Content-Language: am ሌፍትናንት ጀኔራል ጃገማ ኬሎ
header image


ሌፍትናንት ጀነራል ጃገማ ኬሎ (የበጋው መብረቅ)



የጀግናው አርበኛ የሌፍትናንት ጀነራል ጃገማ ኬሎ የአርበኝነት ዘመን ትረካ

በእያንዳንዱ አርዕስት ሥር የሚገኘውን
የድምጽ ማጫወቻ በመጠቀም ትረካውን ማዳመጥ ይችላሉ

ክፍል አንድ

ትውልድ እና የልጅነት የሕይዎት ዘመን

ክፍል ሁለት

የወጣቱ ጃገማ የጀግንነት ገድል

ክፍል ሦስት

የፋሽሰቶች ምሽግ ሰበራ አኩሪ ገድል

ክፍል አራት

የጃገማ ኬሎ የትዳር ሕይዎትና የግል ባህርይ

ክፍል አምስት

ጃገማ ኬሎ ከድል በኋላ ያከናወኗቸው ተግባራት

የመጨረሻ ክፍል

ሕልፈተ ሕይዎትና የቀብር ሥነ ሥርዓት



1. ትውልድ እና የልጅነት የሕይዎት ዘመን

Jagema at the age of 15
ጃገማ ኬሎ በ16 ዓመት ዕድሜ
የጃገማ አባት ኬሎ ገሮ (አባ ጃገማ)፤ የሜጫ ኦሮሞ ናቸው፡፡ በኦሮምኛ ቋንቋ ኬሎ ማለት “የመስቀል አበባ” ማለት ነው፡፡
ጃገማ፤ የአባታቸው የኬሎ ገሮ የፈረሳቸው ስም ነው፡፡
የጃገማ እናታቸው ወይዘሮ ደላንዱ ይባላሉ፡፡
ደላንዱ በኦሮምኛ ቋንቋ “ቄጠማ” ማለት ነው፡፡
ወይዘሮ ደላንዱ ውብ የሆኑ ቆንጆ፤ የባላባትና የጀግና ዘር ሲሆኑ የአምቦ አካባቢ ሴት ናቸው፡፡
የመስቀል አበባው ኬሎ ገሮ እና ቄጠማዋ ደላንዱ ተገናኝተው ትዳር መሠረቱ፡፡
ኬሎ ገሮ በአካባቢው ብዙ ሐብት ያላቸው የታወቁና የተከበሩ ሰው ነበሩ፡፡
የኬሎ ገሮ፤ ባለቤታቸው የሚወልዱት ልጅ ወንድ ከሆነ የፈረሴን ስም አሰጠዋለሁ ብለው ስለነበረ አባታቸው በተናገሩት ቀን የተወለደው ወንድ ልጅ ጃገማ ተባለ፡፡
ጃገማ በኦሮምኛ ቋንቋ “ትልቅ ዛፍ” ማለት ነው፡፡
ጃገማ ኬሎ በቀድሞው አጠራር በጅባትና ሜጫ አውራጃ፣ በደንዲ ወረዳ ዮብዶ በተባለ ስፍራ ጥር 21 ቀን 1913 ዓ.ም. ማክሰኞ ማታ ተወለዱ፡፡
የጃገማ አባት ኬሎ ገሮ ልጃቸውን በ70 ዓመት የአዛውንት እድሜያቸው ወንድ ልጅ በማግኘታቸው ከልክ ያለፈ ደስታ ተሰማቸው፡፡
በአካባቢው ተከስቶ በነበረ በሽታ ምክንያት፤ ጃገማ በተወለደ በአንደ አመቱ እናቱ በመሞታቸው በአክስቱና በሞግዚት እንዲያድግ አባቱ ወሰኑ ።
Jagema Kello with his brother
ጃገማ ከታላቅ ወንዱም ጋር

Photo credit to: ethiobiography.org
አክስቱም ጃገማን ከወንድሙ ጋር ፀበል አስጠምቀው እና ቄስ ቀጥረው ዳዊት እንዲማር አድርገዋል።
የጃገማ አባት ልጃቸው 10 ዓመት እንደሞላው በ1923 ዓ.ም. አረፉ፡፡
የጃገማ አክስት ጃገማን ዘመናዊ ትምህርት እንዲማር በማለት በቀድሞው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አስገብታው ለ 3 ወራት ተምሯል፡፡
በኋላም ወደ ትውልድ ሥፍራው ተመልሶ በወጣትነቱ፤ ፈረስ ግልቢያ፣ ጦር ውርወራ፣ ጋሻ ማንገብ፤ ምክቶሽ እና ውሀ ዋና ተማረ፡፡
ወጣቱ ጃገማ መራብና መጠማትን ሳይቀር ተለማመደ፡፡
አልፎ ተርፎ ዝሆንና ጎሽ አድኖ ለመግደል ወደ ጌድዮ ሄዶ ተይዞ ተመልሷል፡፡

2. የወጣቱ ጃገማ የጀግንነት ገድል

Jagema with his patriots
ወጣቱ ጃገማ ኬሎ ከአርበኛ ጓዶቻቸው ጋር
ፋሺስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ስትወር ጃገማ ገና በ15 ዓመቱ አርበኛ ሆኖ የፋሺስትን ጦር ለመፋለም ወሰነ።
የአጎቱ ልጅ ከሆነው ከአሰፋ አባ ዶዮ ጋር ወደ ጫካ ገቡ። እህቱና ወንድሞቹም ተከተሉት።
ገበሬዎች፣ ወታደሮች እና ሾፌሮች ሳይቀሩ ከጃገማ ጋር የተቀላቀሉት ቁጥራቸው 30 የሚደርሱ አርበኞች ጠላትን ለመውጋት ጫካ ገቡ።
በአባቱ የተመረጠው፣ ግርማ ሞገስና የማስተዋል ችሎታ የታደለውን ወጣት ጃገማን፤ እድሜያቸው ከእርሱ በእጥፍ የሚልቁት አርበኞች ተሰባበስበው ገና በለጋነቱ መሪያቸው አድርገው መረጡት፡፡
የጃጋማ አባት ኬሎ ገሮ በአካባቢው ዘንድ ይወደዱና ይከበሩ ስለነበር የአካባቢው ሕዝብ በታዳጊው ጃገማ የሚመሩትን አርበኞች በልዩ ልዩ መንገዶች ያግዛቸው ነበር።
በፋሺስት ጦር ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመሰንዘር የጠላትን ጦር መፈተን ጀመሩ።
የጃገማ አርበኞች ፋሺስቶች ጥይት የሚጭኑባቸውን እንስሳትን በጥይት በመምታት እና ፋሺስቶችና ባንዳዎች ሲሸሹ ደግሞ መሳሪያና ጥይት እየሰበሰቡ ማከማቸት ቀጠሉ፡፡
ጣሊያኖችም ጃገማንና ተከታዮቹን ለመደምሰስ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም።
የጃገማ ተከታዮች ቁጥራቸው ጨመረ። ፋሺስቶች ተጨማሪ ምሽጎችን ለመገንባት ቢያስቡም ቀድመው በገነቧቸው ምሽጎች ውስጥም እንደልባቸው መንቀሳቀስ ሳይችሉ ቀሩ።
የ18 ዓመት ወጣት በሆነው በጃገማ ኬሎ የሚመሩት አርበኞቹ በሚያዝያ ወር 1931 ዓ.ም. ሐሮታና ጀልዱ የነበረውን የጠላት ጦር ግንኙነት ለመበጣጠስ የወሰዷቸው እርምጃዎች አዲስ አበባ ድረስ ተሰሙ፡፡
ጀነራል ጃገማ ከቤተሰቦቻቸው ጋር
በ2003 ዓ.ም. የ90
ዓመት ልደታቸውን ሲያከብሩ
አግብታ ወለጋ ጠቅላይ ግዛት ትኖር የነበረችውም እህቱ ሌንሴ፤ የወንድሟን መሸፈት ስትሰማ ባሏን ፈታ ወንድሟን ለማገዝ ጫካ ገባች፡፡ ይህም ለወንድሟ ጥንካሬን ፈጠረለት፡፡
ብዙ የነፃነት ተዋጊዎችም እነጃገማ ያሉበት ድረስ ሄደው ተቀላቀሉ፡፡
በጃገማ አባት ያልበላ፣ ያልጠጣ፣ ከብት ያልተቀበለ ስለሌለ፤ የአባቱ ውለታ ያለበት የአካባቢው ነዋሪ ሁሉ ለወጣቱ አርበኛ ለጃገማ ደጋፊው ሆነ፡፡
ዶሮና እንቁላል ለጣሊያን ወታደሮች እየሸጡ በሚያገኙት ገንዘብ ከባንዳዎች ጥይት ገዝተው ለአርበኞች ያቀብላሉ፡፡ ጠላትን እየሰለሉ መረጃ ለአርበኞች ያቀብላሉ፡፡
የነጃገማ አርበኞች የደፈጣ ውጊያ ስልትን በመጠቀማቸው የጠላት ጦር ጥይት እንዲያባክን በማድረግ፣ የአካባቢው ሰው ከፋሺስት ወታደሮችና ከባንዳዎች ላይ ጥይት እንዲገዛ በማስተባበር የመሳሪያ ክምችታቸውን እያጠናከሩ ሄዱ፡፡
በጥቅምት ወር 1933 ዓ.ም. የ20 ዓመት ወጣቱን የጃገማን ጦር ለማጥቃት ወደ ሰንጎታ ተራራ የሄደው 350 የፋሺስት ጦር ጃገማ በሚመራቸው በ17 አርበኞች ተሸነፈ።
Jagema with his family
ጀነራል ጃገማ ከቤተሰቦቻቸው ጋር
(የ 2005 ዓ.ም. ፎቶ)

በዚህ ውጊያ የጃገማ አርበኞች ብዙ የጠላት ወታደሮችን ገደሉ፤ ባንዳዎች የዘረፉትን ንብረት አስመለሱ። የጠላት ወታደሮችንና ብዙ መሳሪያም ማረኩ። የጃገማ ጀግንነትም እየገዘፈ ሄደ ።
የአካባቢው ሕዝብም የጃገማን ጀግንነት ከቅድመ አያቱ ጀግንነት ጋር እያነፃፀረ በማውራቱ በጠላት ጦር ካምፕ ውስጥ ፍርሃት ይበልጥ ነገሠ።
በኋላም ወደ ወሊሶ ሄዶ በአካባቢው ከፋሺስት ጦር ጋር ሲዋጉ ወደነበሩት ወደእነ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ጦር ጋር ሄዶ ተቀላቀለ።
የፋሺስት ጦር በአርበኛው በደጃዝማች ገረሱ ላይ ውጊያ ከፍቶ በነበረበት ወቅት ጃገማም በዚሁ ውጊያ ላይ ተሳታፊ ስለነበረ የማታ ማታ ድሉ የአርበኞቹ ሆነ። በዘህም በተገኘው ድል ምክንያት ደጃዝማች ገረሱ፤
“አንተን የመሰለ ጀግና የወለደች እናት ትባረክ።” በማለት ጃገማን አመሰግነውታል።

ጃገማ በአንድ ውጊያ ላይ የማረከውን የኢጣሊያ ወታደር እንደማይገደል ከነገረው በኋላ ስለአርበኞቹ ኃያልነት፤ ስለፋሺስቶች ፈሪነትና አረመኔነት አስረድቶት፤
“...ከምርኮኝነት ነፃ የምትወጣው ለጥይት መግዣ የሚሆነኝን 10ሺህ ሊሬ ከከፈላችሁኝ ብቻ ነው።” አለው። ጃገማም በአንድ ኢጣሊያዊ መልዕክተኛ አማካኝነት 10 ሺህ ሊሬ ተቀብሎ ምርኮኛውን ፈቶታል፡፡
ምርኮኛውም ወደጦር ሰፈሩ ሄዶ ስለጃገማ ጀግንነት ለአለቆቹ ሲነግራቸው በንግግሩ ደስ ባለመሰኘታቸው ምርኮኛውን ወደ ሌላ ስፍራ አዛውረውታል።
ጀነራል ጃገማ በተለያዩ ጊዚያት
የተሰጧቸው የክብር ሽልማቶች
በአንድ ወቅት ጃገማ ከጭልሞ ወደ አሬራ ሲሄድ ጊንጪ ገበያ ውለው ወደ ጭልሞ ሲሄዱ የነበሩ ገበሬዎች በሽፍቶች ሲዘረፉ ተመለከተ፡፡
ጃገማ ተወርውሮ ሄዶ ዘራፊዎቹን በማባረር የገበሬዎቹን ንብረት አስመለሰ፡፡
በዚህን ወቅት ጃገማን ያዩት ፋሺስቶችና ባንዳዎችም በጃገማ ላይ አደጋ ለመጣል ሞክረው በጃገማ አስደናቂ የአፀፋ ውጊያ ለቁስለኛነትና ለሽሽት ዳረጋቸው፡፡
በአካባቢው የነበረው የኢጣሊያ ጦር አዛዥ ስለሁኔታው ሰምቶ ለጃገማ ደብዳቤ ፃፈለት፡፡ የደብዳቤው ይዘትም ጃገማ የገበሬዎቹን ንብረት ማስመለሱ መልካም እንደሆነ፣ ራሱን ለመከላከል በወሰደው እርምጃ የኢጣሊያ መንግሥት እንደማይጠይቀውና ምኅረት ስለተደረገለት በአካባቢው ለሚገኘው የኢጣሊያ ጦር እጁን እንዲሰጥ የሚገልፅ ነበር፡፡
ጃገማም ደብዳቤውን ተመልክቶ፤
“…ከሰው አገር ላይ መጥቶ፤የሰው መሬት ወስዶ ...‹ሙሉ ምኅረት ተደርጎልሃልና ግባ› አለኝ፡፡ አነዚህ ደፋሮችና ግፈኞች አገሬን ለቀው እስካልሄዱ ድረስ አይማረኝ ብምራቸው፡፡” በማለት ለጓደኞቹ ተናግሯል፡፡
እኔ የማውቀው አለ ጃገማ፤
“እኔ የማውቀው፤ ምኅረት ሰጪ አንድ ፈጣሪን ነው፡፡ ሰው ምኅረት የሚሰጥ ከሆነ ግን ምኅረት ሰጪው አገር የወረረ ሳይሆን አገሩ የተወረረበት እኔ ነኝ፡፡”
በማለት የመልስ ደብዳቤ ለፋሽስቶች ልኮላቸዋል፡፡

3. የፋሽስት ምሽጎች ሰበራ አኩሪ ገድል

3.1 የአዲስ ዓለም የፋሽስት ምሽግ ሰበራ
ጃገማ በአርበኝነት ዘመኑ ከፈጸማቸው አኩሪ ገድሎች መካከል የፋሺስት ጦር ይመካበት የነበረው የአዲስ ዓለም ምሽግ ሰበራ ፈፅሞ የሚዘነጋ አይደለም። ጃገማ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪን ለመርዳት ወደ ወሊሶ ሄዶ በነበረበት ወቅት፤
“...ጃገማ፤ ያን የተመካከርንበትን ጉዳይ ጨርሻለሁና ዛሬ ነገ ሳትል ሰራዊትህን ይዘህ ቶሎ ና።...”
የሚል መልዕክት ከስመ ጥሩዋ የውስጥ አርበኛ ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ ደረሰው።
ጃገማም ከአዲስ አበባ 55 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው አዲስ ዓለም በፍጥነት አቅንቶ የምሽግ ሰበራው የጦር አዝማች ሆነ።
ጥቃቱ እንዴት እንደሚፈፀም የሚያሳይ መመሪያ ለባልደረቦቹ አስረድቶ የሥምሪት ትዕዛዞችን ሰጠ።
ራሱ ምሽጉ ውስጥ ገብቶ ቦምብና ሌሎች መሳሪያዎችን ይዘው የነበሩ የፋሺስት ጦር ባለስልጣናትን ገድሎ 3 ሺህ ጠመንጃዎችንም ማርኮና ዘርፎ እስረኞችንም አስፈትቷል።
በዘመቻው ላይ ከአርበኞቹ ወገን የሞተው አንድ ሲሆን ቁስለኛ አንድ ብቻ ነው፡፡ ከጠላት ወገን ግን 73 የኢጣሊያ የምሽጉ ጠባቂዎች ተገድለዋል፡፡
3.2 የጭልሞ የፋሽስት ምሽግ ሰበራ
በመጋቢት ወር 1933 ዓ.ም ጃገማ የጭልሞን ምሽግ ከቦ በፋሺስት ጦር ላይ ተኩስ ከፈተ። “…እጃችሁን ካልሰጣችሁ አንላቀቅም!” የሚል መልዕክትም አስተላለፈ።
የፋሽስት ጦር እንደራደርና እጅ እንሰጣለን ካሉ በኋላ አዘናግተው ሊያመልጡ ሲሉ ከአርበኞቹ ተኩስ ተከፈተባቸውና 13 የኢጣሊያ ወታደሮችና 1ሺህ 500 ባንዳዎች ተማረኩ። ጊንጪም በጃገማ አርበኞች ቁጥጥር ስር ዋለች።
3.3 የሐሮታ የፋሽስት ምሽግ ሰበራ
ጃገማ ወዲያውኑ የኢጣሊያ ጦር የሚተማመንበት የሐሮታ ምሽግ ላይ ጥቃት እንዲከፈት አዘዘ። የጠላት ጦር አንድ ጊዜ እየሸሸ፤ ሌላ ጊዜ እያጠቃ መፋለሙን ቀጠለ።
በዚህ ጊዜ ጃገማ ብቻውን ሆኖ ቦታ እየቀያየረ መድፍ ሲተኩስ የፋሺስት ጦር ተስፋ ቆርጦ ለመጨረሻ ጊዜ ሸሸ፤ ከሞት የተረፈውም ተማረከ። የጃገማ ጦርም ድል አድርጎ አዲስ ዓለም ገባ። ሆለታንም በቁጥጥሩ ስር አደረገ፡፡
ጃገማ ኬሎ ይመራቸው የነበሩት የአርበኞች ብዛት 3ሺህ 500 ይደርስ እንደነበረ ተገምቷል፡፡

4. የጃገማ ኬሎ የትዳር ሕይዎት

Jagema Kello's First Wife
የጀገማ ኬሎ የመጀመሪያ የትዳር
አጋሩ ወይዘሮ ዘውዲቱ ኃይሉ
ወጣቱ ጃገማ የመጀመሪያ ትዳራቸውን ለመመሥረት የፈለጉት ወይዘሪት ዘውዲቱ ኃይሉ ከምትባል ኮረዳ ጋር ነበር፡፡
ነገር ግን የልጅቱ ወንድም ስለከለከላቸው በራስ መስፍን ስለሽ አማላጅነት እንዲጋቡ ተፈቅዶ ተጋቡ፡፡ ነገር ግን ከሦስት ዓመታት ቆይታ በኋላ የሚወዷት ባለቤታቸው አንድ ልጅ ከወለደችላቸው በኋላ በድንገት በሞት ተለየቻቸው፡፡
በኋላም ጃገማ ኬሎ በ1944 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ ወይዘሪት አስቴር የምትባል ልጃገረድ በማግባት ትዳር መስርተው ልጆችን፤ የልጅ ልጆችን እና የልጅ፣ ልጅ፣ ልጆችን አፍርተው ለ51 ረጅም ዓመታት በትዳር አብረው ከቆዩ በኋላ ባለቤታቸው ወይዘሮ አስቴር በ1995 ዓ.ም. በሕመም ምክንያት በሞት ተለይተዋቸዋል፡፡

Jagema Kello and his Spouse Aster
ጃገማና ሁለተኛዋ ባለቤታቸው
ወይዘሮ አስቴር በወጣትነት እንደተጋቡ

Photo credit to:  ENKSSM
ሌፍትናንት ጀነራል ጃገማ ኬሎ አንድ ወንድና አምስት ሴት ልጆችን፣ 5 የልጅ ልጆችን እና 4 የልጅ ልጅ፤ ልጆችን አፍርተዋል።
የልጆቻቸውም ስም በእድሜ ቅደም ተከተል፤
  1. ሰለሞን ጃገማ
  2. ፀዳሉ ጃገማ
  3. የትምወርቅ ጃገማ
  4. ሸዋዬ ጃገማ
  5. ብሩክታይት ጃገማ
  6. ምህረት ጃገማ
ይባላሉ፡፡
Meheret Jagema
የጀነራል ጃገማ ልጅ ምህረት ጃገማ (በ2005 ዓ.ም.)
የሌፍትናንት ጀነራል ጃገማ ኬሎ የመጨረሻ ልጅ የሆነችው ምህረት ጃገማ፤ እናቷ ከሞቱ በኋላ አባቷን እስከለተ ሞታቸው
jagema's grand daughter
የጀነራል ጃገማ
የልጅ ልጅ (በ2005 ዓ.ም.)
ድረስ በብቸኝነት ትንከባከባቸው እና ታገለግላቸው የነበረች ልጃቸው ነች፡፡ ምህረት ለሀገር ባለውለታ የሆኑትን ጀግና አባቷን ለመንከባከብ በመቻሏ፤ ደስተኛና እድለኛም መሆኗን ትናግራለች፡፡ ብቸኛ ወንድ ልጃቸው የነበረው ሰለሞን ጃገማም በሕይዎት የለም፡፡

5. ጃገማ ኬሎ ከድል በኋላ

jagema-at-young-age
ልጅ ጃገማ ኬሎ በ1934 ዓ.ም.
በ21 ዓመታቸው ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር
ወደ አዲስ አበባ ከሄዱ በኋላ
የተሰጣቸውን ገበርዲን ኮትና ሱሪ
ለብሰው የተነሱት ፎቶግራፍ
በፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት፤ የፋሽስት ወራሪ ጦር በጅማ ጠንካራ ምሽግ ሰርቶ ይኖር ስለነበር ንጉሠ ነገሥቱ ከስደት እንደተመለሱ የጠላትን ምሽግ ሰብረው ጣሊያንን ከቦታው እንዲያባርሩ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ከንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ ተሰቷቸው ነበር፡፡
በዚህን ጊዜ፤ አስፈላጊው አጋዥ ጦርም ከተዋቂ አርበኛ ጋር እንደሚላክላቸው ተነገራቸው፡፡
ደጃዝማች ገረሱም፤ የጅማው ምሽግ እንዲሰበር የሚሹ ከሆነ ሌላ ሳይሆን ጃገማን ይዘዙልኝ በማለት ለንጉሠ ነገሥቱ ጥያቄ ሲያቀርቡ፤ ንጉሠ ነገሥቱም ሌሎች በርካታ እውቅ አርበኞች እያሉ በደጃዝማቹ ጥያቄ ግራ ተጋቡ፡፡
የሆኖ ሆኖ የጠላት ምሽግ በአስቸኳይ እንዲሰበር ንጉሠ ነገሥቱ ስለፈለጉ ወደ ጅማ ከደጃዝማቹ ጋር እንዲዘምቱ የትእዛዝ ደብዳቤ ለጃገማ ኬሎ ላኩ፡፡
ጃገማ ኬሎም ደብዳቤው ሲደርሳቸው፤
“…ወይድ ወደዛ! ጣለው ወረቀቱን! የት ያውቁኝና ነው የሚያዙኝ! እኔ ወታደር አይደለሁ፡፡ ቢፈልጉ መሣሪያቸውን ይውሰዱ እንጅ አልሄድም፡፡”
በማለት መልስ ሰጡ፡፡
በኋላም ተዋቂዋ የውስጥ አርበኛዋ ሸዋአረገድ ገድሌ፤ ጃገማ፤ መልከ መልካምና ጀግና ሰው መሆኑን፣ ንጉሠ ነገሥቱን ባለማየት እንጅ እምቢተኛ ሰው አለመሆኑን፤ እርሳቸው በአካል ጃገማ ኬሎ ያሉበት ቦታ ድረስ ሄደው እንዲያይዋቸው በማስረዳት ለንጉሠ ነገሥቱ ሀሳባ አቀረቡ፡፡
በዚህም መሰረት ንጉሠ ነገሥቱም ሀሳቡን ተቀብለው፤
“…ለልጅ ጃገማ ኬሎ፤ ጦርህን መጥተን እናያለንና ጠብቀን፡፡” የሚል መልእክት የያዘ ደብዳቤ ለጃገማ ኪሎ ተላከላቸው፡፡
ጃገማም ጊንጭ ላይ 3 ሺህ 500 ባለጎፈሬ፤ ባለሹሩባና ባለጋሜ አርበኛ ወታደሮቻቸውን አሰልፈው ንጉሠ ነገሥቱን ጠበቋቸው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም እንደደረሱ በልማዱ መሠረት ጃገማ እንዲፎክሩ በታዘዙት መሠረት፤
“…ጃጌ ጃገማቸው፣
”እንደገጠመ የሚፈጃቸው፤

ገዳይ በልጅነቱ፣
ዶቃው ሳይወጣ ካንገቱ፤”
በማለት መጠነኛ ፉከራ ካሰሙ በኋላ፤
“…ጃንሆይ! እኔ ሥራ እንጅ ፉከራ አላውቅም፡፡”
ብለው ለንጉሠ ነገሥቱ ሲመልሱላቸው፤ ንጉሠ ነገሥቱም፤
“ምን ቀረህና!” ብለው መልስ ሰተዋቸዋል፡፡
jagema-and-his- 2nd wife
ጃገማ ኬሎ የመጀመሪያ
ሚስታቸው ከሞቱ በኋላ
ካገቧቸው ባለቤታቸው ከወይዘሮ
አስቴር ጋር 51 ዓመታትን
በትዳር አሳልፈዋል፡፡
ንጉሠ ነገሥቱም የልጅ ጃገማ ኬሎን ጦር ከአልጋ ወራሽ አስፋወሰን ጋር መጥተው ከጎበኙ በኋላ፤ የአልጋ ወራሹ መኪና ከሾፌሩ ጋር ተዘጋጅቶላቸው ወደ አዲስ አበባ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ተጓዙ፡፡
አዲስ አበባ እንደደረሱም ልጅ ጃገማ ኬሎ ፎቶ እንዲነሱ ከተደረገ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ፤ 15 ሺህ ብር፤ የወርቅ ሰዓትና የገበርዲን ኮትና ሱሪ ለልጅ ጃገማ ኬሎ በሽልማት ሰተዋቸዋል፡፡
ንጉሠ ነገሥቱም ከስደት እንደተመለሱ ፋሽስት ኢጣሊያ ሙሉ በሙሉ ከአገሪቱ ለቆ ስላልወጣ በተለይ በጅማ ጠንካራ ምሽግ አደራጅቶ ይኖር ነበር፡፡
በመሆኑም በደጃዝማች ገረሱ ዱኪ አዛዥነት በጅማ የመሸገውን የጠላት ጦር እንዲደመስሱ በታዘዙት መሠረት፤ ደጃዝማች ገረሱ እዚያው ጊቤ እንዳሉ ልጅ ጃገማ ኬሎ በጅባትና ሜጫ በኩል አድርገው የጠላትን ምሽግ በሽዎች በሚቆጠሩት ወታደሮቻቸው ከበው ፋታ የማይሰጥ ውጊያ በጠላት ላይ ከፍተው ምሽጉን ሰብረው አኩሪ ድል ተጎናጽፈዋል፡፡
ልጅ ጃገማ ለቢቢሲ በሰጡት መግለጫ፤ የጅማን የጠላት ምሽግ በሰበሩበት ወቅት 500 የሚያህሉ የኢጣሊያ ወታደሮችን ማርከው ለእንግሊዝ ወታደሮች ማስረከባቸውን ተናግረዋል፡፡ ድሉን ከተቀዳጁም በኋላ ሁለት የፋሽስት ጀነራሎችን በሚያሰገርም የውጊያ ስልት ማርከው ጅማን መቆጣጠር ችለዋል፡፡
ከዚህ በኋላም አርበኞች የያዛችሁትን አገር እያስተዳደራችሁ ቆዩ ተብሎ ከንጉሠ ነገሥቱ በተላለፈው ትእዛዝ መሠረት ጃገማ ኬሎም፤ አጋሮን፣ ጌራንና በደሌን እንዲያሰተዳድሩ ሹመት ተሰጣቸው፡፡
General Jagema Kello
ልጅ ጃገማ ኬሎ ከግንቦት 1934 ዓ.ም ጀምሮ በ21 ዓመታቸው በንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ ሆለታ ገነት ጦር ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በመግባት የውትድርና ስልጠና አጠናቀው ሲጨርሱ በ1935 ዓ.ም. የሻለቃነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የከፍተኛ መኮንኖች ኮርስም ተከታትለው አጠናቀዋል፡፡
እንደገናም በእርሳቸው ስር ይመሯቸው ከነበሩት 3 ሺህ 500 ሠራዊት መካከል 500 ወታደሮችን መርጠው በጦር ሠራዊቱ ውስጥ እንዲቀጠሩ ካደረጉ በኋላ እርሳቸውም በጦር ሠራዊቱ ውስጥ የሻለቃ አዛዥ ሆነው ተቀጠሩ፡፡
በኋላም በወቅቱ የንጉሠ ነገሥቱን የማእከላዊ የመንግሥት አስተዳደር በመቃወም ራስ ኃይለማሪያም ጉግሣን ለማንገሥ በመፈለግ በቀዳማዊ ወያኔ አማካኝነት በ1935 ዓ.ም ተቀስቅሶ በነረው ጦርነት ምክንያት መንገዶች ተዘግተው ሰላም ደፍርሶ ነበር፡፡
በመሆኑም የጠቅላይ ግዛቱን ፀጥታ ለማስከበር ቀደም ሲል በንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ ራስ አበበ አረጋይ የዘመቻው መሪ ሆነው ተልከው በነበረበት ወቅት፤ ሻለቃ ጃገማም፤ በ1935 ዓ.ም. ወደ ትግራይ ከሄዱ በኋላ አንድ ሻለቃ ጦር ይዘው ወደ ማይጨው ተልከው ለሶስት ወራት ያህል ሲዋጉ ቆይተዋል፡፡
በመጨረሻም ከእንደርታ የመጣውን የራስ ኃይለማሪያምን ጦር ድል በማድረግ ግዳጃቸውን ፈጽመው መቀሌ በመግባት የአካባቢውን ሰላም ከሌሎች አጋር ሠራዊቶች ጋር በመሆን አስጠብቀው ተመልሰዋል፡፡
ከዚያም ለጥቂት ጊዜያት ያህል በአምቦና በቢሾፍቱ ተመድበው አገልግለዋል።
በኋላም በአምባላጌና በራያ አዘቦ በግዳጅ አፈፃፀም ላይ ባሳዩት ብቃት በሜጀር ጀነራል አበበ ዳምጠው ተመስክሮላቸው፤ ሻለቃ ጃገማ የብርጌድ አዛዥ ሆነው ተሾሙ።
jagema-group-photo
ብርጋዴር ጀነራል ጃገማ
ኬሎ በ1955 ዓ.ም.
ከሥራ ጓዶቻቸው ጋር


ከጀነራል ጃገማ በስተቀር ሁለቱም ጀነራሎች፤
ማለትም ጀነራል ኃይሌ ባይከዳኝና
ጀነራል አማን ሚካኤል አንዶም
ከ60ወቹ የመንግሥት ባለሥልጣናት
ጋር በደርግ ተረሽነዋል
የዩጎዝላቪያ ፕሬዝደንት የነበሩት ማርሻል ቲቶ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት የተደረገላቸውን የክብር ሰልፍ የመሩት ሌፍትናንት ኮሎኔል ጃገማ ነበሩ።
በ 1952 ዓ.ም. አካባቢ ወደ ባሌ በመዝመት ተፈጥሮ የነበረውን አመጽ ገተው ሠላም ካስከበሩ በኋላ የባሌ የጦር አዛዥ ሆነው ተሹመዋል፡፡
በ1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወቅት የመፈንቅለ መንግሥቱን ሙከራ ለማክሸፍ የተንቀሳቀሰው ኃይል አዛዥ ሌፍትናንት ኮሎኔል ጃገማ ኬሎ ነበሩ።
በ1954 ዓ.ም በብርጋዴር ጀነራልነት ማዕረግ የአራተኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ሆነው አገልግለዋል፡፡
በ1958 ዓ.ም የሜጀር ጀኔራልነት ማዕረግን አግኝተዋል፡፡
ብርጋዴር ጀነራል ጃገማ በቀድሞው በሐረር ጠቅላይ ግዛት በሶማሌ ጠረፍ በግዳጅ በነበሩበት ወቅት በቀጣዩ ቀን ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ተነግሯቸው፤ ነገር ግን የነበሩበት ቦታ ከአዲስ አበባ 700 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የሶማሌ ጠረፍ በሆነችው ኤልከሬ ውስጥ ስለነበሩ በአንድ ቀን ውስጥ መምጣት እንደማይችሉ ከተናገሩ በኋላ የሌፍትናንት ጀነራልነት ማእረግ የተሸሙ መሆኑን በበረሀ በድንኳን ውስጥ ሆነው በሬድዮ እንደማንኛውም ሰው በድንገት መስማታቸው ከሁሉም የበለጠ እነዳስደሰታቸው ይናገራሉ፡፡
Gen. Jagema Leading Deligation
ጀነራል ጃገማ ኬሎ ልዑካንን
እየመሩ አሜሪካንን በጎበኙበት ወቅት
ሌፍትናንት ጀነራል ጃገማ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን ልዑካን በመምራት ወደ አሜሪካ በመጓዝ ጉብኝት አድርገው ተመልሰዋል፡፡
ሌፍትናንት ጀነራል ጃገማ፤ የአርበኝነትና የጀግና ሜዳዮች፣ የኮርዶን ኒሻኖችና ከውጭም ሀገር በርካታ የተለያዩ ሽልማቶችን ተሸልመዋል፡፡
ጃገማ ኬሎ ከፋሽስት ጋር ባሳለፏቸው የጦርነትና የውጊያ ውሎዎች የተነሳ ከደረሱባቸው የተለያዩ የመኪናና የሄሊኮፕተር አደጋዎች ከመትረፋቸውም በላይ ከ18 ጊዜ በላይ የቀዶ ጥገና ሕክምና ተደርጎላቸዋል፡፡

6. የጃገማ ኬሎ የግል ባህርይ


ጃገማ ሲናገሩ፤
Jagema-on-horseback
“የኔ ፍላጎት ሰው እንዲወደኝ ማድረግ ሳይሆን ሰዎችን የምወድ መሆኔን ማረጋገጥ ነው፡፡”
ይሉ ነበር፡፡
ጃገማ ገና በ15 ዓመት ለጋ እድሜያቸው ጀምሮ፤ ለሰው አዛኝ፣ ትሁት፣ ግፍን የማይወዱ፣ ሰውን ተናግረው የማያስቀይሙና በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ ሰው እንደነበሩ በርካታ ሰዎች መስክረውላቸዋል፡፡
በዚህም የተነሳ ከእድሜያቸው ሁለትና ሦስት እጥፍ የሚበልጡት አርበኞች ሳይቀሩ ጃገማን ለአርበኞች መሪነት መርጠዋቸዋል፡፡

ጃገማ ኬሎ፤ ደፋር፣ የጦር ስልትን፣ የውትድርና አመራርና እውቀትን በተመለከተ፤ ከሥልጠናው ባሻገር ተፈጥሮ የለገሰቻቸው ጀግና የጦር መሪ ነበሩ፡፡

ንጉሠ ነገሥቱ ከስደት እንደተመለሱ ተዘጋጅቶ በነበረው ቲያትር ውስጥ ከቀረበው ግጥም ውስጥ ጃገማ ኬሎ፤ እጅግ የሚዎድቱና ነፍሳቸውን የሚገዛው ግጥም የሚከተለው ነበር፡፡
“እናት ኢትዮጵያ ውዲቱ ውዲቱ፣
በሦስቱ ቀለማት የተሸለምሽቱ፣
ለአንች የማይረዳ ካለ በሕይዎቱ፣
በረከትሽን ይንሳው እስከለተ ሞቱ፡፡"





7. ሕልፈተ ሕይዎትና የቀብር ሥነ ሥርዓት

Jagema Kello Funeral Procession
የሚወዷትን ሠንደቅ ዓላማ ለብሰው
እውቁና ጀግናው አርበኛ ሌፍትናንት ጀኔራል ጃገማ ኬሎ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በጦር ኃይሎች ሆስፒታል
Jagema Kello Funeral Procession
የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ሲከናወን
ሲረዱ ቆይተው ዐርብ ዕለት መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በተወለዱ በ 96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

Jagema-on-horseback
የጀነራል ጃገማ ኬሎ መታሰቢያ ጤና ጣቢያ
ሥርዓተ ቀብራቸው እሑድ፣ ሚያዝያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡
ለጀነራል ጃገማ ኬሎ መታሰቢያ የሚሆን በአዲስ አበባ ነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አንድ የሕዝብ ጤና ጣቢያ በስማቸው ተሰይሞላቸዋል፡፡






ምንጭ፤
  1. Press.et   web site link:   Press.et.com …ምስጋና፤ ለዋለልኝ አየለ - አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 2 ቀን 2014 ዓ.ም
  2. ethiopanorama  web site link:   ethiopanorama.com
  3. allaboutethio   web site link:   allaboutethio.com
  4. EBC የበጋው መብረቅ "ጃገማ ኬሎ" በ2005 ዓ.ም. የቀረበ፤   youtube - link
  5. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ