Content-Language: am ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ገጽ ሦስት
header image


(ድረ ገጽ 3)

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ



Italia war map to invading Ethiopia
ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር ያዘጋጀው ካርታ

Image Credit to: nanopdf(re-touched by the webmaster)
ግራዚያኒ ለደቡብ ጦር ግንባር ያሰለፋቸው ቦንብ ጣይ የጦር አውሮፕላኖች ብዛት 100 ይደርሳል፡፡
የግራዚያኒ ጦር በደቡብ ኢትዮጵያ አቅጣጫ ያለውን ሐረርጌን ለመያዝ በማቀድ፤ የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት ከሆነችው ከሶማሊያ ከሦስት አቅጣጫ በመነሳት በኢትዮጵያ የኦጋዴን ድንበር በሆኑት ቦታዎች በቆራሄና በዶሎ ላይ ጦርነት ከፍቶ እየተዋጋ ወደፊት በመግፋት ደጋሀቡርን አልፎ ጉዞውን ጀመረ፡፡
ራስ ደስታ ዳምጠው፤ ጥሩ ትጥቅ የነበረውን፣ የሰለጠነ፣ ለአገሩና ለንጉሠ ነገሥቱ ታማኝና ተራማጅ አስተሳሰብ ያለውን ቁጥሩ 40 ሺህ የሚደርስ ጥሩ ተዋጊ ወታደሮቻቸውን እየመሩ ከነገሌ ቦረና በመነሳት፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ግንባር የተሰለፈውን በግራዚያኒ በሚመራው የፋሽስት ጦር ላይ ውጊያ ከፍተው የኦጋዴን ድንበር የሀነችውን ዶሎን ከተቆጣጠሩ በኋላ ግራዚያኒን ለመውጋት ወደ ኢጣሊያ ሶማሌላንድ አመሩ፡፡
ራስ ደስታ ዳምጠው፤ ዋና ዋና አሽከሮቻቸው
Ethiopian Fighters at Ogaden
የደቡብ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች
ወደ ጦር ሜዳ ሲጓዙ

Photo Credit to: newafricanmagazine
የሆኑትን ፊታውራሪ አደመ አንበሶንና ፊታወራሪ ታደመ ዘለቃን እፊት በማስቀደም፤ እርሳቸው የኋላ ደጀን ሆነው፤ ጦራቸው ግን ከፊት እየተዋጋ የኢጣሊያ ግዛት የሆነችው ሶማሊያ ሲደርሱ፤ በኢጣሊያ ሶማሌ ግዛት ውስጥ ታላቅ ሽብርና ፍርሀት ነገሠ፡፡
በዚህ ስጋት የገባው ግራዚያኒ፤ በሶማሌ ያለው መቶ ሺህ ጦር አይበቃኝምና ተጨማሪ ጦር ይላክልኝ እያለ ለአለቆቹ መልዕት ያስተላልፍ ነበር፡፡
ግራዚያኒ ይህም አልበቃው ብሎ፤ ሶማሌዎችን ሰብስቦ ስለኢትዮጵያውያን ጦር ያስነገረው አዋጅ፤
“…ኢትዮጵያውያን ሶማሌን ለመውረር ተሰልፈዋል፡፡
…አኛ ተዋግተን ከተሸነፈን፤ በመርከባችን ተሳፍረን ወደ አገራችን እንመለሳለን፡፡
…እናንተ ግን የምትሄዱበት ስለሌላችሁ፤ ኢትዮጵያውያን፤ የእናንተን ወንዶች እየሰለቡ፤ ሴቶችን ጡታቸውን እየቆረጡ ይበሉታል፡፡ ምግባቸውም የሰው ሥጋ ነው፡፡
…ስለዚህ፤ ነጋዴ ነኝ፤ ገበሬ ነኝ ሳትሉ በአንድነት እንዋጋ፡፡”

የሚል መልዕክት የያዘ ነበር፡፡
Ras Abebe Damtew
በጣሊያኖች አይን እንደ አደገኛ ጠላት የሚታዩት
ጀግናው የደቡብ ጦር መሪ ራስ ደስታ ዳምጠው

credit to: Ethiopicus
በዚህም የግራዚያኒ የውሸት ስብከት የተታለሉ የሶማሌ ሰዎች፤ መሣሪያ እየተቀበሉ በሐይማኖት ከሚመሳሰሏቸው ከሊቢያ ከመጡ የቅኝ ግዛት ወታደሮች ጋር ለውጊያ ተሰለፉ፡፡
ግራዚያኒም ቆራሄ የሚገኘውን የኢትዮጵያን ምሽግ በተከታታይ በአይሮፕላን በሙስታርድ ጋስ ቦንብ የኢትዮጵያን ሠራዊት መጨፍጨፍ ጀመረ፡፡
በመጨረሻም የአዲስ አበባው የየካቲት 12ቱ እልቂት በሚካሄድበት ዕለት፤ በጣሊያኖች አይን እንደ አደገኛ ጠላት የሚታዩት ራስ ደስታ ዳምጠው፤ ከረዳታቸው ከደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ ጋር በመሆን፤ ከጠላት ጋር ብርቱ ውጊያ ካደረጉ በኋላ፤ ደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ በጦር ሜዳ ሲሞቱ፤
ራስ ደስታ ዳምጠው ቆስለው ከጦር ሜዳ በማፈግፈግ በጉራጌ አካባቢ መስቃ ከተባለው ሥፍራ ተኝተው በስቃይ ላይ እያሉ በጠላት እጅ ከወደቁ በኋላ ሳይውሉ ሳያድሩ በ45 ዓመት እድሜያቸው በጠላት ጥይት ተረሽነው ተገድለዋል፡፡
በዚህ ጊዜ የባሌ አገረ ገዥ የነበሩት ደጃዝማች በየነ መርድ፤ የጦር ወታደሮቻቸውን እንደያዙ፤ ከባሌ ጊኒር ወደ ዋቢ ሸበሌ ይጓዙ ነበር፡፡
አገሩን ከድቶ ወደ ኢጣሊያ ጦር የወገነው ወሎል ጂሌ፤ የራሱንና ብዙ የሶማሌ ወታደሮችን ይዞ በኢጣሊያኖች መሪነት በድምሩ 7 ሺህ ወታደሮችን ይዞ ወደፊት ይጓዝ ነበር፡፡
Ras Desta Damtew
ራስ ደስታ ዳምጠው በየካቲት ወር
1929 ዓ.ም. እጃቸው በጠላት ሲያዝ

image ink
ከዚህ በኋላ ታህሳስ 17 ቀን 1928 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ወታደሮች በጀግንነት እየተዋጉ ሳለ፤ 19 የኢጣሊያ ቦምብ ጣይ አይሮፕላኖች ደርሰው፤ ሰባት ቶን ክብደት ያለው የሙስታርድ ጋስ ቦምብ፤ በደጃዝማች በየነ መርድ የጦር ወታደሮች ላይ አዘነቡት፡፡
ሆኖም የወገን ጦር፤ ዝቅ ብለው በሚበሩት የጠላት አይሮላኖች ላይ በመተኮስ፤ አንድ አይሮፕላን መተው ሲጥሉ፤ ሁሉም የቀሩት አይሮፕላኖች ተመተው ሳይወድቁ ወደ ሰፈራቸው ተመልሰዋል፡፡
በጦርነቱ መሐል፤ የከዳተኛው የወሎል ጂሌ ወታደሮች ውስጥ፤ 300 የሶማሌ ወታደሮች እርሱን ከድተው ከኢትዮጵያውያን ወታደሮች ጋር ሲቀላቀሉ፤ በተጨማሪም፤ በነቀኛዝማች ሰለባና በነቀኛዝማች አሰፋ ባሕታ መሪነት ጣሊያንን ከድተው ከወገን ጦር ጋር የተቀላቀሉ የኤርትራ ተወላጆችና ስመ ጥሩ ጀግኖች፤ ከጠላት ጋር ብርቱ ውጊያ ካካሄዱ በኋላ ደጃዝማች በየነ መርድ እና ቀኛዝማች ሰለባ በጦርነቱ ላይ ተገደሉ፡፡
በዚህ ጦርነት ውስጥ፤ ከጠላት ጋር ሆነን አገራችንን አንወጋም ብለው ጠላትን ከድተው ከወገን ጦር ጋር ተደባልቀው የተዋጉና በስም የተገለፁ ኤርትራውያን ቁጥራቸው ቢያንስ 23 ይደርሳል፡፡
ከእነርሱም መካከል፤ የፊታውራሪነት፣ የግራዝማችነት፣ የባላምባራስነት፣ ማዕረግና በተጨማሪም የሚሊተሪ ማዕረግ ያላቸው ከመቶ አለቃ እስከ ሌፍትናንት ኮሎኔል ማዕረግ የደረሱ ይገኙበታል፡፡
በዚህ ጦርነት፤ በመርዛማ የቦምብ ጋዝ የተነሣ፤ ከወገን በኩል እጅግ በርካታ ሰው ከሞተ በኋላ፤ የተረፈው ጦር ወደ ኋላው ሊያፈገፍግ ችሏል፡፡



  1. በዐድዋ ጦርነት ወቅት ጣሊያኖች የነበራቸው የጦር መሣሪያ፤ በአይነትም ሆነ በብዛት፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት ከታጠቀው መሣሪያ ጋር ሲወዳደር ያን ያህል የጐላ ልዩነት አልነበረውም ማለት ይቻላል፡፡
    የጠላት ጦር ከ40 ዓመት በኋላ ሲመጣ ግን፤ ታጥቆ የነበረው መሣሪያ፤ ግዙፍና ዘመናዊ ቴክኖሎጅ ያፈራውን መሣሪያ አንድ ሳያስቀር በሙሉ እስከአፍንጫው ታጥቆ የመጣ በመሆኑ፤ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከታጠቁት ጋር በፍፁም ሊወዳደር የሚችል አልነበረም፡፡
    ኢትዮጵያ ለብዙ ዓመታት ከውጭ የጦር መሣረያ እንዳታስገባ በተጣለባት ማዕቀብ የተነሳ፤ ጠላቷን ልትከላከል ቀርቶ ጫፉም አትደረስም ነበር፡፡
    የኢትዮጵያ ሠራዊት የታጠቀው አሮጌ መሣረያ ብዛት፤ ከ50 ሺህ የማይበልጥ ሲሆን፤ የነበረው ጠቅላላ የጥይት ብዛት ደግሞ ጣሊያኖች ሁለት ውጊያ ቢዋጉ የሚጨርሱትን ያህል ብቻ እንደነበር ይነገራል፡፡
  2. በስንቅና ትጥቅ ረገድም በዘመናዊ መንገድ የተደራጀ አልነበረም፡፡
  3. ቁስለኛውም ሕክምና ማግኘት የሚችለው፤ ከወጭ ሀገር በመጡ በፈቃደኝነት ከሚያክሙ ጥቂት የሕክምና ሰዎች ብቻ ስለነበረ ከቁስለኛው ብዛት አንጻር ፈጽሞ ሊዳረስ ስለማይችል ሕክምና ሳያገኝ የሚሞተው ሰው ቁጥር በርካታ ነበር፡፡
  4. የሬድዩ ግንኙነትንም በተመለከተ በደንብ በባለሙያ ያልተደራጀ ከመሆኑም በላይ የመልዕክቱን ሚስጥር ከጠላት ለመጠበቅ ባለመቻሉ ችግር የነበረበትና ከጠላት ጋር ፈጽሞ የሚወዳደር አልነበረም፡፡
  5. በጦር ሠራዊትም ቁጥር ቢሆን የጠላት ጦር ብዛት ያመዝን ነበር፡፡
    በተለይ በደቡብ ጦር ግንባር የነበረው የኢጣሊያ ጦር ብቻውን ሳይሆን፤ ከኢጣሊያ ቅኝ ግዛት አገሮች የመጡ በርካታ የሊቢያ፣ የኤርትራና የሶማሊያ ወታደሮች ነበሩ፡፡
  6. የጀኔቫ ስምምነትን በጣሰ መልኩ በጦር ሜዳ መጠቀም የተከለከለውን የሙስታርድ ጋዝ ቦምብ፤ ቁጥራቸው ከ600 በማያንሱ አይሮፕላኖች ጭኖ፤ በሰሜንና በደቡብ ጦር ግንባር በተሠለፈው የኢትዮጵያ ሠራዊትና እንዲሁም በቁም ከብቶችና እንስሳት ላይ ሳይቀር ያለገደብ በማርከፍከፍና ከፍተኛ እልቂት በማድረሱ፤ በዓለም የጦርነት ታሪክ ይቅር የማይባል ታላቅ ወንጀል የተፈፀመበት ወቅት ነበር፡፡




Ethiopian Patriots
ጀግኖች አርበኞች ከያሉበት ተሰባስበው
ጠላትን ለመዋጋት ሲንቀሳቀሱ
በአጠቃላይ፤ የጠላት ጦር የውጊያ ችሎታ ሲገመገም፤ ከጀግኖች ኢትዮጵያውያን በልጦ ሳይሆን፤ ብቸኛው ጉልበቱና አቅሙ፤ በቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ያለማቋረጥ በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ የሚያዘንበው የሙስታርድ ጋስ ቦምብ ያደረሰው ጭፍጨፋ መሆኑ ግልፅ ነበር፡፡
በዚህም ምክንያት፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰበት፤ ልክ እንደዐድዋው ሁሉ፤ ውጊያውን በለመደው የጀግንነት መንገድ ተዋግቶ ማሸነፍ ባለመቻሉ፤ ኢጣሊያን አሸናፊ፤ የኢትዮጵያን ጦር ተሸናፊ ያደረገው ይህ ጦርነት፤ በዓለም ደረጃ ሲገመገም ኢፍትሓዊ ጦርነት እንደነበረ አስረግጦ መናገር ይቻላል፡፡
በሁሉም የጦርነት አውደ ግንባሮች ሁሉ እጅግ የሚገርመው፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት መሸነፉ ሳይሆን፤ ያን ሁሉ በላዩ ላይ ያለማቋረጥ የሚወረድበትን የእሳት ነበልባል ተቋቁሞ ለሕይዎቱ ሳይሳሳ መዋጋቱ ነው፡፡
ይህም የኢትዮጵያውያን ድፍረት የተሞላበት ጀግንነት፤ በዓለም የጦርነት ታሪክ፤ ልዩ ሥፍራ የሚይዝ ክስተት ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡
ይህ ሁሉ እየሆነ ግን፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሳይዋጋ በወር ወይም በቀናት ውስጥ አልተፈታም፡፡
በመሬትና በአየር የሚደበድበውን ጠላቱን፤ በመሬት ላይ ግንባር ለግንባር በጅግነነት እተፋለመና እየተዋደቀ፤ የጠላትን ጦር ለ7 ወራት ገትሮ ማቆየት የቻለ ወደር የማይገኝለት ጀግና አገር ወዳድ ሠራዊት ነበር፡፡

የጠላት ጦር በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ ያደርስ በነበረው የአየር ጥቃት የተነሳ፤ ከዐድዋ ጦርነት ጀምሮ ተደፍሮ የማያውቀውና ድል ከመሆን ይልቅ መሞትን የሚመርጠው የኢትዮጵያ ሠራዊት፤ ሳይወድ በግድ ባልተለመደ መልኩ ወደኋላው ማፈግፈግ ግድ ሆኖበታል፡፡
አንድ የወገን ወታደር ይህን እንግዳ ነገር በተመለከተ ሲሸልል፤
በማይጨውም በኩል፣ በመቀሌም በኩል መች ይገባ ነበር
በሰማይ ላይ ገባ በማናውቀው ነገር፤

በማለት ግራ መጋባቱን ገልጾታል፡፡

ደሴ ገብቶ አዲስ አበባን ለመያዝ ይጠባበቅ የነበረውም የጠላት ጦር ከደሴ ተነስቶ በየኬላውና በየመንገዱ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ሠራዊትን በቦምብና በሙስታርድ ጋዝ እያጠፋ በጣርማ በርና በደብረብርሃን በኩል ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም. አዲስ አበባ መግባት ችሏል፡፡
የጣሊያን ጦር ሠራዊት መሪ ማርሻል ባዶሊዮ አዲስ አበባ በገባ በአራተኛው ቀን፤ ሙሶሎኒ በኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት የተጠናቀቀና ሰላም መመስረቱን በማብሰር፤ በመጨረሻ ኢጣሊያ ሰፊ የቄሳር ግዛት ማግኘቷን ለኢጣሊያ ሕዝብና ለመላው ዓለም ካስረዳ በኋላ፤
ቪክተር ኢማኑኤል የኢጣሊያ ምስራቅ አፍሪካ፤ (ኤርትራ፣ ኢትዮጵያና የኢጣሊያ ሶማሊያ) ጭምር ያጠቃለለ የኢጣሊያ ንጉሥ እንዲሆን፤
ግራዚያኒ የኢጣሊያ ንጉሥ እንደራሴ በመሆን የኢጣሊያ ምስራቅ አፍሪካን እንዲያስተዳደር ከተሾመ በኋላ ባዶሊዮ ወደ አገሩ ተመለሰ፡፡
ከዚህ በኋላ የኢጣሊያ መንግሥት፤
  • 1ኛ፤ የኢትዮጵያ መሬትና ሕዝቦች በሙሉ በኢጣሊያ መንግሥት ሥር ተገዥዎች ናቸው፤
  • 2ኛ፤ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ስም ለኢጣሊያ ንጉሥና ለተከታዮቹ ዞሯል፤
የሚል በሕግና በአዋጅ አስነገረ፡፡
የጠላት ጦር የቀረውን የኢትዮጵያ ክፍል ለመያዝ ሠራዊት በሚልክበት ወቅት፤ ጠላት አዲስ አበባ ከመግባቱ በፊት፤ በአርበኝነት ተሠማርተው ለመዋጋት የተዘጋጁት የኢትዮጵያ መኳንንቶችና ወጣቶች፤ ከከተማ ያገኙትን የጦር መሣሪያ እየያዙ፤ በቆላና በደጋው፤ በጫካና በተራራው የአገራቸውን ነፃነት ለማስከበር ከያሉበት ቦታ ሁሉ መሰባሰብ ጀመሩ፡፡
በሌላ በኩል፤ ለፋሽስት ኢጣሊያ ተገዝተን እንኖራለን ብለው ወደ ጠላት ጉያ ለገቡት መኳንንቶችና የተማሩ ወጣቶችም ቢሆን ምንም እርኅራሄ ሳያሳይ ቀስ በቀስ እያሰረ የአረመኔ ሥራውን ፈጸመባቸው፡፡
በየዋህነት በፊቱ የተገኙትንም ሰዎች ቢሆን እንደ እንሰሳ እየቆጠረ ይንቃቸው ነበር፡፡
በየቀኑ በሚያደርገውም ንግግር፤
“ዛሬ ኢትዮጵያና እናንተ እመዳፌ ውስጥ ገብታችኋል፡፡
ከመዳፌ ውስጥ ፈልቅቆ አውጥቶ የሚያድናችሁ የለም፡፡”

እያለ የእብሪትና የትምክህት ንግግር ይናገራቸው ነበር፡፡

በዱር በገደሉ የመሸጉት የኢትዮጵያ አርበኞች፤ ከኢትዮጵያ የውስጥ አርበኞች ጋር በመቀናጀት፣ ርሃብና እርዛት ሳይበግራቸው፣ በየበረሀው እና በየሸለቆው ተንከራተው ለአምስት ተከታታይ ዓመታት በቁርጠኝነት ለኢትዮጵያ አርነት ከወራሪው ፋሽስት ኢጣሊያ ጋር ያደረጉት ትንቅንቅ፣ ተጋድሎ እና የከፈሉት መስዋዕትነት ሲታይ፤ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ፤ ለመጭው ትውልድ ሁሉ ታላቅ አርዓያ የሚሆን እጅግ አኩሪ ገድል ሆኖ ሲዘከር የሚኖር ታላቅ ተግባር ሆኖ አልፏል፡፡


Maichew_War_Front


Emperor Haile Selassie addressing the League of Nations
ንጉሠ ነገሥቱ ለጉባኤው ንግግር ሲያደርጉ
ንጉሠ ነገሥቱ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ መወሰድ ስለሚገባው እርምጃ ለመምከር ሚያዝያ 23 ቀን 1928 ዓ.ም. ልዑላን መሳፍንቶች፣ መኳንንቶች፣ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና ታላላቅ የአርበኞች የጦር መሪዎች፣ ተሰብስበው ንጉሠ ነገሥቱ በተገኙበት በታላቁ ቤተ መንግሥት ከፍተኛ ጉባዔ ተደረገ፡፡
ጉባዔው ባደረገውም ሰፊ ክርክር፤ አንደኛው የጉባኤው ሀሳብ፤ “ቤተ መንግሥቱ ወደ ጐሬ ተዛውሮ በዚያ በኩል ጠላትን መከላከል” የሚል ሲሆን ሁለተኛው ሀሳብ ደግሞ “ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ዓለም መንግሥታት ማሕበር ሄደው እንዲያመለክቱ ሆኖ፤ እንስከዚያው ድረስ ግን ጦሩ በየሥፍራው በአርበኝነት ተሠማርቶ አገሩን እየተከላከለ እንዲጠብቅ” በሚሉ በሁለት የተለያዩ ሀሳቦች በመከፈሉ ምክንያት ጉባዔው ለሚቀጥለው ቀን ተላለፈ፡፡
በሚቀጥለው ቀን በተደረገው ጉባዔ፤ ከሁለቱ የተለያዩ ሀሳቦች መካከል ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ዓለም መንግሥታት ማሕበር ሄደው እንዲያመለክቱ ሆኖ፤ እንስከዚያው ድረስ ግን ጦሩ በየሥፍራው በአርበኝነት ተሠማርቶ አገሩን እየተከላከለ እንዲጠብቅ” የሚለው ሀሳብ በአብላጫ ድምፅ ተቀባይነት በማግኘቱ ንጉሠ ነገሥቱ ሚያዝያ 24 ቀን 1928 ዓ.ም. ወደ አውሮፓ ለመሄድ በባቡር ወደ ጅቡቲ ተጓዙ፡፡
ንጉሠ ነገሥቱም አውሮፓ እንደደረሱ፤ በስዊዘርላንድ ጀኔቫ በሚገኘው የዓለም መንግሥታት ማሕበር (League of Nations) አዳራሽ ተገኝተው፤ የዓለም መንግሥታት መሪዎች፣ ተወካዮችና ጋዜጠኞች በተሰበሰቡበት ንግግር ለማድረግ ተገኙ፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ፤ የኢትዮጵያን ጉዳይ ከሥር መሠረቱ ጀምሮ በዝርዝር ለጉባኤው ለማስረዳት ቆመው መጠባበቅ ጀመሩ፡፡
ከስብሰባው ተሳታፊዎች መካከል በተለይ የኢጣሊያ ጋዜጠኞች ንጉሠ ነገሥቱን በመቃወም በአዳራሹ ውስጥ የፈጠሩትን ረብሻ፣ ጩኸትና ስላቅ በታላቅ ትግሥትና ብልሃት በመቋቋም እጅግ የሚደንቅ ግርማ ሞገስን በመላበስ በአዳራሹ ውስጥ ፀጥታ እስኪሰፍን ድረስ ምንም ቃል ሳይተነፍሱ በትዕግሥት ቆመው ጠብቀዋል፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ የፈረንሳይኛ ቋንቋ አቀላጥፈው መናገር የሚችሉ ቢሆንም ቅሉ፤ እርሳቸው ግን ሁኔታው ሲረጋጋ ጠብቀው በአገራቸው በአማርኛ ቋንቋ ንግግር አደርገዋል፡፡

ንጉሠ ነገሥቱ ለጉባኤው ካቀሩቡት ኦፊሴላዊ ንግግር መካከል ከብዙ በጥቂቱ

“...ፈተናችን ከጀመረበት ቀን ጀምሮ፤ እርዳታቸውን በመስጠት ጥንካሬያቸውን ላረጋገጡ ማለትም፤ ለመስኮብ (ሞስኮ)፣ ለቻይና፣ ለሜክሲኮና ለኒውዚላንድ መንግሥታት ለታመነ ወዳጅነታቸው በሕዝቤ ስም ጥልቅ የሆነ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
...ይህ ጥያቄዬ ምላሽ ባያገኝ ለማናቸውም ቢሆን ሕግና እውነተኛ ፍርድ እስኪያሸንፍ ድረስ በኢትዮጵያ ጦርነት የማያቋርጥ መሆኑን እገልፃለሁ፡፡
...የኢጣሊያ አይሮፕላኖች በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ያለማቋረጥ፤ በ9፣ በ15 እና በ18 ቡድን እየሆኑ በወንዞችና በሐይቆች ላይ በማከታተል የሚረጩት የመርዝ ጋዝ ሠራዊታችንን፣ ሰላማዊውን ሕዝብ፣ ሴቶችን፣ ሕፃናትን፣ እንስሳትን ሁሉ ለሞት ዳርጓል፡፡
...ይህም በአይሮፕላናቸው የሚያካሂዱት ህገወጥ ጭፍጨፋ፤ በኢትዮጵያ ምድር ላይ የሚገኙትን ፍጥረታትን፤ ወንዞችን፣ ሐይቆችንና ሳር ቅጠሉን ሳይቀር ለማጥፋት ሆን ብለው ያቀዱት በመሆኑ ለእነርሱ ዋና የጦርነታቸው ማሸነፊያ መሣሪያቸው አድርገውታል፡፡
...ከ12 ሚሊዮን ያልበለጠ ሕዝብ ያላት፤ ሐብትና ምንም አይነት የጦር መሣሪያ የሌላት አገር፤ 42 ሚሊዮን ሕዝብ ካላትና እጅግ መጠነ ሰፊ የሆነ የጦር እይሮፕላኖች ካሰለፈች ጣሊያን ጋር እንዴት አድርገን መቋቋም ይቻለናል?
...ኃይል ህግን ያሸንፋል? ወይስ ሕግ ኃይልን ያሸንፋል?
...ባንድ ውል ግርጌ የተፈረመ ፊርማ የሚረጋው፤ ፈራሚዎቹ መንግሥታት የሚጠቅማቸው በሆነ ጊዜ ብቻ ነውን?
...እግዚአብሔርና ታሪክ ፍርዳችሁን ሲያስታውሱት ይኖራሉ፡፡”
በማለት ንግግራቸውን ለጉባዔው አሰምተዋል፡፡

ንጉሠ ነገሥቱ በንግግራቸው ያስተላለፉት መልዕክት፤ የስብሰባው ታዳሚዎችን ያስደመመ ጠንካራ መልዕክቶች የነበሩበት ሲሆን፤ በአበዛኛዎቹ የስብሰባው ተካፋዮች ዘንድ፤ በ 20ኛው ክፍለ ዘመን ከተደረጉት እጅግ ስሜትን ቀስቃሽ ከሆኑ ንግግሮች ውስጥ እንደ አንደኛው የሚቆጠር ነው በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የንጉሠ ነገሥቱ ንግግር በመላው ዓለም ለሚገኙ ለፀረ ፋሽስት እንቅስቃሴዎች እንደ አንቂ ደወል ሆኖ ተወሰደ፡፡
በዚህም የተነሳ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላማዊ ሕዝቦች ሁሉ ፋሽስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ የፈፀመችወን የግፍ ወረራ አወገዙ፡፡
በጊዜው የሐርለም ነዋሪዎች ዋና የዜና አውታር የነበረው የታይም መጽሔትም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን “ያመቱ ሰው” በማለት ሰይሟቸዋል፡፡
የዓለም መንግሥታት ማሕበር (League of Nations) በኢጣሊያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ቢሞክርም ውጤት የሚያመጣ እገዳ ለማድረግ አልሞከረም፡፡
ከማኅበሩ አባል አገራት መካከልም ስድስት አገሮች ብቻ የኢጣሊያንን ወረራ ሳይደግፉት ቀርተዋል፡፡ እነዚህም አገሮች፤
ቻይና፣ ኒውዚላንድ፣ የሶቪየት ህብረት፣ የሰፔይን ሬፐብሊክ፣ ሜክሲኮና ዩናይትስ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ይገኙበታል፡፡
የዓለም መንግሥታት ማህበሩም ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ የፈፀመውን ወረራ ባለማውገዙ ምክንያት የወደቀ ውጤት አልባ ድርጅት መሆኑ ተረጋገጠ፡፡



Melaku Beyan
የፓን አፍሪካን አቀንቃኝና አርበኛ
የሕክምና ዶክተሩ መላኩ በያን

Photo credit to: ethiopianworldfederation
የፓን አፍሪካን አቀንቃኝ፤ ጀግናው አርበኛና የሕክምና ዶክተሩ መላኩ በያን የተወለደው በ 1892 ዓ.ም. በወሎ ጠቅላይ ግዛት ሲሆን በ 1922 ዓ.ም. ወደ አሜሪካ ለትምህርት ከተላኩት ተማሪዎች ውስጥ አንዱ ነበር፡፡
ትምህርቱንም ተከታትሎ በመጨረሻም ዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘውና ዝነኛ ከሆነው አፍሪካ አሜሪካውያን ከሚማሩበት ከሀዋርድ የህክምና ትምህርት ቤት የህክምና ዲግሪውን አገኘ፡፡
ዶክተር መላኩ በያን፤ ከአፍሪካ አሜሪካውያን ጋር ወዳጅነት መሥርቶ ስለነበር፤ ፈቃደኛ የሆኑ አፍሪካ አሜሪካውያን ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ ተልከው እንዲሠሩ ምዝገባ እንዲያካሂድ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጥያቄ አቅርበውለት ነበር፡፡
ዶክተር መላኩ በታዘዘው መሠረት በርካታ ፈቃደኛ የሆኑ እውቅና ያላቸው መምህራንና ዶክተሮች ሳይቀሩ ተመዝግበው ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙ ነበሩ፡፡
በተለይ ዓለማቀፋዊ ሕጋግትን ጥሳ ኢትዮጵያ ላይ የግፍ ወረራ የፈፀመችው ኢጣሊያ ላይ፤ የዓለም ሕብረተሰብ ተቃውሞ አሰምቷል፡፡
Melak Beyan Protest in Harlem in support of Ethiopia
ዶክተር መላኩ በያንና ባለቤቱ ፊት ለፊት ሆነው የሐርለምን
የጥቁር አሜሪካውያን ፀረ ፋሽስት ሠላማዊ ሠልፉን ሲመሩ

Photo credit to: ethiopianworldfederation
Harlem African American Registering to Fight for Ethiopian Freedom
የሐርለም አፍሪካ አሜሪካውያን ለኢትዮጵያ ነፃነት ለመዋጋት
በሰኔ ወር 1927 ዓ.ም. በፈቃደኝነት ሲመዘገቡ

Photo credit to: ethiopianworldfederation
አፍሪካ አሜሪካውያን፤ ጥንተ ታሪክ ያላትን ዘመናዊ ኢትዮጵያን ከዐድዋ ድል በኋላ ለጥቁር ሕዝቦች የኃያልነትና የኩራት ተምሳሌት አድርገው ይመለከቷት ስለነበረ፤ በወራሪው ፋሽስት ኢጣሊያ ላይ የመረረ ተቃውሞና ውግዘት ያሰሙ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች ሀገር መሆኗን በመገንዘብ፤ በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰው ሕገወጥ ወረራና ጥፋት ሁሉ ነጮች በጥቁሮች ላይ የበላይነት እንደተጎናፀፉ ይቆጠራል ብለው ስለሚያምኑ በርካታ የአፍሪካ አሜሪካውያን ድርጅቶች በመነሳሳት በጥቁሮች ከተማ በሐርለም በፍጥነት ተሰባሰቡ፡፡
በዚህም መሠረት የአፍሪካ አሜሪካውያን ድርጅቶች፤ ሦስት አባላት ያሉት የኢትዮጵያ የእርዳታ ድርጅት በማቋቋም፤ አስፈላጊውን እርዳታ ሁሉ ለኢትዮጵያ ለማድረግና የፀረ ፋሽስት እንቅስቃሴውን በአሜሪካ ለማስተጋባት፤ እንግሊዝ አገር በስደት ወደሚገኙት የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘንድ ሄደው ዓላማቸውን በማስረዳት የኢትዮጵያ መንግሥትን አውቅና አግኝተዋል፡፡

ዶክተር መላኩ በያን ያቋቋመው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን፤ በሚያራምደው ዓላማ ምክንያት ብሔራዊ ፌዴሬሽን ለመሆን በመብቃቱ፤ በ 1932 ዓ.ም. በአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ 22 ቅርንጫፎች ሲኖሩት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ በላቲን አሜሪካና በዌስት ኢንድስ በሽዎች የሚቆጠሩ አባለት ነበሩት፡፡
የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የግል ዶክተር የሆነው መላኩ በያን፤ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን በሚል ስያሜ ፌዴሬሽን አቋቋመ፡፡
የፌዴሬሽኑ ዓላማም፤
“እኛ የዓለም የጥቁር ሕዝቦች፤ አነድነትን፣ ሕብረትን፣ አርነትን፣ ነፃነትን፣ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን፣ ፍትሕን ለመጎናጸፍና በፈጣሪ የተቸረንን የኢትዮጵያን አንድነት ለመጠበቅ ይቻል ዘንድ ይህን ሕግ አቋቁመናል፡፡”
የሚል ነበር፡፡

ሐርለም የሚኖረው ተዋቂው የሕግ ጠበቃ ልዊስ በሰጠው አስተያየት፤
“ለእኔ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘው የጥቁር ሰው ሕይዎት ተከብሮ የመኖር ዋስትና መረጋገጥ፤ በዓለም ለሚገኙት የጥቁር ሕዝቦች እና ሐርለም ለሚኖሩ ጥቁሮች የወደፊት እጣ ፋንታ ወሳኝነት አለው፡፡”

በማለት ገልጾታል፡፡

Melaku Beyan
የንጉሠ ነገሥቱ ፎቶግራፍ
በሐርለም ታይም መጽሔት ላይ ወቷል

Photo credit to: time.com
የራስ ተፈሪ መኮንን ንጉሠ ነገሥት ሆነው ዘውድ ሲጭኑ፤ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለመገኘት ከሐርለም ከተማ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ያከበሩ ነዋሪወች ነበሩ፡፡
የራስ ተፈሪ የዘውድ ሥነ ሥርዓት አከባበርን በተመለከተ፤ የሐርለም ነዋሪዎች ዋና የዜና አውታር የነበረው ታይም መጽሔት፤ የንጉሠ ነገሥቱን ፎቶግራፍ ይዞ ሲወጣ፤ “ንጉሠ ነገሥቱ የኛም ንጉሥ ነው፡፡” እስከማለት ደርሰዋል፡፡
አፍሪካ አሜሪካዊው ጆን ሮቢንሰን ፋሽስት ኢጣሊያ በነፃዋ ምድር በኢትዮጵያ ላይ የፈፀመውን ወረራ በመቃወም ኢትዮጵያን ለማገዝ ይፈልግ ነበር፡፡
ይህን የሰማው ዶክተር በያን ከሮቢንሰን ጋር ከተገናኘ በኋላ፤ ለንጉሠ ነገሥቱ በመንገር ሮቢንሰን ወደ አዲስ አበባ እንዲጓዝ አደረገ፡፡
John Charles Robinson in Ethiopian Air Force Uniform
የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ
የነበረው ቻርለስ ሮቢንሰን
ቻርለስ ሮቢንሰን አዲስ አበባ ከደረሰ በኋላ በከተማው አቅራቢያ በሚገኘው ሥፍራ የአይሮፕላን አብራሪነት የሥልጠና ትምህርት ቤት ከፈተ፡፡
በኋላም ሮቢንሰን የኢትዮጵያ የአየር ኃይል አዛዥ ሆነ፡፡
ሮቢንሰን የሚያሠለጥንባቸው አይሮፕላኖች ተዋጊ ጀቶች ሳይሆኑ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ስለነበሩ ጦርነቱ ሲጀመር ወታደሮችን ከአዲስ አበባ አድዋ ድረስ አመላልሷል፡፡
ሮቢንሰን 19 አውሮፕላኖችንና 50 ፓይለቶችን ያስተዳደር ነበር፡፡
በመጨረሻም ሮቢንሰን ከአንድ አመት አገልግሎት በኋላ ወደ አሜሪካ ተመልሷል፡፡
የሐርለም ጥቁሮች ተሰባስበው የምኒልክ ክበብ የሚል ስያሜ ሰጥተው ለኢትዮጵያ ዕርዳታ ለማድረግ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡
Melaku-Beyan with his wife in Ethiopian costume
ዶክተር መላኩ በያንና
ባለቤቱ ዶርዚ፤ አዲስ አበባ
በነበሩበት ጊዜ የኢትዮጵያ
ባሕላዊ ልብስ ለብሰው

Photo credit to: yale.edu
ዶክተር መላኩ በያን ለኢትዮጵያ ነፃነት ቀናኢ ስለሆነ በየአቅጣጫው እየተንቀሳቀሰ የኢትዮጵያ ድምፅ ለመሆን ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም፡፡
ዶክተር መላኩ፤ በሐርለም ከተማ ቁጥራቸው 20 ሺህ የሚደርሱትን አፍሪካ አሜሪካውያን ነዋሪዎችን፤ የኢጣሊያ ፋሽስት ወታደሮች በነፃይቱ አገር ኢትዮጵያ ላይ የሚፈጽሙትን የግፍ ወረራ በመቃወም ለጥቁር የኢትዮጵያ ሕዝቦች ነፃነት እንዲቆረቆሩ በመቀስቀስ፤ ሠላማዊ ሠልፍ እንዲደረግ አስተባብሯል፡፡
ዶክተር መላኩ፤ ከባለቤቱ ከዶርዚ ጋር በመሆን በሚደረገው ሠላማዊ ሠልፍ ላይ ግንባር ቀደም በመሆን “በፋሽስት ወታደሮች አዲስ አበባ ላይ የሚፈጽሙትን ግድያ እንቃወማለን!” የሚሉና “ኢትዮጵያን አድኑ” የሚል በራሪ ወረቀቶችን በማዘጋጀት ከፍተኛ የአገር ወዳድነት ተግባር ፈጽሟል፡፡
ይህ በዶክተር መላኩ በያን ጥረት የተነሳሳው የአፍሪካ አሜሪካውያን ፀረ ፈሽስት እንቅስቀሴ ተስፋፍቶ በአብዛኛው የአሜሪካ ሰቴት የሚገኙ አፍሪካ አሜሪካውያን፤ የተለያ የኑሮ ደረጃ፣ ጾታ፣ እምነት ያላቸው ምሁራንም ጭምር ሳይቀሩ የኢትዮጵያውያንን ፀረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴን በመደገፍ፤ ይህን በኢትዮጵያ ላይ የተፈፀመውን የግፍ ወረራ በግልጽ አደባባይ ወጥተው ተቃውመዋል፡፡
malaku bayen resting place at New York
ኒውዮርክ የሚገኘው የዶክተር
መላኩ በያን የመቃብር ሐውልት

Photo link
ዶክተር መላኩ በያን ከባሌቱ ከዶርዚ ሃድሊ ጋር ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ በጦርነቱ ወቅት ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር በመሆን የተለያዩ አኩሪ የአርበኝነት ተግባራትን አከናውኗል፡፡
ዶክተር መላኩ በያን፤ ወደ አሜሪካ ከተመለሰ በኋላ፤ ኢትዮጵያ ነፃነቷን ለመቀዳጀት አንድ ዓመት ሲቀራት ሚያዝያ 26 ቀን 1932 ዓ.ም. በተወለደ በ40 ዓመቱ ሕይወቱ አልፎ በኒውዮርክ ከተማ ቀብሩ ተፈጽሟል፡፡
ሐኪሞቹ እንዳስረዱት፤ የሞተበት ምክንያት በተፈጠረበት ከፍተኛ የሥራ ጫናና ድካም እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ዓርብ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ምንም አይነት መሣሪያ ባልያዘው በአዲስ አበባ ሠላመዊ ሕዝብ ላይ የፋሽስት ኢጣሊያ ወታደሮች ታይቶ የማይታወቅ አረመኔያዊ ጭፍጭፋ በማካሄድ፤ የሠላማዊው ሕዝብ ደም እነደ ጐርፍ የፈሰሰበት የሰቆቃ ቀን ነበር፡፡
Grazian with abuna Kirillos
ማርሻል ግራዚያኒ ከአቡነ ቄርሎስ
አራተኛ ጋር ስድስት ኪሎ በሚገኘው
በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት
ለተሰበሰበው ሕዝብ
ንግግር ለማድረግ እንደተዘጋጀ

Photo link
ግራዚያኒ፤ የንጉሣቸውን የልደት ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ ለድሆች ምጽዋት እሰጣለሁ በማለት በያኔው ገነተ ልዑል የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቤተ መንግሥት ይባል የነበረው እና በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሕዝቡ በጥኋት እንዲሰበሰብ ጥሪ አድርጐ ነበር፡፡
በስብሰባው መሀልም አብርሀም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የኤርትራ ወጣቶች ተገኝተው ነበር፡፡
ሁለቱ የኤርትራ ወጣቶች ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት፤ በኢጣሊያ ቅኝ ግዛት ሥር በነበረችው ኤሪትራ የመማር ዕድላቸው ጠባብ ስለነበረ፤ ኢትዮጵያ መጥተው በምኒልክ ትምህርት ቤት ተመዝግበው ለመማር የመጡ ወጣቶች ነበሩ፡፡
አብርሀ ደቦጭ፤ ኤርትራዊ በመሆኑ፣ የኢጣሊያንኛ ቋንቋ መናገር በመቻሉና፤ ከተማዋን በደንብ ማወቁ፤ አዲስ አበባ በሚገኘው በፋሽስቱ የኢጣሊያ የፖለቲካ ቢሮ ውስጥ ተቀጥሮና ራሱን ከአዲሱ የኢጣሊያ አስተዳደር ጋር አስማምቶ በመሥራት ላይ ነበር፡፡
ሟቹ የታሪክ ምሁር የነበሩት ሪቻርድ ፓንክረስት “አብርሃ ፋሺስቶችን እና ዘረኝነታቸውን ይጠላ ነበር፡፡” በማለት ጽፈዋል።
ሞገስ አሰገዶም በ1904 ዓ.ም. ኤርትራ ውስጥ ደቀመሃሪ አቅራቢያ በምትገኝ አልፋልባ በተባለች ቀበሌ ተወለደ።
ሞገስ አስተዋይ እና ታታሪ ተማሪ ነበር። በፀባዩም ደግ እና ለሰው አሳቢ ተደርጎ ይቆጠር ነበር።
ሞገስ በወጣትነቱ ከቅኝ ገዥዎች የኢጣሊያ ባለስልጣናት ፈቃድ ሳያገኝ ነው ኤርትራን ለቆ ወደ ኢትዮጵያ የሄደው።
በህገ ወጥ መንገድ ኤርትራን ለቆ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ በነበረበት ወቅት በጥይት መመታቱ ተነግሯል።
Abraha Deboch and Moges Asgedom
አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም

Photo link
ሞገስ የፈረንሳይኛ ቋንቋ አቀላጥፎ የሚናገርና የሚጽፍ ስለነበረ የፈረንሳይኛ ትምህርትም ያስተምር ነበር፡፡ በተጨማሪም የጣልያንኛ፣ የጀርመንኛ እና የእንግሊዘኛ ቋንቋ እውቀት ነበረው፡፡
አብርሃ ደቦጭ የእውቁ የኢትዮጵያ የጦር መሪ የራስ ደስታ ዳምጠው ዘመድ ከሆነችው ከታደሰች እስጢፋኖስ ጋር በ1928 ዓ.ም. ተጋብቷል፡፡
ሞገስ አስገዶም ግራዚያኒና ፋሽስቶች ላይ አደጋ ለመጣል ስላቀደና ረዳት ስለፈለገ፤ አብርሃምን ጠርቶ፤ “ራስህን ለሀገርህ መስዋዕት ማድረግ አለብህ” በማለት እንደተናገረው ተዝግቧል።
አብርሀም ደቦጭ፤ ፋሽስት ኢጣሊያ በሚያራምደው የዘረኝነት እንቅስቃሴ ላይ ጥላቻ ስለነበረው ወደ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ከመሄዱ በፊት፤ ከቤቱ ሲወጣ የኢጣሊያንን ሰንደቅዓላማ ከተሰቀለበት አውርዶና መሬት ላይ አንጥፎ በሳንጃው ከወጋው በኋላ፤ ሳንጃው ጫፍ ላይ የኢትዮጵያን አርንጓዴ ቢጫ ቀይ ሠንደቅ ዓላማ አስሮ አውለብልቦታል፡፡
አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም፤ በግራዚያኒ እና ፋሽስቶች ላይ አደጋ ለመጣል ያቀዱት አማካሪያቸውና አጋዣቸው ከሆነው ከስምዖን አደፍርስ ጋር ነበር፡፡
ሁለቱም ወጣቶች ወደ ስብሰባው ከሄዱ በኋላ፤ ግራዚያኒ ንግግር ማድረግ ጀመረ፡፡
ሕዝብ ጨፍጫፊ የኢጣሊያ አውሮፕላኖችም በአዲስ አበባ ሰማይ ላይ ይበሩ ጀመር፡፡
በዚህ ወቅት፤ በርካታ ቁጥር ያላቸው በአዲስ አበባ ከተማ የታወቁ ነዋሪዎች አገራቸውን በመክዳት ለኢጣሊያ መንግሥት እውቅና ሰጥተዋል፡፡
ከጧቱ 5 ሰዓት ሲሆን በስብሰባው የተገኙት የኢጣሊያ ባለሥልጣናት ለተሰበሰበው ሕዝብና በስብሰባው ለተገኙት ቀሳውስት እሰጣለሁ ያለውን ምጽዋት ማደል ጀመሩ፡፡
በዚህን ጊዜ አብርሀም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ቀስ እያሉ ግራዚያኒ ንግግር ወደ አደረገበት መድረክ ከተጠጉ በኋላ ደብቀው የያዙትን ቦምብ መወርወር ጀመሩ፡፡
ሁለቱም ወጣቶች በተፈጠረው ግርግር መሐል ከመሸሻቸው በፊት 10 ያህል ቦምቦችን ወርውረዋል፡፡
ሪቻርድ ፓንክረስት እንደገለፁት፤ ሁለቱ ወጣቶች ያመለጡት የውስጥ አርበኛ በመሆን አርበኞችን የሚረዳ ስምዖን አደፍርስ በሚባል የታክሲ ሾፌር አማካኝነት ሲሆን፤ ስምዖን ያደረገው አስተዋጽዖ ይህ ብቻ ሳይሆን፤ ወጣቶቹ የወረወሩትንም ቦምብ ያቀረበላቸው እርሱ ነው፡፡
ስምዖንም በበኩሉ ቦምቦችን ያገኘው የኢትዮጵያ አርበኞች አባል ከሆነ መትረዬስ ተኳሽ ወታደር ጓደኛው ሲሆን፤ ይህም ወታደር አብርሀም ደቦጭና ሞገስ አስገዶምን ቦምቡን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው በማሳየት አሰልጥኗቸዋል፡፡
ቦምቡ ሲወረወር፤ ከኢጣሊያ ባለስልጣኖች ጋር የነበሩትና በኢትዮጵያ የመጨረሻ የሆኑት ከግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን የተሾሙት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ አራተኛ ሲቆስሉ፤ የጳጳሱ ጥላ ያዡ ሞቷል፡፡
በተወረወረው ቦምብ ከቆሰሉት ውስጥ፤ የግራዚያኒ ምክትል የሆነው ጀነራል አርማንዶ ፔትሬቲ ሲሆን፣ የአየር ኃይል አዛዡ ጀነራል ሊዮታ አንድ እግሩን አቷል፡፡
ግራዚያኒም ቢሆን አልቀረለትም፡፡ የተወረወረው ቦምብ አጠገቡ በመፈንዳቱ ሳቢያ 365 የቦምብ ፍንጣሪዎች በሰውነቱ ተሰግስገው ስለነበረ ወደ ኢጣሊያ ሆሰፒታል ተወስዶ አስቸኳይ ቀዶ ጥገና ተደርጐለት ከሞት ሊተረፍ ችሏል፡፡
The then Addis Ababa Municiaplity Building
ሞገስ አስገዶም በካርታ ሥራ ክፍል
ተቀጥሮ የሠራበት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል
ትይዩ የሚገኘው የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ህንፃ

Photo courtesy of:  PROJECT3541
ባለታክሲው ስምዖን አደፍርስ፤ አብርሀም ደቦጭና ሞገስ አስገዶምን ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ወስዶ ለጊዜው እዛው ተደብቀው እነዲቆዩ አድርጐ እርሱም ለአንድ ሳምንት ያህል አብሯቸው ከቆየ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል፡፡
አብርሀም ደቦጭና ሞገስ አስገዶምም በደብረ ሊባኖስ ጥቂት ቀናት ከቆዩ በኋላ የተሻለ መጠለያ ለመፈለግ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የሆነችው ግብፅ ወደ እምታስተዳድረው ሱዳን፤ በጐጃም በኩል አቋርጠው ለመሄድ ወስነው ጐጃም እንደደረሱ፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ሁለቱን ወጣቶች ፀጉረ ልውጥ (ለአገሩ እንግዳ) የሆኑ ሰዎች ናቸው በማለት በጥርጣሬ በማየታቸው ሊገድሏቸው ችለዋል፡፡
ስምዖን አደፍርስም ወደ አዲስ አበባ እንደተመለሰ፤ በፋሽስት ወታደሮች ከተያዘ በኋላ አሰቀይተው ለሞት አብቅተውታል፡፡

Image of the old city of Addis Ababa in the year 1936
የአዲስ አበባ ገጽታ
በ1928ና በ1929 ዓ.ም.

Photo credit to: ebay.com
ዓርብ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. አብርሀም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በወሰዱት እርምጃ የተበሳጩት የኢጣሊያ ባለሥልጣኖች፤ የአፀፋ እርምጃ በመውሰድ የኢጣሊያ ፖሊሶች ወዲያውኑ በተሰበሰበው ሠላማዊ ሕዝብ ላይ ያለምንም ገደብ የጥይት ዝናብ እንዲርከፈከፍባቸው አዘዙ፡፡
ከኢጣሊያ ባለሥልጣኖች ውስጥ አንዱ የሆነው ጊዶ ኮርቴስ፤ አጠገቡ የነበሩትንና በኢጣሊያ ወገን በመሆናቸው ለክብረ በዓሉ በክብር የጠራቸውን ታላላቅ ሰዎች የተባሉትን ኢትዮጵያውያን ሳይቀር የያዘውን ብዙ ጥይቶች ጐራሽ ሪቮልቨር መሣሪያውን አንስቶ የጥይት እሩምታ አርከፍክፎባቸዋል፡፡
ኮርቴስ ይህን እርምጃ ከወሰደ በኋላ ወዲያውኑ “ጥቁር ሸሚዝ” እየተባሉ ለሚጠሩት ለፋሽስት ሚሊሺያ እግረኛ ወታደሮች፤
“…ጓዶች! ዛሬ ለኢጣሊያ መንግሥታችን ወኪል ለሆነው መሪያችን ያለንን ቁርጠኝነት፤ የበቀል እርምጃ በመውሰድ የምናሳይበት ስለሆነ፤ ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት መደዳውን ኢትዮጵያውያንን በማጥፋት ተግባር ላይ እንሠማራለን፡፡
…ከዛሬ ጀምሮ፤ ኢትዮጵያውያንን ለመግደልና ለማጥፋት የሚያስችል ለሦስት ቀናት የሚቆይ ማናቸውንም አይነት ነፃ እርመጃ እንድትወስዱ ፈቅጀላችኋለሁ፡፡”
የሚል የቃል ትእዛዝ አሰተላለፈላቸው፡፡
Addis-Ababa-massacre-by-Fashist-Italians
የፋሽስት ወታደሮች በሰላማዊው
የአዲሰ አበባ ሕዝብ ላይ
የፈፀሙት ዘግናኝ ጭፍጨፋ

Photo credit to: nanopdf
ከዚህ ትእዛዝ በኋላ፤ የኢጣሊያ ወታደሮች፤ በመንገድ የሚተላለፈውን ማንኛውንም ሰላማዊ የአዲስ አበባ ኑዋሪውን ሁሉ፤ “ዱቼ ሙሶሎኒ” “ስልጡኗ ኢጣሊያ” እያሉ እየጮሁ በያዙት የቆመጥ ዱላ፣ በሳንጃ፣ በአካፋ፣ በመዶሻና በያዙት መትረየስ ሳይቀር ጨፈጨፉት፡፡
ብዙዎችንም ኢትዮጵያውያን ከነነፍሳቸው መኪና ላይ በገመድ አስረው እየጐተቱ አሰቃይተው ገደሏቸው፡፡
የቀሩትንም ሰላማዊ ሰዎች በመኪና እያፈሱ ወደ የካ፣ እንጦጦ፣ ፉሪ፣ አቃቂና ገፈርሳ እየወሰዱ በመትረየስ እሩምታ ፈጇቸው፡፡
በአካባቢው ያገኙትን የሠላማዊውን ሕዝብ ቤት ነዳጅ እያርከፈከፉ አቃጠሉት፡፡
በቤቱ ውስጥ የተገኘ፤ ወንድም ሆነ ሴት፤ ልጅ ታቅፋ የምታጠባ እናትም ብትሆን ከቤት እንዳይወጡ ከውጭ እየተቆለፈባቸው ያለምንም ምህረት ነዳጅ እያርከፈከፉ እጅግ ዘግናኝ በሆነ ጭካኔ አቃጠሏቸው፡፡
የግሪክና የአርመን መኖሪያ ቤቶችም ሳይቀሩ እየሰበሩ እየገቡ በቤት ውስጥ ተቀጥረው የሚያገለግሉትን ኢትዮጵያውያንን እያወጡ ገደሏቸው፡፡
የገደሏቸውንም ሰዎች ሬሳ ፎቶ ያነሱ ነበር፡፡
Addis-Ababa-massacre-by-Fashist-Italians
አሰቃቂውና ዘግናኙ ጭፍጨፋ ይህን ይመስላል

Photo credit to: nanopdf
በዚህ ታላቅ ግፍ በተፈፀመበት የሰቆቃ ቀናት ውስጥ፤ ወንድ፣ ሴት፤ ሕፃን፣ ሽማግሌ፣ ሙስሊም ሆነ ክርስቲያን ሳይለይ፤ በሰው ዘር ላይ ወደር የማይገኝለት የዘር ማጥፋት በኢትዮጵያውያን ላይ ተፈፀመ፡፡
የንጹሀን የአዲስ አበባ ሰላማዊ ነዋሪዎች ጭንቅላት እንደ ዶሮ እየተቀነጠሰ በየሥፍራው ወደቀ፡፡
መኖሪያ ቤቶች በመደዳ በእሳት እየተለኮሱ ከነነዋሪዎቻቸው እንዲጋዩ ተደረጉ፡፡ እርጉዝ ሴቶች ያለርህራሄ በሳንጃ እየተወጉ ተገደሉ፡፡
ሌላው ቀርቶ በርካታ ንፁሀንን ራስ መኮንን ድልድይ ጋ በመሰብሰብ ከድልድዩ እየገፈተሩ ወደ ወንዙ እየገቡ አለት ላይ እየተፈጠፈጡ እንዲሞቱ አድርገደዋል፡፡ ሙሶሎኒ ቀደም ብሎ ሚያዝያ 25 ቀን 1928 ዓ.ም. የሰጠውን ትእዛዝ መሠረት በማድረግ፤ አሜሪካና አውሮፓ ድረስ ሄደው
Addis-Ababa-massacre-by-Fashist-Italians
የፋሽስት ወታደሮች በሰላማዊው
የአዲሰ አበባ ሕዝብ ላይ
የፈፀሙት ዘግናኝ ጭፍጨፋ

Photo credit to: nanopdf
የኮሌጅ ትምህርታቸውን አጠናቀው የተመለሱትን ጥቂት ኢትዮጵያውያን ምሁራን ወጣቶች ከሰበሰቧቸው በኋላ ምንም ጥፋት ሳይገኝባቸው ያለምንም ፍርድ በጥይት ተረሽነው ተገድለዋል፡፡
በተለይ የጥቁር አንበሳ ወጣት አባላት፤ ከራስ እምሩ ጋር እጃቸውን ከሰጡ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ ይገኙ ስለነበረ፤ አንድ በአንድ እየተለቀሙ ተረሽነዋል፡፡
ይህ የምሁራን ጭፍጨፋ በዘመኑ የነበረውን አንድ ትውልድ ያጠፋ በመሆኑ፤ በኢትዮጵያ የፖለቲካና ምሁራዊ ታሪክ ላይ የማይሽር ትልቅ ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡
በዚሁ ወጣቶች በተረሸኑበት ቀን፤ ፋሽስቶች፤ በእኩለ ሌሊት የፋሽስት ወታደራዊ ፍርድ ቤት አቋቁመው፤ የሞት ፍርድ ይገባቸዋል ብለው ዓለም በቃኝ በተሰኘው እስር ቤት ታስረው የነበሩትን 62 ኢትዮጵያውያንንም እረሽነዋል፡፡
Abraha Deboch and Moges Asgedom
የየካቲት 12 ሐውልት ከፊል እይታ

Photo courtesy of:  PROJECT3541
ከዚህ የግፍ ጭፍጨፋ በኋላ፤ እግዚአብሔር ሰውሮ ያተረፈውን፤ መኳንንቱንና ተራውን ሕዝብ፤ የተማረውንም ሆነ ያልተማረውን ሁሉ ሰብስበው በየስፍራው አከማችተው ማሰር ጀመሩ፡፡
ከታሰሩትም መካከል የሚፈልጉትን ሰው እያወጡ በየጫካው እየወሰዱ ሲገሉ ሰነበቱ፡፡
በመጨረሻም የታሰረውን ሰው በሙሉ በመኪና ጭነው እያሳፈሩ፤ ከፊሉን ወደ ሶማሊያ መቃዲሹ፤የቀረውንም ኢጣሊያ ወደሚገኘው አሲናራ ወደተሰኘው እስር ቤት አጓጓዙት፡፡
የጦር መሪዎችና አርበኞች የሆኑት፤ ክቡር ራስ ደስታ ዳምጠው፣ ክቡር ደጃዝማች በየነ መርድና ክቡር ራስ ገብረ ማሪያም በላንቃ እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ በጀግንነት ታዋግተው ለውድ አገራቸው ነፃነት መስዋዕት ሆነዋል፡፡
Yekatit-12-Martyrs-Square
ፋሽስት ኢጣሊያ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም.
ለ3 ቀናት ሳይቋረጥ መደዳውን በአዲስ አበባ
ንፁሃን ነዋሪዎች ላይ ላደረሰው ጭፍጨፋ
በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ
የቆመው የመታሰቢያ ሐውልት


Photo credit to: nanopdf
ከየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ጀምሮ በሦስት ቀናት ውስጥ በግፍ የተጨፈጨፉት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 30 ሺህ ይደርሳል፡፡
ይህ የፋሽስት ጭፍጨፋ በወራሪና በተወራሪ ወገን የነበረውን ቅራኔ በማካረር፤ የፀረ ኢጣሊያ ተቃዉሞውን ከመደበኛ ጦርነት ወደ ሁለተኛ ምዕራፍ ወደ ሆነው ወደ ሽምቅ ውጊያ (guerilla fighting) አሸጋግሮታል፡፡
ከላይ የተዘረዘረውን የፋሽስት ኢጣሊያ ያደረሰውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ ለመዘከር፤ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፤ አንቱን አውጉስቲንቺ እና ፍራኖ ክሪሺኒ በተባሉ የክሮሺያ ንድፍ አውጪዎች አማካይነት የሰማዕታት መታሰብያ ሐውልት ተሠርቶ ስድስት ኪሎ አደባባይ በተባለው ቦታ ላይ የ “የካቲት 12 መታሰብያ ሐውልት” በመባል ተሰይሞ በ 1947 ዓ.ም. በስፍራው በይፋ እንዲቆም ተደርጓል፡፡



ምንጭ፤

  1. "የኢትዮጵያ ታሪክ - ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ"  ደራሲ፡- ተክለ ጻድቅ መኩሪያ 1961 ዓ.ም.
  2. "የኢትዮጵያ ታሪክ ከ 1847 እሰከ 1983"  ደራሲ፡- ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ
  3. "የታሪክ ማስታወሻ"  ደራሲ፡- ደጃዝማች ከበደ ተሰማ 1962 ዓ.ም.
  4. "ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ - ፩ኛ መጽሐፍ"  ደራሲ፡- ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት 1928 ዓ.ም.
  5. Courtesy to:   PROJECT3541