Content-Language: am የውስጥ አርበኛዋ ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ
header image




የውስጥ አርበኛዋ ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ



የውስጥ አርበኛዋ የወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ የሕይወትና የአርበኝነት ዘመን ታሪክ
በእያንዳንዱ አርዕስት ሥር የሚገኘውን የድምጽ ማጫወቻ በመጠቀም
ትረካውን ማዳመጥ ይችላሉ

ክፍል አንድ


ትውልድ፣ ዕድገት፣ የትዳር
ሕይወትና የአርበኝነት ተግባር

ክፍል ሁለት


የሸዋረገድ ገድሌ በተደጋጋሚ መታሰር፣ ወደ ኢጣሊያ
እስር ቤት መወሰድና ወደ ሀገራቸው መመለስ

ክፍል ሦስት


የጀልዱ የጠላት ምሽግ መሰበር፣ የአዲስ ዓለም
ምሽግ ሰበራ እቅድና የአዲስ ዓለም ምሽግ ኦፐሬሽን

የመጨረሻ ክፍል


የአዲስ ዓለም የምሽግ ሰበራ
ውጤቱና የሸዋረገድ ገድሌ ህልፈተ ሕይወት

በየአርዕሰቱ የተገለፀውን ጽሁፍ ለማንበብ ይህን ማውጫ መጠቀም ይችላሉ

1. ትውልድ፤ ዕድገትና
የትዳር ሕይዎት
2. የሸዋረገድ ግልጽ
የአደባባይ ተቃውሞ
3. የሸዋረገድ ገድሌ
የአርበኝነት ተግባር
4. የሸዋረገድ ገድሌ
በተደጋጋሚ ስለመታሰር
5. ሸዋረገድ ወደ
ኢጣሊያ መወሰድ
6. ከኢጣሊያ
ወደ ሀገራቸው መመለስ
8. 7. የጀልዱ የጠላት
ምሽግ መሰበር
የአዲሰ ዓለምን ምሽግ
ለመስበር የተነደፈው እቅድ
9. የአዲስ ዓለም የምሽግ
ሰበራ ኦፐሬሽን
10. የአዲስ ዓለም የምሽግ
ሰበራና ውጤት
11. የሸዋረገድ ገድሌ
ሕልፈተ ሕይዎት

1. ትውልድ፤ ዕድገት እና የትዳር ሕይዎት


Shewareged gedle
ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ
የውስጥ አርበኛዋ ሸዋረገድ ገድሌ ከአዲስ አበባ በሰተሰሜን 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በተሪካዊቷ ደብረ ብርሃን ከተማ በ1878 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡
ወላጅ አባታቸው ፊታውራሪ ገድሌ በዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት እንደማደጋቸው መጠን ስለ መንግሥታዊ አስተዳደር ጠንቅቀው የሚያውቁ ሀብታም እንደነበሩ ይነገራል፡፡
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፤ ‘ሸዋ’ ብለው ይጠሯቸው የነበሩት ሸዋረገድ ገድሌ፤ በሕፃንነታቸው አማርኛ ትምህርትን እየተማሩ፤ በተጨማሪም ጎን ለጎን የቤት አስተዳደርን ትምህርት እየቀሰሙ አደጉ፡፡
አባታቸው ፊታውራሪ ገድሌ፤ ልጃቸውን ለማግባት ጥያቄ ሲቀርብላቸው ለፊታውራሪ ደቦጭ ሊድሩላቸው ወሰኑ፡፡ ከአባታቸው ትእዛዝ መውጣት ያልፈለጉት ሸዋረገድ፤ የአባታቸውን ትእዛዝ በመቀበል ጋብቻውን ፈጸሙ፡፡
ሁለቱም ጥንዶች በፍቅር አብረው ከኖሩ በኋላ ባለቤታቸው በድንገት ታመው ይህን ዓለም በሞት ተሰናበቱ፡፡
ወይዘሮ ሸዋረገድ በባለቤታቸው ሞት ምክንያት ልባቸው በሐዘን በመጎዳቱ ወደ መንፈሳዊው ሕይወት በማዘንበል ወደ ገዳም ገብተው ነበር፡፡ ሆኖም አባታቸው ከገዳም አውጥተው ይዘዋቸው ተመለሱ፡፡

ከሴት አርበኛዋ ሸዋረገድ ገድሌ የሕይዎት ምእራፍ ውስጥ ትልቁን ሥፍራ የሚይዘው የአርበኝነት ተጋድሎ የተጀመረው፤ የወጣትነት እድሜያቸው አልፎ በ52 ዓመት እድሜያቸው ነበር፡፡

2. የሸዋረገድ ግልጽ የአደባባይ ተቃውሞ


Shewareged gedle
በሁለተኛው የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት በክተት አዋጅ ወደ ሰሜን ግንባር ሲዘምት፤ ሸዋረገድ ገድሌ እና መሰሎቻቸው ከካኪ የተሠራ ልብስ ለብሰው፣ ወገባቸውን በወታደር ቀበቶ ታጥቀውና ሽጉጣቸውን በወገባቸው ሻጥ አርገው፤ እኔም ሴቲቷ ከወንዶች እኩል እዘምታለሁ በማለት እየሸለሉና እየፎከሩ የሠራዊቱን ሞራል ያነቃቁት ነበር፡፡
በክብር ከፍ ብሎ ሲውለበለብ የነበረው የሀገራቸው ሠንደቅ ዓላማ ልክ ቆሻሻ እንደነካው እንደተራ እራፊ ጨርቅ ተቆጥሮ በፋሽስት ወታደሮች እግር ሲረገጥ የተመለከቱት ሸዋረገድ፤ ድርጊቱ እጅግ ያሳዘናቸውና ቁጭት ውስጥ ያስገባቸው ተግባር ነበር፡፡
ይህን አሳፋሪ ተግባር አይተው እንዳላዩ ማለፍ ያልቻሉት ሸዋረገድ ገድሌ፤ በእምቢተኝነትና በድፍረት ተነሳስተው፤ በፋሽስት ወታደሮች ፊት ተቃውሟቸውን ለማሰማት፤ በአዲስ አበባ አደባባይ ላይ ወጥተው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በግልጽ መቃወም ጀመሩ፡፡
በወቅቱ፤ የፋሽስት ጥቁር ሸሚዝ ለባሽ ወታደሮች በተሰማሩበት በአዲስ አበባ ከተማ ይቅርና፤ በቤቱ ውስጥ እንኳን የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ወይም የአርበኞችን ፎቶግራፍ ደብቆ የተገኘ ሰው ከባድ ቅጣት እንደሚደርስበት ይታወቅ ስለነበረ፤ ሸዋረገድ ገድሌ ያሳዩት የአደባባይ ግልጽ ተቃውሞ፤ የፋሽስት ወታደሮችን ያስቆጣ ተግባር ነበር፡፡
ፋሽስቶች የሸዋረገድ ገድሌን ተግባር ሲመለከቱ ዝም ብለው አላለፏቸውም፡፡ ወዲያውኑ ለፈፀሙት ጥፋት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ከአአደረጓቸው በኋላ በጨካኝ የፋሽስት ሹማምንቶች ፊት አቀረቧቸው፡፡
ሸዋረገድም የፋሽስት ሹማምንቶች ፊት ከቀረቡ በኋላ፤ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ የአላትን ክብርና ሞገስ ያለምንም ፍርሀት ለፋሽስት ሹማምንቶች ማብራራት ጀመሩ፡፡
ይህ በፋሽስት ሹማምንቶች ፊት ለፊት ቀርበው የፈጸሙት የሸዋረገድ ጥፋት የሞት ቅጣት የሚያሰጥ ቢሆንም ቅሉ በጥቂት አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ልመናና ተማጽኖ የሞት ፍርዱ ወደ እስር እንዲለወጥላቸው ተደረገ፡፡
በርካታ ኢትዮጵያውያን ሰለፋሽስት ዓላማና ምንነት አምብዛም ያላወቁና ግንዛቤ እንደሌላቸው የተረዱት ሸዋረገድ፤ ጠላትን በምን አይነት መንገድ እነደሚያጠቁ አውጥተውና አውርደው ስልት ቀየሱ፡፡

3. የሸዋረገድ ገድሌ የአርበኝነት ተግባር

ጠላት በመላ ሀገሪቱ በዘረጋቸው መዋቅሮች ውስጥ ሠርገው ከገቡ እትዮጵያውያን ዘንድ የነጠረ መረጃ እያነፈነፉ በዱር በገደል ተሰማርቶ ጠላትን ለሚፋለመው የወገን ጦር መረጃ ለማቀበል ሸዋረገድ ገድሌ ቆርጠው ተነሱ፡፡
በአዲስ አበባ ዙሪያ ላደፈጡት አርበኞች መረጃውን በሚስጥር ለማድረስ ልክ እንደ እንቁላል ነጋዴ ጭድ በተነሰነሰበት ቅርጫት ውስጥ የደብዳቤ መልእክቱን ደብቀው ዘወትር ያመላልሱ ነበር፡፡
ከእለታት አንድ ቀን እነዚህን የሚስጥር ደብዳቤ ደብቀው በተለመደው መንገድ አሽከሮቻቸው እንዲያደርሱላው መልዕክት አስተላልፈው ኖሮ፤ አሽከሩም መልእክቱን ይዞ አርበኞች ወደአሉበት ስፍራ ተጓዘ፡፡
መልእክተኛው መንገዱን እያጋመሰ ሳለ የፋሽስት ወታደሮች ወደ እርሱ አቅጣጫ እየመጡ እንደሆነ አስተዋለ፡፡ መልእክተኛውም የያዘው ሚስጥር በጠላት እጅ እንዳይገባ በማሰብ ደብዳቤውን በጥርሱ እንደእህል አላምጦ ከዋጠው በኋላ ወደመጣበት ሰፈር ተመለሰ፡፡
መልእክተኛው ሸዋረገድ ገድሌ ያሉበት ሰፈር እንደደረሰም በእርግጥ መልእክቱ በጠላት እጅ እንዳልገባ ለማረጋገጥ መልእክተኛውን ኮሶ በጥብጠው ካጠጡት በኋላ የመልእክተኛው ድርጊት ትክክል መሆኑን ማረጋገጣቸው ተዘግቧል፡፡

4. የሸዋረገድ ገድሌ በተደጋጋሚ ስለመታሰር


Dejazmach Gebre Mariam Gari
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በአብርሃም ደቦጭና በሞገስ አስገዶም ድፍረት በተሞላበት ግራዚያኒን ለመግደል በተቃጣው እርምጃ የተነሳ በፋሽስት ወታደሮች በአዲስ አበባ ነዋሪ ላይ የተወሰደው የጅምላ ጭፍጨፋና ግድያ ወቅት ሸዋረገድ ገድሌ በድጋሚ በቁጥጥር ስር ውለው ወደ እስር ቤት ተወረወሩ፡፡
የፋሽስት ወታደሮችም ሸዋረገድን በኤሌክትሪክ ገመድ ያለርሕራሔ ሰውነታቸው እስኪቆስል ድረስ በመግረፍ የግድያ ሙከራው እንዴትና በማን እንደተፈፀመ እንዲናገሩ ጠየቋቸው፡፡
ይሁን እንጅ ሸዋረገድ የሚፈጸምባቸውን ድብደባ መቋቋም እማይችሉበት ደረጃ ሲደርሱ እራሳቸውን ስተው መሬት ላይ ወደቁ፡፡ አራሳቸውን ከሳቱበት ሰመመን ከነቁ በኋላ ለአንድ ሳምንት ያህል በመኖሪያ ቤታቸው እንዲቆዩ ተደረገ፡፡
ከዚያ በኋላ አምቢተኛዋ ሸዋረገድ እንደገና ለሶስተኛ ጊዜ ወደተዘጋ እስር ቤት ተወረወሩ፡፡
ይሁን እንጅ ፋሽስቶች የሚፈጽሙት ግፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመሄዱ ይህንኑ የጠላት ተግባር በመቃወም በታሰሩበት ስፍራ ከአንድ ሳምንት በላይ የረሀብ አድማ አድርገዋል፡፡

5. ሸዋረገድ ወደ ኢጣሊያ ተወስደው ስለመታሰር


Dejazmach Gebre Mariam Gari
እምቢተኛዋን የሸዋረገድ ገድሌን ፀባይ የተረዱት ጣሊያኖች፤ ቁጥራቸው 400 ከሚደርሱ ከሌሎች የኢትዮጵያ ምሁራንና መኳንንቶች ጋር ወደ ኢጣሊያ ሀገር በመውሰድ በአሲናራ ደሴት በሚገኘው እስር ቤት ውስጥ እንዲታሰሩ አደረጉ፡፡
በዚህ አሰከፊ በሆነ እስር ቤት ውስጥ በርካታ ንጹሀን ኢትዮጵያውያን በሕክምና እጦትና በእስር ቤት በሚደርስባቸው ስቃይ የተነሳ ሕይታቸው እያለፈ እዚያው የተቀበሩ ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል፡፡
በአሲናራ ደሴት ከታሰሩት ቁጥራቸው ከ30 በላይ ከሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ሴቶች መካከል፤ የከንቲባ ገብሩ ደስታ ልጆች ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ እና ወይዘሮ ደስታ ገብሩ (እማሆይ ፅጌማሪያም ገብሩ) ይገኙበታል፡፡

(የታዋቂው ዲፕሎማት፣ የመጀመርያው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት እና የመጀመርያው የጎንደር ከተማ አስተዳዳሪ የነበሩት የክቡር ከንቲባ ገብሩ ልጅ የሆኑት ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ፤ የመጀመሪያዋ ሴት የፓርላማ ተመራጭና ፀሐፊ ተውኔት ሲሆኑ፤ በተጨማሪም ላበረከቷቸው አስተዋጽዖዎች፤ የወርቅ ሜዳሊያ፣ የንግሥት ሣባ የወርቅ ኒሻን፣ የቀይ መስቀል የወርቅ ሜዳሊያ እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ያገኙ ታላቅ ሴት ነበሩ፡፡) ...የበለጠ ለማንበብ  ethioreference.com


6. ከጣሊያን ሀገር ወደ ሀገራቸው መመለስ


ሸዋረገድ ገድሌ እድለኛ ሆነው ከታሰሩበት እስር ቤት ለአንድ ዓመት ከሶሰት ወር ያህል ታስረው ወደ ሀገራቸው መመለስ ችለዋል፡፡
ሸዋረገድ ወደ አገራቸው እንደተመለሱም የአባታቸውን ንብረት በመሸጥ የጦር መሳሪያ እየገዙ በድብቅ አርበኛውን ማስታጠቅ ከመጀመራቸውም ባሻገር ቀደም ሲል የጠላትን እቅድ እየሰለሉ ለወገን ጦር በሚስጥር መልእክት የማቀበሉን ተግባር ቀጠሉበት፡፡
የንጉሠ ነገሥቱን ወደ ሀገር መመለስ ወሬ የሰሙ አርበኞችም በየስፍራው ያለውን ጠላት በሽምቅ ውጊያ መግቢያ መውጫ ማሳጣቱን አፋፍመው ቀጠሉበት፡፡

7.የጀልዱ የጠላት ምሽግ መሰበር


የጀልዱ ምሽግ በሜጫና ጅባት አውራጃ ከሚገኙት የፋሽስት ኢጣሊያ ምሽጎች መካከል በአሰራሩም ሆነ በአቀማመጡ ጠንካራ የመከላከያ ምሽግ እንደነበረ ይነገራል፡፡
ሚያዝያ 8 ቀን 1932 ዓ.ም. ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ሲሆን በምሽጉ የነበሩት የፋሽስት ወታደሮች ተሰባስበው እራት በመብላት ላይ ነበሩ፡፡
ጀግኒት ሸዋረገድ ገድሌ፤ የጦር መሀንዲስ ከሆኑት ከባላምባራስ ዘውዴ ጥላሁን (በኋላ ደጃዝማች)፣ ከአቶ ሰለሞን ውብሸት፣ ከአቶ ጌራ መድሐኒት፣ ከአቶ ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ከአቶ ስነ ውብሸት፣ ከሻምበል ሹምየ ደበሳይ እና ከመቶ አለቃ ተስፋየ ግዛው እና በድምሩ 14 ከሚደርሱ ከሌሎች ጀግኖች ጋር በመሆን በተጠቀሰው ቀንና ሰዓት በምሽጉ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሲያደርሱ ጠላት እራሱን ለመከላከል ባለመቻሉ፤ በምሽጉ ውስጥ የነበሩትን የፋሽስት ወታደሮች በሙሉ ገድለው 400 ባንዳዎችን ማርከዋል፡፡
በዚህ የምሽግ ሰበራ ወቅት 700 ጠመንጃዎችን፣ 2 ከባድ መትረየሶችን፣ 18 ሳጥን የእጅ ቦምቦችን እና በርካታ ጥይቶችን ከማረኩ በኋላ ምሽጉን በእሳት ሙሉ በሙሉ አቃጥለውታል፡፡
አርበኞቹ፤ ሚያዝያ 11 ቀን 1932 ዓ.ም. በተቃጠለው ምሽግ አጠገብ ሆነው የማረኩትን የጦር መሣሪያ ለባላገሩ ሕዝብ ካከፋፈሉ በኋላ አቅራቢያቸው ወደአለው ጥቅጥቅ ወደአለው ጫካ ውስጥ በፍጥነት ሄደው ተደበቁ፡፡
በርካታ ቁጠር ያለው የጠላት ጦርም አርበኞችን አድኖ ለመያዝ ከያለበት ተሰባስቦ ቢመጣም ጀግኖች አርበኞች ግራና ቀኙን በመድፍ ተኩስ ጠላት ላይ የጥይት ናዳ ስላወረዱበት የፋሽስት ወታደር በየቦታው ተበታተነ፡፡
የጀልዱ ምሽግ ከወደመ በኋላም፤ የክረምቱ ወራት እስኪያልፍ ድረስ አርበኞቹ ሜጫ ጋጂ ዮብዶ ከሚባሉ ጫካዎች ውስጥ ተደብቀው የቆዩ ሲሆን፤ እነዚህም አገሮች የነልጅ ጃገማ ኬሎ አገር በመሆኑ በስንቅ በኩል ችግር ሳያጋጥማቸው ቆዩ፡፡

8. የአዲሰ ዓለምን የጠላት ምሽግ ለመስበር የተነደፈው እቅድ


Dejazmach Gebre Mariam Gari
ልጅ ጃገማ ኬሎ በአርበኝነት ዘመኑ ከፈጸማቸው አኩሪ ገድሎች መካከል የፋሺስት ጦር ይመካበት የነበረው የአዲስ ዓለም ምሽግ ሰበራ ፈፅሞ የሚዘነጋ አይደለም።
ጃገማ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪን ለመርዳት ወደ ወሊሶ ሄዶ በነበረበት ወቅት፤
“…ጃገማ፤ ያን የተመካከርንበትን ጉዳይ ጨርሻለሁና ዛሬ ነገ ሳትል ሰራዊትህን ይዘህ ቶሎ ና፡፡ …”
የሚል መልዕክት ከስመ ጥሩዋ የውስጥ አርበኛ ከወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ ደረሰው።
በሌላም በኩል የአዲሰ ዓለምን ምሽግ ለመስበር ባላምባራስ ዘውዴ ጥላሁንም እቅድ ስለነበራቸው በሚኖሩበት ሀገር ያሉትን ታላላቅ ሰዎች አማክረው ፈቃደኛ ሆነው መገኘታቸውን ካረጋገጡ በኋላ ወደ ሸዋረገድ ገድሌ ዘንድ ሰዎችን ልከው፤
“… በንግግራችን መሰረት ወደ አዲስ ዓለም ምሽግ ለመግባት ተዘጋጅተን መምጣታችን ስለሆነ እርሰዎ የአዲስ ዓለም ከተማን ለቀው ወደ አዲሰ አበባ እንዲሄዱ አሳስባለሁ፡፡”
የሚል መልእክት ላኩባቸው፡፡ ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌም በበኩላቸው ሲመልሱ፤
“…ሆነም ቀረም በዚህ ሰሞን ጉዳዩ አንድ ውሳኔ እንዲያገኝ አደራየን በአንተ ላይ ጥያለሁ፤ እኔም ይህን ከተማ ትቸ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ ነው፡፡”
በማለት ለባላምባራስ ዘውዴ መልእክት ላኩባቸው፡፡
ባላምባራስ ዘውዴም አርበኞቻቸው ተዘጋጅተው እንዲጠብቁ ካዘዙ በኋላ የአዲስ ዓለም ከተማን ሁኔታን በቅርብ ሆነው የሚከታተሉ ሰዎችን ማለትም፤
  1. ቀኛዝማች ተሰማ ካሣን
  2. ሻለቃ በለው ወልደፃድቅን
  3. ሻምበል ኃይለጊዮርጊስ ጥላሁንን
  4. አቶ መንግሥቱ ወልደአማኑኤልን
  5. አቶ ኃይለማሪያም ወልደፃድቅን
  6. መቶ አለቃ ተስፋየ ግዛውን
  7. አቶ አበራ ማቴዎስን
  8. አቶ አድምቄ በሻህን
  9. የሀምሣ አለቃ ጽጌ ሜጫን
በማስከተል ህዳር 21 ቀን 1933 ዓ.ም. ሌሊት ሲጓዙ አድረው ህዳር 22 ቀን ከንጋት በፊት አዲስ ዓለም ከተማ ነዋሪ ከሆኑትና የክብር ዘበኛ አባል ከነበሩት ከአቶ ዓለማየሁ ቤት ደርሰው እዚያው ዋሉ፡፡ ያረፉበት ቤት ጠላት ከሠፈረበት ምሽግ ያለው እርቀት 3 ኪሎ ሜትር ብቻ ነበር፡፡
የባላምባራስ ዘውዴ ጥላሁን ሰላዮች በሚቀጥለው ቀን ህዳር 22 ቀን 1933 ዓ.ም. በሌሊት ጨለማ ለብሰው ወደ ከተማው በመግባት ተባበሪ ከሆኗቸው ሰዎች ቤት ውስጥ በመግባት ሌሊቱን ሙሉ መግቢያና መውጫውን ካጠኑ በኋላ የአርበኞች ጦር መጥቶ የሚድርበት እና የሚውልበት ቦታ በበርጋ ወንዝ አጠገብ የሚገኝ በብዙ ቁጥቋጦ የተሸፈነ ሰዋራ ጫካ እንዲሆን ተወሰነ፡፡
ይህ ሥፍራ ከአዲስ ዓለም ከተማ 3 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ቦታ ነው፡፡
የአዲሰ ዓለም ምሽግ እንዴት እንደሚደመሰስ ስልቱ በደንብ ከተጠና በኋላ ስምንት የአርበኞች መሪዎች ማለትም፤
  1. ባላምባራስ ዘውዴ ጥላሁን
  2. ልጅ ጃገማ ኬሎ
  3. መቶ አለቃ ወልደ ዮሐንስ ተክሉ
  4. ልጅ በላይ ቦጋለ
  5. አቶ ከበደ
  6. አቶ ወርቅነህ መሸሻ
  7. ሻለቃ የሻነው ወርቅነህን እና
  8. አቶ ተገኝ ባዩ
በአንድነት ሆነው ሲጠባበቁ ቆዩ፡፡

Dejazmach Gebre Mariam Gari
ለወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ በገቡት ቃል ኪዳን መሰረትም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በመገኘት በአርበኞች መሪዎች እና በአርበኞች መካከል ቃለ መሀላ ከፈፀሙ በኋላ የአርበኞቹ መሪዎች በየግላቸው ምሽጉን የሚያጠቁበትን አቅጣጫና ስልት ነደፉ፡፡
በኋላም ባላምባራስ ዘውዴ፣ ልጅ ጃገማ ኬሎ እና መቶ አለቃ ወልደ ዮሐንስ ተክሉ ባዘጋጁት የማጥቃት ስልት መሰረት ምሽጉን የማፍረስ እርምጃው እንዲከናወን ተወሰነ፡፡
ተዋጊው አርበኛ ከያለበት ስፍራ እንዲሰባሰብ መላክተኛ ተልኮ ጦሩም ህዳር 24 ቀን 1933 ዓ.ም. በሙሉ ተሰባስቦ ከተመደበበት ስፍራ ደርሶ ትእዛዝ ይጠባበቅ ጀመር፡፡
የተሰባሰበውም ጦር እንዳይራብ ሁለት ለጋሶች ምግብ እያዘጋጁ ያቀርቡላቸው ነበር፡፡
በዚህም መሰረት የሚያጠቁበት ሰዓት ሲደረስ፤ አቶ መንግሥቱ ወልደ አማኑኤል እና አቶ ስዩም ወልደ አማኑኤል 15 ባለጠመንጃዎችን በመያዝ በሁለት አቅጣጫ በኩል ቀድመው በሜሄድ ወደ ምሽጉ ተጠግተው አደጋ እንዲጥሉ ወታደራዊ ግዳጅ ተሰጣቸው፡፡
ልጅ ኃይለጊዮርጊስ ጥላሁንና እና አቶ ሙሊሳ ቀርጫ ደግሞ 15 ባለጠመንጃዎችን ይዘው ወደ ምሽጉ ገብተው በካምፑ በሚገኘው የኢጣሊያ አገረ ገዥ መኖሪያ ቤት እና በባንዳዎች ሠፈር አደጋ በመጣል እና በምሽጉ ውስጥ በሚገኘው እስር ቤት ውስጥ የታሰሩትን እስረኞች እንዲያሶጡ ግዳጅ ተሰጣቸው፡፡
ባላምባራስ ዘውዴ፣ ልጅ ጃገማ ኬሎ እና መቶ አለቃ ወልደ ዮሐንስ ተክሉ ባዘጋጁት የማጥቃት ስልት መሰረት ምሽጉን የማፍረስ እርምጃ እንዲወሰድ ተወሰነ፡፡

9. የአዲስ ዓለም የምሽግ ሰበራ እርምጃ (ኦፐሬሽን)


የአዲሰዓለም ምሽግ በዘመናዊ መንገድ የተሰራ ጠንካራ እና የማይደፈር የሽቦ አጥር ያለው ምሽግ ነበር፡፡
ህዳር 25 ቀን 1933 ዓ.ም. ሌሊት ሁሉም በተመደቡበት ሥፍራ ለመገኘትና የተሰጣቸውን ግዳጅ ለመፈፀም እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡
ባላምባራስ ዘውዴ ጥላሁን እና ጓዶቹ በቤተ ክርስቲያኑ ሰሜን ምስራቅ በኩል በሚገኘው የምሽጉ አቅጣጫ ቦታውን የሚመራቸው ሰው በማስቀደም ወደ ስፍራው በጥንቃቄ ተጠጉ፡፡
ከዚያም ወደ ምሽጉ አጥር ተጠግተው በዝግታ እና በብልሀት እየተንጠላጠሉ ወደ ምሽጉ ግቢ ገቡ፡፡
እንደገቡም በእቅዳቸው መሠረት በምሽጉ ዘበኞችና በተጠመደው የጠላት መትረየስ ላይ የእጅ ቦምብ በመወርወር አና የእሩምታ ተኩስ በየስፍራው ልክ እንደርችት በመተኮስ የማጥቃት እርምጃውን ጀመሩ፡፡
የወገን ጦር ላይ እምብዛም ጉዳት ሳይደርስ በታቀደው መሠረት የተሳካ እንቅስቃሴ (ኦፐሬሽን) ተከናወነ፡፡
በዚህም መሠረት በጠላት ላይ በተርከፈከፈው ከፍተኛ የተኩስ ኃይል ሽፋን አማካኝነት፤ ፋሽስት በግፍ በወህኒ ቤት አስሮ ሞታቸውን ይጠባበቁ የነበሩትን እስረኞች ያለአንዳች ጉዳት ከእስር ቤቱ ሰብረው እንዲወጡ ተደረገ፡፡
የጠላት የመሳሪያ ማከማቻ ግምጃ ቤቱም ተዘረፈ፡፡
በተለይ ተኩስ ከተከፈተ በኋላ የወገን ጦር ጩኸት እና ሁካታ ሰለተጨመረበት ፋሽሶቶችን ድንብርብራቸውን ሰላወጣቸው እራሳቸውን ለመከላከል ተስኗቸው ሲወናበዱ በተኮሱት ጥይት ሁለት የወገን ጦር ብቻ አቁስለዋል፡፡

10. የአዲስ ዓለም የምሽግ ሰበራና ውጤቱ


ልጅ ጃገማ ኬሉ ምሽጉ ውስጥ ከራሱ ጦር ጋር በመግባት ቦምብና ሌሎች መሳሪያዎችን ይዘው የነበሩ የፋሺስት ጦር ባለስልጣናትን ገድሎ 3 ሺህ ጠመንጃዎችንም ማርኮና ዘርፎ እስረኞችንም ለማስፈታት የራሱን ድርሻ በብቃት ተወቷል።
በሌሎች ተመሳሳይ ግዳጅ በተሰጣቸው አርበኞች በኩል፤ ከአንድ የፋሽስት ኮሎኔል ጋር በድምሩ 73 የጠላት ወታደሮች ሲገደሉ ሁለት ከባድ መትረየሶች ተማርከዋል፡፡
የተማረከውን የጠላት መሣሪያ ህዳር 28 ቀን 1933 ዓ.ም. ወደ ጫካ ወስደው ለባላገሩ አከፋፍለዋል፡፡
ባላምባራስ ዘውዴ ጥላሁን እና ሌሎች የአርበኞች መሪዎች የአዲስ ዓለምን ምሽግ ከሰበሩ በኋላ የፋሽስት ኢጣሊያንን ሠንደቅ ዓላማ አውርደው በምትኩ የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ ሰቅለው በክብር አውለብልበዋል፡፡

11. የሸዋረገድ ገድሌ ሕልፈተ ሕይዎት


Dejazmach Gebre Mariam Gari
ሕዳር 3 ቀን 1942 ዓ.ም. ለሕትመት የበቃው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ፤ አገር ወዳዷ የውስጥ አርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ እስከወዲያኛው ማሸለባቸውን የሚገልጽ ንባብ ይዞ ወጣ፡፡

ጀግናዋ የውስጥ አርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ በመስከረም ወር 1942 ዓ.ም. ወደ ግሸን ማሪያም በማቅናት ሥጋ ወደሙ ተቀብለዋል፡፡
(ግሸን ማሪያም፤ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል በማሪያም ቤተ ክርስቲያን ሥር ተቀብሮ የሚገኝበት ስፍራ በመሆኑ፤ በሀገሪቱ ውስጥ ካሉት አብያተ ክርስቲያናት መካከል እጅግ የተቀደሰ ሥፍራ መሆኑ ይታወቃል፡፡)
ከዚያም ጥቅምት 7 ቀን 1942 ዓ.ም. ቅዱስ ላሊበላን ጎብኝተው ጸሎተ ምህላ ከተደረገላቸው በኋላ በጠና ታመው ስለነበረ የሐኪም እርዳታ እንዲደረግላቸው ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ቢጀምሩም በሕይዎት ሊተርፉ ባለመቻላቸው፤ ማክሰኞ ጥቅምት 22 ቀን 1942 ዓ.ም. በተወለዱ በ 64 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ለወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ መታሰቢያ የሚሆን በአዲስ አበባ ወደ ቀበና የሚወስደው መንገድ በስማቸው ተሰይሞላቸዋል፡፡






ምንጭ፤
  1. “ቀሪን ገረመው የአርበኞች ታሪክ”  ደራሲ፤ ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ 1960 ዓ.ም.
  2. Africaportal   ምስጋና፤ ለምናለ አዱኛ  africaportal.org
  3. 623 channel   ዩቲውብ ሊንክ
  4. Addis 1879 /አዲስ 1879   ዩቲውብ ሊንክ
  5. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ