Content-Language: am ራስ ሙሉጌታ ይገዙ
header image




ራስ ሙሉጌታ ይገዙ



የራስ ሙሉጌታ ይገዙ የዐድዋና
የማይጨው ጦርነት የአርበኝነት ታሪክ











1. በዐድዋ ዘመቻና ከዓድዋ ዘመቻ በኋላ

Ras Mulugeta Yigezu
ራስ ሙሉጌታ ይገዙ
ራስ ሙሉጌታ ይገዙ በወጣትነት እድሜአቸው በዐድዋ ዘመቻ ዘምተው ተዋግተው ተመልሰዋል፡፡
ራስ ሙሉጌታ ከዐድዋ ዘመቻ መልስ ዳግማዊ ምኒልክ በ1900 ዓ.ም. የምኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ሲያቋቋሙ ሙሉጌታ ይገዙ የበጅሮንድ ሥልጣን ተሰጥቷቸው የገንዘብ ሚኒስትር ሆነው ተሹመው ነበር፡፡
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከአረፉ በኋላም ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ሲተኩና ልዑል ራስ ተፈሪ መኮንን አልጋወራሽነቱን ሲይዙ፤ የንግሥቲቱ ባል የሆኑት ራስ ጉግሳ ወሌ በራስ ተፈሪ ላይ አምፀው ጦር ሲያደራጁ በወቅቱ ደጃዝማች የነበሩት ሙሉጌታ ይገዙ የጦር ምኒስትር ስለነበሩ በራስ ጉግሳ ላይ ጦር ላኩ፡፡
ንግሥት ዘውዲቱ ባለቤታቸውን ከጥፋት ለማዳን ሲሉ ለአልጋወራሽ ተፈሪ አሜን ብለው እንዲገቡ ቢወተውቱም፤ ራስ ጉግሳ ግን አሻፈረኝ ብለው በአመጹ ቀጠሉ፡፡
ይህም በደጃዝማች ሙሉጌታ የጦር ምኒስትርነት የሚመራው የልዑል ራስ ተፈሪ ጦር፤ በጦር መሣሪያም ሆነ በጦር አይሮፕላን ብልጫ ያለውና ከፍተኛ ስነ ልቦናዊና ቁሳዊ የበላይነቱን ያረጋገጠ ስለነበረ ከራስ ጉግሳ ጦር ጋር የተደረገው ይህ ‘አንችም‘ ተብሎ በሚጠራው ጦርነት የደጃዝማች ሙሉጌታ ጦር አሸነፈ፡፡
በወጊያውም ራስ ጉግሳ ተመቶ ተመተው ወደቁ፡፡

2. በሰሜን ጦር ግንባር የነበራቸው ተሳትፎ

ራስ ሙሉጌታ ይገዙ፤ ፊታውራሪ ሐብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ከሞቱ በኋላ በእርሳቸው ምትክ የጦር ምኒስትር በመሆን በሰሜን ጦር ግንባር በአምባ አራዶም የጦር ቀጠናን ተቆጣጥረው ጦራቸውን አስፍረዋል፡፡
በሰሜን ጦር ግንባር የተምቤን የመጀመሪያ ጦርነት ከጥር 11 እስከ 15 ቀን 1928 ዓ.ም. ድረስ በተካሄደበት ወቅት፤ የልዑል ራስ ካሣ ኃይሉና የልዑል ራስ ስዩም መንገሻ ሠራዊት ከፋሽስት ጦር ጋር ከፍተኛ ፍልሚያ ቢያደርግም የጠላት አይሮፕላኖች በሚያዘንቡት የሙስታርድ ጋስ ቦምብ ምክንያት ከባድ ጉዳት ስልደረሰበት ድል አልቀናውም፡፡
ከተምቤን የመጀመሪያ ጦርነት ቀጥሎ የጠላት ጦር ዒላማ በአምባራዶም ኮረብታማ ሥፍራ የሠፈረውን የራስ ሙሉጌታን ጦር ማጥቃት ነበር፡፡
በአምባራዶም ለውጊያ የተዘጋጀው የራስ ሙሉጌታ ይገዙ ሠራዊት 80 ሺህ ይደርስ ነበር፡፡
የጠላት ጦር የአምባ አራዶምን ጦርነት የጀመሩት ከየካቲት 2 እስከ የካቲት 7 ቀን 1928 ዓ.ም. ድረስ ለተከታታይ 7 ቀናት የፈጀ ከፍተኛ የአየር ጥቃት እና የመድፍ ድብደባ በኋላ ነበር፡፡
ይህም የአየር ጥቃትና የመድፍ ድብደባ፤ አሮጌ የጦር መሣሪያ ለያዘና በጦርና በጎራዴ ፊት ለፊት ጠላትን በጨበጣ ውጊያ መፋላም ለለመደው ለሞት አይፈሬው ጀግና የኢትዮጵያ ሠራዊት ፈጽሞ ሊቋቋመው የማይችለው እንግዳ ነገር ስለሆነበት ከባድ ጉዳት ከማስተናገድ በስተቀር ሌላ አማራጭ ስለአልነበረው የያዘውን የአምባራዶምን ኮረብታ መልቀቅ ግድ ሆነ፡፡
የጦር ምኒስትሩ ራስ ሙሉጌታ ይገዙ አምስት ቀን ሙሉ ከጠላት ጋር ሲዋጉ ሳሉ፤ በአይሮፕላን የሙስታርድ ጋዝ የቦንብ ጥቃት ምክንያት ብዙ የኢትዮጵያ ሠራዊት እነዳለቀባቸው ባዩ ጊዜ፤ በጦርነት የደከመውን ሠራዊታቸውን ይዘው ከነልዑል ራስ ካሣና ከነልዑል ራስ ሥዩም መንገሻ ጦር ጋር ተደባልቀው ለመዋጋት ወደኋላ ሊመለሱ ሲሉ፤ የጠላት ጦር አይሮፕላኖች፤ በሙስታርድ ጋዝ ቦምብ በተከታታይ የኢትዮጵያን ሠራዊት በመደብደብ ከፍተኛ ጉዳት አደረሱበት፡፡
የኢትዮጵያ ጦር ግን በዚህ እሳት መካከል ሆኖ ተስፋ ሳይቆርጥ በጀግንነት ይዋጋ ነበር፡፡
ብዙውን ጊዜ የያዘውን የነፍስ ወከፍ ጠመንጃውን እየተወ፤ በፉከራ እየገሠገሠ እስከ ጠላት ታንክና መድፍ አፍ ድረስ እየደረሰ፤ ጠላቱን በእጁ ጨብጦ በያዘው ሠይፍና ጐራዴ ይጨፈጭፈው ነበር፡፡
እነዚህን ሞት ምንም የማይመስላቸውን የኢትዮጵያ ጀግኖች ወታደሮችን ደፋርነት በቦታው ያዩ የጣሊያን ጋዜጠኞች እጅግ ይገረሙ እንደነበር ተዘግቧል፡፡
በዚህ የውጊያ ቀን፤
  1. ከኢትዮጵያ ወገን፤ 1,000 ሞተው፤ 2,000 ደግሞ በአይሮፕላን ቦምብ ቆስለዋል፡፡
  2. ከጠላት ወገን ደግሞ፤ 1,500 ሲሞቱ፤ ብዙ ምርኮኞች ተይዘዋል፡፡

  3. ይህን በጦርነት ፋታ ያላገኘውንና የተጐሣቆለውን የኢትዮጵያ ሠራዊት በጉዞ ላይ ሳለ ሌላ ያልጠበቀው ፈተና ገጠመው፡፡
    ይኸውም ጣሊያን የራያና ያዘቦ ሕዝቦችን አስቀድሞ በቃል ስብከትና በገንዘብ በመደለል፤ የጦር መሣሪያ እየሰጠ ኢትዮጵያን ከድተው የወገንን ጦር እንዲወጉ ይልካቸው ስለነበር፤ በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ ተኩስ ከፍተው ውጊያ ሲጀምሩ፤ በነዚህ ሰዎች በተተኮሰች ጥይት ሳቢያ፤ አይበገሬው የዐድዋው ጀግና አርበኛ ራስ ሙሉጌታ ይገዙ፤ 40 ዓመት ከሞላው የዐድዋው ድል በኋላ በዚህ ጦርነት ላይ በጀግንነት ወደቁ፡፡

    ራስ ሙሉጌታ ይገዙ፤ የኢትዮጵያ ባለውለታ የሆኑ አገር ወዳድ ጀግና እና አዋጊ የጦር መሪ ነበሩ፡፡



ምንጭ፤
  1. "የኢትዮጵያ ታሪክ ከ 1847 እሰከ 1983"  ደራሲ፡- ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ
  2. "የኢትዮጵያ ታሪክ - ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ"  ደራሲ፡- ተክለ ጻድቅ መኩሪያ 1961 ዓ.ም.
  3. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ጎራው - በኦርኬስትራ ኢትዮጵያ   ዩቲውብ