድሩ የአስተዳደር ሥርዓት በማበጀት የጦርነት ጊዜ አስተዳደር የመሠረተ ሰው ነበር፡፡
- በምሥራቅ ጎጃም በበላይ ዘለቀ ሥር ይተዳደሩ የነበሩት አገሮች ቁጥር ሲዘረዘሩ፤ ግራ ቀኝ ሸበል፣ ደባይ ጥላት ግን፣ አዋባል፣ አራራ፣ በረንታ፣ ጉባያ፣ ናዝሬት፣ ይናጭ፣ እነማይ፣ ውድሚት፤ እናርጅ እናውጋ፤ ቅንቧት እነብሴ ከተባለውም አገር በግማሹ፤ ከአባይ ወንዝ ማዶ የሚገኙትን ቦረናን፣ ጫቀታን እና ደራን ጨምሮ በጥቅሉ 16 ሲደርሱ እነዚህ ሁሉ አገሮች ሙሉ ግብር ይገብሩለት ነበር፡፡
- ለሚመራው ሠራዊት የሚከፍለው ደመወዝ ስለሌለው፤ ከጦርነቱ ፋታ ሲያገኝ ሠራዊቱ ወደ ተውልድ አገሩ እየተመለሰ አርሶ እንዲበላና ለውጊያ ሲፈለግም እነዲጠራ በማድረግ እና ሕዝቡም በበኩሉ የበሰለም ሆነ ደረቅ ስንቅ ለሠራዊቱ እንዲያቀርብለት ያደርግ ነበር፡፡
የበላይ ዘለቀ የአመራርና የአስተዳደር ዘይቤ ከሌሎች አርበኞች ሁሉ የተለየ ስለነበረ፤ ጊዜው በሚፈቅደው መጠን ለማስተዳደር የሚችለውን ሰው እየመረጠና እያበረታታ ይሠራ ነበር፡፡
ከበላይ ዘለቀ ጋር የነበሩት የአርበኞች ቁጥር ከሌሎች ጋር ሲወዳደር እጅግ ብልጫ እንደነበረው አዛዥ ከበደ ተሰማ ለንጉሠ ነገሥቱ ባስተላለፉት መልእክት፤
“ ካየናቸው አርበኞች ሁሉ በአርበኞች ብዛት እጅግ ብልጫ ያለው ከፍ ያለ የአርበኞች ሰልፍ ከጦር ሜዳ ላይ አሳዩን፡፡ ”
በማለት በሰጡት ምስክርነት የአባ ኮስትር ሠራዊት የነበረውን ከፍተኛ ደረጃ አረጋግጠዋል፡፡
ደጃዝማች በላይ ዘለቀ፤
- የሻሽወርቅ በላይ
- የሽመቤት በላይ
- ጎሹ በላይ
- ባሕሩ በላይ
- መላኩ በላይ እና
- አድማሱ በላይ
የሚባሉ ሁለት ሴት ልጆች እና አራት ወንድ ልጆች ነበሩት፡፡