Content-Language: am የጎሬው ሰማዕት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሚካኤል
header image




የጎሬው ሰማዕት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሚካኤል



የጎሬው ሰማዕት ብፅዑ ወቅዱስ አቡነ
ሚካኤልን የሰማዕትነት ታሪክ ያዳምጡ















1. ትውልድ እና ጵጵስናን ስለመቀበል

Abune Mikael of Gorie
የጎሬው ሰማዕት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሚካኤል

 ምስግና፤   ለ ኢት/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ድረ ገጽ
ሰማዕቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሚካኤል፣ ከአባታቸው ከቄስ ገብረ ክርስቶስ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ትኩዬ በ1874 ዓ.ም ተወለዱ፡፡
የተወለዱበት ስፍራም በቀድሞው አጠራር በጎንደር ጠቅላይ ግዛት በደብረ ታቦር አውራጃ፤ አፈረዋናት ድምበር ወረዳ፣ ልጨ መስቀለ ክርስቶስ ተብሎ ይጠራል፡፡
የጥንት ስማቸው ኃይለ ሚካኤል ይባላል፡፡
ግንድ አጠመም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፤ ክርስትና ተነሥተውና በዚያው አድገው፣ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ወላጆቻቸው መምህር ዋሴ ለሚባሉ አስተማሪ እንዲያስተምሯቸው ሰጧቸው፡፡
ፊደል ከቆጠሩበት ቀን አንስቶ እንደ ልጅ አንድም ቀን ጥፋት ሳይኖርባቸው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ለማዕረገ ዲቁና እንደበቁ፤ መምህራቸው፣ የዜማ ትምህርት እንዲቀጥሉ መካነ ሰማዕት ገላውዴዎስ ለነበሩት መምህር ተድላ ከሰጧቸው በኋላ ጾመ ድጓ እና ምዕራፍ በሚገባ አደላደሉ፡፡
ዝማሬና መዋስዕት፣ ድጓ፣ መዝገብ ቅዳሴ ከነትርጓሜው፣ አቋቋም እና ቅኔ በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ከታላላቅ መምህራን ተምረዋል፡፡
ማዕረገ ዲቁና እና ማዕረገ ቅስና ከግብፃዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ከተቀበሉ በኋላ ቤተ ክርስቲያንን በንጽሕና እና በድንግልና በጥሩ ሕይወት አገልግለዋል፡፡
ግንቦት 25 ቀን 1921 ዓ.ም ከአራት አባቶች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ግብፅ በማቅናት ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ተብለው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡፡
ከብፁዕነታቸው ጋር ጵጵስናን ከተቀበሉት ሌሎች ብፁዐን አባቶች መካከል፤ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ይሥሐቅ እና ብፁዕ አቡነ አብርሃም ይገኙበታል፡፡

ከግብፅ እንደተመለሱም፤
  1. ብፁዕ አቡነ ሚካኤል በምዕራብ ኢትዮጵያ የኢሉባቦር፣ ከፋ እና የወለጋ ጠቅላይ ግዛት ሊቀ ጳጳስ፣
  2. ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ፣
  3. ብፁዕ አቡነ ይሥሐቅ የትግራይ እና የሰሜን ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ፣
  4. ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጎንደር እና የጎጃም ጠቅላይ ግዛት ሊቀ ጳጳስ
ኾነው ተሹመው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ሀገርን አገልግለዋል፡፡

2. ከወራሪው ፋሽስት ኢጣሊያ ጋር የፈፀሙት ተጋድሎ

ግፈኛው የኢጣልያ ፋሽስት ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ ሀገራቸውን በአጥንታቸው እሾኽነት አስከብበው፣ በደማቸው የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖትን ክብር አስጠብቀዋል፡፡
በሀገረ ስብከታቸው፣ ሕዝቡን ሰብስበው ለጠላት እንዳይገዛ በማስተባበር፣ የቤተ ክርስቲያኑን ክብር እንዲጠብቅ በማደፋፈር የአርበኝነት ተግባር ፈጽመዋል፡፡
ከብዙ አርበኛ ወንድሞቻቸው ጋር ከሀገር ወደ ሀገር በመዞር ቃለ ወንጌል በማስተላለፍ ሲፋጠኑ፣ የፋሽስት ጦር ሰቢ ከሚባል ጫካ ደርሶ ከበባቸው፡፡ በዚኹ ቦታ አድረው በማግሥቱ በጠላት ጦር ተያዙ፡፡
ፋሽስት ኢጣሊያ በ 1928 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ሲወር በተፈጠረው የፖለቲካ ሁኔታ የተወሰኑ ጳጳሳት የተለያዩ አቋሞችን ሲይዙ፤ አቡነ ሚካኤል እና አቡነ ጴጥሮስ ለአገራቸውና ለቤተ ክርስቲያናቸው ታማኝ ሆነው ”መንጋችንን ለነጣቂ ፋሽስት ተኩላ በትነን አንሄድም” ብለው በፋሽስቶች እጅ ሰማዕትነትን ሲቀበሉ፣ ግብፃዊው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ ደግሞ ወደ ካይሮ አመሩ፡፡
በተቃራኒው ደግሞ ትውልዳቸው ከትግራይ የሆኑት አቡነ አብርሃም እና አቡነ ይስሃቅ የወራሪው ጠላት የፋሽስት ኢጣሊያ አገልጋዮች መሆንን መረጡ።
አቡነ ሚካኤል፤ ፋሽስት ኢጣሊያ አገራችንን በወረረችበት ጊዜ የኢሉባቦር ሠራዊት ወደ ምሥራቅ ጦር ግንባር ኦጋዴን ሲዘምት ስለ ሀገሩ ነፃነት በርትቶ እንዲከላከል አስተምረው ከመከሩ በኋላ ቡራኬ ሰጥተው አሰናብተዋል።
እሳቸውም በጾም፣ በፀሎት እና በምህላ ወደ እግዚአብሔር እየማለዱ ሕዝቡን በማፅናናት ቆይተዋል።
የፋሽስት ኢጣሊያ ጦር አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ቆራጡ የልብ ጓደኛቸው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ለሃይማኖታቸው እና ለአገራቸው ነፃነት መሥዋዕት ለመሆን መዘጋጀታቸውን እንዲሁም ከነፃነት አርበኞች ጎን በመሰለፍ ሕዝቡ ስለ ሃይማኖቱ እና ስለ ሀገሩ ነፃነት እንዲዋጋ በመቀስቀስ ላይ መሆናቸውን ሲሰሙ በጣም ተደሰቱ።

3. የብፁዕ አቡነ ሚካኤል በጠላት እጅ መውደቅ

Abune Mikael of Gorie
በህዳር ወር 1929 ዓ.ም. በፋሽስቱ የጦር አዛዥ በኮሎኔል ማልታ የሚመራው የፋሺስት ኢጣሊያን ጦር የጎሬን ከተማ ተቆጣጠረ።
አቡነ ሚካኤል ደግሞ በጎሬ ከተማ አጠገብ ‘ሳንቤ ቀበሌ’ በምትባል ስፍራ ሆነው ሕዝቡ ጠላትን እንዲከላከል በመቀስቀስ ላይ ነበሩ።
ብፁዕነታቸው ከብዙ አርበኛ ወንድሞቻቸው ጋር ከሀገር ወደ ሀገር በመዟዟር ቃለ ወንጌል በማስተላለፍ ላይ እንዳሉ ከሁለት አርበኞች ማለትም፤ ከግራዝማች ተክለሐይማኖት እና ከቀኛአዝማች ይነሱ ጋር በመሆን ከጎሬ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ወረድ ብሎ በሚገኝ ሰቢ ከሚባል ጫካ ሲደርሱ ይህን የሰማው የፋሽስት ጦር በአፋጣኝ ወታደር ልኮ አስከበባቸው።
ከብፁዕነታቸው ጋር የነበሩት አርበኞች ከከበቧቸው የኢጣሊያ ጦር ጋር ተኩስ ከተለዋወጡ በኋላ የጠላት ጦር ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ እያፈገፈጉ ሳለ፤ አቡነ ሚካኤል በቅሎዋቸው ላይ ተቀምጠው መንገድ እንደ ጀመሩ በኢጣሊያ ወታደሮች ተያዙ።
ኢጣሊያዊው የጦር መኮንን ብፁዕነታቸውን ከበቅሎዋቸው አስወርዶ በእግራቸው እንዲሄዱ ካደረገ በኋላ እርሱ በቅሎው ላይ ተቀመጠ። ይህን የጦር መኮንኑን አድራጎት የተመለከቱት ከጠላት ጋር የነበሩት የሐማሴን ተወላጆች ተቆጥተው፤
“የሃይማኖት አባታችን የሆኑትን አዛውንት በቅሎእቸውን ቀምተህ በእግራቸው እንዲሄዱ ማድረግህ ግፍ ነው፡፡ በቅሎዋን መልስላቸውና አንተ በእግር ሂድ። አለበለዚያ እኛ ከዚህ ስፍራ አንንቀሳቀስም።”
በማለት ድርጊቱን ተቃወሙ።
ኢጣሊያዊው መኮንን በሁኔታው ደንግጦ ከበቅሎው ላይ በመውረድ በቅሎውን ለጳጳሱ መለሰ።
አቡነ ሚካኤል በበቅሎው ተቀምጠው ጎሬ እንደደረሱ በጠላት ሠፈር በተዘጋጀ እሥር ቤት በጥብቅ እንዲታሠሩ ተደረገ።
በአንፃሩ ደግሞ በጊዜው ፈጥነው ከኢጣሊያ ጦር ጋር የተስማሙ አባቶች የአቡነ ሚካኤልን ጠንካራ አቋም ከተረዳው ጠላት ተልከው ወደ እርሳቸው ጋ መጡ።
ተልከው የመጡት መልዕክተኞችም አቡነ ሚካኤል ከጣሊያን ጋር እንዲስማሙ፤ ሕዝቡን እንዲያባብሉ፤ “ለኃያሉ የኢጣሊያ መንግሥት ለመገዛት ቃል ይግቡና ሕዝቡም እንዲገዛልን ይስበኩልን። ይህንን ካደረጉ እንለቅዎታለን።” በማለት በልዩ ልዩ መደለያ ጭምር አባበሏቸው።
ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ግን ከሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጠላት ጋር እንደማይተባበሩ በፅናት ሲገልጹ፤
“እኔ የማምነው በአንድ እግዚአብሔር ነው።
የምቀበለው የነፃነታችን ምልክት የሆነውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ብቻ ነው።
ኢጣሊያ የሚባል ገዥ አላውቅም።
ለፋሽስት ኢጣሊያ የተገዛ እንደ አርዮስ የተረገመ ይሁን።
እንኳንስ ሕዝቡ ምድሪቱም እንዳትገዛላቸው አውግዣለሁ።”
በማለት በዚያ ለተሰበሰበው ሰው ሁሉ ውግዘታቸውን አሰሙ።
“አቡነ ሚካኤል መንፈሳዊ አባትና ሽማግሌ ስለ ሆኑ ይፈቱልን” በማለት የጎሬ ሕዝብ ልመና ቢያቀርብም የጠላት ጦር አዛዥ ልመናውን ሳይቀበለው ቀረ።

4. በጠላት እጅ መረሸንና ሰማዕትነትን መቀበል

የጠላት ጦር አዛዥ ኮሎኔል ማልታ እሥረኛውን ጳጳስ ከእሥር ቤት አስመጥቶ ሕዝቡ በተሰበሰበበት አደባባይ አቀረባቸው።
ፋሽስቱ ኮሎኔል ማልታ የብፁዕነታቸውን የዓላማ ፅናትና ቆራጥነት ተገነዘበ።
እሳቸውን መሸንገል እንደማይቻል ሲያረጋግጥ በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ ወሰነ።
ከጎሬ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በታች አሮጌው ቄራ አጠገብ ጉድጓድ ተቆፈረ።
በጉድጓዱ ዳር በሁለት ስመጥር አርበኞች በቀኛዝማች ይነሱ እና በግራዝማች ተክለ ሐይማኖት መካከል ጳጳሱ እንዲቆሙ ተደረገ።
በዚህን ጊዜ አቡነ ሚካኤል ለጥቂት ደቂቃዎች ፀሎት እንዲያደርጉ ጠይቀው ተፈቀደላቸው። ፀሎታቸውን አድርሰው ሲያበቁ መስቀላቸውን በግንባራቸው አድርገው፤
“በል እንግዲህ የፈለከውን አድርግ” በማለት ተናገሩ።
ወዲያውኑ የወታደሮቹ አዛዥ የተኩስ ትዕዛዝ ሰጠ።
ከእነ አቡነ ሚካኤል እና ከአርበኞች ፊት ለፊት በተርታ ተደርድረው ጠመንጃቸውን ያነጣጠሩት የጠላት ወታደሮች የእሩምታ ተኩስ ተኮሱ።
ብፁዕነታቸውና ሁለቱ አርበኞች በተተኮሰባቸው ጥይት ተመተው ወደቁ።
ብፁዕነታቸው በዕለተ ሐሙስ ኅዳር 17 ቀን 1929 ዓ.ም. በተወለዱ በ 55 ዓመታቸው በፋሽስቱ እጅ በመትረየስ ጥይት ተደብድበው ለእናት ሀገራቸው ለኢትዮጵያ የነፃነት ታጋይ አርበኛ መሆናቸውን አስመስክረው ሰማዕትነትን በመቀበል ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጡ፡፡
ፊቱኑም ቢሆን፣ በሰማዕትነት በክብር ማለፍን ይሹ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሚካኤል፤ ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ አዲስ አበባ ላይ በፋሺስት ኢጣሊያ ከተገደሉ ከአራት ወራት በኋላ ጎሬ ላይ የሀገራቸውን ገናናነት እና የሃይማኖታቸውን ክብር መስክረው ፋሺስትን በማውገዝ ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፡፡

ስዊድናዊው ኮሎኔል ካውንት ካርል ስለ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሚካኤል ሲናገር፤
“ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ከማልዘነጋቸው ቆራጥ ኢትዮጵያውያን አርበኞች አንዱ ናቸው፡፡
ጳጳሱ በሞት ፊት ያሳዩት ድፍረት እና የሀገር ፍቅር ስሜት ምንጊዜም አይረሳኝም።”

በማለት ገልጿቸዋል፡፡
የቀብራቸውም ሥነ ሥርዓት በአግባቡ አልተፈፀመም ነበር።
አቶ ወልደአብ የተባሉ የአገር ፍቅር ያደረባቸው የአካባቢው ነዋሪ በሌሊት ተነስተው ቀበሯቸው።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሚካኤል ከተረሸኑ በኋላ አፅማቸው ከነበረበት አልባሌ ሥፍራ ተለቅሞ በሣጥን ተደርጎ፣ በጎሬ ደብረገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በክብር የተቀመጠው፤ ጠላት ከሀገር ተባሮ ነፃነት ከተመለሰ ከ1935 ዓ.ም. በኋላ ነው፡፡

5. የሰማዕትነት መታሰቢያ

Statue of Abune Mikael of Gorie

ግንቦት 14 ቀን 2008 ዓ.ም.
መስዋዕት በሆኑባት ጎሬ ከተማ በሚገኘው
በደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ
ክርስቲያን ደጀ ሰላም ውስጥ የቆመላቸው ሐውልት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፤ በመደበኛ ጉባኤው ለጎሬው አቡነ ሚካኤል ቅድስናን ሰጥቷል።
ጎሬ ከተማ ውስጥ በ1960 ዓ.ም. በስማቸው የተቋቋመው አቡነ ሚካኤል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ 1054 ወንድ እና 603 ሴት ተማሪዎች፤ እንዲሁም 24 ወንድ እና 6 ሴት መምህራን የሚያዝ የአቡነ ሚካኤል ትምህርት ቤት በማስታወሻነት ተገንብቷል።
የኢሊባቡር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የአቡነ ሚካኤልን ፎቶግራፍ ከግብፅ አሌክሳንድርያ አስመጥተው በጎሬ ከተማ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት በሚገኘው አደባባይ ላይ ከ 1952 ዓ.ም እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ በመስታወት ውስጥ አስቀምጠውት ነበር።
በደርግ አስተዳደር ወቅትም በቦታው መንገድ አቋርጦ ያልፍበታል ተብሎ ፎቶግራፋቸው እንዲነሣ ተደረገ።
በተጨማሪም፤ ጠላት እንኳን ለመውሰድ ያልደፈረው የአቡነ ሚካኤል የወርቅ መስቀል ከሃምሣ ዓመታት በላይ በቤተክርስቲያን ውስጥ ተከብሮ ቆይቶ ነበር። ሆኖም በወቅቱ በነበሩት የጊዜው ባለስሥልጣናት ትዕዛዝ በእግዚቢሽን ሰበብ ተወስዶ ሳይመለስ መቅረቱ ተዘግቧል።
ቀደም ሲል የኢሉባቦር ጠቅላይ ገዥ የነበሩት ደጃዝማች ጣሰው ዋለሉ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል በተረሸኑበት ቦታ ላይ ድንጋይ በማስካብ መታሠቢያ እንዲሆናቸው አድርገው ነበር።
የኋላ ኋላ ግን ቢዘገይም የሰማዕቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሚካኤል የምስክርነት ሐውልት፤ ግንቦት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት፣ ማኅበረ ካህናት እና ማኅበረ ምእመናን በተገኙበት ሰማዕትነትን በተቀበሉበት በጎሬ ከተማ ተመርቋል፡፡


ምንጭ፤
  1. የኢት/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ድረ ገጽ
    → ምስጋና የስም ማዕረግ ላልተጠቀሰው ለ፤  ( ካሣ ንጉሥ )
  2. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ





>