Content-Language: am ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ገጽ ሁለት
header image



(ድረ ገጽ 2)


ደጃዝማች በላይ ዘለቀ (አባኮስትር)



አባኮስትር በጦር ሜዳ ተጋድሎ የማይበገር፣ በእምነቱም የማይደራደር መሆኑን የኢጣሊያ ባለሥልጣኖች ስላመኑበት፤ በማግባባት ዘዴ ለማጥመድ ኢጣሊያዊው የጎጃም ገዥ ደብዳቤ ጽፎ ላከለት፡፡
የተላከውም ደብዳቤ ሲነበብ፤
“ደብረ ማርቆስ ድረስ መጥተህ እጅህን ብትሰጥ የኢጣሊያ መንግሥት መሐሪ ስለሆነ ምሕረት ያደርግልሃል፡፡ ልጅህንም ለቀን አንተንም የጎጃም እንደራሴ ስለምናደርግህ ለኢጣሊያ መንግሥት ታማኝ ሆነህ ግባ፡፡”
የሚል ነበር፡፡
አባኮስትርም ለተጻፈለት ደብዳቤ፤
“ጎጃምን ያህል አገር እንደራሴነት ካገኘሁ፣ ልጄም ከተለቀቀች ሌላ ምን እፈልጋለሁ፡፡ ለኢጣሊያ መንግሥት ታማኝ ናቸው የሚላቸውን መልእክተኞች ይላክልኝና እመጣለሁ፡፡”
የሚል መልስ ላከ፡፡
የኢጣሊያ ባለሥልጣናትም በአባኮስትር ደብዳቤ ተደስተው ታማኝ የሚሏቸውን መልክተኞች ላኩ፡፡ መልክተኞችም አባኮስትር ዘንድ ደረሱ፡፡
ወደ አባኮስትር የተላኩት መልዕክተኞች፤ ቀኛዝማች እጅጉ ለማ፣ ቀኛዝማች አደራና ሌላ ሦስተኛ ሰውም ነበር፡፡
አባኮስትር ወደ መልክተኞች እያፈጠጠ፤
“በሉ የምትሉትን ልስማ፡፡ ምን ዝም አሰኛችሁ? አንተ ሶስተኛው ሰው ደግሞ ማን እሚሉህ ነህ?”
በማለት በንዴት ስሜት እየተንጎራደደ ጠየቃቸው፡፡
ቀኛዝማች አደራም ሶስተኛው ሰው አስተርጓሚ መሆኑን አስረዳ፡፡
አባ ኮስትርም ድጋሚ በሚያሰፈራ አስተያየት ወደመልክተኞች እያፈጠጠ፤
“ዛሬ ደግሞ ምን ይፈልጋሉ ጌቶቻችሁ? የኢጣሊያ ታማኞች እጄን ለማያዝ ቸኩላችኋል እሳ?” ኧረ ለመሆኑ ምን መስየ ታየሁት? እጄን ይዞ ለመሾም ነው እንዲህ የቸኮለው?
በማለት ተናገረ፡፡
መልክተኞችም፤
ከናንተ ጋር ይምጣ ተብለን ታዘን ነው እንጅ እኛ ጦር አስከትለን አልመጣንም ብለው መለሱ፡፡
አባ ኮስትርም፤
“እነ አጅሬ ታማኝ መሆናችሁን መች አጣሁት? እነዚህ ሰዎች እንወደዳለን በማለት በወገናቸው ላይ እየፈረዱ ብዙ ጀግኖች ወንድሞቻችንን አስለቅሰዋል፡፡ ጎበዝ፤ እናንተም ታውቃላችሁ ፍረዱ!”
በማለት ዙሪያውን የተቀመጡትን አርበኞች ጠየቃቸው፡፡
አርበኞችም፤ “በቤልጅግ ጠመንጃ ግንባራቸውን ፈልጦ እንጨት ላይ መስቀል ነው” በሚለው ፍርድ ተስማምተው ለኢጣሊያ ታማኝ በነበሩት በሁለቱ ዳኞች ላይ ወዲያውኑ የሞት ቅጣቱ ተፈጸመባቸው፡፡
አባኮስትር በጣሊያኖች ስለተማረከችው ልጁ ሲናገር፤
“ልጄ እናቷ በጦር ሜዳ ስትሞትባት ያለኋት እኔ መሆኔ እርግጥ ነው፡፡
ቢሆንም ቅሉ አካሌ የሆነችው ልጄም ሆነች ነባቢት ነፍሴ ከኢትዮጵያ ነፃነት እንደማይበልጡብኝ አምናለሁ፡፡
ስለዚህ ራሴን የኢጣሊያ መሣሪያ በማድረግ ልጄን ከምርኮኛነት አላወጣትም፡፡”
በማለት ቁርጥ ያለ አቋሙን ተናገረ፡፡
ከዚህ በኋላ አባኮስትር በላይ የደብረ ማርቆስ ገዥ ለሆነው ለኢጣሊያ አዛዥ በጻፈው ደብዳቤ ላይ፤
“የላክልኝን እንግዶች በሚገባ አስተናግጃቸዋለሁ፡፡
ወሬውን እንዲነግርህ የላካችሁትን አስተርጓሚ መልሼ ልኬዋለሁ፡፡
ጎጃም የእኔ አገር ሲሆን፤ አንተ ደግሞ ከሮማ መጥተህ የጎጃምን እንደራሴነት እሰጥሀለሁ ማለትህ ያሳዝናል፡፡
ልጄንም፣ እኔንም የፈጠረን እግዚአብሔር ነው፡፡
ልጄን እንደፈለክ አድርጋት እንጅ እኔ ለኢጣሊያ መንግሥት ታማኝ ሆኘ አልገዛም፡፡”
የሚል መልስ ላከላቸው፡፡
Shashework Belay, the Daughter of Belay Zeleke
በ10 ዓመት ዕድሜዋ በጠላት ተማርካ የነበረቸው
የበላይ ዘለቀ ሴት ልጅ ወይዘሮ ሻሸወርቅ በላይ
በመካከለኛ የዕድሜ ዘመኗ የተነሳችው ፎቶ

ፎቶው ተወስዶ የተስተካከለው ከ፤ borkena.com
የአባኮስትር ልጅ ሻሸወርቅ በላይ የተወለደችው በ1920 ዓ.ም. አካባቢ ሲሆን ስትማረክ ገና የ10 ዓመት ልጅ ነበረች፡፡
ጣሊያኖች አባ ኮስትርን አባብሎ ወደ እነርሱ ለማስገባት ያሰቡት ሁሉ ሳይሳካ ቀረ፡፡
የአባኮስተር ሠራዊት የኢጣሊያንን ጦር ገጥሞ በጠላት ላይ ከፍተኛ ጉዳትና ውርደት በማድረሳቸው በተገኘው ድል አርበኞች ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸዋል፡፡
በዚህም ጦርነት፤ የኢጣሊያ ጦር አዛዥ አንድ ኮሎኔል ጨምሮ 28 የኢጣሊያ ወታደሮች፣ አንድ ሺህ ያህል የባንዳ ወታደሮች፣ ሲሞቱ፤ በከብት የሚጫን አንድ የውሃ መትረየስ፣ 9 የራዲዮ መገናኛ፤ 9 ባዙቃና በርካታ ጠመንጃዎችና ጥይቶች ተማርከዋል፡፡
ጠላት በዚህ በደረሰበት ከፍተኛ ሽንፈት ምክንያት ሽብር ላይ በመሆኑ፤ አራቱ ያባ ኮስትር ታማኝ አሽከሮች ከሻሸወርቅ ሞግዚት ጋር በአንድነት ሆነው ልጅቷን ከኢጣሊያ የጦር ካምፕ ለማሶጣት አቀዱ፡፡
እቅዳቸውንም በድብቅ ሄደው ለአባኮስትር በማማከር በነሐሴ ወር 1932 ዓ.ም. በግምት ከምሽቱ 3 ሰዓት ነጎድጓዳማ ካፊያ በነበረበት ጥቅጥቅ ባለ ጨለማ ውስጥ ልጅቷን ይዘው ከጠላት ካምፕ አውጥተው ወደ ሸበል በረንታን በረሃ ይዘዋት ሄዱ፡፡
በመጨረሻም ያባ ኮስትር ታማኝ አሽከሮች፤ እነአባኮስትር የሠፈሩበት የጦር ካምፕ ሲደርሱ፤ አባኮስትር እና አርበኞቹ በተሰበሰቡበት በትልቅ አዳራሽ ውስጥ ሰፊ ድግስ ተደግሶ፣ እየተበላና እየተጠጣ፣ ፉከራው እና ቀረርቶው ደምቆ ነበር፡፡
አባኮስትርም ልጁ የሻሽወርቅ በላይ ከጠላት እጅ ወጥታ በደህና መድረሷና ከእርሱ ጋር በመገናኘቷ ከፍተኛ እፎይታና ደስታ ተሰምቶታል፡፡
አባኮስትር ለሚያቅራራው ሰው የሚከተለውን የሽለላ ግጥም ነገረው፡፡
አህያ ነው ጣሊያን ክብሩን የማይጠብቅ፣
ከሰው ሀገር መጥቶ እማይጠነቀቅ፡፡
እማይሆንለትን ከጀግና አገር ገብቶ፣
ከእኛ እጅ ጣለው ኃጢያቱ በርክቶ፡፡
ለገንዘብ የሚሞት የቅጥር ወታደር፣
ራሱን ያፈቅራል አይሆንም ለሀገር፡፡
አይሆንም ለሀገር አይሆንም ለዘመድ፣
ለገንዘብ የሚሞት ይቅር አይወለድ፡፡

የአባኮስትር አርበኞችም ስለአባኮስትር ሲናገሩ፤
“ከግል ክብርና ዝና ይልቅ ለሀገርና ለሕዝብ ደህንነት የሚጥር ወጣት የጦር መሪ በማግኘታችን ዕድለኞች ነን፡፡
ንቁነቱ፣ ደፋርነቱ፣ ለጭፍራው አሳቢነቱ፣ ሐይማኖተኛነቱ፣ ለሕዝብ ተቆርቋሪነቱ እና ለሀገር ነፃነት ታጋይነቱ፤ አባኮስትር በላይን የልጅ አዋቂ አድርጎታል፡፡”
በማለት መሪያቸውን አሞግሰውታል፡፡
በመስከረም ወር 1933 ዓ.ም. ላይ፤ ጠላት ከመሸገባቸው ከተሞች ለማስለቀቅ ስለሚቻልበት ሁኔታ ለመመካከር አባኮስትር ከ 20 በላይ የሚሆኑ የጦር አለቆቹን ሰብስቦ በቅድሚያ በአቅራቢያቸው በብቸና በመሸገው የጣላት ጦር ላይ ድንገተኛ አደጋ ለመጣል እቅድ እያወጡ ይወያያሉ፡፡
በስብሰባው ከተገኙትም የጦር አለቆች መካከል፤

  1. ራስ ተመስገን ፈንታ
  2. ደጃዝማች እጅጉ ዘለቀ (የበላይ ዘለቀ ታናሽ ወንድም)
  3. ደጃዝማች አያሌው መሸሻ
  4. ደጃዝማች ለገሠ ሐሰኔ
  5. ደጃዝማች በቀለ ቦጋለ
  6. ፊታውራሪ ተሻለ ዓለሙ
ይገኙበታል፡፡
በጎጃም ክ/ሐገር በእነማይ ወረዳ
በወይብላ ማሪያም ቀበሌ የሚገኘው
ይህ ዋርካ ጣሊያኖች በመድፍ ስለመቱት እና
ሁለቱ ከባድ ቅርንጫፎቹ ተገንጥለው ስለወደቁ
"የቆሰለው ዋርካ" የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
አባኮስትር በላይ የጦር አዛዦቹን ሰብስቦ
የጦር አመራርና ሹመት የሚሰጥበት፣
ግብዣ የሚደረግበት ሥፍራ እንደነበረ
በቦታው የነበሩ እድሜ ጠገብ አባቶች ያስረዳሉ

ምስግና፤ ለአርሶአደሮች ወግ ፐሮግራም (አሚኮ)
በመካከሉ እራስ ኃይሉ ተክለ ሐይማኖት ከአባኮስትር ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ ይዘው ኖሮ በቀጠሯቸው መሰረት ጥር 22 ቀን 1933 ዓ.ም. አባኮስትር በላይ በሚገኝበት በለምጨን ሰቀላ ገብርኤል በተባለው ቦታ ደርሰው ከአባኮስትር ጋር ከተገኛኙ በኋላ፤
“ወደ አንተ የመጣሁበት ምክንያት በጎጃም የሰላም ድርድር ለማድረግ ከኢጣሊያ መንግሥት ሥልጣን ተሰጥቶኝ ነው፡፡” በማለት ለአባኮስትር ነገሩት፡፡
አባኮስትርም በበኩሉ በዚህ አይነት ንግግር እንዲሸነገል እንደማይፈልግ እና ወደመጡበት እንዲመለሱ ሲነግራቸው፤ እርሳቸውም በበኩላቸው፤ ጠላት በቅርቡ የብቸናን ምሽግ በፈቃዱ ለቆ ስለሚወጣ እንዳቶጋው፤ ከወጋኸው አገሩን ያጠፋል፣ ሕዝብ ይጨርሳል፤ ብለው ስለነገሩት አባ ኮስትርም አገር እንዳይጠፋና ሕዝብ እዳያልቅ በማሰብ በነገሩ ተሰማማ፡፡
ራስ ኃይሉም ከንግግሩ በኋላ ከእንግዲህ ወዲያ እርሳቸውም ለኢጣሊያ ወግነው እንደማይዋጉ ለአባኮስትር አረጋገጡለት፡፡

ራስ ኃይሉ ተክለ ሐይማኖት በ 1924 ዓ.ም. ልጅ እያሱን ከእስር ቤት እንዲያመልጡ አድርገዋል ተብሎ ንብረታቸው ተወርሶ አሩሲ ውስጥ ታስረው ነበር፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ውጭ ሐገር ሲሄዱ ራስ ኃይሉ ከእስር ቤት ወጥተው ከአዛዥ ከበደ ተሰማ ጋር ተቆራኝተው ድሬዳዋ ድረስ ወስደዋቸው እዚያው ድሬዳዋ ትተዋቸው ሄደው ስለነበረ ራስ ኃይሉ የጠላት ተባባሪ በመሆን “ርዕሰ መኳንንት” የሚል ማእረግ በኢጣሊያ ሹመት ተሰጥቷቸው ለጠላት ያገለገሉ የነበሩ ሰው ናቸው፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ ነፃ አውጭ ጦር ይዘው በመግባት ምእራብ ጎጃም በሚገኘው ኦሜድላ በተባለው ቦታ ጥር 12 ቀን 1933 ዓ.ም. ደረሱ፡፡
የንጉሠ ነገሥቱ መልዕክተኛ የሆኑት አዛዥ ከበደ ተሰማ ለኢትዮጵያ መኳንንቶችና ለአርበኞች መሪዎች የግርማዊ ጃንሆይን ምክርና ትእዛዝ ሲያስተላልፉ ለአባ ኮስትርም በተጻፈለት ደብዳቤ መሰረት እርሱም በጽሁፍ የተስማማበትን በፊርማው አረጋግጦ ህዳር 10 ቀን 1933 ዓ.ም. ለአዛዥ ከበደ ተሰማ በላከው ደብዳቤ፤
“የሸዋን በር ከጠላት አስከፍቶ ጎጃምን ከሸዋ ለማገናኘት የቦረናን፣ የጫቀታንና የደራን አርበኞች ለማሳመን የሚቻለኝን እሠራለሁ፣
በደብማርቆስ፣ በብቸናና በደጀን በኩል የሚገኙትን ባንዳዎች ከጠላት ለመነጠል እሠራለሁ፣
ለመሣሪያ መጓጓዣ የሚሆኑ አጋሰሶችን የሚፈለገው ቦታ ድረስ እልከለሁ፣
ማንኛውንም የንግድ ዕቃ ጠላት ወዳለበት ከተማና ምሽግ እንዳይገባ አስከለክላለሁ፡፡
በእግዚአብሔር አጋዥነት በሚቻለኝ ሁሉ ጠላትን ለማጥቃትና የእኛ ኃይል በርትቶ ንጉሠ ነገሥታችን የነፃነት ባንዲራ ይዘው የኢትዮጵያ መሬት እንዲገቡ በመተባበር እሠራለሁ ስል በፊርማዬ አረጋግጣለሁ፡፡”
የሚል ነበር፡፡
አባኮስትርን ከኢጣሊያ ሌላ እጅግ ያሳሰበው ጉዳይ ከኢጣሊያ አገዛዝ ነፃ አወጣችኋለሁ ብሎ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የመጣው የነጭ ጦር (የእንግሊዝ ወታደር) ነው፡፡
አባ ኮስትር፤ “ነጭ ምንጊዜም ለኛ አይተኛም፤ ዘመድ አይሆኑንም፡፡” የሚል ሀሳብ አለው፡፡
አዛዥ ከበደ ተሰማ በድሉ ዋዜማ የንጉሠ ነገሥቱን መልእክት ለማድረስ ጎጃም ሲመጡ ከአባኮስትር ጋር በመጻጻፍ በሕዳር ወር 1933 ዓ.ም. ከአባኮስትር ጋር ለመገኛኘት ቀጠሮ ይዘው በእነማይ ወረዳ፣ መንግሥቶ ማርያም ቀበሌ ተገናኝተው ተነጋግረዋል፡፡
ኮሎኔል ስታንፈርድን ከአባኮስትር በላይ ጋር ለማስተዋወቅ ከተገናኙ በኋላ አባኮስትር ወደ ኮሎኔሉ እየተመለከተ፤ “ያንኑ ጣሊያንን ነው የሚመስሉት፡፡” እያለ በማንገራገር ለመተዋወቅና እጁን ሰንዝሮ ለመጨበጥ አልፈቀደም፡፡
ኮሎኔል ስታንፈርድም ከአባኮስትር ጋር በንግግር ባለመጣጣማቸው ሊቆዩ ስላልፈለጉ ተመልሰው ሄዱ፡፡
ከንግግሩም በኋላ አዛዥ ከበደ ተሰማ ለንጉሠ ነገሥቱ ባስተላለፉት መልእክት፤
“ካየናቸው አርበኞች ሁሉ በአርበኞች ብዛት እጅግ ብልጫ ያለው ከፍ ያለ የአርበኞች ሰልፍ ከጦር ሜዳ ላይ አሳዩን፡፡”
“ስንገናኝም ሰለአቀባበሉ ደስታ መትረየስ ይተኮስ ነበር፡፡
በአቀባበላቸውም በጣም ደስ አሰኝተው የተቀበሉን ሲሆን ለሥራ ጉዳይ በምንነጋገርበትም ጊዜ ጥቂት ወደ ባላገርነት ስለሚያደሉ ደስ የሚያሰኝ መልስ ሊሰጡን አልቻሉም፡፡
ሆኖም ያለውን አርበኛ አግባብተን በማነጋገር ነገሩን አለዝበን ምክሩን እንዲቀበሉ አደረግን፡፡”

በማለት ስለ አባኮስትር ያላቸውን አስተያየት በማስታወሻቸው አስፍረዋል፡፡
አባኮስትር የእንግሊዞችን የወደፊት ዓላማ በመጠራጠሩና ኮሎኔል ስታንፈርድን በቀና መንፈስ አለመቀበሉን የሰማው ሻለቃ ውንጌት አባ ኮስትርን የተለየ ዓላማ እንዳለው ሰው አድርጎ ቆጠረው፡፡
ሻለቃ ዊንጌት በእንግሊዝ በታወቀው የሳንድኸርስት ሚሊተሪ አካደሚ ውስጥ በጦር መኮንንነት ሙያ ይሰለጠን በነበረበት ወቅት፤ ፊት ለፊት ጦርነት ከመግጠም ይልቅ የሽምቅ ውጊያ ሥልት የበለጠ ውጤታማ መሆኑን የምርምር ጽሁፍ ያቀረበ በመሆኑና ጽሁፉንም ያነበቡት የብሪታንያ መንግሥት ባለሥልጣናት ሻለቃ ዊንጌት የጻፈውን ጽሁፍ በሥራ ለመተርጎም ከኢትዮጵያ ምድር የኢጣሊያን ፋሽስት ጦር ለማሶጣት በምእራብ ኢትዮጵያ ግንባር ለዘመተው የእንግሊዝ ጦር አዛዥ እንዲሆን መርጠው ወደ ኢትዮጵያ የላኩትና በአጭር ጊዜ ውስጥም በሙያው ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ የጦር አዛዥ ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ አባኮስትር በላይ ዘለቀ፤ በትምህርት ሳይሆን በልምድ ባገኘው እውቀት የደፈጣ የጦር ስልትና ውጊያ ውጤት እንደሚያስገኝ ያመነና በፊት ለፊት ውጊያም ቢሆን በተግባር ያስመሰከረ፣ በዚሁ የውትድርና አመራር በርካታ ጀብዶዎችን ያሰመዘገበ፣ በፋኖነት ተሠማርቶ በዱር በገደሉ እየተንከራተተ ጠላትን መግቢያ መውጫ ያሳጣ፣ ለሚወዳት ለእናት አገሩ ለኢትዮጵያ ነፃነት ሲል በሀቅና በቆራጥነት የታገለና የእርሱ ተከታይ የሆነው ሁሉ የሚወደውና የሚያከብረው ጀግና አርበኛ ነው፡፡

ሻለቃ ውንጌት የጀግናውን በላይ ዘለቀን ትክክለኛ አቋምና በአርበኝነት ዘመኑ ለእናት አገሩ ነፃነት ሲል የከፈለውን መስዋዕትነት፣ የፈፀማቸውን ጀብዶዎችና ያጋጠሙትን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተረድቶ ቢሆን ኖሮ የሞት ፍርድ እንዲፈረድበት ባላሳሰበም ነበር፡፡
የጠላት ጦር 154 መኪና ቀርቦለት እቃውን ጭኖ ጥር 23 እና 24 ቀን 1933 ዓ.ም. ከብቸና ለቆ ወደ ደብረ ማርቆስ ለመጓዝ ሥፍራውን ለራስ ኃይሉ ተክለ ሐይማኖት አስረክቦ ሲወጣ፤ ራስ ኃይሉ በበኩላቸው ጣሊያን ጎጃምን ለቆ ሲወጣ መሣሪያውን ተቀብለን እኛ ባላባቶች ጎጃምን እንገዛለን የሚል ፍላጎት ነበራቸው፡፡
አባኮስትር በላይ ዘለቀ ደግሞ፤ ጣሊያን ብቸናን ይልቀቅልን እንጅ ለንጉሠ ነገሥታችን ነው የምንረዳው በማለት አቋሙን ቀደም ብሎ ለንጉሠ ነገሥቱ መኳንንቶችና ለብዙ አርበኞቻቸው አስረድቷል፡፡
ራስ ኃይሉ በበኩላቸው ከአባኮስትር በላይ ዘለቀ ጋር ለመታረቅ ፈልገው አልተሳካላቸውም፡፡
በዚህም ምክንያት ራስ ኃይሉ ብቸና ድረስ ቀርበው አባኮስትር በላይ ዘለቀ ወደ እርሳቸው እንዲገባ ቢጠይቁት አምቢ ሰላላቸው ራስ ኃይሉ የላኩትን ጦር ወግቶ 18 የነፍስ ወከፍ መሣሪያ ማርኮ መልሷቸዋል፡፡
አባኮስትር በላይ በበኩሉ የንጉሠ ነገሥቱ ወደ አዲስ አበባ የጉዞ መንገድ ከጣለትና ከባንዶች እንቅፋት እንዳይገጥመው ለመከላከል የሚሠራውን ሥራ በቀጥታ ለአዛዥ ከበደ ተሰማ ጽፎ የላከውና ለንጉሠ ነገሥቱ የደረሰው ደብዳቤ፤
“ወደ እኔ ከተላኩለት፤ ከልጅ መርድ መንገሻ፣ ከካፒቴን ቴሴንጀር፣ ከካፒቴን ፎሊና ከሊፍተናንት ካላርክ ጋር በመገናኘት ሠራዊቱን አሰልፌ በደጀን ዙሪያ ያለውን ጠላት ሁሉ አስከብቤ እጠባበቃለሁ፡፡
መድፍ፣ መትረየስና ጥይት ቢላክልኝ በዓባይ በረሃ ሁሉ ጦር እያዘጋጀሁ ሥራ መሥራት እችላለሁ፡፡
…በጎጃም የቆዩ ባላባቶችና መኳንንቶች፤ አሁን ለንጉሠ ነገሥቱ ክብር አስመስለው ቢያሶሩ ሁሉም የጠላት ሹም መሆናቸውን ሰምተውታል፡፡
ስለዚህ እኔን በምቀኝነት ስለሚጣሉኝ የእኔን ድካም እንዳይረሱት ለክቡርነትዎ አስታውሳለሁ፡፡
...መጋቢት 16 ቀን 1933 ዓ.ም.
...በላይ ዘለቀ”

(መስመር የተጨመረ)
የሚል ነበር፡፡
ንጉሠ ነገሥቱም የበላይ ዘለቀ ደብዳቤ እንደደረሳቸው መጋቢት 23 ቀን 1933 ዓ.ም. ለአዛዥ ከበደ ተሰማ በጻፉት ደብዳቤ ከማረጋገጣቸውም በላይ ንጉሠ ነገሥቱ በድጋሚ መጋቢት 26 ቀን 1933 ዓ.ም. አርበኞች የሚጠባበቁበትን ሥፍራ ለማሳወቅ ለአዛዥ ከበደ ተሰማ በጻፉት ደብዳቤ ላይ በላይ ዘለቀ የሚጠባበቅበትን ሥፍራ በግልጽ ጠቅሰው ማሳወቃቸው ለበላይ ዘለቀ ያለቸውን ቀና አመለካከት የሚያሳይ ነበር፡፡
ጠላት ደብረማርቆስን ለቆ ከወጣ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ ደብረማርቆስ ገብተዋል፡፡
በከተማው የሚወራው የአባኮስትር ዝና ሆኗል፡፡
በጀግንነቱ በአምስት አመታት የጠላት ወረራ ወቅት የኢጣሊያንን መንግሥት ሥልጣን ፈጽሞ ባለመቀበልና በምስራቅ ጎጃም ሙሉ ሥልጣን ያለውን ይህን ታላቅ የአርበኛች መሪ በዚህን ወቅት በጥፋተኝነት መቅጣት የማይሞከር ሆኖ በመገኘቱ ክሱ ሰሚ ሊያገኝ አልቻለም፡፡
አባ ኮስተር፤ የጠላትን ጦር በደጀን በኩል ለምን ዝም ብሎ እንዳሳለፈው ንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ ቀርቦ ተጠይቆ ነበር፡፡
ያልተዋጋበትን ምክንያት ለንጉሠ ነገሥቱ መልስ ሲሰጥ፤ የተሟላ ድርጅትና ትጥቅ ይዞ በአይሮፕላንና በመድፍ እየታገዘ በቀቢፀ ተስፋ ከሚዋጋ የጠላት ጦር ጋር መጋፈጡ ሰው ማስጨረስ ብቻ እንደሚሁን በማሰቡ መሆኑን አስረድቷል፡፡
የሞት ፍርድ እንዲፈረድበት ቀርቦበት የነበረው ክስም ተግባራዊ ሳይሆን የቀረው በዚህ በተጠቀሰው ምክንያት እንደነበረ ይገመታል፡፡
Grand children of Belay Zeleke
የበላይ ዘለቀ የልጅ ልጆች
ወ/ሮ ገነት እና አቶ ሄኖክ

Credit to: borkena.com
(adapted by the webmaster)
image link
ስፍር ቁጥር የሌለው የአባኮስትር ሠራዊት በአምስት ረድፍ ተሰልፎ በጦር አለቆች እየተመራ መትረየሱንና ጠመንጃውን በትከሻው ላይ ይዞ፣ ትጥቁን አሳምሮ ጎፈሬውን አጎፍሮ ወኔ በሚቀሰቅስ ሽለላና ፉከራ ጀብዱን እየዘረዘረ መትመም ጀምሯል፡፡
የሠራዊቱ ጠቅላይ አዛዥ ጀግናው በላይ ዘለቀ ካኪ ኮት ለብሶ፣ ከጉልበት ወረድ ያለ ሱሪ ታጥቆ፣ ባርኔጣ አድርጎ በበቅሎ ላይ ተቀምጦ በጋሜዎች ታጅቦ በልበ ሙሉነትና በክብር መጥቶ ንጉሠ ነገሥቱ ከተቀመጡበት ሰገነት ፊት ለፊት ሲደርስ ከበቅሎው ወርዶ ከጋሻ ጃግሬው ጠመንጃውን ተቀብሎ በመያዝ፤
ባንዲራው የዘለቀ ልጅ፣
ሶላቶ ገዳይ ጦር ሳይደራጅ፡፡
የዘለቀ ልጅ ቆራጥ ወታደር፣
ጠላቱን ገዳይ ሳይውል ሳያድር፡፡
በላይ ዘለቀ የባንዳ እረኛ፣
የማያስቀምጥ የማያስተኛ፡፡
ብሎ ከፎከረ በኋላ፤
“እኔ የዘለቀ ልጅ በዚች ናስ ማስር ጠመንጃ ተነስቼ ነው ከዚህ ደረጃ ለመድረስ የቻልኩትና የጣሊያንን ጦር ያርበደበድኩት፡፡” በማለት በአጭሩ ተናግሮ ለንጉሠ ነገሥቱ እጅ ነሣ፡፡
የሁሉም ሰው ዓይን በእርሱ ላይ አረፈ፡፡
በላይ ዘለቀ ቁመናው ሲታይ፤ መልኩ ቀይ፣ ጎፈሬው ክርክም፣ ግንባሩ የተቆጣጠረ፣ አፍንጫው ስልክክ ያለ፣ ዓይኖቹ ትልልቅ፣ ከንፈሩ ከበድ ያለ፣ ፂሙ ለስላሳና ረጅም፣ጣቱ ወዛም፣ እግሩ ቀጭን ሆኖ ቁመቱ መካከለኛና ሰውነቱ ከሲታ የሆነ ሰው ነው፡፡
በላይ ዘለቀ፤ በጀግንነቱና በከፍተኛ የጦር አመራር ችሎታው ስሙና ዝናው እጅግ የገነነ ሲሆን ዝናውን የሚያወቁት ሁሉ መች መጥቶ ባየነው እያሉ እጅግ ጓጉተው የጠበቁት በላይ ዘለቀ፤ በአካለ ስጋ ሲታይ ግን፤ የአካል ግዝፈት የሌለው፣ ለዓይን የማይሞላ፣ በአለባበሱ ያልተሽቀረቀረ፣ በባዶ እግሩ የሚሄድ፣ አንድ ትሁት ሰው በመሆኑ የዚህ ግዙፍ ቁጥር ያለው ሠራዊት የጦር መሪ እርሱ ነው ብሎ ለማመን አብዛኛው ተመልካች ተችግሮ ነበር፡፡
የተመለከቱት ሰው አባኮስትር በላይ ዘለቀ መሆኑን ያመነቱትም ቢሆኑ ሳይወዱ በግድ በመጨረሻ ከልዑል ራስ ኃይሉ አጠገብ የተወሰነለትን የክብር ሥፍራ ይዞ ሲቀመጥ ማመን ቻሉ፡፡
በመጨረሻም በአጭር ማስታዎቂያ ብቻ ለሠልፍ የተጠራው የበላይ ዘለቀ ሠራዊት በ17 የጦር ምድብ ተከፍሎ የየምድቡ አለቆች እየመሩት በሰልፍ ሆኖ እየፎከረና እየሸለለ በክብር ትሪቡን ፊት ማለፍ ጀመረ፡፡
በሰልፉ የተገኘው የበላይ ዘለቀ ሠራዊት ቁጥሩ እጅግ ብዙ ስለነበረ ሰልፉ ታይቶ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከ4 ሰዓት በላይ ፈጅቷል፡፡
ከሰልፉም በኋላ ከተማው በሰልፈኛው ብዛት እንዳይጨናነቅ በማለት ከከተማው ወጣ ባለ ስፍራ እንዲሰፍር ተደረገ፡፡
የበላይ ዘለቀ ሰልፍ በታየ ማግስት፤ የአባ ኮስትርን የጀግንነት ዝና የሰሙትና በሠልፉም የተደሰቱት ንጉሠ ነገሥቱ፤ ደብረማርቆስ ቤተ መንግሥት ተቀብለው ለማነጋገር አስጠሩት፡፡
አባ ኮስትርም ወደ ቤተ መንግሥቱ ሰተት ብሎ ከገባ በኋላ ጥቂት እንደተራመደ ዞር ብሎ ወደኋላው ሲመለከት ማንም የተከተለው ሰው ባለመኖሩ በብስጭት እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ወደኋላው በፍጥነት ተመለሰ፡፡
ብቻውን የገባበትም ምክንያት የቤተ መንግሥቱ ጠባቂዎች የሆኑት የእንግሊዝ ወታደሮች የአባኮስትር አጃቢዎችን ማለትም ታናሽ ወንድሙን ደጃዝማች እጅጉ ዘለቀንና ሌሎችን የጦር አለቆቹን አናስገባም በማለታቸው መግቢያው ላይ መገፈታተር ስለነበረ እረብሻ በመፈጠሩ ነበር፡፡
በዚህ መካከል አባኮስትር መሆኑን ያላወቀ አንዱ ዘበኛ፤ “የማነው ዘበናይ! የእናቱ ቤት መሰለው?” እያለ ሲናገር አባኮስትር ሰምቶ፤
“ይችን ይወዳል የዘለቀ ልጅ!”
በማለት አስደንጋጭ አይኑን ሲያጉረጠርጥ ሁኔታውን የተመለከቱት ሻለቃ መስፍን ስለሽ በብልሀት የአባ ኮስትርን ወንድም ደጃዝማች እጅጉ ዘለቀንና ጥቂት ሹማምንቶች እንዲገቡ ሲያደርጉ፤ አባ ኮስትርም ከንዴቱ መለስ ብሎ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ አመራ፡፡
ንጉሠ ነገሥቱም ዘንድ ከቀረበ በኋላ፤
“ትላንትና ባየነው የሠራዊትህ ሰልፍ እጅግ ተደስተናል፡፡ አሁን ያስጠራንህም ይህን ልንገልጽህ ነው፡፡ ከዋናው ቤተ መንግሥታችን እንደገባን ውለታህን ለመክፈል ቃል እንገባለን፡፡
ለመሆኑ ወንድሞችህ እነማን ናቸው?”

በማለት ንጉሠ ነገሥቱ በፈገግታ ጥያቄ አቀረቡለት፡፡
አባ ኮስትርም በበኩሉ ሲመልስ፤
“ጃንሆይ! አብረውኝ የደከሙት ሁሉ ወንድሞቸ ናቸው፡፡ ታናሽ ወንድሜ ይህ ነው፡፡”
በማለት ደጃዝማች እጅጉን አቅርቦ አስተዋወቀ፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ቀጥለውም፤
“አገርን እንደማስተዳደር ያለ ተግባር አለ...”
ሲሉት አባ ኮስተር በበኩሉ ሲመልስ፤
“እኔ ተራ ሰው ነኝ፡፡ የ‘ዘር’ ሐረግ የሚቆጥሩ ሰዎች አያሰሩኝም፡፡ ከርስዎም ጋር ያጣሉኛል፡፡”
በማለት ያለውን ስጋት ገለፀላቸው፡፡
ንጉሠ ነገሥቱም አያይዘው፤
“እኛ የማንንም ወሬ በአንተ ላይ አንሰማም፡፡ እንደአባትህ ቁጠረን፡፡
በዚህ በልጃችን በመኮንን ይሁንብን፡፡”

የሚል ቃል ከገቡለት በኋላ፤
“ወደ አዲሰ አበባ አብረን ብንሄድስ?፡፡”
ብለው ሲጠይቁት አባ ኮስትርም፤
“በጦርነት ላይ የወደቁትን የወንድሞቸን አፅም ከየቦታው ሰብስቤ ወደ ቤተ ክርስቲያን አድርሼ፣ ተስካራቸውን ካወጣሁ በኋላ እመጣለሁ፡፡”
በማለት በትህትና መለሰላቸው፡፡ ከዚያም ንጉሠ ነገሥቱ የተስካር ማውጫ ይሁንህ ብለው የተወሰነ ገንዘብ ሰጥተው አሰናበቱት፡፡







ምንጭ፤
  1. "አባኮስትር - ታሪካዊ ልብወለድ"  ደራሲ፡- አበራ ጀምበሬ 1983 ዓ.ም.
  2. "የታሪክ ማስታዎሻ"  ደራሲ፡- ደጃዝማች ከበደ ተሰማ 1962 ዓ.ም.
  3. "የኢትዮጵያ ታሪክ ከ 1847 እሰከ 1983"  ደራሲ፡- ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ