Content-Language: am ደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን
header image



ደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን



በ2ኛው የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት
የደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን የአርበኝነት ታሪክ













1. የጀልዱ የጠላት ምሽግ መሰበር


Dejazmach Zewudie Telahun
የጠላት ምሽግ ሰባሪው አርበኛ
ደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን
የጀልዱ ምሽግ በሜጫና ጅባት አውራጃ ከሚገኙት የጠላት ምሽጎች መካከል በአሰራሩም ሆነ በአቀማመጡ ጠንካራ የመከላከያ ምሽግ ነበር፡፡
ሚያዝያ 8 ቀን 1932 ዓ.ም. ከምሽቱ አነድ ሰዓት ተኩል ሲሆን በምሽጉ የነበሩት የፋሽስት ወታደሮች ተሰባስበው እራት የሚበሉበት ሰዓት ነበረ፡፡
ለዚህ የጠላት ምሽግ መሰበር የጦር መሀንዲስ የሆኑት ባላምባራስ ዘውዴ ጥላሁን ሲሆኑ፣ ከአቶ ሰለሞን ውብሸት፣ ከአቶ ጌራ መድሐኒት፣ ከአቶ ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ከአቶ ስነ ውብሸት፣ ከሻምበል ሹምየ ደበሳይ፣ ከመቶ አለቃ ተስፋየ ግዛውና በድምሩ 14 ከሚደርሱ ከሌሎች ጀግኖች ጋር በመሆን በተጠቀሰው ቀንና ሰዓት በምሽጉ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሲያደርሱ ጠላት እራሱን ለመከላከል እንኳን ባለመቻሉ፤ በምሽጉ ውስጥ የነበሩትን የፋሽስት ወታደሮች በሙሉ ገድለው 400 ባንዳዎችን ማርከዋል፡፡
በዚህ የምሽግ ሰበራ ወቅት 700 ጠመንጃዎችን፣ 2 ከባድ መትረየሶችን፣ 18 ሳጥን የእጅ ቦምቦችን እና በርካታ ጥይቶችን ከማረኩ በኋላ ምሽጉን በእሳት ሙሉ በሙሉ አቃጠሉት፡፡
አርበኞቹ ሚያዝያ 11 ቀን 1932 ዓ.ም. በተቃጠለው ምሽግ አጠገብ ሆነው የማረኩትን የጦር መሣሪያ ለባላገሩ ሕዝብ ካከፋፈሉ በኋላ አቅራቢያቸው ወደአለው ጥቅጥቅ ወደአለው ጫካ ውስጥ ተደበቁ፡፡
በርካታ ቁጥር ያለው የጠላት ጦርም አርበኞችን አድኖ ለመያዝ ከያለበት ተሰባስቦ ቢመጣም ጀግኖች አርበኞች ግራና ቀኙን በመድፍ ተኩስ ጠላት ላይ የጥይት ናዳ ስላወረዱበት በየቦታው ተበታተነ፡፡
በጭራሽ አይበገርም እየተባለ ሲነገርለት የቆየው የጀልዱ ምሽግ አንድ ሌሊት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወድሞ መታየቱ እንኳን ወገንን ጠላትንም ሳያስገርመው አልቀረም፡፡
የጀልዱ ምሽግ ከወደመ በኋላ የክረምት ወራቱ አልፎ አርበኞቹ እሰከ ህዳር 21 ቀን 1933 ዓ.ም. ድረስ ሜጫ ጋጂ ዮብዶ ከሚባሉ ጫካዎች ውስጥ ተደብቀው የቆዩ ሲሆን እነዚህም አገሮች የነልጅ ጃገማ ኬሎ አገር በመሆኑ በስንቅ በኩል ችግር ሳያጋጥማቸው ቆዩ፡፡
ከዚህ ድል በኋላ ባላምባራስ ዘውዴ ጥላሁን እና ተባባሪዎቻቸው ሰባት ወራት ሙሉ ሲዘዋወሩ ከቆዩ በኋላ ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ባላምባራስ ዘውዴ ጥላሁን እንዲመጡላቸው ባሳሰቡት መሰረት ባላምባራስ ዘውዴም ጀግንነታቸው እንደሳት አደጋ ተከላካይ ፈጥነው በርጋ ሸለቆ ደርሰው የአዲስ ዓለም ምሽግን ለመስበር የሚያሰችላቸውን እቅድ ማሰላሰል ጀመሩ፡፡

2. የአዲሰ ዓለምን ምሽግ የመስበር እቅድ


ጃገማ በአርበኝነት ዘመኑ ከፈጸማቸው አኩሪ ገድሎች መካከል የፋሺስት ጦር ይመካበት የነበረው የአዲስ ዓለም ምሽግ ሰበራ ፈፅሞ የሚዘነጋ አይደለም።
ጃገማ ደጃዝማች ገረሱን ለመርዳት ወደ ወሊሶ ሄዶ በነበረበት ወቅት፤
“…ጃገማ፤ ያን የተመካከርንበትን ጉዳይ ጨርሻለሁና ዛሬ ነገ ሳትል ሰራዊትህን ይዘህ ቶሎ ና፡፡”
የሚል መልዕክት ከስመ ጥሩዋ የውስጥ አርበኛዋ ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ ደረሰው።
በሌላም በኩል የአዲሰ ዓለምን ምሽግ ለመስበር ባላምባራስ ዘውዴ ጥላሁንም እቅድ ስለነበራቸው በሚኖሩበት ሀገር ያሉትን ታላላቅ ሰዎች አማክረው ፈቃደኛ ሆነው መገኘታቸውን ካረጋገጡ በኋላ ወደ ሸዋረገድ ገድሌ ዘንድ ሰዎችን ልከው፤
“… በንግግራችን መሰረት ወደ አዲስ ዓለም ምሽግ ለመግባት ተዘጋጅተን መምጣታችን ስለሆነ እርሰዎ የአዲስ ዓለም ከተማን ለቀው ወደ አዲሰ አበባ እንዲሄዱ አሳስባለሁ፡፡”
የሚል መልእክት ላኩባቸው፡፡
ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌም በበኩላቸው ሲመልሱ፤
“…ሆነም ቀረም በዚህ ሰሞን ጉዳዩ አንድ ውሳኔ እንዲያገኝ አደራየን በአንተ ላይ ጥያለሁ፤ እኔም ይህን ከተማ ትቸ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ ነው፡፡”
በማለት ለባላምባራስ ዘውዴ መልእክት ላኩባቸው፡፡
ባላምባራስ ዘውዴም አርበኞቻቸው ተዘጋጅተው እንዲጠብቁ ካዘዙ በኋላ የአዲስ ዓለም ከተማን ሁኔታን በቅርብ ሆነው የሚከታተሉ ሰዎችን ማለትም፤
  1. ቀኛዝማች ተሰማ ካሣን
  2. ሻለቃ በለው ወልደ ፃድቅን
  3. ሻምበል ኃይለ ጊዮርጊስ ጥላሁንን
  4. አቶ መንግሥቱ ወልደ አማኑኤልን
  5. አቶ ኃይለማሪያም ወልደ ፃድቅን
  6. የመቶ አለቃ ተስፋየ ግዛውን
  7. አቶ አበራ ማቴዎስን
  8. አቶ አድምቄ በሻህን
  9. የሀምሣ አለቃ ጽጌ ሜጫን
Dejazmach Zewudie Telahun
ደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን
በማስከተል ህዳር 21 ቀን 1933 ዓ.ም. ሌሊት ሲጓዙ አድረው ህዳር 22 ቀን ከንጋት በፊት አዲስ ዓለም ከተማ ነዋሪ ከሆኑትና የክብር ዘበኛ አባል ከነበሩት ከአቶ ዓለማየሁ ቤት ደርሰው እዚያው ዋሉ፡፡ ይህ ስፍራ ጠላት ከሠፈረበት ምሽግ ያለው እርቀት 3 ኪሎ ሜትር ብቻ ነበር፡፡
የባላምባራስ ዘውዴ ጥላሁን ሰላዮች በሚቀጥለው ቀን ህዳር 22 ቀን 1933 ዓ.ም. በሌሊት ጨለማ ለብሰው ወደ ከተማው በመግባት ተባበሪ ከሆኗቸው ሰዎች ቤት ውስጥ በመግባት ሌሊቱን ሙሉ መግቢያና መውጫውን ካጠኑ በኋላ የአርበኞች ጦር መጥቶ የሚያድርበት እና የሚውልበት ቦታ በበርጋ ወንዝ አጠገብ የሚገኝ በብዙ ቁጥቋጦ የተሸፈነ ሰዋራ ጫካ እንዲሆን ተወሰነ፡፡
ቦታው ከአዲስ ዓለም ከተማ 3 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ስፍራ ነው፡፡
የአዲሰ ዓለም ምሽግ እንዴት እንደሚደመሰስ ስልቱ በደንብ ከተጠና በኋላ ስምንት የአርበኞች መሪዎች ማለትም፤
  1. ባላምባራስ ዘውዴ ጥላሁን
  2. ልጅ ጃገማ ኬሎ
  3. መቶ አለቃ ወልደ ዮሐንስ ተክሉ
  4. ልጅ በላይ ቦጋለ
  5. አቶ ከበደ
  6. አቶ ወርቅነህ መሸሻ
  7. ሻለቃ የሻነው ወርቅነህ እና
  8. አቶ ተገኝ ባዩ
በአንድነት ሆነው ሲጠባበቁ ቆዩ፡፡
ለወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ በገቡት ቃል ኪዳን መሰረትም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በመገኘት በአርበኞች መሪዎች እና በአርበኞች መካከል ቃለ መሀላ ከፈፀሙ በኋላ የአርበኞቹ መሪዎች በየግላቸው ምሽጉን የሚያጠቁበትን አቅጣጫና ስልት ከነደፉ በኋላ ባላምባራስ ዘውዴ፣ ልጅ ጃገማ ኬሎ እና መቶ አለቃ ወልደ ዮሐንስ ተክሉ ባዘጋጁት የማጥቃት ስልት መሰረት ምሽጉን የማፍረስ እርምጃው እንዲከናወን ተወሰነ፡፡
ተዋጊው አርበኛ ከያለበት ስፍራ እንዲሰባሰብ መላክተኛ ተልኮ ጦሩም ህዳር 24 ቀን 1933 ዓ.ም. በሙሉ ተሰባስቦ ከተመደበበት ስፍራ ደርሶ ትእዛዝ ይጠባበቅ ጀመር፡፡
የተሰባሰበውም ጦር እንዳይራብ ሁለት ለጋሶች ምግብ እያዘጋጁ ያቀርቡላቸው ነበር፡፡
በዚህም መሰረት የሚያጠቁበት ሰዓት ሲደረስ፤ ወንድማማቾቹ አቶ መንግሥቱ ወልደ አማኑኤል እና አቶ ስዩም ወልደ አማኑኤል 15 ባለጠመንጃዎችን በመያዝ በሁለት አቅጣጫ በኩል ቀድመው በሜሄድ ወደ ምሽጉ ተጠግተው አደጋ እንዲጥሉ ወታደራዊ ግዳጅ ተሰጣቸው፡፡
ልጅ ኃይለጊዮርጊስ ጥላሁንና እና አቶ ሙሊሳ ቀርጫ ደግሞ 15 ባለጠመንጃዎችን ይዘው ወደ ምሽጉ ገብተው በካምፑ በሚገኘው የኢጣሊያ አገረ ገዥ መኖሪያ ቤት እና በባንዳዎች ሠፈር አደጋ በመጣል እና በምሽጉ ውስጥ በሚገኘው እስር ቤት ውስጥ የታሰሩትን እስረኞች እንዲያሶጡ ግዳጅ ተሰጣቸው፡፡

3. የአዲሰ ዓለም የጠላት ምሽግ መሰበር


የአዲሰዓለም ምሽግ በዘመናዊ መንገድ የተሰራ ጠንካራ እና የማይደፈር የሽቦ አጥር ያለው ምሽግ ነበር፡፡
ህዳር 25 ቀን 1933 ዓ.ም. ሌሊት ሁሉም በተመደቡበት ሥፍራ ለመገኘትና የተሰጣቸውን ግዳጅ ለመፈፀም እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡
ባላምባራስ ዘውዴ ጥላሁን እና ጓዶቹ በቤተ ክርስቲያኑ ሰሜን ምስራቅ በኩል በሚገኘው የምሽጉ አቅጣጫ የሚመራቸው ሰው በማስቀደም ወደ ስፍራው በጥንቃቄ ተጠጉ፡፡
ከዚያም ወደ ምሽጉ አጥር ተጠግተው በዝግታ እና በብልሀት እየተንጠላጠሉ ወደ ምሽጉ ግቢ ገቡ፡፡
እንደገቡም በእቅዳቸው መሠረት በምሽጉ ዘበኞች እና በተጠመደው የጠላት መትረየስ ላይ የእጅ ቦምብ ከወረወሩ በኋላ የጥይት እሩምታ ከመቅጽበት በየስፍራው ልክ እንደርችት ተኮሱ፡፡
የወገን ጦር ላይ እምብዛም ጉዳት ሳይደርስ በታቀደው መሠረት የተሳካ እንቅስቃሴ (ኦፐሬሽን) ተከናወነ፡፡
በዚህም መሠረት በጠላት ላይ በተርከፈከፈው ከፍተኛ የተኩስ ኃይል መሠረት ፋሽስት በግፍ በወህኒ ቤት አስሮ ሞታቸውን ይጠባበቁ የነበሩ እስረኞች ያለአንዳች ጉዳት ከእስር ቤቱ ሰብረው እንዲወጡ ተደረገ፡፡
የጠላት የመሣሪያ ማከማቻ ቤቱም ተዘረፈ፡፡
በተለይ ተኩስ ከተከፈተ በኋላ የወገን ጦር ጩኸት እና ሁካታ ሰለተጨመረበት ፋሽሶቶችን ድንብርብራቸውን ሰላወጣቸው እራሳቸውን ለመከላከል ተስኗቸው ሲወናበዱ በተኮሱት ጥይት ሁለት የወገን ጦር ብቻ አቁስለዋል፡፡

4. የአዲሰ ዓለም ምሽግ መስበርና ውጤቱ


ጃገማ ኬሎ የተማረከውን የጠላት መሣሪያ ህዳር 28 ቀን 1933 ዓ.ም. ወደ ጫካ ወስደው ለባላገሩ አከፋፍለዋል፡፡
ባላምባራስ ዘውዴ ጥላሁን እና ሌሎች የአርበኞች መሪዎች የአዲስ ዓለምን ምሽግ ከሰበሩ በኋላ የፋሽስት ኢጣሊያንን ሠንደቅ ዓላማ አውርደው በምትኩ የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ ሰቅለው በክብር አውለበለቡ፡፡
ባላምባራስ ዘውዴ ጥላሁን ከአርበኞች ጦር ጋር በመሆን የገሩን ፀጥታ ለማረጋጋት ከዚያው ቆይተው ነበር፡፡
በኋላም ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በድል አድራጊነት መናገሻ ከተማቸው አዲስ አበባ እንደገቡ ባላምባራስ ዘውዴ ጥላሁን ጅማ ያለውን የጠላት ጦር ለመውጋት ወደ ጅማ አመሩ፡፡
ወደ ጅማ ሲያመሩም በሊሙ አውራጃ ውስጥ እንዲሁም ጅማ ሰቃ በተባለው ቀበሌ የሚገኘውን ጠላት በመደምሰስ 1ሺህ 700 የሚደርሱ የጠላት ወታደሮችን፣ 500 መኪናዎችን፣ 8 ቀላል መትረየሶችን እና 20 ከባድ መትረየሶችን ማርከዋል፡፡






ምንጭ፤
  1. “ቀሪን ገረመው የአርበኞች ታሪክ”  ደራሲ፤ ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ 1960 ዓ.ም.
  2. 623 channel   ዩቲውብ ሊንክ
  3. የድምፅ ትረካ አጃቢ ሙዚቃ፤ ጎራው - በኦርኬስትራ ኢትዮጵያ