Content-Language: am ራስ ውብነህ ተሰማ (አሞራው ውብነህ)
header image

ራስ ውብነህ ተሰማ (አሞራው ውብነህ)



የራስ ውብነህ ተሰማ (አሞራው ውብነህ) በ2ኛው
የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት የአርበኝነት ዘመን ታሪክ













የአርበኝነት ዘመን ተጋድሎ

Ras Wubneh Tesema
ራስ ውብነህ ተሰማ (አሞራው ውብነህ)
“አሞራው ውብነህ” በመባል የሚታወቁት ደጃዝማች ውብነህ ተሰማ (በኋላ ራስ) ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም. ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት በምእራብ ቤጌሚድር ግዛት በተደረገው የፀረ-ፋሽስት ትግል ግንባር ቀደም መሪ ነበሩ።
ከሱዳን ጋር በሚያዋስነው ቆላማ አካባቢ የአርማጭሆ አውራጃ ተወላጅ የሆኑት ውብነህ ተሰማ በ 16 ዓመታቸው ነበር ከበርካታ ሽፍቶች አመራሮች መካከል አንዱ በመሆን ትግላቸውን ጀመሩት።
በልጅነታቸው የአባታቸውን ጠመንጃ በመያዝ አደን ያድኑ እንደነበር ልጃቸውና የልጅ ልጃቸው ይናገራሉ፡፡
ፋሽስት ኢጣሊያ በወረረበት ወቅት ውብነህ ተሰማ ተልዕኮውን ከሽፍትነት ወደ አርበኝነት ደረጃ ከፍ በማድረግ ወራሪውን ፋሽስት ባገኟቸው ቦታዎች ሁሉ ማጥቃትን ተያያዙት፡፡
ራስ ውብነህ ተሰማ አገርንና ወገንን የሚወዱ፤ ታሪክን የሚያስተምሩና ከአገር የሚበልጥብኝ ነገር የለም በማለት እራሳቸውን ያሳመኑና ፀሎተኛም እንደነበሩ የልጅ ልጃቸው ገብርኤላ አድማሱ ይናገራሉ፡፡
grand daughter of Ras Wubneh - Gebriela
የራስ ውብነህ ተሰማ
የልጅ ልጅ ገብሬላ አድማሱ

Photo link
ውብነህ ተሰማ፤ ባለቤታቸውን ጨምሮ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ የመጣው የአርበኞች ቡድን በምስራቅ ሱዳንና በምዕራብ ኢትዮጵያ መካከል በነፃነት በመጓዝና በድንበር አካባቢም ካሉ ታዋቂ ሰዎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ስለፈጠሩ ፋሽስት ኢጣልያ ቤጌሚድርን አረጋግቶ ለመቆጣጠር በፍጹም አልቻለም።
ራስ ውብነህ በተለያዩ ጊዜያት በሌሎች የአርበኞች ግንባር እንደተገለጸው ሁሉ ጠላትን በመፋለምና በኢትዮጵያ ዙፋን ላይ ተቀናቃኝ ናቸው በሚባሉት ላይ ፀረ ተቃውሞ ትግል በመምራት ለንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በነበራቸው ጽኑ የግል ታማኝነት ጎልተው ታይተዋል።
ምንም እንኳን ከጠላት ጋር ሲፋለሙ በአንድ ወገን የራስነት የማዕረግ ስም ቢይዙም ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ግን የደጃዝማችነትን ማዕረግ ያረጋገጡላቸው በ1933 ዓ.ም. ነበር፡፡
ራስ ውብነህ ባመኑበት ነገር ንጉሠ ነገሥቱን ጨምሮ ፊት ለፊት ከመናገር የማይቆጠቡና የማይፈሩ ደፋር ተናጋሪ ነበሩ፡፡
ምንም እንኳን ይህ ድፍረት የተሞላበት ንግግራቸው ለተወሰነ ጊዜ ለቁም እስር ቢዳርጋቸውም ቅሉ፤ ንጉሠ ነገሥቱ ግን ለራስ ውብነህ ከፍተኛ ፍቅር ስለነበራቸው ምክራቸውን ከፍ አድርገው ይመለከቱት እንደነበር ይነገራል፡፡
ኢትዮጵያ በፋሽስት የኢጣሊያ አገዛዝ ትማቅቅ በነበረበት ዘመን የኢትዮጵያ ጀግና የቁርጥ ቀን ልጅ በመሆን ባስመሰከሩት እና ለንጉሠ ነገሥቱም ጽኑ የግል ታማኝ አርበኛ የሆኑትን ራስ ውብነህን ማሰር አሳፋሪ በደል እንደመፈፀም የሚቆጠር ተግባር መሆኑን የታሪክ ጸሐፊዎች ሳይዘግቡት አላለፉም፡፡
Ethiopian Wubneh, Daughter of Ras Tesema Wubneh
በሱዳን ገዳሪፍ የተወለዱት
የራስ አሞራው ውብነህ ልጅ
ወይዘሮ ኢትዮጵያ ውብነህ

Photo link
በሱዳን ገዳሪፍ የተወለዱት የራስ አሞራው ውብነህ ልጅ ወይዘሮ ኢትዮጵያ ውብነህ፤ ራስ አሞራው ውብነህ፤ በጎንደር፣ በምጽዋ፣ በአዲስ አበባና በተለያዩ ቦታወች እየተዘዋወሩ የአርበኝነት ተግባር ማከናወናቸውን ይናገራሉ፡፡
በአቡነ መልከጸዴቅ የመቃብር ጽሁፍ ላይ እንደተገለፀው፤ አሞራው ውብነህ የምድር አርበኛ ብቻ ሳይሆኑ የሰማይ አርበኛ ጭምር እንደነበሩ እና ከነፃነት በኋላ እንግሊዞች ጎንደር ገብተው የራሳቸውን ሠንደቅ ዓላማ ሲሰቅሉ የተመለከቱት ራስ አሞራው ውብነህ፤ በአገሬ ላይ የውጭ ሀገር ሠንደቅ ዓላማ አይሰቀልም በማለት እንግሊዞችን አስገድደው የእነርሱ ሠንደቅ ዓላማ ወርዶ በምትኩ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ እንዱሰቀል ማድረጋቸውን ሱዳን ገዳሪፍ የተወለዱት ልጃቸው ወይዘሮ ኢትዮጵያ ውብነህ ያስረዳሉ፡፡

ጀግናው አገር ወዳድ አርበኛ ራስ አሞራው ውብነህ፤ ከጥቂት ዓመታት ቆይታ በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
አስከሬናቸው አዲስ አበባ በሚገኘው የታላላቅ አርበኞች አፅም ባረፈበት በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡





ምንጭ፤
  1. …ምስጋና፤ ለለፋና ቀለማት - ፋና ቴሌቪዥን  youtube link.
  2. ... የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ጎራው - በኦርኬስትራ ኢትዮጵያ   ዩቲውብ