የፋሽስት ኢጣሊያ ጦር በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ወረራ በፈፀመበት ወቀት አቡነ ጴጥሮስ ከ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጋር ተገናኝተው በሰሜን ግንባር ካለው የኢትዮጵያ ጦር ጋር በመሆን ፋሽስት ኢጣሊያ በአይሮፕላን የሙስታርድ ጋስ ቦምብ በሠላማዊው ሕዝብ ላይ በማርከፍከፍ እንስሳቱን፤ የመኖሪያ መንደሮችንና ጫካውን ሳይቀር ፋታ በሌለው ጥቃት ሲያቃጥልና ሲያወድም የነበረውን አሰቃቂ ውርጅብኝ በአይናቸው ተመልክተዋል፡፡
በዚህ አስከፊ የመከራ ወቀት አቡነ ጴጥሮስ ሕዝቡን ሲያስተምሩ ይጠይቁ የነበረው ጥያቄ፤
“ እንዴት እነደኢጣሊያ ያለ የክርስቲያን እምነት የሚከተል ሀገር ኢትዮጵያን በመሰለ ሰላማዊ የክርስቲያን ሀገር ላይ እንደዚህ አይነት አስከፊና አሰቃቂ ሽብር ይፈጽማል? ”
የሚል ነበር፡፡
በዚህም የተነሳ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ፋሽስት ኢጣሊያ በንፁህ ሕዝባቸው ላይ ይፈጽመው የነበረው ኢሰብአዊ የሆነ የጭካኔ ድርጊት በጣም ስላስቆጣቸው በቆራጥነት ተነሳስተው ድርጊቱን በገሀድ በማውገዝ ሕዝቡ እንዳይገዛና በኢጣሊያ ላይ እንዲያምጽ ቅስቀሳ ጀመሩ፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጠቀሰው፤
ለጊዜው በኃጥያት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን መቀበልን መረጠ:: (ወደ ዕብራውያ 11፡25)
በተባለው መሠረት በአቋማቸው ጸንተው ወደ ደበረሊባኖስ በመሄድ በጾምና በጸሎት ቆዩ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብም በእምነቱ ጸንቶ የፋሽስት ኢጣሊያን የግፍ ወረራ እንዲቋቋምና እንዳይተባበረው፣ ያለምንም ፍርሀት እረፍት ሳይሰጠው እንዲፋለመው፣ ይልቁንም እግዚአብሔር አንድ ቀን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ከዚህ የግፍ ወረራ እንደሚታደጋት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እየጠቀሱ በየቦታው እየተዘዋወሩ ሕዝቡ በትግሉ እነዲበረታ ያለማሰለስ ማስተማር ቀጠሉ፡፡
ለናንተም ለወዳጆቸ እላችኋለሁ፤ስጋን የሚገድሉትን በኋላም አንድስ እንኳ የሚበልጥ ሊያደርጉ የማይችሉትን አትፍሩ፡፡ (የሉቃስ ወንጌል 12፡4)
አቡነ ጴጥሮስ በአንድ ወቀት ብድግ ብለው የጵጵስና ማዕረግ ልብሳቸውን ለብሰውና ሰማያዊ ቀለም ባለው ከለሜዳ የተጠቀለለ መስቀላቸውን ይዘው ወደ አዲስ አበባ አቀኑ፡፡
በዚያን ወቅት የአዲስ አበባ ሕዝብ የኢጣሊያ ፋሽስት ጦር በፈጠረው ስጋትና ጭንቀት ውስጥ ወድቆ ነበረ፡፡
አቡነ ጴጥሮስም ብዙም ሳይቆዩ በፋሽስት ወታደሮች ተይዘው እንዲታሰሩና ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተደረገ፡፡ እንደተያዙም ማታውኑ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት (ቀድሞ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የነበረውና የአሀኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) በሚገኘው ጉድጓድ ቤት ውስጥ እንዲታሠሩ ከተደረገ በኋላ ሲመረመሩ፣ ሲገረፉና ሲሰቃዩ አደሩ፡፡
አቡነ ጴጥሮስ በእስር ቤት እያሉ እንዲፈጽሙት የተሰጣቸው የመጨረሻ የማስጠንቀቂያ ጽሁፍ እንዲህ የሚል ነበር፤
የኢጣሊያን ወታደሮች በሕዝቡ ላይ የግፍ ወረራና ሽብር እየፈጠሩ ነው የሚለውን የማነሳሳት ስብከትዎን እንዲያቆሙ፤ የኢጣሊያንን ገዥነት አምነው እንዲቀበሉ፤ በተጨማሪም የኢጣሊያን ጦር ፋታ ሳይሰጡ በየሥፍራው የሚዋጉትን የነፃነት አርበኞች፤ ለኢትዮጵያ ነፃነት የሚዋጉ አርበኞች ሳይሆኑ ‘ሽፍቶች’ መሆናቸውን ለህዝቡ እንዲያሳምኑ፤ይህን የማይፈጽሙ ከሆነ ግን በሞት ይቀጣሉ፡፡
አቡነ ጴጥሮስም የተሰጣቸውን ይህን የማስጠንቀቂያ ጽሁፍ አልቀበለም በማለት ጥያቄ ላቀረቡላቸው የኢጣሊያን የጦር መኮንኖች በአሰተርጓሚ አማካይነት መልስ ሲሰጡ፤
እናንተ ባመጣችሁት የጦር መሣሪያና በነርቭ ጋዝ ህዝቤን በጭካኔ ያለርሕራሔ እየገደላችሁና
እያሰቃያችሁ እያየሁ የናንተን ጥያቄ ህሊናዬ እንዴት ሊቀበለው የሚችል ይመስላችኋል?
እንደዚህ አይነት ወንጀል እየፈፀማችሁስ እያየሁ፤ አላየሁም ብል እግዚአብሔር ፊት እንዴት መቅረብ እችላለሁ?
በማለት ከተናገሩ በኋላ፤ የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ተናገሩ፡፡
ጽድቅን የምታውቁ ሕጌም በልባችሁ ያለ ሕዝብ ሆይ፤ስሙኝ፤ የሰውን ተግዳሮት አትፍሩ፤ በስድባቸውም አትደንግጡ፡፡ እንደልብስም ብል ይበላቸዋል፤ እነደበግ ጠጉርም ትል ይበላቸዋል፤ ጽድቄ ግን ለዘላለም ማዳኔም ለትውልድ ሁሉ ይሆናል፡፡ (ትንቢተ ኢሳይያስ 51፡7-8)
ስለጽድቅ የሚሰደዱ ብፁአን ናቸው፤መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና፡፡ (የማቴዎስ ወንጌል 5፡10)
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስም ፋሽስቶችና ግብረ አበሮቻቸው ያቀረቡላቸውን ጥያቄ ውድቅ ስላደረጉባቸውና ሊያሳምኗቸው ስላልቻሉ በበነጋው ጧት የኢጣሊያ ፋሽስት ባስቸኳይ ባቋቋመው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተደረገ፡፡
ፋሽስቶች ያቋቋሙት ፍርድ ቤትም ወዲያውኑ በሞት እንዲቀጡ ወሰነ፡፡
ይህም ፋሽስቶች የወሰኑት የሞት ፍርድ ዜና በሀገሪቱ በሙሉ ተሰማ፡፡
ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም. አቡነ ጴጥሮስ የሞት ቅጣት ወደሚፈፀምበት ሥፍራ ከተወሰዱ በኋላ የመጨረሻ እስትነፋሳቸው የሆነውን ንግግር እንዲያደርጉ ዕድል ተሰጣቸው፡፡
በሚረሸኑበትም ሥፍራ እንዲቆሙ ከተደረገ በኋላ ከያዙት መስቀል ላይ የተጠቀለለውን ከለሜዳ ካነሱ በኋላ በመስቀላቸው አራቱንም የዓለም ማዕዘናት ባርከው የሚከተለውን ተናገሩ፡፡
የሀገሬ ሕዝቦች ሆይ! ፋሽስቶች አርበኞችን 'ሽፍቶች ናቸው' ቢሏችሁ አትመኗቸው፡፡ አርበኞች ሀገራቸውን ከግፈኛው ፋሽስት ነፃ ለማውጣት በጽናት የሚታገሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ሽፍቶችስ ከሩቅ ሀገር መጥተው ሰላማዊና አቅም በሌለው ኢትዮጵያ ሀገሬ ላይ የግፍ ወረራና ጭፍጨፋ የፈፀሙ እነዚህ በእናንተና በእኔ ፊት ቆመው የምታይዋቸው የፋሽስት ወታደሮች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የፋሽስት ጦር ለሚፈጽመው የግፍ ወረራ እንዳይንበረከክ እግዚአብሔር ፅናቱንና ብርታቱን ይስጠው፡፡ የኢትዮጵያ ምድርም በፋሽስት ወራሪ ጦር እንዳይገዛ አውግዣለሁ!
በማለት ንግግራቸውን ጨረሱ፡፡
ስምንት ወታደሮች በስተጀርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተንጠቀቅ ቆሙ። ወዲያው የፋሽስት ገዳይ ቡድኑ አዛዥ «ተኩስ» በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም የፋሽስት ወታደሮች በአንድላይ በአቡኑ ላይ የጥይት እሩምታ አዘነቡባቸው፡፡ መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ።
ወዲያውኑ አቡነ ጴጥሮስን በጥይት ደብድቦ ለመግደል የተመደቡት ፋሽስት ያሰለጠናቸው የሰሜን ባንዳዎች ወንድሞቻችን በድጋሚ ተኩስ ከፍተው ብዙ ጥይቶችን በሰማዕቱ ላይ በማርከፍከፍ ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም.በተወለዱ በ 53 ዓመት ዕድሜያቸው የግፍ ግድያ ተፈጽሞባቸው በሰማዕትነት ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡
ይህ በሰማዕቱ ላይ የተፈጸመው የግፍ ግድያ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለሀገሩ ነፃነት በቁጭትና በቆራጥነት ይበልጥ እንዲታገልና ለፋሽስት ጦር በፍጹም እንዳይንበረከክ ጉልበትና ብርታት ስለሰጠው ፀረ ፋሽስት ትግሉ እየተጋጋለ ሄደ እንጅ ፈጽሞ አልበረደም፡፡
ቅዱስ አቡነ ጴጥሮስ ለሀገራቸው ነፃነት ሲሉ ያሳዩትን ፅናት፣ ቆራጥነት፣ ተጋድሎና የከፈሉትን ቅዱስ መስዋዕትነት
ለመዘከርና እነዲሁም መጭው የኢትዮጵያ ትውልድ ፈለጋቸውን በመከተል፤ የሀገሩን ነፃነትና አንድነት ለድርድር ሳያቀርብ እንዲጠብቃት ለማስተማር ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቅዱስ ሰማዕቱ በተሰዉበት ሥፍራ ላይ የመታሰቢያ ሐውልት አቁመውላቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስም፤ “አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕት ጻድቅ ዘኢትዮጵያ” በማለት አጽድቆ ሠይሟቸል፡፡