Content-Language: am ልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ
header image



ልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ


የልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ የሕይወትና የአርበኝነት ዘመን ታሪክ
በእያንዳንዱ አርዕስት ሥር የሚገኘውን የድምጽ
ማጫወቻ በመጠቀም ትረካውን ማዳመጥ ይችላሉ

ክፍል አንድ

ትውልድ፣ ዕድገት፣ ትምህርት፣
የትዳር ሕይዎትና የሥራ ዘመን

ክፍል ሁለት

የልዑል ራስ እምሩ
የደምበጊና መተላለፊያ የጦርነት ውሎ

ክፍል ሦስት

በማይጨው የጦርነት ግንባር
ያበረከቱት አስተዋፅዖ

የመጨረሻ ክፍል

ከንጉሠ ነገሥቱ ስደት በኋላ ከጠላት ጋር
የጀመሩት ፍልሚያና ከነፃነት በኋላ የነበራቸው ሕይወት



1. ትውልድ፣ ዕድገትና ትምህርት

Leul Ras Imiru Haile Selassie
ልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ
ልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ ከአባታቸው ከደጃዝማች ኃይለ ሥላሴ ዓባይነህና ከእናታቸው ከወይዘሮ መዝለቂያ አያልወርቅ ህዳር 15 ቀን 1885 ዓ.ም. በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት በጉርሱም አውራጃ ተወለዱ፡፡
ልዑል ራስ እምሩ የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ የአጎታቸው ልጅ ናቸው፡፡
የራስ እምሩ እናት ወይዘሮ መዝለቂያ የራስ መኮንን እህት የወይዘሮ እኅተ ማርያም ልጅ ስለነበሩ የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ አብሮ አደግና የቅርብ ዘመድም ነበሩ።
እድሜአቸው አራት አመት ሲሆን፤ ትምህርታቸውን መማር እንዲችሉ፤ የእናታቸው የወይዘሮ መዝለቂያ አያልወርቅ አጎት ወደሆኑትና ወደ ተፈሪ ወላጅ አባት ወደ ልዑል ራስ መኮንን ቤተ መንግሥት ተወሰዱ፡፡
እምሩ እና ተፈሪ አብረው አድገው አብረው መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርታቸውን ከተማሩ በኋላ መደበኛ ትምህርታቸውንም በካቶሊክ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡
ራስ እምሩ እና ደጃዝማች ተፈሪ ሁለቱም ያደጉት የንጉሠ ነገሥቱ “እውነተኛ አባት” በሚባሉት በእምሩ አባት በደጃዝማች ኃይለሥላሴ ዓባይነህ ቤት ነበር።
እምሩ እድሜአቸው 13 አመት ሲሞላ፤ አሳዳጊያቸው ራስ መኮንን በሕመም ምክንያት በሞት ስለተለዩ፤ ትምሕርታቸውን ለመቀጠል እንዲችሉ ወደ አዲሰ አበባ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ከአብሮ አደጋቸው ከተፈሪ ጋር ተወሰዱ፡፡
እምሩ እና ተፈሪ ቀደም ሲል ሐረርጌ በነበሩበት ወቅት ጥሩ ትምህርት ገብይተው ስለነበርና የላቀ ዕውቀት ስለነበራቸው ከሐረር ለመጡ ለወንዶች ልጆች በተዘጋጀው ልዩ ክፍል ውስጥ ገብተው ትምህርታቸውን በአንድ ዓመት ውስጥ አጠናቀቁ፡፡

2. የትዳር ሕይዎት

ልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ፤ ወይዘሮ ጽጌ ማሪያምን አግብተው 7 ሴት ልጆችንና አንድ ወንድ ልጅ አፍርተዋል፡፡ ወንድ ልጃቸው ልጅ ሚካኤል እምሩ ይባላሉ፡፡
Lij Mikael Imiru Haile Selassie
ልጅ ሚካኤል እምሩ
ህዳር 12 ቀን 1922 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተወለዱት ልጅ ሚካኤል እምሩ፤ ከሰለሞናዊው ሥርዎ መንግስት የዘር ሐረግ የሚመዘዙ ናቸው።
ልጅ ሚካኤልም ሆኑ አባታቸው በተለይ በመሬት ይዞታ እና በሀብት ክፍፍል ጉዳዮች ላይ ጠንካራ የሶሻሊዝም ዝንባሌ እንደነበራቸው ይነገራል፡፡
ልጅ ሚካኤል እንግሊዝ አገር በሚገኘው በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተምረው ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ በተለያዩ ከፍተኛ የኃላፊነት ሥራዎች ላይ ተመድበው አገልግለዋል፡፡
በመጨረሻም፤ በ1974 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ጠቅላይ ምኒስትር ሆነው ተመድበው የነበሩት ልጅ እንዳልካቸው ከሥልጣን ሲወርዱ፤ እርሳቸውን ተክተው የአገሪቱ ጠቅላይ ምኒስትር ሆነው ጥቂት ጊዜያት አገልግለዋል፡፡
ልጅ ሚካኤል፤ ምንም እንኳን ከንጉሣዊ ቤተሰብ የተወለዱ ቢሆንም ቅሉ፤ የግራ ዘመም ፖለቲካን የሚደግፉ ስለነበሩ፤ የደርግ አስተዳደር እርሳቸውን እና አብዛኛወቹን ዘመዶቻቸውን አላሰራቸውም።

3. የሥራ ዘመን

በ1901 ዓ.ም. እምሩ የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ ሆነው ሲሾሙ፤ የአሥራ ሰባት ዓመቱን ልጅ ተፈሪ መኮንንን አስከትለው ሄደዋል፡፡
በ1903 ዓ.ም. እምሩ ተፈሪን ተከትለው ወደ ሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ከሄዱ በኋላ፤ እምሩ በተፈሪ የግራዝማችነት ሹመት ከተሰጣቸው በኋላ የጃርሶና የጅጅጋ አውራጃ አስተዳዳሪ ሆነው ተሸሙ፡፡
በ1909 ዓ.ም. ግራዝማች እምሩ ፤ በአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን የደጃዝማችነት ማዕረግ ተሰቷቸው የሐርረጌ ጠቅላይ ገዥ ሆኑ፡፡
ደጃዝማች እምሩ የሐርረጌ ጠቅላይ ገዥ ሆነው ለ11 ዓመታት በቆዩባቸው ጊዚያት፤ በራስ ተፈሪ የተጀመሩ የፖለቲካ ማሻሻያ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል፡፡
በዚህን ወቅት ደጃዝማች እምሩ ፤ ሁለቱን ተራማጅ አስተሳሰብ የነበራቸውን በአውሮፓ የተማሩትን ምሁራን፤ ማለትም ሀኪም ወርቅነህ እሸቴንና በጅሮንድ ተክለ ሐዋርያትን ከውጭ ሀገር በማስመጣት በስራቸው በሚያስተዳድሯቸው አውራጃዎች ውስጥ ተመድበው እንዲያገለግሉ አድርገዋል፡፡
ደጃዝማች እምሩ ፤ በእነዚህ ምሁራን በመታገዝ የአውራጃወችንና በኋላም የቤገምድርን የዳኝነትና የግብር አወሳሰን ሥርዓትን ማሻሻል ችለዋል፡፡
በኋላም አልጋ ወረሽ ተፈሪ መኮንን የንጉሠ ነገሥትነት ዘውድ ከጫኑ በኋላ ደጃዝማች እምሩ የወሎ ጠቅላይ ግዛትን እንዲያስተዳድሩ ተሸሙ፡፡
ይሁን እንጅ በቅርቡ በታተመው ማስታወሻቸው ላይ እንዳሰፈሩት፤ ወሎን ማስተዳደሩ እንደ ሐረርጌ ቀላል እንዳልነበረ ያስታውሳሉ፡፡
Ras imuru with his family
ልዑል ራስ እምሩ ከቤተሰቦቻቸው ጋር

Photo courtesy of:  wemezekir
ይህም ሁሉ ሆኖ፤ መንገዶችን ፣ ድልድዮችን እና ትምህርት ቤቶችን በመገንባት የወሎን ግዛት ከማዕከላዊ መንግስት ጋር ለማገናኘት ተችሏል ፡፡
ደጃዝማች እምሩ በ1924 ዓ.ም. የራስነት ማዕረግ ካገኙ በኋላ የጎጃም ገዥ የነበሩትን ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖትን ተክተው የጎጃም ጠቅላይ ገዥ ሆነው ተሸሙ፡፡
ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት፤ ልጅ እያሱ ከእስር እንዲያመልጡ ረድተዋል በሚል በክህደት ወንጀል ተከሰው የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው ከሥልጣናቸው እንዲወገዱ ተደርገው ነበር፡፡
ልዑል ራስ እምሩ ም ጎጃም ሲደርሱ እንደጠበቁት መልካም አቀባበል አልገጠማቸውም፡፡
የራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት ልጅ የሆኑት ፊታውራሪ አድማሱ ኃይሉ አምጸው ለአጭር ጊዜም ቢሆን የደብረ ማርቆስ ከተማን ተቆጣጥረውት ነበር፡፡
በኋላም ፊታውራሪ አድማሱ በፈፀሙት ሕገወጥ ተግባር በመጸጸታቸው ለንጉሠ ነገሥቱ መልዕክተኞችን ልከው ይቅርታ እንዲደረግላቸው ተማጽነዋል፡፡
ልዑል ራስ እምሩ ፤ ልክ እንደሐረርጌ ሁሉ ዘመናዊ የትምህርት፣ የህግ፣ የጉምሩክ እና የግብር ማሻሻያዎችን ለማቋቋም ቢሞክሩም በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡
ይልቁንም የጎጃም ሕዝብ፤ በንጉሠ ነገሥቱ የተሾሙትን ልዑል ራስ እምሩ ን እንደባይታወር አይቶ በሠላም ሊቀበላቸው እንዳልቻለ ሲረዱ የኃይል እርምጃ በመውሰድ፤ በሞት ቅጣትና እንዲሁም በአካባቢው አመጸኞችን እና ሽፍቶችን አድኖ በማሰር ህግና ስርዓትን ለማስፈን ጥረዋል፡፡
በአብዛኛው አውራጃወች ውስጥ የመሬት ይዞታ ማሻሻያ ለማድረግ ቢሞክሩም፤ ሰፊውን መሬት የተቆጣጠረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናት ተቃውሞ በመኖሩ ሊሳካ አልቻለም፡፡
ልዑል ራስ እምሩ የሸዋ መኳንንት ሲሆኑ፤ ተራማጅ አስተሳሰብ የነበራቸው፣ የጦር አዝማች፣ ዲፕሎማት፣ ፖለቲከኛ እና ጸሐፊም ነበሩ፡፡

4. የደምበጊና መተላለፊያ የጦርነት ውሎ

ቁጥሩ 40 ሺህ የሚደርስ የራስ እምሩ ጦር ህዳር 26 ቀን 1928 ዓ.ም. ከጎጃም ተነስቶ ወደ ዘመቻ ሲጓዝ ለመጀመሪያ ጊዜ የቦምብ ጥቃት ደረሰበት፡፡
በደረሰውም የቦምብ ጥቃት ግማሽ ያህሉ የራስ እምሩ ጦር ተደናግጦ ወደ ሀገሩ በመመለስ ላይ ነበር፡፡
Dejazmach Ayalew Birru
የቤገምድር ገዥ ደጃዝማች አያሌው ብሩ

Photo courtesy of:  alchetron  (edited by: the webmaster)
በዚህም የተነሳ ራስ እምሩ የቀረውን ጦራቸውን አሰባስበው የደጃዝማች አያሌው ብሩ ግዛት ወደሆነው ወደ ጎንደር ገብተው ከደጃዝማች አያሌው ብሩ ጦር ጋር ተቀላቀሉ፡፡
ንጉሠ ነገሥቱም ደሴ ሆነው በአይሮፕላን ባስተላለፉት መልእክት፤ ደጃዝማች አያሌው ብሩ በሰቲት ሁመራ የሚያካሂደውን ውጊያ አቁሞ ከራስ እምሩ ጋር በመሆን ጦራቸውን ወደ ተከዜ ወንዝ እንዲያመሩ ትእዛዝ ደረሳቸው፡፡
የተከዜ ወንዝ፤ በፋሽስት ኢጣሊያ የተያዘውን የምእራብ ትግራይን ግዛት ከቤገምድር ግዛት የሚለይ በጥልቅ ገደል መሐል የሚያልፍ ትልቅ ወንዝ ነው፡፡
ራስ እምሩ ጠላትን ለማታለል በማሰብ በጠራራ ፀሐይ በሰሜን ምእራብ ተቃራኒ አቅጣጫ ጦራቸውን በረድፍ በማሰለፍ ጉዞ ሲጀምሩ፤ ጠላት ነቅቶ ኖሮ በአይሮፕላን የቦምብ ጥቃት አደረሰባቸው፡፡
በኋላም የራስ እምሩና የደጃዝማች አያሌው ጦር በጋራ ሆኖ በምሽት አቅጣጫቸውን ቀይረው ወደ ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ ጉዞ በመጀመር ከንጋት በፊት የተከዜን ወንዝ ተሻገሩ፡፡
ቁጥሩ 2 ሺህ የሚደርስ የራስ እምሩ ጠንካራ ቀዳሚ ጦርም ምንም አይነት የጠላት ውጊያ ሳያጋጥመው ተከዜን ተሻገረ፡፡
የደጃዝማች አያሌው የጦር መሪ የሆነው ፊታውራሪ ሽፈራው ጦሩን እየመራ ወደ ደምበጊና መተላለፊያ የሚወስደውን የእግረኛ መንገድ ለማስከፈት ማይ ጥምቀት የተባለውን ቦታ እንዳለፉ የጠላት ፈረሰኛ ጦር ተኩስ ሲከፍትባቸው ወዲያውኑ የወገን ጦር የመልስ ተኩስ በጠላት ላይ ሲከፍቱ ፊታውራሪ ሽፈራው ተኩሱን ለማስቆም ትእዛዝ ቢሰጥም ተኩስን ማስቆም አልቻለም፡፡
ወዲያውኑ የጠላት ጦር ሁለት አፍ መትረየስ ባለው ታንክ ተኩስ ሲከፍት፤ አንድ የኢትዮጵያ ደፋር ወታደር ወደ ታንኩ እየሮጠ ሄዶ ታንኩ ላይ ዘሎ ወጣ፡፡
የታንኩ ሹፌርም ወዲያውኑ አቅጣጫውን ወደ ኋላ ሲያዞር፤ ወታደሩ የታንክ መትረየስ ተኳሹ የሚቀመጥበትን የታንክ ክፍል (turret) ከፍቶ የመትረየስ ተኳሹን አንገት በያዘው ጎራዴ ቀላው፡፡

ከደምበጊና መተላለፊያ በርቀት ሆነው ይህን የኢትዮጵያ ደፋር ወታደር ተግባር የተመለከቱ የጠላት ወታደሮች የቀራቸውን ዘጠኝ ታንኮቻቸውን ይዘው እየተኮሱ ወደ ወገን ጦር ሲጠጉ፤ የኢትዮጵያ ጦር ወደኋላው ማፈግፈግ ጀመረ፡፡
በዚህ ውጊያ የፋሽስት ጦር አዛዡና ሁለት መኮንኖች ከሞቱ በኋላ የጠላት ጦር ወደ ደምበጊና መተላለፊያ አፈገፈገ፡፡
የጠላት ጦር፤ የኢትዮጵያውያንን ወታደሮች ለማዘናጋት ሲል ከደምበጊና የጦር ሠፈራቸው የተጫኑ በቅሎዎቻቸውን ነድቶ በማሶጣት ኢትዮጵያውያን ወታደሮች በበቅሎዎች የተጫነውን ለመዝረፍ ሲሰማሩ፤ የጠላት ጦር የወገንን ጦር አዘናግቶ ተኩስ ከፍተው ለመጨረስ አቅደው ነበር፡፡
ሆኖም የጠላት ጦር እንዳሰበው አልተሳካለትም፡፡
Ethiopian Attacking on Dembegina Pass
በካርታው ከላይ ቀኝ ጥግ እንደሚታየው የልዑል ራስ እምሩ ጦር
ደምበጊና መተላለፊያን (Dembegina pass) በጦርነት አሸንፈው
ሽሬ እንዳ ስላሴን ከጠላት ይዞታ ነፃ አድርገዋል
የኢትዮጵያ ወታደሮች ግን ተንኮሉ ስለገባቸው በቅሎዎቹን ተከትለው ደምበጊና ላይ ወደ ሰፈረው የጠላት ጦር ካምፕ ደርሰው እዚያ የሚገኙትን የቆሰሉ የጠላት ወታደሮችን ገድለው በካምፑ ውስጥ ያገኙትን ጠላት የሚጠቀምባቸውን መሣሪያና ቁሳቁሶችን ሁሉ ዘረፉ፡፡

በደምበጊና የጦር ካምፕ ውስጥ የነበሩት አብዛኛዎቹ የፋሽስት መኮንኖች ስለተገደሉ የተረፈው የጠላት ጦር ምንም የጦር መሣሪያ ሳይዝ ሸሽቶ በአካባቢው ወደሚገኘው ተራራ ላይ ወጥቶ በመሰበሰብ እጁን ወደላይ በማውጣት መማረኩን አሳየ፡፡
ነገር ግን የኢትዮጵያ ወታደሮች የጠላት እጅ ማውጣት ምን ማለት እንደሆነ ስላልገባቸው፤ እየተንደረደሩ ሄደው በባዶ እጃቸው ያገኟቸውን የጠላት ወታደሮች ገደሏቸው፡፡
የተረፉትም የጠላት ወታደሮች ከተራራው በመውረድ በመኪናቸው ተሳፍረው ቦታውን በፍጥነት ለቀው ሸሹ፡፡
በዚህ የተፋፋመ ውጊያ ላይ፤ የኢትዮጵያ የፊት ጦር መሪ የነበረው ፊታውራሪ ሽፈራው በጦርነቱ ተገደለ፡፡
ነገር ግን በውጊያው አብረውት ያልተለዩት የፊታውራሪ ሽፈራው አባት፤ የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ኋላ ሳይመለሱ የጠላትን ጦር እየተከተሉ እንዲዋጉ ነገሯቸው፡፡
በዚህ በደምበጊና ጦርነት፤ የኢትዮጵያ ወታደሮች ጠላት ሰፍሮበት ከነበረው ተራራ ስር ያገኙትን የጠላት መኪና ገልብጠው በእሳት አጋይተውታል፡፡
ሁለቱም የጠላት ታንክ ተኳሾችም ወደ ወንዝ ሊሸሹ ሲሉ ተገድለዋል፡፡
ሦስተኛው የጠላት ታንክ ተኳሹ ግን ‘ክርስቶስ’ የሚል ድምፅ በማሰማቱ፤ የወገን ወታደሮች ቃሉን ሰምተው በመገረም ሳይገደል አምልጧል፡፡

የተቀናጀው የራስ እምሩ ጦር በዚህ ጦርነት ድል እየተቀዳጀ፤ የኤርትራ ወታደሮችን በመከተል ከአክሱም የ48 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን ሽሬ እንዳ ስላሴን ከጠላት ይዞታ ነፃ ካደረጉ በኋላ እርፍት ወሰደ፡፡
የተቀኛጀው የራስ እምሩ ጦርም ጉዞውን ወደ አክሱም አቅጣጫ ቀጠለ፡፡
የጠላት ጦርም የኢትዮጵያን ጦር ለመመለስ አክሱም የሚገኙትን 10 ታንኮችና ጥቁር ሸሚዝ ለባሽ የኢጣሊያ ሚሊሽያዎችን ለውጊያ አሰማራ፡፡
የኢትዮጵያ ጦር ግን በከፍተኛ ሞራል ላይ ስለነበር፤ የጠላት ታንኮች እንዳይንቀሳቀሱ በናዳ መንገዳቸውን በመዝጋትና የጠላትን ጦር በደፈጣ ውጊያ መውጫ መግቢያ አሳጣው፡፡
ሁለት የጠላት ታንኮች መንቀሳቀስ ሰላልቻሉ ከመንገድ ወተው ተገትረው ቀሩ፡፡
በዚህም ጊዜ የኢትዮጵያን ጦር በቆሙት ታንኮች ላይ እሳት ለኩሰው አቃጠሏቸው፡፡
ሁለት የጠላት ወታደሮችንም ማርከዋል፡፡
ይህ የኢትዮጵያ ጦር የውጊያ እንቅስቀሴ በጠላት ጦር ላይ የበላይነትን ስላገኘ፤ በከፍተኛ ሞራል ጠላትን መዋጋት እንደሚችል የተማመነ በመሆኑ፤ 12 ኪሎ ሜትር ብቻ ወደ ቀረው ወደ አክሱም ከተማ በማምራት ውጊያውን ቀጠሉ፡፡
የእንዳስላሴ ከጠላት ቁጥጥር ነፃ መሆን ኢትዮጵያውያን የተከዜ መሸጋገሪያ ምሽጎች ላይ የበላይነት እንዲኖራቸው አስችሏል፡፡
በዚህ ኢትዮጵያውያን የበላይነት ባገኙበት ውጊያ ላይ፤
  • 500 የፋሽስትና የኤርትራ ወታደሮች ተገድለዋል፣
  • 4ሺህ 700 የጠላት ወታደሮች ተማርከዋል፣
  • በትንሹ 3 ሺህ የጠላት ወታደሮች ተደምስሰዋል፤
  • 18 ታንኮች፤
  • 33 መድፎች፤
  • 175 መትረየሶችና፤
  • 2ሺህ 605 ጠመንጃዎች ተማርከዋል፡፡
በአጠቃለይ ‘የጥቁር ሸሚዝ ለባሽ የሆነው 2ኛው ዲቪዚዮን’ የጠላት ጦር ከጥቅም ውጭ መሆኑ ታውቋል፡፡

በዚህ ውጊያ ድል የቀናው የራስ እምሩ ጦር በግራ ረድፍ በኩል ጉዞውን በመቀጠሉና ለሌሎች የኢትዮጵያ ጦር ዘማቾች ሽፋን የሰጠ በመሆኑ፤ ሌላው የወገን ጦር ጉዞውን ወደ ጠላት አቅጣጫ ቀጥሏል፡፡
በዚህም የተነሳ በልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ የሚመራውም ጦር ወደ አቢ አዲ በመገስገስ በመሐል ረድፍ ከተሰለፈው ከልዑል ራስ ስዩም መንገሻ ጦር ጋር ተቀላቀለ፡፡
በቀኝ ረድፍ የተሰለፈው የራስ ሙሉጌታ ይገዙና መሐል ሰፋሪ የተሰኘው ጦር ድግሞ፤ በጣላት እጅ ወደ ወደቀው ወደ መቀሌ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡
ይህ የኢትዮጵያ ጦር አሰላለፍና እንቅስቀሴ፤ የጠላት ጦር ከተከዜ ነቅሎ አክሱም ላይ ብቻ እንዲወሰን አስችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ጦር በጠላት ጦር ላይ የበላይነት እያገኘ መሄድ ያሳሰበው የጠላት ጦር፤ የኋላ ኋላ ሽንፈትን ተከናንቦ የኢትዮጵያን ምድር ለቆ እንደሚወጣ ተረዳ፡፡
በዚህም መሰረት የፋሽስት ጦር አዛዥ ማርሻል ባዶሊዮ በዓለም አቀፍ የጄኔቫ ስምምነት የተከለከለውን የኬሚካል ጦር መሳሪያ የሆነውን የሙስታርድ ጋዝ ቦምብ ካልተጠቀመ በስተቀር የኢትዮጵያን ጦር በጭራሽ ማሸነፍ እንደማይችል በመገንዘቡ ኬሚካሉ እንዲላክለት ጠይቆ ተላከለት፡፡
በዚህም መሠረት የጠላት ጦር የሙስታርድ ጋዝ በመድፍና በጦር አይሮፕላኖች ላይ እየተጫነ እንዲተኮስ በመደረጉ፤ የረባ የጦር መሣሪያ ባልታጠቀው፤ ነገር ግን ጅግና ልብ ብቻ በያዘው የኢትዮጵያ ጦር ላይ ሲያዘንብበት የጦርነቱ አቅጣጫ መልኩን መቀየር ተገደደ፡፡
በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ጦር ከላይ የሚዘንብበትን የኬሚካል ጋዝ ተቋቁሞ መዋጋት አልቻለም፡፡

5. የማይጨው ጦርነት ውሎ

ከላይ በደምበጊና ጦርነት ላይ እንደተገለፀው፤ ልዑል ራስ እምሩ በርካታ ቁጥር ያላቸውን የታጠቁ የጎጃም ጦራቸውን ከደጃዝማች አያሌው ብሩ ጦር ጋር በማጣመር ወደ ሰሜን ጦር ግንባር በመዝመት የራስ ስዩም መንገሻ ጦር ከሠፈረበት ስፍራ በስተግራ በማስፈር ጠላትን ተዋግቷል፡፡
በዚህ በሰሜኑ የጦር ግንባር የተሻለ ውጤት የታየበት በሽሬ ግንባር የነበረው በራስ እምሩ የሚመራው ሠራዊት ሲሆን፤ በኢጣሊያ የቅኝ ግዛት ወታደሮች ላይ ከፍተኛ ድል ተቀዳጅቷል፡፡
የራስ እምሩ የጦር አመራር ከሌሎች የጦር አዛዦች ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ስለነበር በኢጣሊያ ወታደሮች ሳይቀር የእርሳቸው ጦር የተፈራ ነበር፡፡
ሆኖም የጠላት አይሮፕላን ሳያቋርጥ የሚያዘንበውን መርዛማ የጋስ ቦምብ ተቋቁሞ መዋጋት የማይቻል በመሆኑ፤ የኢትዮጵያ ጦር የሚዋጋበትን ሥፈራ ለቆ ወደኋላ ወደ ተከዜ በመመለሱ ጠላት ሽሬን ሊይዝ ችሏል፡፡

በሰሜን ግንባር በተከፈተው ጦርነት፤ አጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው የኢትዮጵያ ጀግኖችና የጦር ሹማምንቶች በጦርነት መሐል እየገቡና ግንባር ለግንባር በጨበጣ ውጊያ እየተዋጉ በጀግንነት በአንድላይ ወድቀዋል፡፡

6. ከንጉሠ ነገሥቱ ስደት በኋላ ከጠላት ጋር የጀመሩት ፍልሚያ

የጣሊያን ወታደሮች አዲስ አበባን ከተቆጣጠሩ በኋላ፤ንጉሠ ነገሥቱ ፋሽስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ የፈፀመችው ወረራ ሕገወጥ መሆኑን ለዓለም መንግሥታት ማህበር ለማመልከት ከአገራቸው ተሰደው ሲሄዱ፤ ራስ እምሩ ንጉሠ ነገሥቱን በመወከል ጦራቸውን እንደገና አደራጅተው ጣሊያኖችን ለመፋለም ወደ ኢሉባቦር ጠቅላይ ግዛት ተጓዙ፡፡
የፋሽስት ወታደሮች ወደ ደቡብ ጥቃት መሰንዘር ሲጅመሩ፤ ራስ እምሩ ጎሬ መቆየት ስላልቻሉ ጦራቸውን ይዘው ወደ ደቡብ ምስራቅ በማፈግፈግ ጎጀብ ወንዝ አካባቢ ሲደርሱ፤ በቁጥሩ የተመናመነው የራስ እምሩ ጦር ታህሳስ 10 ቀን 1929 ዓ.ም በጠላት ጦር ተከቦ ተማረከ፡፡
በዚህ ውጊያ ላይ የጦሩ አዛዥ ራስ እምሩም ተማርከው ኢጣሊያ ሀገር ወደሚገኘው ፖንዛ ወደተባለው ደሴት ተወስደው ታሰሩ፡፡
ራስ እምሩ የኢጣሊያንን አገዛዝ የሚቀበሉ ከሆነ፤ የተወሰደባቸው መሬት ሁሉ እነደሚመለስላቸው የኢጣሊያ ባለሥልጣናት አባብለዋቸው ነበር፡፡
በአርበኝነት ያገለገሉት አዲስ ዓለማየሁ ስለራስ እምሩ ሲናገሩ፤
“ዋናው ነገር የአገሬ ነፃነት እንጅ የግል መሬት ለእኔ ምንም ማለት አይደለም፡፡”
የሚል መልስ ለጣሊያኖች እንደሰጧቸው መስክረዋል፡፡

7. ኢትዮጵያ ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ

ራስ እምሩ ኢትዮጵያ ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ በ1935 ዓ.ም. በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን የመጀመሪያውን የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ስብሰባ ተካፍለዋል፡፡
በህንድም የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን አገልግለዋል፡፡
ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱም በኋላ የልዑልነት ማዕረግ ተሰቷቸው ልዑል ራስ እምሩ ተሰኙ፡፡
በአርሲ ለግላቸው የተሰጣቸውንም መሬት ለኢትዮጵያ አርበኞች እንዲከፋፈል በማድረግ መልካም ተግባር ፈጽመዋል፡፡
የልዑል ራስ እምሩ ሊበራል የሆነው ተራማጅ አመለካከቶችና እንዲሁም በስራ ዘመናቸው ሁሉ የገነቡት የተሃድሶ እና የዘመናዊነት ሥራዎቻቸው ሁሉ በፊውዳሉ ንጉሳዊ አገዛዝና በተቃዋሚዎቻቸው ሳይቀር እንኳን አክብሮት እና እውቅና እንዲያገኙ አስችለዋቸዋል፡፡
የ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት ጠንሳሾቹ፤ ጠቅላይ ምኒስትር የነበሩትን ራስ አበበ አረጋይን ከገደሉ በኋላ በንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ምትክ ልዑል አልጋወራሽ አስፋወሰን ኃይለ ሥላሴን አስቀመጡ፡፡
ልዑል አልጋወራሽ አስፋወሰን በበኩላቸው ደግሞ ልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴን ጠቅላይ ምኒስትር አድርገው ሾመዋቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጅ ሹመቱ ለ3 ቀናት ብቻ የቆዬ ነበር፡፡

በ1966 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱን ከሥልጣን ያሶገደው የደርግ መንግስትም፤ ለልዑል ራስ እምሩ ከፍተኛ አክብሮት ነበረው፡፡
ልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ፤ ኢትዮጵያ ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ ለ39 ዓመታት ኖረው ነሐሴ 11 ቀን 1972 ዓ.ም. በተወለዱ በ87 ዓመታቸው ሕይወታቸው አልፏል፡፡ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው በደርግ መንግሥት በክብር ተከናውኗል፡፡



ምንጭ፤
  1. "የኢትዮጵያ ታሪክ - ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ" ደራሲ፡- ተክለ ጻድቅ መኩሪያ 1961 ዓ.ም.
  2. ምስጋና ለ፤ ወመዘክር ብሎግ ፖስት  wemezekir
  3. ከዊኪፒዲያ የተተረጎመ
  4. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ