Content-Language: am ሜጀር ጀነራል ደጃዝማች በየነ መርድ
header image




ሜጀር ጀነራል ክቡር ደጃዝማች በየነ መርድ




የሜጀር ጀነራል ክቡር ደጃዝማች በየነ
መርድን የአርበኝነት ታሪክ ያዳምጡ











Ras Mulugeta Yigezu
ደጃዝማች በየነ መርድ

image link


ደጃዝማች በየነ መርድ በሰሜን ሸዋ በ1889 ዓ.ም እንደተወለዱ ይገመታል፡፡
ደጃዝማች በየነ መርድ፤ የደጃዝማች መርድ ልጅ ናቸው፡፡
ደጃዝማች በየነ መርድ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ልጅ ልዕልት ሮማነወርቅን አግብተዋል፡፡
ደጃዝማች በየነ አብዛኛውን ጊዜያቸውን የባሌ ጠቅልይ ግዛት ሹም ሆነው አገልግለዋል፡፡
በ1947 ዓ.ም. የጎሙ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት ሹም ሆነው አገልግለዋል፡፡


1. የደጃዝማች በየነ መርድ የአርበኝነት ተጋድሎ

በሜጀር ጀነራል በየነ መርድ የበላይ የጦር አዛዥነት ሥር ተመድበው የነበሩት የጦር አለቆችና የሚያዙት ጦር የሚከተለው ነበር፡፡
  1. የባሌ ጦር፤ በራሳቸው በደጃዝማች በየነ መርድ መሪነት
  2. የክብር ዘበኛ ጦር፤ በኮሎኔል (በኋላ ብርጋዴር ጀነራል) አስፋው ወልደ ጊዮርጊስ መሪነት
  3. የጉማይ ጦር፤ በፊታውራሪ አጥናፍ ሰገድ ወልደ ጊዮርጊስ አዝማችነት
  4. የኤርትራ ተወላጆች ከጠላት ከድተው ከተመለሱ በኋላ ሁለት የሻለቃ ጦር የሚሆን ሥልጠና ወስዶ በስመ ጥሩ ጀግኖች በቀኛዝማች ሰለባና በቀኛዝማች አሰፋ ባሕታ መሪነት
የኢጣሊያ ፋሽስት ጦር በታንክና በናፓል ቦንብ እየታገዘ ሰሰበኒ፣ ገርሎግቢ እና ቆራሄ የተባሉ ቦታዎችን ከያዘ በኋላ ጦርነቱን ወደፊት ለመቀጠል ይዘጋጅ ነበር፡፡
ከመቃዲሾ ወደ አዲሰ አበባ የሚያስመጣው መንገድ በሁለት አቅጣጫ ነው፡፡
አንደኛው መንገድ፤ ከመቃዲሾ በበለደወይን፣ በቆራሔ፣ በደጋሀቡር፣ በጅጅጋ፣ በሐረር አድረጎ አዲስ አበባ የሚያደርሰው ሲሆን፤
ሁለተኛው መንገድ፤ ከመቃዲሾ በባይደዋ፣ በሉክ፣ በዶሎ፣ በነገሌ፣ በይርጋዓለም፣ በሞጆ አድርጎ አዲስ አበባ የሚያደርሰው መንገድ ነው፡፡
የግራዚያኒ ጦር ዋና እቅዱ በቆራሔና በደጋሀቡር በኩል አልፎ ሐረርጌን ለማያዝ ነው፡፡
Rudolf Graziani
ሩዶልፍ ግራዚያኒ
ሆኖም የጠላት ጦር ወደ ጅጅጋ በሚያመራበት ጊዜ በጀርባው አልፎ የራስ ደስታ ጦር ሶማሊያን እንዳይወርበት ስለሰጋ ግራዚያኒ በሶማሊያ የሚገኘውን አንድ መቶ ሺህ ጦር ስለማይበቃኝ ተጨማሪ ጦር ይላክልኝ እያለ ለሙሶሎኒና ለጀነራል ባዶሊዮ ቴሌግራም መላኩን ተያያዘው፡፡
ግራዚያኒም በሞቃዲሾ መንደሮች ሁሉ የሶማሌ ነዋሪዎችን በአዋጅ አሰባስቦ፤
“ይኸውላችሁ፤ ኢትዮጵያውያን ሶማሊያን ለመውረር ተሰልፈዋል፡፡ እኛ በጦርነቱ ብንሸነፍ በመርከባችን ተሳፍረን ወደአገራችን እንመለሳለን፡፡ እናንተ ግን የምትሄዱበት ሥፍራ ስለሌላችሁ፤ ኢትዮጵያውያን የሴቶቻችሁን ጡት እየቆረጡ ይበሉታል፡፡ ምግባቸውም የሰው ሥጋ ነው፡፡ ስለዚህ ነጋዴ ነኝ፣ ገበሬ ነኝ ሳትሉ ኢትዮጵያውያንን መዋጋት አለባችሁ፡፡”

በማለት የውሸት ፕሮፓጋንዳ ሲነዛላቸው እውነት መስሏቸው ለውጊያ ተሰለፉ፡፡
በዚህን ወቅት ነው የባሌ አገረ ገዥ የነበሩት ክቡር ደጃዝማች በየነ መርድ 4 ሺህ ጠንካራና የሰለጠነ ጦራቸውን አሰልፈው ከጊኒር የዋቢ ሸበሌን ወንዝ ተከትለው መጓዝ የጀመሩት፡፡
የበየነ መርድ ሠራዊት የሸበሌ ወንዝ ዳርቻ ለጉዞ አመች በመሆኑ በፍጥነት ወደፊት መጓዝ ቻሉ።
Somalia Soldier fighting on the land of Ethiopians
ከጠላት ጦር ጋር ከተሰለፈው
የሶማሊያ የጦር አለቃ ወሎል ጂሌ
ታጣቂዎች ውስጥ አንዱ
ከኢጣሊያ ወገን የተሰለፈው የሶማሌያ ተወላጅ የነበረው ወሎል ጂሌ፤ ቁጥራቸው 1 ሺህ የሚደርሱ የሶማሊያ ወታደሮችንና የራሱን ሰዎች ይዞ በጥቂቶች የኢጣሊያ ወታደሮች መሪነት እየታገዘ በድምሩ 7 ሺህ ወታደሮችን በማያዝ ወደ ፊት ጉዞውን ቀጠለ፡፡
ወሎል ጂሌም የእግረኛ ወታደሮቹን አሰልፎ የደጃዝማች በየነ መርድን ጦር ለመግጠም ስለፈራ፤ ውጊያውን ወዲያውኑ እንደጀመረ ብዙ የኢጣሊያ አውሮፕላኖች መጥተው እንዲረዱት ለግራዚያኒ መልእክት ላከ፡፡
የክቡር ደጃዝማች በየነ መርድ ወታደሮችና የራስ ደስታ ዳምጠው ጦር በጋራ ለጦርነቱ ተሰልፈዋል፡፡
ከዚያም ታህሳስ 17 ቀን 1928 ዓ.ም. በወሎል ጂሌ የእግረኛ ወታደሮቹ እና በኢትዮጵያውያን ወታደሮች መካከል ጦርነቱ ተጀመረ፡፡

ጦርነቱም በመፋፋም ላይ ሳለ ግራዚያኒ ከሞቃዲሾ የላካቸው 19 ቦንብ ጣይ የጠላት አይሮፕላኖች ደርሰው 7 ቶን ክብደት ያለውን እና ተቀጣጣይ የሆነውን የሙስታርድ ጋስ ቦንብ በኢትዮጵያውያን ተዋጊዎች ላይ አዘነቡበት፡፡

አይሮፕላኖቹም ለመምታት እንዲመቻቸው ዝቅ ብለው ይበሩ ስለነበረ፤ ከ 19ኙ ቦምብ ጣይ አይሮፕላኖች ውስጥ 18ቱ የኢትዮጵያ ወታደሮች በመትረየስ ተኩሰው ሲመቷቸው ወዲያውኑ ወደመጡበት ሲመለሱ፤ አንዱ አይሮፕላን ግን ወድቆ ተከሰከሰ፡፡
በጦርነቱም ወቅት፤ ከወሎል ጂሌ ወታደሮች ውስጥ 300 ሶማሌዎች ከድተው ከኢትዮጵያውያን ወታደሮች ጋር ተቀላቅለዋል፡፡ ወሎል ጂሌም ወደኋላው አፈግፍጎ ተመለሰ፡፡
ከሁለቱም ወገን በርካታ ሙትና ቁስለኛ ተመዝግቧል፡፡

እውቁ ተዋጊ አርበኛና የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ ክቡር ደጃዝማች በየነ መርድ፣ ከሚመሯቸው አጋር የጦር አለቆች፤ ከቀኛዝማች ሰለባና ከቀኛዝማች አሰፋ ባሕታ ጋር በመሆን ከጠላት ጋር እየተዋጉ ሳለ በጦር ሜዳ ተመተው ወደቁ፡፡

የባሌ ገዥ የነበሩት ደጃዝማች በየነ መርድ በደቡብ ግንባር ከጠላት ጋር በሚፋለሙበት ወቀት ባለቤታቸው ልዕልት ሮማነወርቅ ኃይለ ሥላሴ ባለቤታቸው ደጃዝማች በየነ መርድ በሞት እስከተለዩዋቸው ድረስ አብርዋቸው ነበሩ፡፡
ልዕልት ሮማነወርቅ ባለቤታቸው ከሞቱ በኋላ ራስ ደስታ ዳምጠውን ተከትለው ሄደዋል፡፡
በኋላም ራስ ደስታ ዳምጠው በአካባቢው ባንዳዎች ጠቋሚነት ለጠላት ተላልፈው ሲሰጡ፤ ልዕልት ሮማነወርቅም በጠላት ቁጥጥር ሥር ውለው በአዳሜ ቱሉ ከቆዩ በኋላ ወደ ኢጣሊያ አገር በግዞት ተልከዋል፡፡

2. የጋብቻና የቤተሰብ ሁኔታ

Prince Romanwork Haile Selassie
ልዕልት ሮማነወርቅ ኃይለ ሥላሴ
ልዕልት ሮማነወርቅ ኃይለ ሥላሴ ከአባታቸው ቀዳማዊ ባለቤት ከነበሩት ከወይዘሮ አልታየች የተወለዱ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የበኩር ልጅ ነበሩ።
በእንግሊዝኛ የተጻፈው የንጉሠ ነገሥቱ የሕይወት ታሪክ ስለ ልዕልት ሮማነወርቅም ሆነ ስለ ንጉሠ ነገሥቱ የቀድሞ ጋብቻ ምንም የጠቀሰው ነገር የለም፡፡
ምንም እንኳን በዋናው የአማርኛ ቅጂ ቢጻፍም የፋሽስት ጦር ሽንፈትን ተከትሎ ንጉሠ ነገሥቱ ወደ መንበረ ንግሥናቸው ከተመለሱ ከጥቂት ቀናት በኋላ የመጀመሪያ ሴት ልጃቸው ልዕልት ሮማነወርቅ ወደ ኢጣሊያ አገር በምርኮ ከተወሰዱ በኋላ ቱሪን በሚገኘው አሲናራ አስር ቤት ውስጥ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ታስረው ነበር፡፡
በወቅቱ ልዕልቷ እስር ቤት ውስጥ ታመው ስለነበረ ማግዮሬ በተሰኘው ሆሰፒታል ውስጥ ሲታከሙ ቆይተው ጥቅምት 4 ቀን 1933 ዓ.ም. መሞታቸውን ንጉሠ ነገሥቱ ሲሰሙ የተሰማቸውን መሪር ሀዘን መግለጻቸው ተመዝግቧል።
በአሲናራ ከነበሩት እስረኞች መካከል አንዱ የነበሩት ባለምባራስ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል በአማርኛ ጽፈው ባሳተሙት “ዕፁብ ድንቅ” በተሰኘው መጽሐፋቸው አጠቃላይ የእስረኞች ቁጥር ከ400 በላይ እንደነበር ገልፀዋል።
የልዕልት ሮማነወርቅ እናት ስም በውል ባይታወቅም፤ “ወይዘሮ አልታየች” የሚለው የምትጠቀምበት የቅጽል ስም ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡
Ethiopian Prisoners at Asinara
በአሲናራ እስር ቤት ውስጥ ታስረው ከነበሩት
ከፍተኛ ትምህርት የተማሩና ተደማጭነት ያላቸው
የኢትዮጵያ መኳንንቶችና መሳፍንቶችት
የልዕልት ሮማነወርቅ የእናት ስምን በተመለከተ፤ ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፤ ወይዘሮ ወይኒቱ አመዴ እንደሚባሉ ገልጸዋል።
በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የቤተ መንግሥት መኳንንት የነበሩና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ውስጥ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጣቸው ታላቁ ሰው ብላታ መርሴ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ እንደሚገልጹት ከሆነ፤ የልዕልት ሮማነወርቅ እናት ወይዘሮ ወይኒቱ አመዴ፤ ልጃቸው ሮማነወርቅ ከደጃዝማች በየነ መርዕድ ጋር ባደረጉት የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተገኙ በመጽሐፋቸው ጠቅሰዋል። (የእንግሊዝኛውን ጽሁፍ ለማንበብ --> ሊንክ)
ክቡር ደጃዝማች በየነ መርድ፤ ከባለቤታቸው ከልዕልት ሮማነወርቅ አራት ወንድ ልጆችን አፍርተዋል፡፡
የልጆቻቸውም ስም ከተወለዱበት ዓ.ም. ጋር እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡
  1. ጌታቸው በየነ በ1922 ዓ.ም.
  2. ደጃዝማች መርድ በየነ በ1924 ዓ.ም.
  3. ደጃዝማች ሳምሶን በየነ በ1926 ዓ.ም.
  4. ልጅ ጌዲዮን በየነ በ1927 ዓ.ም.

በኢጣሊያ ወረራ ወቅት በሕይዎት ከተረፉት የክቡር ደጃዝማች በየነ መርድ ልጆች መካከል፤ ደጃዝማች መርድ እና ሳምሶን በየነ ብቻ ይገኙበታል፡፡
በ1933 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከኢጣሊያ ወረራ ነፃ መውጣቷን ተከትሎ የክቡር ደጃዝማች በየነ መርድ አጽም ጣሊያኖች ከቀበሩበት መቃብር ወጥቶ አዲስ አበባ ወደሚገኘው ወደ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተወስዶ ሥርዓተ ቀብሩ በክብር ተፈጽሟል፡፡

ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለቆ ከወጣ በኋላ የልዕልት ሮማነወርቅን እና የሁለቱን ታናናሽ ልጆቻቸውን አስከሬን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በአዲስ አበባ በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በሚገኘው የንጉሠ ነገሥቱ ቤተሰብ መቃብር እንዲቀበር ታስቦ ነበር፡፡
ነገር ግን የታቀደው ሊሳካ ስላልቻለ ልዕልት ሮማንወርቅ በኢጣሊያ ቱሪን ውስጥ የመታሰቢያ ሐውልት ተሰርቶ ከሜጀር ጀነራል ደጃዝማች በየነ መርድ ከተወለደው ከጌታቸው በየነ ጋር አብረው ተቀብረዋል፡፡

መታሰቢያ

ለውድ አገራቸው ነፃነት መጠበቅ ለከፈሉት አኩሪ መስዋዕትነትና ለፈፀሙት የአርበኝነት ተግባራቸው ሲባል ሜጀር ጀነራል ክቡር ደጃዝማች በየነ መርድ፤ በአዲስ አበባ ውስጥ ለገሀር ከካቶሊክ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በስተጀርባ የሚገኝ አንድ የአንደኛና የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በተጨማሪም ወሎ ሰፈር የሚገኝ አንድ መንገድ በስማቸው ተሰይሞላቸዋል፡፡






ምንጭ፤
  1. "የታሪክ ማስታወሻ"  ደራሲ፡- ደጃዝማች ከበደ ተሰማ 1962 ዓ.ም.
  2. "የኢትዮጵያ ታሪክ - ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ"  ደራሲ፡- ተክለ ጻድቅ መኩሪያ 1961 ዓ.ም.
  3. ከዊኪፒዲያ ተውጣቶ የተተረጎመ
  4. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ
  5. courtesy of: Rare WW2 Footage - German Infantry - No Music, Pure Sound  ዩቲውብ