Content-Language: am ዘርዓይ ድረስ
header image




ዘርዓይ ድረስ




የአገር ወዳዱ የዘርዓይ ድረስ
የሕይወትና የጀግንነት ታሪክ















1. ትውልድና ዕድገት

Zerai Deres
አገር ወዳዱ ዘርዓይ ድረስ
ዘርዓይ ድረስ በፋሽስት ኢጣሊያ በቅኝ ግዛት ተይዛ በነበረችው ኤርትራ ምድር በሠራዬ አውራጃ ተወለደ፡፡ የተወለደበትም ዓመት በ 1908 ዓ.ም. እንደሆነ ፀሐፊያን ዘግበዋል፡፡
በሁለት ዓመት ዕድሜው አባቱ በሞት ሲለዩ የእናቱ የትውልድ ቦታ ወደሆነችው ሀዝጋ ወደ ተባለች አነስተኛ መንደር ከቤተሰቡ ጋር ተጓዘ፡፡
ዘርዓይ ድረስ በወጣትነቱ የቅኝ ገዥዎች ሐይማኖት የሆነውን የካቶሊክ ሐይማኖት በመቀበል የጣሊያኖች ትምህርት ቤት ገብቶ የሐይማኖቱን ትምህርት በመከታተል ላይ ሳለ የኢጣሊያንኛ ቋንቋም እየተማረ በደንብ መናገር ቻለ፡፡
ዘርዓይ ድረስ የሐይማኖቱን ትምህርት አቋርጦ በኤርትራ ድንበር ላይ ወደምትገኘው ራማ ወደተባለችው የትግራይ ከተማ በመጓዝ የኢጣሊያንኛ ቋንቋ አስተርጓሚ ሆኖ ተቀጠረ፡፡
ዘርዓይ ድረስ፤ መስከረም 26 ቀን 1929 ዓ.ም. ኩሪየር ኤርትሮ በተሰኘው የኢጣሊያ ዕለታዊ ጋዜጣ ላይ እንዲታተምለት ልኮ ጋዜጣው ያወጣው ጽሁፍ ላይ፤
“...የአገሬው ነዋሪወች ለእናንተ በጣም የሚያፀይፏችሁ ሆነው እንደ እቃ የምትቆጥሯቸው ቢሆኑ እንኳ፤ እነሱ ግን ክብር ያለቸው ፍጡሮች ናቸው፡፡
...በሊቢያ፣ በሶማሊያና በሌሎችም ለአገራቸው ነፃነት የሚታገሉ፤ ለእናንተ እንደጋሻ መከታ በመሆንና ሕይወታቸውንም ጭምር እስከመገበር ደርሰዋል፡፡
...ለኢጣሊያ ሲባል የተከናወኑ የብዙ የጀግንነት ድርጊቶች በተሳሳተ መንገድ የተተረጎሙና የኢምፔሪያሊዝም ሀሳብ አመላካቾች ናቸው፡፡”

በማለት፤ የፀረ ፋሽስት እና ፀረ ቅኝ ግዛት አቋም የነበረው ዘርአይ፤ በጋዜጣ በግልጽ ባወጣው ጽሁፉ ላይ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡

የኢጣሊያ ፋሽስት ወታደሮች በአዲስ አበባ ንፁሀን ነዋሪዎች ላይ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ሦስት ቀን ሙሉ መደዳደውን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ባደረጉበት ወቅት፤ ቁጥራቸው 400 የሚጠጋ የአማራ መኳንንቶችን እና ምሁራንን በኢጣሊያ ሀገር አሲናራ በተባለው ደሴት ውስጥ በሚገኘው እሥር ቤት ውስጥ አጓጉዞ አስሯቸው ነበር፡፡

2. የዘርዓይ ድረስ ወደ ኢጣሊያ መጓዝ

Zerai Deres
ዘርዓይ ከካቶሊክ ሚሲዮናዊያን ጋር
በ19 ዓመት እድሜው የተነሳው ፎቶ
(ከግራ ወደ ቀኝ አራተኛው 4 ቁጥር የለበሰው)
በዚያን ጊዜ የኢጣሊያ ቅኝ ግዛቶችን የሚያስተዳድረው መሥሪያ ቤት ሠራተኞችን ሲቀጥር፤ ዘርዓይ ድረስም ወደ ኢጣሊያ እሥር ቤት ለተጓዙት እስረኞች አስተርጓሚ እንዲሆን በ23 ዓመት እድሜው ተቀጥሮ ወደ ኢጣሊያ ተጓዘ፡፡
ዘርዓይ ድረስ ሮም በሚኖርበት ወቅት፤ ከኢትዮጵያ የሚላከው ዜና በኢጣሊያ ጋዜጦች ላይ በየጊዜው የሚወጡትን ጽሁፎች ሲመለከት ልቡ በሐዘን ተሰብሮ ተስፋ በመቁረጥ የሚፈጠረውን ነገር ሁሉ ለታሰሩት ለኢትዮጵያ መኳንንቶችና በላባቶች ወደ አማርኛ ቋንቋ ይተረጉምላቸው ነበር፡፡

ስለ የይሁዳ አንበሳ ሐውልት

በለገሐር ባቡር ጣቢያ ፊት
ለፊት በሚገኘው አደባባይ ላይ
የቆመው የይሁዳ አንበሳ ሐውልት
በዚያን ወቅት የኢትዮጵያ ነገሥታት ከተጠቀሙባቸው የማዕረግ ስሞች አንዱ “የይሁዳ አንበሳ” ነው።
ይህ የማዕረግ ስም፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተጠቀሰው ንግሥት ሳባ ንጉሥ ሰሎሞንን ከጐበኘችበት ዘመን ይጀምራል፡፡
የይሁዳ አንበሳ የንጉሠ ነገሥቱን ማንነት ከማመልከቱም በላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምልክትም ነው ተብሎ ይታመናል።
የይሁዳ አንበሳ ሐውልት፤ በወርቅና በነሐስ የተሠራ ሐውልት ሲሆን፤ በዳግማዊ ምኒልክ፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ በንግሥት ዘውዲቱና በልዑል ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል ምስሎች ያጌጠና በጥቁር ግራናይት በተሠራ ምሰሶ ላይ የቆመ ድንቅ ሐውልት ነው፡፡
ሐውልቱ የቆመው በአዲስ አበባ ለገሐር ባቡር ጣቢያ ፊት ለፊት በሚገኘው አደባባይ ላይ ነበር፡፡
ሐውልቱ የተቀረፀው በ1922 ዓ.ም. በፈረንሣዊው ቅርፃ ቅርፅ ባለሙያ ጆርጅ ጋርዴት ሲሆን፤ የተሰራውም ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም. ለሚከበረው ለለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የዘውድ ሥርዓተ ንግሥን ምክንያት በማድረግ ነው፡፡
ኢጣሊያ በዶጋሊ ጦርነት ለወደቁት የፋሽስት ወታደሮቻቸው
በብሔራዊ ሙዚየም የሚገኘው በወርቅ ቅብ
ነሐስ የተሠራው የይሁዳ አንበሳ
መታሰቢያ እነዲሆናቸው በማሰብ፤ ይህን የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የይሁዳ አንበሳ ዓርማ የሆነውን ወርቃማ ሐውልት ነቅለው በምርኮ መልክ ወደ አገራቸው በመውሰድ በሮም ኤዜድራ በተባለው አደባባይ ላይ የኢጣሊያ ባንዲራ ተሰቅሎበት ከእነርሱ ሐውልት ስር አቁመውት ነበር፡፡
በንጉሠ ነገሥቱ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ባደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ተወስዶ የነበረውም ሐውልት በ1952 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ የዘራይ ድረስን የአርበኝነት ስሜት ለማስተወስ ሲሉ ንጉሠ ነገሥቱ ወታደራዊ ዩኒፎርም ለብሰው በሐውልቱ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ነበር፡፡

3. ዘርዓይ ድረስ በሮም አደባባይ የወሰደው እርመጃ

ዘርዓይ ወደ አገሩ ለመመለስ ባሰበበት ሰሞን፤ ሰኔ 7 ቀን 1930 ዓ.ም. በሮም ዲፒያመንት አደባባይ በዶጋኣሊ ጦርነት ያለቁትን የፋሽስት ወታደሮቻቸውን ለመዘከር የኢጣሊያ ባለሥልጣናትና ሕዝቡ ተሰብስበው ነበር፡፡
ወጣቱ ዘርአይም ለኢጣሊያ ንጉሥና ለሙሶሎኒ ገፀ በረከት የሚሆን ጎራዴ ከአንድ ትልቅ ኢትዮጵያዊ መኮንን ተቀብሎ እንዲያመጣ ይላካል፡፡
ወጣቱ ዘርአይም ከተቀበለው ጎራዴ ላይ የተጻፈውን ጽሁፍ አንብቦ እንደተረዳው፤ ጎራዴው የራስ አሉላ አባ ነጋ እንደነበር ተገነዘበ፡፡
የ22 ዓመት ወጣቱ ዘርአይ ድረስ፤ ጎራዴውን በእጁ እንደያዘ አደባባይ ከደረሰ በኋላ ኢጣሊያኖች በይሁዳ አንበሳ ሐውልት ላይ ሲሳለቁና ሲዘባበቱ ተመለከተ፡፡
Zerai Deres
ጣሊያኖች ከአዲስ አበባ በምርኮ መልክ
ወደ ሮም በመውሰድ በዶጋኣሊ ጦርነት
ለወደቁት ወታደሮቻቸው ማስታወሻ በሮም
አደባባይ የቆመው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት
የይሁዳ አንበሳ ዓርማ የሆነው ሐውልት
በዚህን ጊዜ ነው ዘርአይ ድረስ ወዲያውኑ የኢጣሊያንን አገዛዝ በማውገዝና የኢትዮጵያን ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን በማወደስ የያዘውን ጎራዴ በንዴት አንስቶ በአንድ የኢጣሊያ የጦር መኮንን ላይ ያሳረፈበት፡፡
ወዲያውኑ አደባባዩ በጩኸትና በሁከት ተሞላ፡፡
የ20ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ በሚለው መጽሐፍ ላይ እንደተጠቀሰው፤ ዘርአይ ድረስ ድርጊቱን እንደፈፀመ ወዲያውኑ ቀረርቶና ሽለላ ማሰማቱን ዘግቦታል፡፡
ዘርዓይን ከድርጊቱ ለማስቆም የሞከሩትን ሌሎች አምስት የኢጣሊያ መኮንኖችንም በያዘው ጎራዴ ቀቷቸዋል፡፡
አከታትለውም ሌሎች የኢጣሊያ መኮንኖች ደርሰው ዘርዓይ ድረስ ላይ አራት ጥይት ተኩሰው ጭኑ ላይ አቆሰሉት፡፡
የዘርአይ ድረስን ድርጊት የሰማው ቤኒቶ ሙሶሎኒ፤ ወደ ሮም አምጥተው ያሰሯቸውን የኢትዮጵያ መኳንንቶችና ባላባቶች በሙሉ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ወሰነ፡፡
ይሁን እንጅ ከታሰሩት መኳንንቶች መካከል የዘርዓይን ድርጊት አነሳስተዋል ተብለው የተጠረጠሩት፤ ልዑል ራስ ሥዩም መንገሻ፤ ራስ ከበደ መንገሻ፣ ራስ ሙሉጌታ ይገዙና ደጃዝማች አስራት ሙሉጌታ ወደ አገራቸው ከመመለስ ይልቅ ወደ ሊቢያ ተወስደው የፋሽስት ኢጣሊያ የማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ማሰሩ ይሻላል የማለት ፍላጎት አደረባቸው፡፡
ዘርዓይ ድረስ የፈፀመው ድርጊት በኢጣሊያ ባለሥልጣናት ዘንድ እንደ አእምሮ ሕመም በመቆጠሩ የሲሲሊ አውራጃ ወደሆነው ወደ ባርሴሎና ፖዞ ዲ ጎቶ ወደተሰኘ የወንጀለኞች ማሪፊያ ተይዞ ተወሰደ፡፡
በቆይታውም ወቅት ዘርአይ ምንም ዓይነት የአእምሮ ሕመም እንደሌለበት ቢናገርም የጣሊያን ዶክተሮችን ማሳመን አልቻለም፡፡
በዚህም ምክንያት ዘርዓይ ድረስ ታስሮ እንዲታከም ወደ ኢጣሊያ ሲስሊ ወደብ ወደሚገኝ ወረዳ ተልኮ ማንም አጋዥና ረዳት በሌለበት ለ7 ዓመታት ታስሮ ተሰቃይቷል፡፡
በቆይታውም ወቅት ዘርአይ ጽፎ የተዋቸው መጣጥፎች እንደሚያመለክቱት፤ ምንም ዓይነት የአእምሮ ሕመም እንደሌለበት ለጣሊያን ዶክተሮች ለማስረዳት ቢሞክርም ማሳመን እንዳልቻለ ይገልጻሉ፡፡
ዘርአይ ድረስ ጤንነቱ ደህና መሆኑን ለቤተሰቦቹ ደብዳቤ ጽፏል፡፡ ለወንድሙ ለተስፋጽዮንም ጭምር በመጻፍ የኢጣሊያ መንግሥት የሰጠውን ማዕረግ እንዲያስወግደው ነግሮት ነበር፡፡
የዘርዓይ ድረስ ወንድም ተስፋጽዮን ወንድሙ በሕይዎት ያለ መስሎት፤ ንጉሠ ነገሥቱ አይሮፕላን ወደ ኢጣሊያ ልከው ዘርዓይ ድረስን ወደ አገሩ እነዲመልሱት ለመማጸን ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ዘርዓይ ድረስ በጥይት ሲመታ የተናገረውን ሲጠቅስ፤
“…አሁን ደሜ እየፈሰሰ ነው፡፡ ነገር ግን በሰማይ ላይ ወጥቶ ይጮሀል፡፡ በኋላ እግዚአብሔር እና ንጉሤ (የአገሬ ንጉሥ) ይረዱኛል፡፡ …ለግሞች ጣሊያኖች ዶጋሊ ላይ ለሞቱት ወንድሞቻችሁ አሁን ሐውልት ጨምሩላቸው፡፡”
በማለት ገልጾታል፡፡
ተስፋጽዮን የወንድሙን ጉዳይ ለንጉሠ ነገሥቱ እንዲቀርብለት በማሰብ በወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ለነበሩት ለአቶ አምባዬ ወልደማሪያም ቢያመለክትም ሊሳካለት አልቻለም፡፡
ተስፋጽዮን በሐምሌ ወር 1931 ዓ.ም. ወንድሙን ዘርአይ ድረስን ከእስር ነፃ ለማውጣት ወደ ሲሲሊ ተጉዞ ነበር፡፡ ነገር ግን ወንድሙን ማስፈታት ሳይችል ቀረ፡፡
Zerai Deres
ባልታወቀ ሰው የተሳለ
የዘርዓይ ድረስን ጀግንነት የሚያሳይ
አገር ወዳዱና ቆራጡ ጀግና ወጣት ዘርአይ ድረስ ከ7 አመታት የእስር ቤት ቆይታ በኋላ ሰኔ 23 ቀን 1937 ዓ.ም. ገና በለጋ እድሜው በተወለደ በ31 ዓመቱ በሚያሳዝን ሁኔታ ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል፡፡

ወንድሙ መሞቱን የሰማውም ተስፋጽዮን፤ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ አስክሬኑን ይዞ ወደ ኤርትራ ለመመለስ ችሏል።

በመጨረሻም የጀግናው ዘርአይ ድረስ አስከሬን በሐዘጋ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በክብር የተቀበረ ሲሆን፤ ከመቃብሩም ፊት ለፊት የአርበኛውን ምስል ከሁለት አንበሶች ጋር የሚያሳይ መታሰቢያ ሐውልት እንዲቆምለት ተደርጓል።

ዘርዓይ ድረስ ለፈፀመው አኩሪ ገድል፤፤ በኤርትራና በኢትዮጵያ ባለው ትውልደ ሁሉ ሲታወስ የሚኖር ነው።
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፤ ለዘርዓይ ድረስ መታሰቢያ እንድትሆን የመጀመሪያዋ የጦር መርከብ በስሙ እንድትሰየም ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡






ምንጭ፤
  1. ምስጋና ለ፤  sewasew.com
  2. ከውኪፒዲያ የተተረጎመ
  3. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ጎራው - በኦርኬስትራ ኢትዮጵያ   ዩቲውብ